ኢትዮጵያ ባለም መናቅ የያዘችው፣
ሴቶች ወንድን መምረጥ ያቋረጡ እለት ነው፡፡
እንደተባረኩት እንደ አያቶቻችሁ፣
ወንድ መምረጥ ጀምሩ ሴቶች እባካችሁ፡፡
እንደ ሸክላ ገላ እንደ ፈረንጅ ሴት፣
ፍርክስክስ አትበሉ በጅንጀና ስብከት፡፡
የሴት ልብ ሲገዛ ገንዘብና ስልጣን፣
ወንዱም ተሰለበ አፍርጦ ቆለጡን፡፡
እናት እህቶቼ አትሳቱት ይህን ሀቅ፣
ጀግናን የምትወልድ የምትፈጥረውም ሴት፡፡
ደረቱ የሰፋን መለኮ ተውና፣
ልቡ የተነፋ ተከተሉ ጀግና፡፡
አሙለጭላጭ ደንደሳም ከሚታከካችሁ፣
ተያዘ እማይለቀው ይሁን ምርኩዛችሁ፡፡
ቅልስልስ ልምጥምጥ ያለውን ተውና፣
ቆፍጠን ብሎ እሚሄድ ተከተሉ ጀግና፡፡
ቀጣፊ ቀላማጅ ከሀዲን ትታችሁ፣
በቃሉ አዳሪውን አርጉ ትራሳችሁ፡፡
አሳማውን ጅቡን ሆዱን ዘርግፋችሁ፣
ከአንበሳው ከነብሩ ይሁን ትዳራችሁ፡፡
መሐል ወላዋዩን መሬት አንጥፋችሁ፣
ቀጥ ያለውን ጎበዝ አርጉ መቋሚያችሁ፡፡
እጅ አስታጣቢውን አድርጋችሁ አሽከር፣
በአደባባይ ታዩ ከደም መላሹ ጋር፡፡
እግር አጣቢ አጪታ ከተሞሸረቸው፣
ትሻል ቆሞቀሯ በክብር የኖረቸው፡፡
ከድፍድፍ ከሊጡ ከምትጣበቁ፣
እንደ አቃቤ እማሆይ መንኩሳችሁ ኑሩ፡፡
እንደ አያቶቻችሁ ወንድን ስትመርጡ፣
ጡርቂም ይጀግናል እንኳንስ ደፋሩ፡፡
ኢትዮጵያ እንድትሆን ዳግም ያገር አውራ፣
በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ፣
ሴቶች ወንድ ምረጡ እህቶቼ አደራ፡፡
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ጥቅምት ሁለት ሺ አስራ አንድ ዓ.ም.