መስከርም አበራ
ባለፈው እሁድ ጋሽ ታዲዎስን ልንጠይቅ ወደ ቂሊንጦ ጎራ ብለን ነበረ። ፍተሻውን አልፈን ከገባን በኋላ ረዘም ያለ ጉዞ የሚጠይቀውን የታሰሩበትን ዞን ሶስት ስንቃረብ ጭርታው አንዳች ደስ የማይል ነገር ይናገራል። “ማንን ልጥራላችሁ?” አለን ከውጭ የቆመው ጠባቂ፣ ነገርነው፣ ገባብሎ ተጣራና ተመለሰ።
ጋሽ ታዲዮስ ብቅ አሉ። ፀጉራቸው ከማደጉ በቀር ደህና አካላዊ ሁኔታ ላይ ናቸው። በንቁ አይኖቻቸው ቃኜት ሲያደርጉ እጄን አነሳሁላቸው። ወዲያው ቀልጠፍ ብለው መጡ። እኔን ሰላም ብለውኝ አብሮኝ ያለውን እንግዳ ግራ በመጋባት ማየት ጀመሩ። እሳቸው እንደማያውቁት እሱ ግን የከፈሉለት ዋጋ ግድ ብሎት ሊጠይቃቸው እንደመጣ ነገራቸው “አመሰግናለሁ የኔ ጌታ” አሉ በትህትና። “ኧረ! እንኳን እርስዎን ቤተሰብም መጠየቅ ነበረብን” አላቸው። “ምን ቤተሰብ ጋ ብትሄዱ ሻይ ቡና ተፈልቶላችሁ ትመጣላችሁ ይሆናል እንጅ እነሱ ምን ጥየቃ ይፈልጋሉ ብለህ ነው አሉት”
ወዲያው ወደ እኔ ዞረው ስሜን ጠርተው “እንዴት ነሽ!መቼ ተፈታሽ?” አሉኝ። “ቆየሁ እኮ! እርስዎ እንዴት ነዎት?” አልኩኝ ። “አካል ይደክም ይሆናል እንጅ በመንፈስ ጠንካራ ነኝ፣ ስለጠየቃችሁኝ አመሰግናለሁ፣እዚህ ስንሆን ሰው ይናፍቀናል ፣እንዲህ ስትመጡና ስትጠይቁን ደስ ይላል” አሉኝ ጠያቂ በናፈቀ ቅላፄ። እዳ ተሰማኝ ፣ሃፍረት ነገርም ሽው አለኝ።
ቀጠሉ “እኔ ሰው ነው የሚናፍቀኝ፣ ፍትህማ ቢናፈቅስ ከየት ይገኛል? አሁን አሁን የሚያደርጉኝን ዝም ብዬ ማየት ጀምሬያለሁ” አሉኝ። አብሮኝ የመጣው ሰው በሃዘን አንገቱን ሲደፋ አየሁት ። ስለፍርድ ቤት ጉዳይ ጠየቅኳቸው። “አንዷ ተከላካይ ምስክር ነሽ፣ ክሱን ወስደሽ አንብቢና መጥሪያ ሲደርሰሽ መገኘት ነው፣ታለማ አልነገረሽም? ” አሉኝ ፈርጠም ብለው ። ታለማ ጠበቃቸው ናቸው። “ነግረውኛል፣ እሽ እገኛለሁ” አልኩኝ ። አይበገሬነታቸው፣ንቁነታቸው ገረመኝ!!! “በሉ ሂዱ ይበቃል ፣ሲመቻችሁ ብቅ በሉ መቼም በቶሎ የሚለቀኝስ አልመሰለኝም” አሉ እንደመሳቅ ብለው። ሰው እንደናፈቃቸው አስተዋልኩ፣ልቤ አዘነ! “ፍትህ ከፈጣሪ ነው ይፈታሉ ፣እኔ መጥቼ እጠይቅዎታለሁ” ብዬ ተሰናብተን ወጣን።
ጠንካራው ሰው በእጅጉ ሰው ይናፍቃቸዋል፣ ለምን እንደታሰሩ የሚገባው፣ውለታ የሚከብደው ሁሉ ሊጠይቃቸው ይገባል። ማስፈታት በሰው እጅ ነው፣መጠየቅ ግን በእጃችን ነው!