የኢትዮጵያ፤የውዪዪትና፤መፍትሔ፤መድረክ
Ethiopian Dialogue Forum
9900 Greenbelt RD. E#343 – Lanham, MD 20706
የካቲት 14 2015
የሉዓላዊነታችን መደፈር የእኛ የኢትዮጵያውያን ትዕግስት መጨረሻ
የደቡብ ምዕራብ ክልል ኢትዮጵያን በሚያዋስነው የደቡብ ሱዳን ድንበር ታጣቂዎች ወደ ኢትዮጵያ እስከ ፪፻ ኪሎ ሜትር ዘልቀው በመግባት የአንድ ብሄር አባላትን በመጨፍጨፍ ጨርሰዋቸዋል ። ከዚያ ብሄር አባላት ውስጥ በህይወት የተረፉት እጅግ ጥቂቶች እንደሆኑ ስንሰማ እንደ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ሳይሆን እንደ ሰብአዊ ፍጡር እጅግ አዝነናል። አስቆጥቶናልም።
መንግስት በአንድ በኩል ድንበሩን ክፍት አድርጎ አገራችንን ድንበር የሌላት ሲያደርጋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሱዳን ታጣቂዎች የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው እስከ ሁለት መቶ ኪሎ ሜትር ዘልቀው በመግባት ሱሪ፣ ቢሮና፣ ማጂና ሱርማ በተባሉ ወረዳዎች አካባቢ ዘረፋ ይዘዋል። ሱሪ የተባለውን ወረዳ ዋና ከተማ በቁጥጥራቸው ስር አድርገው በነዚህ አካባቢዎች ወታደራዊ ካምፖችን ዘርግተው ሰፍረዋል። በዚያ አካባቢ ያለው ወገናችን የወገን ያለህ፣ የመንግስት ያለህ እያለ ቢጮህም ሰሚ አጥቶ እያለቀ አየተዘረፈ ነው።
ከህዝብ አብራክ የወጣህ የኢትዮጵያ ሰራዊት ሆይ ህዝብና አገር ከአራት ኪሎ ወንበር በላይ ናቸዉ ። አገርህንና ህዝቧን በመታደግ የጀግኖች ታሪክ ባለቤት ሁን ።
ኢትዮጵያውያን ድንበራችን ተደፍሮና ዜጋዊ ክብራችን ተነክቶ ዝምታን አንመርጥም! በመሆኑም የኢትዮጵያ የዉይይትና የመፍትሄ መድረክ (EDF)ና የእምቢልታ ስብስብ በጋራ የሚከተለውን ጥሪ ያቀርባሉ።
. ይህ የሉዓላዊነታችን መደፈርና ዘር የማጥፋት ዜና የተነገረው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንደመሆኑ ፣ ይህ ኮሚቴ ያየውን ይህንን ከባድ ወንጀል ለኢትዮጵያ ህዝብ ቀርቦ ማብራሪያ ሊሰጥ ይገባል እንላለን።
ዓለማቀፍ ተቋማትና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በአስቸኳይ ይህንን በመጥፋት ላይ ያለ ብሄረሰብ ለመታደግ የደረሰውን ሰብዓዊ ኪሳራ መጠን በማጥናት አስቸኳይ ክስ እንዲመሰርቱና የወንጀሉ ተሳታፊዎች በአለም አቀፍና በሃገራዊ ህግ ፊት እንዲቀርቡ ጥሪ እናደርጋለን!
የሰራዊቱ አባላት፣ አዛዦችና ባለሙያዎች ሁሉ የሃገርን ሉዓላዊነት የመጠበቅ ስራ ዋና ሃላፊነታችሁ ነውና፣ ይህንን በሱዳን ታጣቂዎች የተያዘ ኣካባቢ ነጻ እንድታደርጉ፣ ድረሱልኝ ለሚለው ወገናችሁ መከታ መሆናችሁን በተግባር እንድታሳዩ ጥሪ እናደርጋለን።
ከመቼውም ጊዜ በላይ ዛሬ ብሄራዊ ክብራችን ሁሉ ተደፍሯል። ትናንት በአኝዋክ፣ ዛሬ በዐማራ፣ በጉራጌ፣ በኮንሶ፣ በትግራይ፣ በቤንሻንጉል፣ በኦሮሞ፣ በኩሱሜ ፣ በአፋር ፣ በኦጋዴን ፣ በሶማሌ ፣
በቡርጂ ፣ በጉጂ ፣ በጌዲዮ ፣ በቦረና ፣ በአማሮ ኬሎ ፣ እና በሌሎች አካባቢዎች ነዋሪዎች ላይ በየተራ በዘረኞች የሚፈጽሙትን ግፎች ለማስቆምና ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ ቆራጥ ትግል ማድረግ ይጠበቅብናል። ይህ መንግስት በአንድ በኩል ለብሄር ብሄረሰቦች ቆሚያለሁ እያለ በሌላ በኩል የአንዳንድ ብሄረሰብ አባሎች ህልውናቸው እስኪጠፋ ድረስ ለጉዳት አጋልጦ የሚሰጥ ስለመሆኑ ከዚህ የበለጠ ማስረጃ የለም።
በመጨረሻም በመላው ዓለም ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ዘርና ሃይማኖት ሳይለያየን ለፖለቲካዊ ስርዓት ለውጥ በአንድነት እንቁም።
አንድነት ሃይል ነው!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
የኢትዮጵያ፤የውዪዪትና፤መፍትሔ፤መድረክ
Ethiopian Dialogue Forum
9900 Greenbelt RD. E#343 – Lanham, MD 20706