June 2, 2023
7 mins read

በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞን በመስጂድ ጊቢ ማሰማት ለሞት የሚያበቃ ወንጀል ነውን?

ኢናሊላሂ ወኢና ኢለይሂ ራጂኡን።

ከኡስታዝ አህመዲን ጀበል

ዛሬ በአንዋር መስጂድ የጸጥታ አካላት በምዕመናን ላይ የወሰዱት ድርጊት እጅግ አሳዛኝና አስደንጋጭ ነው። በሸገር ከተማ የተፈጠመውን መስጂዶችን በጅምላ የማፍረስ ደርጊት ሙስሊሙን ማኅበረሰብ ሲያስቆጣ መክረሙ ይታወቃል። መስጂዶቹ እንዳይፈርሱና ለፈረሱትም ምትክ ቦታ እንዲሰጥ የፌዴራል፣ የኦሮሚያና የአዲስ አበባ መጅሊሶች ባለፉት ሳምንታት ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ጥረቶች ተስፋ ሲያሳዩና መልሰው ሲባባሱ ቆይተው ሁኔታዎች ወደ አደባባይ ተቃውሞ ተቀይረዋል። የመንግሥት የጸጥታ አካላት ባለፈው ሳምንት ጁሙዓና ዛሬ ምዕመናንን ገድለውብናል፣ አቁስለውብናል። በርካቶችንም አስረዋል።

አንዋር መስጂድ
አንዋር መስጂድ

መንግሥት «እያካሄድኩት ነው» ባለው የጸጥታ ተቋማት የሪፎርም ሥራ ግርግሮች ሲከሰቱ ሰው ሳይሞት በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በጸጥታ አካላት አዳዲስ ኪህሎቶችና ዲሲፕሊን ሁኔታዎችን ማረጋጋት የሚያስችል ሁኔታዎች ተፈጥርዋል ተብሎ ከዚህ ቀደም ተነግሮን ነበር። እኔን ጨምሮ በርካታ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ አመራሮችና ታዋቂ ሰዎች የተገኙበት ጉብኝት ከዚህ ቀደም ወደ ፌዴራል ፖሊስ ተቋማት አድርገን ነበር። በጉብኝታችን ወቅት አድማ ብተና ልክ እንደ አደጉት አገራት ሰው ላይ ሞትና የከፋ አደጋዎች ሳይደርሱ የአድማ ብተና ስራ ለመስራት የሚያስችል አቅምና ቴክኖሎጂ እንደተገነባ ተገልጾልን ነበር።

ነገር ግን ባለፈው ሳምንትና ዛሬ በአንዋር መስጂድ የሆነው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው። የጸጥታ አካላት በቀጥታ ምእመኑ ላይ በመተኮስ ወደ ግድያ ነው የገቡት። እንደተባለው ሁከት ፈጣሪ አካላት ካሉ ውሃ በመርጨትና ጉዳት በማያደርስ መልኩ መከላከል ሲቻል ወደ ግድያ የሚገባበት ምክንያት ምንድን ነው?

አንዋር መስጂድ ጊቢ
አንዋር መስጂድ ጊቢ

ሌላው ሙሉ የአዲስ አበባ ከተማ የአንዋር መስጂድና አካባቢውን ጨምሮ አብዛኛውን የአዲስ አበባን ክፍል የፌዴራል ፖሊስ በካሜራ 24 /7(ዘወትር ለ24 ሰዓት) እንደሚቃኝ ይታወቃል። ይኽንን በጉብኝታችን ጊዜ ጭምር ሚክሲኮ ከሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ዋና ማዕከል ላይቭ ሲከታተሉ አሳይተውናል። ሂደቱንም በቪዲዮ እንደሚቀረጹ ና በማስረጃነት እንደሚያዝ በርካታ የአደባባይ ወንጀል ናሙና ቪዲዮዎችን አሳይተውናል። ይህ ማለት በየትኛውም የአዲስ አበባ ክፍል ግርግር ከተነሳ የግርግሩ ጀማሪ ማን እንደሆነና እንዴት እንደተጀመረ በትክክል መለየት ይችላሉ። በዚህም መሰረትም ግርግሩ የተነሳበትን ቦታና ማንነት ለይቶ የጸጥታ ማስከበርና ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር የማዋል ሥራ ከመስራት ይልቅ እየተመለከትን ያለነው ግን መላው ምዕመን ላይ መሳሪያ የመተኮስ አካሄድ ነው ።

ዛሬ በአዲስአበባ በአንዋር መስጊድ ውስጥ በፌዴራል ፖሊስ ብዙ ሺ ሙስሊሞች ታፍነው በመጨረሻ አካባቢ ሴቶቹ ውጡ ወንዶቹ ይቆዩ ሲባሉ የሙስሊም ሴቶች መልስ ምን እንደነበር ታውቃላችሁ? ከዚሁ ከወንድሞቻችን ጋር አብረን እናልቃለን እንጂ ጥለናቸው አንወጣም ‼️ አሏህዋአክብር
ዛሬ በአዲስአበባ በአንዋር መስጊድ ውስጥ በፌዴራል ፖሊስ ብዙ ሺ ሙስሊሞች ታፍነው በመጨረሻ አካባቢ ሴቶቹ ውጡ ወንዶቹ ይቆዩ ሲባሉ የሙስሊም ሴቶች መልስ ምን እንደነበር ታውቃላችሁ? ከዚሁ ከወንድሞቻችን ጋር አብረን እናልቃለን እንጂ ጥለናቸው አንወጣም ‼️
አሏህዋአክብር

የፌዴራል መጅሊስ ባደረገው ጥሪ መሰረት በዛሬው እለት የተቃውሞ አንቅስቃሴ በአንዋር መስጂድ እንዳልነበር ብዙዎች መስክረዋል። የጸጥታ ተቋሙ ተቃውሞ ነበረ ካለም ማስረጃ ይፋ ማድረግ አለበት። እንደው ተቃውሞ ነበረ አልያም ፖሊስ ሁሌም ቶክስ ለመክፈት «ድንጋይ ተወርዉሮብኝ ነው።» በማለት እንደው ጥቂት ሰዎች ድንጋይ ወርዉረው የነበሩ ቢሆኑ እንኳን ወርዋሪዎቹን በሚቀርጹት ቪዲዮ ለይተው በሕግ መጠየቅ እየተቻለ ነፁሓንን ሙስሊሞችን ጨምሮ በሺህ የሚቆጠረውን በመስጂዱ የሰገደውን ምዕመናንን እንዲሁም በዜናው ተደናግጦ የሚሸበረውን በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝበ ሙስሊምንና ሌሎች ኢትዮጵያውንን ማሸበር መች ወንጀል ሆኖ ያስጠይቅ ይሆን? በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞን በመስጂድ ጊቢ ማሰማት ለሞት የሚያበቃ ወንጀል ነውን?

ፖሊስ ሌሎችን ወንጅሎና ራሱን ንጹህ አድርጎ መግለጫ ስላወጣ አንዳች የማጣራት ሂደት ሳይደረግ ለጊዜው ተድበስብሶ ቢቀር እነኳ እውነታው ዘላለም ተደብቆ አይቀርም።

በመስጂዱ ጊቢ ውስጥ የነበረ ምዕመን ድምጹን ቢያሰማ እንኳ፣ ሕዝቡ ላይ በጅምላ መተኮስና ከመስጂድ እንዳይወጣ ፣ የሞቱና የቆሰሉና ሰዎች በአምቡላንስ እንዳይነሱ ለረጅም ሰዓታት መከልከል በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው የወንጀል ድርጊት ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop