ምክር ቢጤ ለዶክተር ደሳለኝ ጫኔ፤ ካሳማ ጋር ትግል አትግጠም

ያሳማ ዋና ፍላጎት ተጨማልቆ ማጨማለቅ ስለሆነ፣ ካሳማ ጋር በጭራሽ አትታገል፡፡

(Never wrestle with a pig.  You both get dirty and the pig likes it.  George Bernard Shaw)

አቶ ኤርምያስ ለገሰ በገዛ ራሱ ፈቃድ፣ ራሱን በራሱ የወያኔና የኦነግ አሳማ አድርጓል፡፡  አሳማ ሲባል ደግሞ አረንቋ ውስጥ መጨማለቅ ስለሚወድና ከፍተኛ እርካታ ስለሚሰጠው፣ ዋና ምኞቱ ተጨማልቆ ማጨማለቅ ነው፡፡  ስለዚህም ፀራማሮቹ ወያኔና ኦነግ ላቶ ኤርምያስ ከሰጡት ተልዕኮወች ውስጥ አንዱ፣ ካማራ ሕልውና ታጋዮች ጋር አተካራ ገጥሞ፣ ራሱ ተጨማልቆ እነሱን በማጨማለቅ ባማራ ሕዝብ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ዝቅ ማድረግ ነው።

ወያኔና ኦነግ ላቶ ኤርምያስ የሰጡት የመጀመርያውና ዋናው ሥራ ኢትዮ360ን ማምከን ነበር፡፡  ያቶ ኤርምያስ ሙከራ ግን ኢትዮ360ን ከማምከን ይለቅ ስላገነነው አለቆቹ ወያኔና ኦነግ ከመጠን በላይ ቅር ተሰኝተውበታል፡፡  ስለዚህም አቶ ኤርምያስ ቅር የተሰኙበትን አለቆቹን ለማስደሰት የማይፈነቅለው ዲንጋ፣ የማይቆፍረው ጉድጓድ የለም፡፡  ከዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ጋር አተካራ የገጠመውም በዚሁ ምክኒያት ነው፡፡  ዐላማው ደግሞ ራሱ ተጨማልቆ ዶክተር ደሳለኝን በማጨማለቅ፣ ዶከተር ደሳለኝን አራክሶ ያማራ ለምድ የለበሰውን ፀራማራውን በለጠ ሞላን ለማዋደድ ነው።

ያማራ ሕዝብ የሕልውና ጠላቶቹን ወያኔንና ኦነግን በተመለከተ ያሉት ምርጫወች ሁለት ብቻ ሲሆኑ፣ እነሱም ወይ እነሱን ማጥፋት ወይም በነሱ መጥፋት ናቸው፡፡   ወያኔነና ኦነግን በማጥፋት ራሱን ከጥፋት ለማዳን ደግሞ ከወዳጆቹ ጋር ይቅርና ከጠላቶቹ ከራሳቸው ከወያኔና ከኦነግም ጋር ቢሆን መተባበር የግዴታ ውዴታው ነው።  እሾህን በሾህ ነውና፣ ወያኔን በኦነግ ወይም ደግሞ ኦነግን በወያኔ ማጥፋት ከቻለአንድ የሕልውና ጠላት ተነቀለለት ማለት ስለሆነ፣ ዕደሉ ሊያመልጠው አይገባም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  መልስ ለኃይሉ የሺወንድም፤ በወልቃይት ፀገዴ ባህልና ማንነት ጥያቄ እኔም ቅሬታ አለኝ!

ስለዚህም፣ ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ የኦነግን ጉዳይ በይደር ይዞ፣ ጠመንጃ እንግቦ፣ ዝናር ታጥቆ ወያኔን ሊወጋ መዝመቱ በግልጽ የሚያሳየው፣ እሱ ራሱ እንዳለው “ታማኝነቱ ላማራ ሕዝብና ለህሊናው” የሆነ፣ ያማራ ሕዝብ መዳኛ መንገድ በግልጽ የታየውግቡን (goal) ጠንቅቆ የሚያቅ፣ የተዋጣለት ትልመኛ (strategist) እና ስልተኛ (tactician) መሆኑን እንጅ መርሕ አልባ መሆኑን አይደለም፡፡  መርሕ አልባ የሆኑት የወያኔና የኦነግ ቅጥረኛ የሆነው አቶ ኤርምያስ ደግሞ ስለ መርሕ ቢያወራ ጆሮ /ሊሰጠው/ አይገባም፡፡

ስለዚህም ውድ ወንድሜ ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ፣ ካፈርኩ አይመልሰኝ ከሚለው፣ የጨምላቃ አሳማ ባሕሪ ከተጠናወተው ካቶ ኤርምያስ ለገሰ ጋር እሰጥ አገባ ገጥመህ ተጨማልቆ እንዳያጨማልቅ በትህትና እመክርሃለሁ፡፡  አፍ ሲከፈት ይታያል ማንነት እንዲሉ፣ አቶ ኤርምያስ ለገስ ስድ አፉን በመክፈት “ሱሪውን አውልቆ ቅቤ በጠጣ ዱላ ደበደበው” እያለ ጭራቅ አሕመድን በማሞገስ እውነተኛ ማንነቱን እሱ ራሱ እያሳየ፣ አንተን ያዋረድ ቢመስለውም እሱን ራሱን ይበልጥና ይበልጥ ያዋረደ ስለሆነ፣ ንቀህ ተወው፡፡  አንሶ እንዳያሳንስህ መልስ እንዳትሰጠው፡፡

 

ካልተውት በስተቀር ንቀው ብለው ቀላል

ትንሽ ሰው ትንሽ ነው አንሶ ያሳንሳል፡፡

 

መስፍን አረጋ

mesfin.arega@gmail.com

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share