ፕሮፊሰር መሥፍን እንዳሉት ” በዶ ቤት በቁንጫ ይወረራል ። ” እናም ሀገሬ ዛሬ በየትኛውም ተቋም ፤ በመንፈሳዊ ተቋማት ጭምር ፤ ምሁራኑ በሰበብ አስባብ ተጠርገው እየወጡ ፣ አሰስ ገሰሱ የአገልግሎት መድረኩን ይዞ መሪነትን የልጅ መጫውቻ ሲያደርገው እያሥተዋልን ነው ።
እስቲ ዓለማዊ ተቋማቱን ተመልከቱ ። በህግ አውጪው ፣ በህግ ተርጓሚው እና በህግ አሥፈፃሚው የመንግሥት ሥልጣን ተቋም ውሥጥ ያሉ ሰዎችን በአንክሮ አሥተውሉ ፣ 98% ለሆዳቸው የተገዙ ፣ ከራሥ በላይ ነፋስ በማለት ” ጎመን በጤና ! ” በማለት የሚሞዝቁ አይደሉምን ?
ህዝብ በየዕለቱ በሚያሻቅብ የዋጋ ንረት የተነሳ መኖር እያቃተው ነው ። በጣም ጥቂቱ በቀን ሦሥቴ የሚበለው ወደ ሁለቴ መብላት ተንከባሏል ። ጥቂቱ ሁለቴ ይበላ የነበረው ደሞ አንዴ መብላት ግዴታ ሆኖበታል ። የዕለት ጉርሱን ለማግኘት ተቀጥሮ የሚሰራ እና በቀን ሥራ የተሰማራው የሚያገኘው ለቤት ኪራይም አልበቃውም ። “… ባገኝም በልቼ ባጣም ተደፍቼ …” በማለት በገሃድ በለቅሶ ሲያዜም ውሎ ሲያዜም ማደሩን ቀየቀበሌው ያለ ካድሬና አጫፋሪ ወይም አሥገፋፊ ያውቃል ። ከአጠቃላይ ህዝቡ እጅግ በጣም ጥቂቱ ብቻ ነው ፤ በአፓርታይድ ፓለቲካዊ ሆያ ሆዬ እየዘረፈ ፣ ያለአግባብ ተጠቃሚ ሆኖ ያለፋበትን እየበላ በቁንጣን እየተቸገረ መኖሩን ዘወትር የምንመለከተው ።
አገሬ ፈፅሞ ኃላፊነት በማይሰማቸው በነዚህ እፍኝ በማይሞሉ የፓለቲካ ፣ የኢኮኖሚ የማህበራዊ ኑሮ ፅንሥ ሃሳብ ያልሰረፀባቸው ፤ ሆዳቸው ጭንቅላታቸው በሆነ ሰዎች እየተመራች ወደ መፍረስ እየተቃረበች ነው ። ታላቋ አገር ታሪክ ለመሆን እየተደረደረች ነው ።
ይኽንን ድርዳሮት ዛሬ የተነቃቃው አዲሱ ትንታግ ትውልድ ( በመከላከያ ውስጥ ያለውን ይጨምራል ) እንደሚቀለብሰው ባምንም ያለመሰዋትነት ሠላምሟዴሞክራሲ፣ፍትህ፣ነፃነት እና እኩልነት እንደማይመጣ ግን እገነዘባለሁ ።
በምጣኔ ሀብት አገር እየደቀቀች ፤ ዜጎች “ አገራቸው አገራችሁ አይደለችም “ እየተባሉ ከቀያቸው ሲባረሩ ፤ ሰውነታቸው ተዘንግቷ በቋንቋቸው ሲገደሉ ፤ የአፓርታይድ ሥርዓታችን ማን እንደሚኖርበት ና እንደሚዝናናበት የማይታወቅ የቅንጦት መዝናኛ ይገነባል ። ቤተ መንግሥትም በትሪሊዮን ብር ልሥራ ነው ብሎ በማንአለብኝነት ይነሳል ።
ዜግነት በዲንጋይ ራሥ ፓለቲከኞች ተክዶ በነፃ አውጪ ሥም አጋንንቶች በማህል አገር ተሠማርተው በጠራራ ፀሐይ ሰው የሚረሽኑበት ፣ የሚያርዱበት ምቹ ሁኔታ ከእውቀት በፀዳው መንግሥት ተመቻችቶላቸው ሣለ እና ህዝብ ጎመን አሮበት በረሃብ እየተሰቃየ ሣለ ፣ አምባገነኖቹ ፣ ህዳሙን የፓርላማ አባልና ሚኒስትር በሥጋ ምቾት ጠፍረው በቅንጦት ቤተ መንግሥት ግንባታ ላይ ለመሠማራት ዳር ሯ ዳር እያሉ ነው ። ይኽ ድርጊት የሚያሳየን አእምሮ ቢሥነት ብቻ አዬደለም ፣ ማን አለብኝነትን እና የህዝብ ንቀትን ነው ። ህውብ ተንቋልም ተዋርዷልም ።
እግዜር ያሳያችሁ ፣ ወታደራዊ ተቋማቱ አንዳችም ሎጀስቲክ ሣይኖራቸው ፣ የተከበረው ወታደር ህይወቱን ለህዝብ ለመሳዋት በሲኖ ትራክና በአይሱዙ እንደ እቃ እየተጫነ እያየን ፣ ህዝብን ካልናቁ እንዴት በቀን አንድ ጊዜ ህዝብን ማብላት ያቃተው መንግሥት ፣ በዘጠኝ ቢሊዮን ብር ቤተ መንግሥት ለመሥራት ተነስቻለሁ ብሎ ይለፍፋል ። ይኼ ያለማፈር ነው ። የሚኒሥቴሮች ምክር ቤት እንደሌለ እንቁጠረውና ? ፓርላማው ( የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ) እንዴት ዝም ብሎ በህግ ያልተደገፈ ተግባሩን ይመለከታል ? ( ጠቅላዩ እናንተን አይመለከትም ለምኜ ነው ፣ ያገኘሁት እያሉ ሲናገሩ ፣ የመለመን ፈቃድ ማነው የሰጣቸው ? ህገ መንግሥቱ ላይ የፀደቀ የልመና ህግ አለን እንዴ ? ጠቅላዩ ራሳቸውን ንጉሥ ካላደረጉ በሥተቀር ፓርላማው ሳይፈቅድላቸው ህግ ፣ መመሪያና ደንብ ሳያግዛቸው በአምባገነንነት በኢትዮጵያዊያን ምድር እንደአሻቸው ከህግ ውጪ የመጋለብ መብት የላቸውም ። )
በገልባጭ “ ሲኖ ትራክ “ እና በጭነት አይሱዙ የሚጓጓዙ ፣ በቂ አልባሳትና ሥንቅ የሌላቸው የመከላከያና የፖሊስ አባላት እያሉን ፣ “ በ9 ቢሊዮን ዶላር የፊደራል መንግሥት ቤተ መንግሥት እሠራለሁ ። “ ማለት እብደት አይገልፀውም ። ከዚህ አንፃር “ ቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ከዛሬው የኢትዮጵያ ጠ/ሚ ወይም “ ራሱን ንጉሥ ካደረገው “ ከአብይ አህመድ የባሰ ግፍ በወታደሩ ላይ አልፈፀሙም ማለት ይቻላል ። “ ብለን ብንናገር ሐሰት የሚል አንድም ሰው በዓለም አይገኝም ። ንጉሥ ቀዳማዊ ግርማዊ ጃንሆይ “ በሥንቅ ፣ በትጥቅ ፣ በሎጀሥቲክ ወታደሩን አልበደሉም ። ወታደሩን እንደ ዕቃ በሲኖ ትራክ እና በአይሱዙ አልጫኑም ። በደረቅ ኮሾሮ ለቀናት አላስራቡም ። የተጋነነ ኢ ሰብዓዊነት በአገዛዛቸው የታየው በሥልጣናቸው ለመጡባቸው ብቻ ነበር ። “ አቶ ሽመልሥም ቢሆን የኦሮሞ ህዝብ በችጋር ውሥጥ እያለ ፣ በመጠጥ ውሃ ችግር ጉሮሮው እየተቃጠለ እና ከእንሥሣ ጋር እየጠጣ ፣ የ3 ቢሊዮን ቤተ መንግሥት ለመገንባት መነሳታቸው ፣ ማንን ለማሥደሠት አስበው ነው ? በውስጡ የመኖር ህልም ያላቸው ከቶ እነማን ናቸው ?
አቶ ሽመልሰሰ ለመሆኑ “ ሚዶ ለመላጣ ምን ይሰራለታል ? “ ብለው ነው ?
ሃቁ ሁለቱም ህዝብ አገልግሉን ያላቸው መሪዎች ፣ ከህዝብ አሁናዊ ፍላጎትና ዘላቂ ጥቅም አንፃር ሣይሆን ከውጪ ሀብታሞች የወደ ፊት ህልም አንፃር ነው ቤተመንግሥት ለመገንባት ያቀዱት ። ቤተመንግሥታቸው በዛሬው የአፓርታይድ ሥርዓት እውን ከሆነ ግን ” የአውሬ መፈንጫ ” ይሆናል እንጂ ወደፊት ሰው ሊኖርበት አይችልም ።
በበኩሌ ወታደሩ ሮቦት ካልሆነ በሥተቀር የአብይንም ሆነ የሽመልስን የእብድ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን አይፈቅድም ። በሠላም ጊዜ ፣ የተሟላ መቀመጫ የሌለው ።… በቂ ማደሪያ ቤት ንፁህ አንሶላና ፍራሽ ይቅርና ፣ ምግብ ፣ መጠለያ ና ልብስ በወቅቱ የማያገኘው መከላከያ በተቀደደ ዩኒፎርም አገርን እያገለገለና ፤ እየተራበና እየተጠማ ፣ በሲኖትራክ እየተጫነ ፣ ይህንን የዕብድ ሥራ በዝምታ በማለፍ ቢሊዮን ዶላሮችን እነአብይ ሲያቃጥሉ ዝም ብሎ ያያቸዋል ብዬም አላሥብም ። መቼም አገር በቁንጫና በትሆን መወረሯን የሚያጣው አይመሥለኝም ።
ሌላው የዚች አገርን በቁንጫ እና በትሆነ መወረር የሚያሣዩን የእምነት ተቋማት ናቸው ። በተለይም ዛሬ የኦርቶዶክስ ኃይማኖት በአንዳንድ ፃድቅ ፣ ብፁዕ በተሰኙ በተግባር ግን የዳቢሎስ ልጅ በሆኑ ፣ በዓለማዊ ሥልጣን ጥም በናወዙ ፣ እግዚብሔርን በካዱ ዘረኞች ክብሯ እየተደፈረ ብቻ ሣይሆን ዓለማዊ እንድትሆን እየተገደደች ነው ።
እነዚህ ጳጳስ ነን ፣ ሥልጣነ ፈጣሪ አለን የሚሉ ሆኖም ግን በሥልጣነ ዳቢሎስ የሚመሩ ዘረኞች የሰውን በዘፍጥረት አንድነት በመካድ በጎሳው ከፋፍለው ገንዘብ መሰብሰቢያ ሊያደርጉት ቆርጠው ተነሥተዋል ። በትግራይም ፣ ኦሮሚያ በተባለው ክልልም ።
የትግራዮቹ እሥከ አሜሪካ ድረሥ ጳጳስ እንሾማለን ብለዋል ። የኦሮሚያዎቹ ደግሞ እሥከ ደቡብ የኦርቶዶክስ አገረሥብከት ጳጳሳትን ለመሾም አሥበዋል ።
እኔም እላለሁ ፣” እውነተኞቹ ለእግዚአብሔር የተገዙ የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ልጆች ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቅዱስ ፓትርያርክ እውቅና ባልተሰጣቸው ጳጳሶች በሚመሩ ቤተክርስቲያናት ውስጥ እግራቸው ለመግባት እንደሚጠየፍ ይወቁት ። “ ይኼ ከወዲሁ ሊነገራቸው ይገባል ። ምእመናኑ የሤጣን መሥቀል የሚሳለምበት አንዳችም ግዴታ የለበትም ።
በዛሬው ዓለም ሴጣን ዘመናዊ ሆኖ መምጣቱንም በዚህ አጋጣሚ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ልጆች ሁሉ ተገንዘቡ ። በዚህቺ ምድር የምትኖሩት አንዴ እንጂ ሁለቴ አይደለም ። ለፈጣሪ ታምነን ለመሞት እና የድል አክሊል ለመጎናፀፍ እንነሣ !!
አብይም ሆነ ሽመልስ ሰዎች ናቸው ። ትላንት ህፃን ነበሩ ። እድገታቸውም እንደብዙዎቻችን ደሃ ኢትዮጵያዊያን መሆኑ ይታወቃል ። ከሰማይ የወረዱ መልዕክት አይደሉም ። የመንግሥት ሥልጣን ላይ በአጋጣሚ … ሥለወጣ ማንም መለኮታዊ ኃይልን አይጎናፀፍም ። ዘላለማዊ ህይወትም የለውም ። ፈረሽ ገላ ተሸክሞ የሚዞር ነው ። ሞት አይቀርለትም ።
“ከቶ አይቀርም ሞቱ ፣ ምንም ቢታክቱ ፣ ምን ቢሰነብቱ ! … “ ከመሞታቸው አስቀድሞ ግን አሁን እንደሚያደርጉት ፣ ጥቂት ለሆዳቸው ያደሩ ፤ እንደ ቀኃሥ የአገዛዝ ዘመን አይነት “ ባሮች “ ከጎናቸው አሠልፈው አብይና ሽመልሥ ሊመፃደቁ ይችላሉ ። ነገ እነዚሁ ባሮች መጠቀሚያነታቸውን ያወቁ ጊዜ ግን አፈሙዙን ወደ እነሱ እንደሚያዞሩ አልጠራጠርም ። በትግራይም እንዲሁ ነው የሚሆነው ። የአፍሪካ “ ማን ከማን ያንሣል ? “ ጫዎታ በኢትዮጵያም ይጀመራል ። ዛሬ ጨዋውን የትግራይ ሰው ፕሬዝዳንት ሆኖ እየመራ ያለው ማን ነው ? በእምነትስ እንደትግራዋይ ያለ ኩሩ ነበር እንዴ ? ዛሬ ፈጣሪን ክዶ ካድሬ የሆነ ጳጳስና ቄስ ምን ይባላል ? ይኽ ለትግራይ ህዝብ ሞት ነው ። ከእምነት ታሪክ አንፃር ፣ ፈጣሪውን ዘግይቶ ካወቀው ይልቅ ፣ የቁጣ እሣት የሚዘንበው በትግራይ ህዝብ ላይ መሆኑን መገንዘብ መልካም ነው ።
በበኩሌ እጅግ የማዝነው “ ጊዜ የሰጠው ቅል ዲንጋይን ሲስብር “ በማየቴ ብቻ ሣይሆን ኃቀኛ የሆነ ፣ ምሁር ፣ ጥበበኛ ና አዋቂ ከኢትዮጵያ ተቋማት ቁልፍ ቦታ ሁሉ ድርሽ እንዳይል ተደርጎ ፣ ቤቱን ማሥተዳደር የማይችል ግብዝ ሁሉ ከቀበሌ ጀምሮ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ተቀምጦ ፣ ዘወትር ለከርሱ ብቻ በማሠብ ደሃን ሲበድል ፣ሲዘርፍ ፣ ሲያሥለቅስ ና ሲገድል በማየቴ ነው ። ኢትዮጵያ በዚህ አምሥት ዓመት ብቻ 40 ዓመት ወደ ኋላ ሄዳለች ። ከሞራል አንፃር ደግሞ ከደርግም ከወያኔም የባሱ ጥቂት እፍረተ ቢሥ አመራሮችን አፍርታ ወደፊት አምጥታለች ። ይኽንን ግን በሚሊዮን የሚቆጠረው ጨዋና ኩሩው ወጣት ኢትዮጵያዊ ! በቃ ! ሊለው ይገባል ።
እውነት ነው ፣ ” በዶ ቤት የቁንጫ መራቢያ ነው ። ” ደሞም በበገና ዝማሬ ድምፅና ቁንጫ ባዶቤት ይወዳል ፤ ያትልቅ ወንበርም በትሆን ተሞልቷል ። ” ተብሎ ሲዜም ሰምተናል ። እናም ቤታችንን ከቁንጫና ከትሆን ለማፅዳት ሳይረፍድብን መነሳት አለብን !!