ለምንድን ነው የሴቶች ጤና እና ንፅህና መመሪያዎች ከግብረ-ሥጋ ግንኙነት በኋላ ሽንትዎን እንዲሸኑ ይነግሩዎታል? በዚህ አጭር መጣጥፍ፤ ከግብረ-ሥጋ ግንኙነት በኋላ ሽንት መሽናት፤ ከሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን (UTI) እና ከሽንት ፊኛ ጋር ምን ግንኙነት እንዳለው እናብራራለን።
ከግብረ-ሥጋ ግንኙነት በኋላ ለምንድነው ሽንቴን መሽናት ያለብኝ?
ከግብረ-ሥጋ ግንኙነት በኋላ ሁል ጊዜ ሽንት መሽናት ጥሩ ሀሳብ ነው። በተለይ ለሴቶች ጤና በጣም ጠቃሚ ነው። ለምን ጠቃሚ እንደሆነ ጥቂት ምክንያቶች እነዚህ ናቸው:-
የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን | Urinary Tract Infection (UTI)
የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን (UTI) በማንኛውም የሽንት ስርዓት ውስጥ የሚከሰት ኢንፌክሽን ነው። ለምሳሌ:- በሽንት ፊኛ፣ ዩሬትራ ወይም ኩላሊት ማለት ነው።
በአብዛኛው የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን የሚከሰተው ባክቴሪያዎች በዩሬትራ በኩል ወደ ሽንት ቧንቧዎ ውስጥ ገብተው ፊኛዎ ውስጥ መባዛት/መራባት ሲጀምሩ ነው። የሽንት ቧንቧዎ ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከል ሥርዓቱ ከከሸፈ ባክቴሪያዎች ሊያድጉና ኢንፌክሽን ሊያስከትሉ ይችላሉ።
ለሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን መንስኤ የሚሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው?
የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን በአብዛኛው የሚከሰተው በሴቶች ላይ ነው። የሴቶችን በዚህ በሽታ የመያዛቸውን አጋጣሚ ከፍ የሚያደርጉ አንዳንድ ነገሮች የሚከተሉት ናቸው:-
የሴት አናቶሚ (ተፈጥሮ) – የሴቶች ዩሬትራ (Urethra) ከወንዶች ያነሰ ነው። ይህም ባክቴሪያዎች ወደ ፊኛ ለመግባት የሚጓዙትን ርቀት ይቀንሳል።
የተወሰኑ የወሊድ መቆጣጠሪያ አይነቶች – ዳያፍራም እና/ወይም ስፐርሚሲድ (Spermiciidal) የወሊድ መቆጣጠሪያ የሚጠቀሙ ሴቶች በሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን የመያዝ እድላቸው ከፍ ያለ ነው።
ወሲብ የመፈጸም እንቅስቃሴ – የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ለመፈጸም ተቃራኒ ጾታ የሚቀርቡ ሴቶች በሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም አዲስ የወሲብ ጓደኛ ከያዙ ለአደጋ የመጋለጥ ህልውናዎ ይጨምራል።
ማረጥ – ከማረጥ በኋላ የኢስትሮጂን ሆርሞን መጠን መቀነሱ የሽንት ቧንቧ ሥርዓት ለውጥ ስለሚያስከትል ለኢንፌክሽን ይበልጥ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል።
በሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን የመያዝ አጋጣሚያችሁን ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ሌሎች ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው:-
የሽንት ቱቦዎች ጤናማ አለመሆን:- የሽንት ፍሰት መስተጓጎል የሚያስከትል የሽንት ቧንቧ ጤናማ አለመሆን ኖሮባቸው የሚወለዱ ሕፃናት፤ ለሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ይበልጥ የተጋለጡ ናቸው።
የሽንት ቱቦዎች መዘጋት:- በኩላሊት ወይም በፊኛ ውስጥ ያሉ ጠጠሮች ሽንት በፊኛዎ ውስጥ ተከማችቶ እንዳይወጣ ያግዳሉ። ይህም ለሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ያለንን ተጋላጭነት ይጨምራል።
በቅርቡ የተደረገ የሽንት ቱቦ ሥርዓት ህክምና:- የህክምና መሳሪያዎችን ያካተተ የሽንት ቱቦ/ቧንቧ ቀዶ ጥገና ወይም ምርመራ በሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን የመያዝን አጋጣሚ ከፍ ሊያደርግ ይችላል።
የካቴተር (Catheter) አጠቃቀም:- ሽንት ለመሽናት ካቴተር መጠቀም ዩቲአይ ለማዳበር የተጋለጠ ሊያደርግ ይችላል። ሆስፒታል ከገቡ፣ የሰውነት መስነፍ ወይም ሽባ መሆን ካጋጠመ፣ ሽንት የመሽናት ችሎታዎ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ የነርቭ ችግሮች ካሉብዎት ካቴተር መጠቀም ሊኖርብዎ ይችላል።
የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ምልክቶች እና መገለጫዎች የሚከተሉት ናቸው:-
በድንገት ሽንት ለመሽናት መጣደፍ
የሽንት ድግግሞሽ መጨመር (አነስተኛ መጠን ያለው ሽንት በተደጋጋሚ ሊሸኑ ይችላሉ)
ሽንት በሚሸኑበት ጊዜ የማቃጠል ወይም የህመም ስሜት
ደመናማ (ነጭ) ወይም መጥፎ ሽታ ያለው ሽንት
በሽንት ውስጥ ደም መኖር
በታችኛው የሆድ ክፍል አካባቢ የሕመም ስሜት
የድካም ስሜት
የጤነኝነት ስሜት አለመሰማት
በተለይ በአረጋውያን ላይ እንደ መረበሽ ወይም ከባድ ግራ መጋባት ያሉ የባሕርይ ለውጦች፤ የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ምልክቶች ናቸው።
የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ህክምና
የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ምልክቶችና መገለጫዎች ካጋጠሟችሁ ሐኪምዎን ያማክሩ። እነዚህን ለማከም አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች ሊታዘዝልዎ ይችላል።
የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ሕክምና ከጀመሩ በኋላ በአምስት ቀናት ውስጥ ምልክቶቹ መጥፋት ይጀምራሉ። የሕመሙ ምልክቶች ወዲያውኑ ቢሻሻሉም የታዘዙልንን ሁሉንም መድሃኒቶች በሙሉ ወስደን ማጠናቀቅ አለብን።
የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን መከላከያ ዘዴዎች
በሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የመያዝን አጋጣሚ ለመቀነስ የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ ይችላሉ:-
ብዙ ፈሳሾችን፤ በተለይም ውሃ ይጠጡ:- ይህ ደግሞ ሽንታችን እንዲቀጥን (Dilute) እና በተደጋጋሚ ሽንት እንድንሸና ይረዳናል፤ በተጨማሪም ከሽንት ቱቦ ሥርዓታችን ውስጥ ባክቴሪያዎችን ጠራርጎ ለማስወጣት ይረዳል።
የክራንቤሪ ጭማቂ (Cranberry Juice) ይጠጡ:- ምንም እንኳ የክራንቤሪ ጭማቂ መጠጣት የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን እንዳይከሰት ሊከላከል እንደሚችል የሚያረጋግጥ አንድም ጥናት ባይኖርም አንዳንድ ሴቶች ፍቱን እንደሆነ ይምላሉ።
የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ከፈጸሙ በኋላ ሁሌም መሽናትዎን ያረጋግጡ:- የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ከፈጸማችሁ በኋላ ከፊኛችሁ ውስጥ ባክቴሪያዎችን ለማስወጣት ይረዳል።
ሽንት ቤት ከተጠቀሙ በኋላ ከፊት ወደ ኋላ ይጥረጉ:- ይህም ባክቴሪያዎች ከፊንጢጣ ወደ ዩሬትራ እና ብልት እንዳይዛመቱ ይረዳል።
እንደ ዲዮዶራንት ስፕሬይ፣ ፓውደርና የመሳሰሉ የሴት ንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን መጠቀም እና ዶች (Douches) ማድረግ፤ ዩሬትራ እንዲያብጥና እንዲቆጣ ሊያደርጉ ስለሚችሉ ከመጠቀም ወይም ከማድረግ ተቆጠቡ።
የሚጠቀሙትን የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴ ለመቀየር ያስቡ:- ዲያፍራም ወይም ስፐርም ገዳይ መድኃኒቶች ያላቸውን ኮንዶሞች መጠቀም ባክቴሪያዎች እንዲያድጉ ሊያደርግ ይችላል።
የሴቶች ዩሬትራ | The Female Urethra
ዩሬትራ ከፊኛ ሽንትን ለማስወገድ የሚረዳ ቱቦ መሰል የሰውነት ክፍል ነው። የሴቶች ዩሬትራ (ከ2.5 እስከ 4 ሴንቲ ሜትር ገደማ) ከወንዶች (ከ15 እስከ 20 ሴንቲ ሜትር ገደማ) ያነሰ ነው።
ባክቴሪያዎች ወደ ሽንት ፊኛ ለመግባት አጭር ርቀት መጓዝ ብቻ ይጠበቅባቸዋል። ይህ ሁኔታ ሴቶች በሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን የመያዝ አጋጣሚያቸው ሰፊ እንዲሆን ያደርጋል።
የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ዋናው ምልክት ሽንት በሚሸኑበት ጊዜ በዩሬትራ ውስጥ የማቃጠል ስሜት መሰማት ነው። ይህ የማቃጠል ስሜት የሚመጣው፤ ባክቴሪያዎች በሽንት ፊኛ፣ በኩላሊት ወይም በዩሬትራ ውስጥ ሊያድጉ ስለሚችሉ ነው።
የሽንት ፊኛ | The Bladder
የሽንት ፊኛ ጤንነት በጾታዊ ግንኙነት (በሴክስ) ህይወታችን ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።
የሽንት ፊኛ የሚገኘው በዳሌ አጥንቶች መካከል ሲሆን ሽንትን ለመያዝ መስፋት ወይም መለጠጥ የሚችል ጡንቻማ እና ባዶ (Hollow) የሰውነት ክፍል ነው።
ፊኛዎ በሽንት ሲሞላ የእርስዎ የፊኛ ጡንቻዎች ይለጠጣሉ። ነገር ግን ሽንት የመያዝ ሙሉ አቅሙ ላይ ከደረሰ በኋላ፤ ፊኛን ባዶ ለማድረግ ወደ አንጎልዎ መልዕክቶችን ይልካል።
በወሲብ ወቅት ባክቴሪያዎች ወደ ዩሬትራ ሊገቡ ይችላሉ። ይህ ደግሞ በኢንፌክሽን የመያዝ አጋጣሚዎን ከፍ ያደርጋል። በዚህም ምክንያት ከግብረ-ሥጋ ግንኙነት በኋላ ሁልጊዜ ሽንትዎን መሽናት ያስፈልጋል። ከግብረ-ሥጋ ግንኙነት በኋላ ሽንት መሽናት ጀርሞችን ጠራርጎ ያስወጣል።
በተጨማሪም የሽንት ፊኛ ከሞላ በኋላ ወሲብ መፈጸም ስትረስ ዩሪናሪ ኢንኮስሲተንስ (stress urinary incontinence) የመያዝ አጋጣሚያችሁን ከፍ ያደርገዋል። እነዚህ ሁኔታዎች የሚፈጠሩት በዳሌ ወለል ጡንቻዎች እና/ወይም ደካማ በሆነ የዩሬትራ ስፊንክተር (weak urethral sphincter) ምክንያት ነው።
እንደ:- ሳል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ መሳቅ፣ ማስነጠስ ወይም ወሲብ በመሳሰሉ ትግበራዎች ጊዜ የሽንት ፊኛ ላይ ጫና ስለሚፈጥሩ ሽንታችን ሊያመልጠን ይችላል።
ከግብረ-ሥጋ ግንኙነት በኋላ ሁሌ ሽንትዎን ይሽኑ
ከወሲብ በኋላ በተለይ ለሴቶች ሽንት መሽናት ሁሌም ጥሩ ሀሳብ ነው።
የሴቶች ዩሬትራ (Urethra) ከወንዶች ያነሰ በመሆኑ ባክቴሪያ በቀላሉ ሊገባና የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሊያስከትል ይችላል።
የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ከፈጸማችሁ በኋላ በዩሬትራ ውስጥ የሚገኙ ባክቴሪያዎችን ለማውጣት ይረዳችኋል። ይህም የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽንን ለመከላከል ይረዳል።
መልካም ጤንነት!!
ኢትዮ ጤና