ያዩትን ወይስ የሰሙትን ማመን ይቀላል? – አሰፋ በድሉ

ጽሁፋ ረጅም ነው፡፡እየጻፍሁ እያለ ሌላ ግፍ ሰማሁ፡፡ስላለፈውም ስለ አሁኑም ስሜቴን ለማጋራት ስሞክር ጽሁፋ ረዝሞ አገኘሁት፡፡በመጀመሪያ ለወ/ሮ አዳነች አቤቤ ሳታማኸኝ ብላ የሚለውን የጎሳየን ዘፈን ጋብዙልኝi ለካ የጌታ ሰው ናቸው፡፡ ሃጢያት ይሆንባቸዋል፡፡ ዘር ማጥፋት ግን ለእሳቸው ጽድቅ ነው፡፡ ዋና ዋና የሚባሉ ሚዲያወች ኦነግን ማጋለጥና ግፋን መዘገባቸው መልካም ሆኖ ሁሌ ምሬት ብቻ ማስተጋባቱ ችግሩ ላይ ብቻ ማተኮሩ መፍትሄውን አያርቀውም ወይ? መውጫ መንገዱን የሚያመላክቱ ምሁራንም፤የትግል መሪወችን ጋብዞ እንዲደመጡ ማድረጉ ይረዳል እላለሁ፡፡ ኦነግ ስል በአሁኑ ሰዓት ሁሉም የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች የኦሮሞ ብልጽግናን ጨምሮ የኦነግን ግብር እየሰሩ ስለሆነ ኦነጋውያን እንላቸዋለን፡፡በግለሰብ ደረጃ አልፎ አልፎ የማይተባበሩ አሉ፡፡ ብልጽግና ወይ በሀሉት ማኒፌስቶ ነው የተወዳደረው፡የመጀመሪያው ለምርጫ ያቀረበው ሌላው ደግሞ በውስጥ የተወሰነ የኦነግ ፕሮጄክት ወይ ደግሞ ብልጽግና ከምርጫ በኋላ በኦነግ ተጠለፈ እንበል አውነቱን የሚያውቀው አብይና አንድየ ብቻ ይመስሉኛል፡፡ኦነግ ግብሩ፤ጠባዩ የተገለጠ ፤ የታወቀ ነው፡፡ይኸውም ዘረኝነትና ጥላቻ መላ ነፍሱን የተቆጣጠረው ነው፡፡ይህንን ዘር በማጥፋትና ዘር በማጽዳት እየገለጸው ነው፡፡ለዚህ ማስረጃ አቅርብ የሚለኝ የለም፡፡ጎረቤቶቹ ምን እንደሆኑ ራሱ የኦሮሞ ህዝብ ያውቃልና፡፡ኦነግ የትግል መነሻው ውሸት መሆኑ የሚታወቀው በአጨራረሱ ነው፡፡ መጀመሪያ በቅኝ ግዛት ውስጥ ነኝ አለ፡፡ እናም ነጻ አገር እመሰርታለሁ አለ፡፡ቅኝ ከመያዝህ በፊት አገርህ ማን ይባል ነበር ቢባል መልስ የለውም፡፡የውጊያው ነገር አላዋጣ ሲለው በቋንቋየ፤በራሴ በእውነተኛ ፌደራሊዝም አልተዳደርሁም አለ፡፡ ቋንቋውም ክልሉም ተሰጠው፡፡

እውነተኛ ፌደራሊዝም አይደለም አለ፡፡ ከዚህም ያለፈ ኢትዮጵያን ምራ ተብሎ ታዝሎ አራት ኪሎ ገባ፡፡ በነገራችን ላይ የኦነግና የወያኔ ትግላቸውም፤ፍቅራቸውም፤ጠባቸውም የታወቀ ነው፡፡ ኦነግ አድሜ ዘመኑን ወያኔን ታግሎ ያውም በውጭ ሃይሎች እየታገዘ ከወያኔ ላይ አንድ ቀበሌ መውሰድ አልቻለም፡፡ወያኔ ማን ከአራት ኪሎ እንዳባረረው ያውቃል፡፡ለዛ ነው ሞታችን ሰርግ የሆነለት፡፡ወደ ነገሬ ልመለስ፡፡ ኦነግ በል እንግዲህ ተበድያለሁ ስትል ነበርና ያንተን አስተዳደር ደግሞ አሳየን ተባለ፡፡ በሉ እንግዴህ የባህል ልብስ የሚለበሰው የእኔ እንጂ የእናንተን መልበስ አትችሉም አለ፡፡መኪና ላይም ባህላችሁን እንዳላይ አለ፡፡ሃይማኖት ማምለክ የሚቻለው የእኔ እንጂ የእናንተ አይደለም አለ፡፡ሰንበት ተማሪወችን በዝማሬ ላይ እያሉ ተኮሶ ገደለ፡፡ ብሔራዊ በዐል ማክበር አትችሉም አለ፡፡ከለከለም፡፡ተኩሶም ገደለ፡፡ቅርስ፤ታሪክ የእኔ እንጂ የእናንተ መደምሰስ አለበት አለ፡፡በአፍ መፍቻ የሚማሩ የእኔ ልጆች እንጂ ለእናንተ ልጆች ኦሮሞኛና የኦሮሞኛ መዝሙር ነው መማር ያለባቸው አለ፡፡ ይህ ሁሉ አላረካውም፡፡ከከተማውም፤ከገጠሩም ውጡልኝ አለ፡፡ ቻው እያለም ተሳለቀ፡፡ ቤታቸውንም በለሌት እያፈረሰ ለአውሬ ሰጣቸው፡፡ይህም አላረካውም፡፡በመጨረሻ ከምድሪቷ ብትጠፋስ ብሎ የዘር ማጥፈት አዋጅ አወጀ፡፡ምግብ በመከልከል ጀምሯል፡፡ ውሃም ያክልበት ይሆናል፡፡የህግ ነገር ስለቀረ እንጂ ፌደራል መንግስቱን የመሰረቱት ክልሎች ግዴታ የለባቸውም ወይ? ይሄን ልርሳው፡፡ እኛስ እናምናለን አንጠፋም፤ መከራ ግን አለብን፡፡ መከራውንም የጋበዝነው እኛው ራሳችን ነን፡፡ ይህንን መከራ ለመቀበል የሃይማኖት አባትም፤የአባት አርበኛም መካሪ ያስፈልገናል፡፡ ኦነግ ጥያቄው ከመጀመሪያውም የፍትህ፤የእኩልነት አልነበረምና  አስተዳድር አይደለም ግዛ ቢባል አሻፈረኝ አለ፡፡ ኦነግ ጥላቻ ነው ፖሊሲው፡፡ ይህንን በይፋ የሚቃወም የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅት ስላልሰማን ስማቸው ቢለያይም በግብራቸው ኦነጋውያን እንላቸዋለን፡፡ የዛሬው ጽሁፌ ከርዕሴ ጋር ባይሄድ ይቅርታ እላለሁ፡፡በመሃል አዳነች መጣብኝ ነው፡፡ ወደ ሌላ ልሻገር፡፡

እስኪ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ራሳችንን እንጠይቅ፤እንመርምር፡፡ ኢትዮጵያ ህልውናየ ናት ብሎ የሚያምነው ህዝብ ለምንድን ነው አገሩን በሚያፈርሰው ድንኳን ውስጥ አብሮ መዶሻ የሚያቀብለው፡፡ አትዮጵያውያን አየር መንገድን ጨምሮ፤ንግድ ባንክን፤ አባቶቻችችን ደግሞ አፍሪካ ህብረትን መስርተው መቀመጫውን አዲስ አበባ እንዲሆን አድርገው ዛሬ ከአለም ውስጥ ከፍተኛ የሆነች የዲፕሎማቲክ መቀመጫ አንድትሆን አድርገው፤መላው ኢትዮጵያ ሃብታቸውን በቀጥታም በተዘዋዋሪም ያፈሰሱት አዲስ አበባ ነው፡፡ ህወሃት እንኳን ሰማይ ጠቀስ ህንጻወች ለምሳሌ ወጋገን ባንክን ጨምሮ ዘርፎም ቢሆን አዲስ አበባ ውሥጥ ገንብቷል፡፡ ህወሃት ስልጣን እስከሚለቅ ከአገሪቱ ኢንቨስትመንት ውስጥ 85 በመቶ አካባቢ የሚሆነው አዲስ አበባና ዙሪያው ነበር ኢንቨስት የሚደረገው፡፡ በዕውነቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አዲስ አበባን ገንብቷታል፡፡ ታዲያ የምናየው ከበባ፤አትገቡም አትወጡም፤ምንድን ነው እየነገረን ያለው? ሁሉም የኦሮሞ ፓርቲወች ኦነግ ከውጭ እንደገባ አካባቢ አዲስ አበባ ባለቤትንነቷ ለኦሮምያ ነው ብለው በይፋ ነበር ያወጁት፡፡ኦህዴድ አጋርነቱን በወቅቱ ካልተሳሳትሁ በም/ፕሬዘዳንቷ በኩል ይመስለኛል የገለጸው፡፡ በወቅቱ ብአዴንን ጨምሮ ሁሉም ከህወሃት ውጭ ያሉ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዋና ከተማ ናት የሚል መግለጫ ማውጣታቸውን እናስታውሳለን፡፡የደቡብ የድርጅት መሪ ሙፈሪያት ነበረች፡፡ህወሃት ምን ያህል ተንኮለኛ ድርጅት እንደሆነ በዚህ ብቻ መታዘብ ይቻላል፡፡ ህወሃት ከማንም በላይ አዲስ አበባ ሃብት አለው፡፡ሃብቱንም በእጅጉ ይፈልገዋል፡፡ግን በተቃርኖ የተሞላ ድርጅት ነው፡፡ በወቅቱ አብይ ሁሌም እንደሚያደርገው የማምታታቱን አካሄድ ነበር የመረጠው፡፡ አብይ አዲስ አበባ የእገሌ የእገሌ ከምንል እስኪ መጀመሪያ ውብ እናድርጋት፤እናልማት ነበር ያለው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ድንቄም ምርጫ! “ልመርጥ” ሄጄ ሳልመርጥ ተመለስኩ - ግርማ በላይ

የአማራ ህዝብም ዕድል ፈንታው ኢትዮጵያ ናት፡፡ሌሎች ብሔሮችም ከኦነጋውያን ውጪ ኢትዮጵያ ብትፈርስ እንደሚጎዱ ያምናሉ፡፡ግን ለምን የፖለቲካ ጾመኛ ሆኑ? ጉራጌ ትግል መጀመሩ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ቢያንስ የኑሮ ውድነቱ እኩል እየደቆሰው አይደለም ወይ? ተቃዋሚ ፓርቲወች አገራቸውን ለማዳን መቀራረብ የለባቸውም ወይ? በዕውነት የምናየው ነገር ይህንን እንድታደርጉ ግድ አይልም ወይ? በኋላ የደርግ ፖለቲከኞችና ወታደርች እንዳደረጉት ለቁጥር የሚያታክት የቁጭት መጽሃፍ ብትጽፋልን ምን ይረባናል? ለምንድን ነው አገራችን ስትፈልገን የምንደበቀው? እንደ ጋሽ ታዲዮስ አገር አፍራሾቹ እውነትን እንዲጋፈጡ አናደርግም፡፡ሁሉም ከግለሰብ ጀምሮ አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላል፡፡አብርሆት ነው የሚያስፈልገው፡፡ በእውነቱ ዛሬ መጻፍ የፈለግሁት ስለ አዲስ አበባ አልነበረም፡፡ይልቁንም ወደ ውስጥ እንደ ግልም እንደ ቡድንም እንደ አገርም በተለይ ኢትዮጵያ ህልውናየ ናት የሚለው ምናልባትም ወደ 80 በመቶ የሚጠጋው እንዴት በየኣዳራሹ ተበታትኖ አይኑ እያየ አዲስ አበባ፤ኢትዮጵያ እጁ ላይ እንደ ጨው ሲሟሙ አያስተውልም/አያይም ወይ? የምናየውን አናምንም ግን የምንሰማውን እንድናምን እባካችሁ መስማት የምንወደውን ንገሩን የሚል የትግል ሽሽት አባዜ በግልም ፤በጋራም ይስተዋላል፡፡ ይህ በተለይ ጠ/ሚ/ሩን የሚደግፋት ላይ የሚጎላ ጠባይ ነው፡፡አብይ እግዜር ይስጠው ትንሽም እንኳን ሰበብ ነስቷቸዋል፡፡ለዚህም ነው ህሊናቸውን ለመደፍጠጥ ይመቻቸው ዘንድ ከምናየው ይልቅ መስማት የምንፈልገውን ተናገርልን የዘወትር ተማጽኖ የሆነው፡፡በዚህ ረገድ የስነ-ልቦና ምሁራን ፤የማህበረሰብ ተመራማሪወች ፤ የታሪክ ምሁራን በራሳቸው ጉዳይ ለምን እንደለገሙ በእውነቱ ራሳቸውም አጥኝ ይፈልጋሉ፡፡እነ ፕ/ር ሃብታሙ ተገኝ፤ፕ/ር አቻሜለህ ታምሩ፤ፕ/ር ሃይሌ ላሬቦ ፤ፕ/ር ጌታቸው ሃይሌ፤ጋዜጠኛ እና የታሪክ ተመራማሪ ጋሽ ታዲዮስ ታንቱ፤ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም(አፈሩን ገለባ ያርግላቸው) እና ሌሎችም ውለታቸውን መዘንጋት አይገባም፡፡ ድካማችሁም እንዲሁ የቀረ አይደለም፡፡የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ ያ ሁሉ ፕሮፌሰር እና ተመራማሪ በሃሰት ትርክት የሆነው ሁሉ ሲሆን ለስሙ ያህል እንኳን አንዲት ኮንፈረንስ ማዘጋጀት አልፈለገም፡፡ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ማህበሩ በፕሬዘዳንቱ ዶ/ር ገበያው ጥሩነህ ስለታፈነ ነው፡፡ ሌላው አቶ ብናልፍ አንዷለም ነው ይህ ሰው፡፡በዘር ማጥፋት ወንጀል ከተባበሩት ውስጥ ናችሁና ቢዘገይም ከተጠያቂነት አታመልጡም፡፡ወገናችሁን፤አገራችሁን በምስር ሸጣችኋልና፡፡

የህልውና ጉዳይ ስለሆነ ምሁራዊም ባይሆን የተሰማንን ማካፈል ተገቢ ነውና ይህን የሚያዩትን፤የሆኑትን ትቶ የሚሰሙትን ለማመን የመፈለግ አባዜ ለምን ተጠናወተን ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ምክንያቱም ይሄ ጤናማ ስላይደለ ትግሉን በእጅጉ ይጎዳል፡፡ለዚህ መነሻ የሆነኝ የዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ መግለጫ ነው፡፡ይህ የጋራ መግለጫ የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋትን ጨምሮ ሃያ ሶስት ታላላቅ ወንጀሎችን እና ጥፋቶችን ከዘረዘረ በኋላ በመጨረሻ ማጠቃላያው ወይም ጥሪው የዘረዘሩትን ማመን ትተው መስማት የሚፈልጉት እንዲነገራቸው ለአብይ ልመና በማቅረብ ዘግተውታል፡፡ ከአውድ ውጭ እንዳላቀርበው ማጠቃላያው ይኸውና”በሰከነና በእውነት መንፈስ የሚወሰዱ እርምጃዎች ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ባለድርሻ አካላት አሳትፎ ሀገራችንን ለማዳን በአስቸኳይ ስራ እንዲጀመር አጥብቀን እናሳስባለን።” ይላል፡፡ ሺህ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ እንዲሉ  ያንን ሁሉ ወንጀል ዘርዝረው በመጨረሻ በማሳሰቢያ ነው ያሰሩት፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለኢትዮጵያ ባለስልጣናትና ፖለቲከኞች ሁሉ ለራሳችሁ ስትሉ ተለመኑ - ሠርፀ ደስታ  

በአንድ አጋጣሚ ሳይሆን በየዕለት ዕለት ያለማቋረጥ፤ያለ ፋታ እየተከሰተ ያለን ወንጀልና በአገር ህልውና ላይ የተጋረጠን አደጋ ይህን መሰል ጥሪ ነው ወይ የሚመጥነው ብለን እንጠይቃለን? ታዲያ ለዚህ የማያባራ ወንጀል ወንጀሉን መዘርዘርና ማሳሰቢያ መስጠት ይመጥናል ወይ? ከባድ ምርጫ አይደለም ከተጎጂወችና ከወገናችሁ ጋር መቆም ነው፡፡ ደግሞም ህዝባችሁንና አገራችሁንም መታደግ የምትችሉት በማሳሰቢያ ሊሆን አይችልም፡፡ ይሄ ጊዜው አልፏል፡፡በጦርነቱ ወቅት በተለይም ህወሃት ጠንከር ባለበት ወቅት ቢያንስ መስማት የምንፈልገው ይወራልን ነበር፡፡ አሁን ግን እናንተን ጨምሮ ሁላችንም ጊዜአችንን የጨረስን ይመስለኛል፡፡ ከማሳሰቢያ ያለፈ ትግል ለማድረግ ዝግጁ ካልሆናችሁ አረፋችሁ ተቀመጡልን፡፡ እንደ አባቶቻችን በክብር፤በጽናት መከራችንን እንቀበልበት፡፡አሁን መስማት የምንፈልገው ቅ/ጊወርጊስ ይመጣል አይዟችሁ፤አትሽሹ የሚል አጽናኝ ድምጽ ነው፤ከሞትንም ሞታችን የክብር እነዲሆን ነው፡፡ላይምረን ነገር አምባገነን ጫማ ስር ወድቀን መማጸን ያተረፈልን የገዳያችንን ትዕቢት መጨመርና መሳለቂያ መሆን ብቻ ነው፡፡ዛፍ እተክልላችኋለሁ አይደል የተባልነው፡፡በሹክሹክታ አይደለም በይፋ በፓርማ ፊት እንጂ፡፡ ከሰደበኝ ስድቡን የነገረኝ አትሁኑብን፡፡አሁንም አብይ ላይ የተጠያቂነት ቃላት መሰንዘር ቀርቶ በመግለጫው የተዘረዘሩትን (ለአብይ ለማስታወስ መሰለኝ)  ድጋፎች እንኳን ለማቋረጥ እንገደዳለን የሚል ዐረፍተ ነገር የለበትም፡፡ታዲያ ይህ መግለጫ ለተጎጂወች እና ለትግሉ ርባናው ምኑ ላይ ነው? ለአብይ ዛሬም ከጎንህ ነን ግን አስተካክል የሚል የድጋፍ ማረጋገጫ መልዕክት ነው የሚመስለው፡፡ይህ ማለት በአብይ ገና እምነት አላቸው ማለት ነው፡፡ምን ሲሰራ ነው ድጋፋቸውን የሚተውት? የሚያዩትን ወይስ የሚሰሙትን ነው ማመን የሚፈልጉት? በትንሹ እንጠብቅ የነበረው መግለጫ ለተሰሩት ወንጀሎችና ጥፋቶች ተጠያቂነት የማይሰፍን ከሆነ፤እነዚህ እነዚህ ተብለው ተጠቅሰው በቀነ ገደብ ውስጥ የማይስተካከሉ ከሆነ ድጋፋችንን ማቋረጥ ብቻ ሳይሆን ከተጎጂወችና ከህዝባችን ጎን በመሰለፍ ይህንን መንግስታዊ ወንጀል የምንታገለውና በዲሞክራሲያዊና ህጋዊ ስርዐት እንዲተካ በጽናት የምንታገል መሆናችንን አንገልጻለን ነው፡፡ከዚህ ያነሰ መግለጫ ከድጋፍ አይተናነስም፤በተጎጂወችም ቁስል እንጨት መስደድ ነው፡፡ ቪዢን ኢትዮጵያ በተናጠል ትክክለኛ መግለጫ በጋራ ከተሠጠው በኋላ ሰጥቷል፡፡አቋም ስለወሰደ ፤ከግፋዓን ጎንም ስለቆም ሊመሰገን ይገባል፡፡

 

ምን አልባት የመረጃ ክፍተት ሊኖር ይችላል

በመግለጫው ከተካተቱት ውስጥ ለ የአድዋ ታላቅ አፍሪካዊ ድል ማህበር (አጋቫ) አንድ ነገር ላንሳ፡፡የአብይ መንግስት ስለ አድዋ ያለውን ዕቅድ ከመቼ ጀምሮ መረጃ ነበራቸው? እኔ እንደ ግለሰብ አደዋን ዕና መሪውን አጼ ምኒልክን ለማደብዘዝ የማክበሪያ ቦታው እንደሚቀየር ከሶስት ዓመት በፊት መረጃ ነበረኝ፡፡ በተለየ መንገድ ያገኘሁት መረጃ አልነበረም፡፡የአደባባይ ምስጢር ነበር፡፡ ቢሆንም ግን መረጃውን የነገረኝ ወዳጄ በጊዜ ከአብይ መንግስት እንድሰናበት ረድቶኛል፡፡ይህ ብቻ አይደለም ቤተ-መንግስቱም ስሙ ተቀይሮ ወደ መናፈሻነት እንደሚቀየር ለእኔ አዲስ አልነበረም፡፡በኦነግ የተጠለፈው የብልጽግና መንግስት የሚሰራቸው ተቆጥረው የሚታወቁ ፐሮጄክቶች ናቸው፡፡እናም በማሳሰቢያ የሚሆን ነገር አይደለም፡፡የዚህ ፊታውራሪ ደግሞ አብይ እንደሆነ ማወቅ ከፈለጋችሁ ብዙ ከባድ አይደለም፡፡የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ የዚህ ፕሮጄክት መሪ ሽመልስ ወይም ቀጀላ ብላችሁ ማመን የፈለጋችሁ ያው እንዳልሁት የምትሰሙትን እመኑ፡፡  አብይ በአሁኑ ሰዓት ፍጹም የሆነ ስልጣን ነው ያለው፡፡አንድ ማሳያ ብቻ ከቅርብ ጊዜው ላንሳ፡፡በሲኖዶስ ኩዴታው ወቅት ቤተ-ክርስቲያን እየሰበረ አስገባ ተብሎ ሲወቀስ የነበረው ሽመልስ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሃገሪቱ የተነሰራፋው ዘረኝነት፣ የደህንነት ሥጋትና አድልዎ አውሮፕላን እንዲጠለፍ አድርጓል

 

የቆሞ ቀር ስድብም በመግለጫ መልክ አወጣ

አብይ የአባቶች መጠንከር አላምር ሲለው በጎችን የት እንዳሰማራቸው ያውቅ ነበርና ”አባ የጠፋት በጎች ተገኙ” ብሎ ነገሩን በይደር አቆየው፡፡ ወደ አደዋ ልመለስ፡፡መጀመሪያ የዛሬ ሶስት ዓመት ሽመልስ እሱን መሰሎቹን ሰብስቦ መስቀል አደባባይ አከበረ፡፡በዚያ ትንሽ ሙቀታችንን ለኩ፡፡ከዚያ ቀጀላ አደዋ ድልድይ አከበረ፡፡ዘንድሮ ደግሞ መስቀል አደባባይ በአውቶቡስ ተጭነው በመጡ ካድሬወች ሲከበር፤ምኒልክ አደባባይ እንዳይከበር አብይ ትዕዛዝ ቢሰጥም ጀግና ተሰውቶ በትግል አልፏል፡፡ የአመት ሰው ይበለንና በሚቀጥለው ዓመትስ? እንደ የአድዋ ታላቅ አፍሪካዊ ድል ማህበር (አጋቫ) ያለ ማህበር አስቀድሞ በዚህ ላይ ስራ ቢሰራ በዚሁ ጥቆማ መስጠት እወዳለሁ፡፡የህዝብ ንቅናቄ በአገርና ውስጥና በውጭ አገር መፍጠር ይገባል፡፡እውነተኛ ወዳጅ በዚህ ወቅት ነው የሚለካው፡፡ጣይቱን እወዳለሁ፤ሃውልት ካላሰራሁ ሲሉ የነበሩ ከጣይቱ ጠላቶች ጋር አብረው ግብር ሲበሉ አይተናልና ከስም ያለፈ ስራ የሚጠይቅ ዘመን ነው፡፡ሁላችንም እንዳችን አንዳችንን እያጀገንን አገራችንን ከኦነግ እንታደጋት፡

እዚህ ላይ ከጋሽ ማሞ ውድነህ ግለ-ታሪክ መጽሃፍ- አንድ ስብሰባ ላይ በደርግ ወቅት ተናገረው ብለው የመዘገቡትን እኔም አስከ አሁን ስለማይረሳኝ እሱን እንደ መውጫ እነሆ!

አገር እግር አለው ይሄዳል እንደ ሰው፤
ከድንበር ላይ ቆሞ ጀግና ካልመለሰው፡፡

ስምን መላዕክ ያወጣዋል እንዲሉ የደጀን ህዝብ ደጀን ሆኖ ከታንኩ ፊት ቆሞ ያስመዘገበው ታሪክ የማይረሳ ነው፡፡ ብአዴንም ዥንጉርጉር እየሆነ መምጣቱ ተስፋ የሚሠጥ ነው፡፡ፖሊሶችም ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ይሄ ስለ እስክንድር አይደለም፡፡ይሄ ስለ ባህል፤ስለ ታሪክ፤ስለ አገር ነው፡፡ኦነግ በደህንነት አላስወጣ አላስገባ ሲለው ትንሽ ዞር ብየ ልቆይ ያለን የቁርጥ ቀን ልጅ አሳልፎ መስጠት የሚቆጭ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ስለ ረዳንም ምስጋና ይድረሰው፡፡

 

ስለ ኢዜማና አብን መግለጫ የምለው የለኝም

የእነዚህ ሁለት ድርጅቶች መሪወች ከአብይ ጋር እየዋሉ እንዴት ነው ወጥተው አብይን በሚዲያ ሊያብጠለጥሉ የሚችሉት? አያደርጉትም፡፡ባለፈው ጽሁፌ ስለ አብን ስናገር መግለጫ እንዲሰጡ ሊፈቅድ ይችለል ብየ ነበር፡፡ያ ብዙ ችግር የለውም፡፡ ተግባራዊ ትግል ይጀምሩና እስኪ ይፈትሹት? እነዚህ ሁለት ድርጅቶች በመሪወች የግል ፍላጎትና የህዝብ ፍላጎት ውስጥ አጣብቂኝ ውስጥ ወድቀው ባሉበት እየረገጡ ያሉ ድርጅቶች ናቸው፡፡ወደ እናታችን ወደ ኢትዮጵያ ድንኳን መሰብሰብ ያለበት ብዙ አባል አስረው ተቀምጠዋል፡፡መፍትሄው በአባላቱ እጅ ያለ ነው፡፡እነዚህ ድርጅቶች ከብልጽግና መንግስት ጋር ያላቸውን አጋርነት ሰርዘው ወደ ሙሉ ተቃዋሚ ፓርቲነት መሸጋገር አለባቸው፡፡የድርጅቱን መሪወችም አንዱን ማስመረጥ ይኖርባቸዋል፡፡ መሪወቹ የእናቴ ቀሚስ ምክንያት ሲሉ ሰምተናል፡፡ አንዱ ከፓርቲ ለአገር ቅድሚያ ስለሰጠሁ ነው ሲል ሌላው ደግሞ የህልውናና አገር የማዳን ጦርነት ላይ ስለነበርን ነው ብለው ይላሉ፡፡ እውነቱ ግን በምንም ፖሊሲ ላይ የማይመሳሰል መንግስትን መቀላቀል ያመጣው ጣጣ ነው፡፡

ይህንን ካላደረጉ ግን እኛም የሃዲስ አለማየሁን  ውሳኔ እንዋሳለን፡፡ሃዲስ በጣሊያን ጦርነት ወቅት ንጉሱ ወደ እንግሊዝ ሲሰደዱ እሳቸው ከራስ እምሩ ጋር ሆነው የአርበኝነት ትግል ለማድረግ ራስ እምሩ ሱዳን ይልኳቸዋል፡፡በወቅቱ ሱዳን በእንግሊዝ ስር ነበረች፡፡ እናም ለሚፈልጉት ጉዳይ እንግሊዛዊውን ማናገር ነበረባቸው፡፡እንግሊዛዊው ግን እንዲህ አላቸው፡፡ ንጉሱ ተሰደዋል፤አሁን እናንተ ብቻችሁን ተዋግታችሁ የምትቀይሩት የለም፡፡አንተ ወጣት ነህ፤ሄደህ ከምትሞት እንግሊዝ አገር ልላክህና ተማር የሚል የወዳጅ አይሉት የጠላት ምክር ለሃዲስ ያቀርብላቸዋል፡፡በሃገር ፍቅር የነደዱት ደራሲ ግን የመለሱት ሳያስገርመው፤ስለ ኢትዮጵያውያንም ደግሞ እንዲያስብ ያደረገው ይመስለኛል፡፡ ሃዲስ እንዲህ ነበር ያሉት” ንጉሱ ቢሰደዱም የአገሬ ጋራና ሸንተረር አብሮ አልተሰደደም፡፡እሱን ይዘን እንዋጋለን ” ነበር ያሉት፡፡ ይህ መልዕክት ኢትዮጵያ ስትፈልጋቸው ለተደበቁ ሁሉ የሚሆን ነው፡፡

በዚህ ላብቃ!

 

 

1 Comment

  1. እውነት ለመናገር ፁሁፎትን እረጅም ነው ግን ስለዛ ደግሞ እራሶም ገልፀውልን በፍቃደኝነት እንድናነበው ነው የነገሩን እና እኔም በፍቃደኝነት አንብቤ ጨርሸዋልእሁኝ ግን ከዛውስጥ ያገኘሁት በኔ እይታ ምናልባት ያገኘሁት አንድ አንቀፅ የሚሞላ ብቻ ቁምነገር ነው እና እርሶ ከቁምነገሩ ይልቅ ብዙ ለማሳመር የደከሙ ነው የሚመስለኝ:: ሆኖም ግን በስተመጨረሻ በጥሩ ሰው ንግግር ስለጨረሱት ክሰውኛል::

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share