ከይነጋል በላቸው
ከተቀረው የእንስሳት ዓለም በአእምሮ የብስለት ደረጃ (አይ ኪው) ወደሰው ከሚጠጉ ሌሎች እንስሳት ውስጥ ዝንጀሮ አንደኛው ነው፡፡ አንዱን የዝንጀሮ ታሪክ ቀጥለን እንይና ከሰሜን ኮሪያ ወቅታዊ ጉዳይ ጋር እናመሳስል፡፡
ወንዱ ዝንጀሮ በጣም ቀናተኛ ነው ይባላል፤ እንዲያውም ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁት አባቶች እንደሚሉትማ – በጣም ከመቅናቱ የተነሣ በእንቅልፍ ልቡ ሌላ ዝንጀሮ እንዳይተናኮልበት በማሰብ – የባልተቤቱን የመዋለጃ አንቀጸ ማኅፀን (የማኅፀን በር) በእጁ ግጥም አድርግ ሸፍኖ በመያዝ ነው አሉ የሚተኛ፡፡ በዚያም ምክንያት ሴቶች ዝንጀሮዎች በእናታቸው ጀርባ እየታዘሉ እንደፈለጉ ተንፈላሰው ሲያድጉ ወንዶች ግን በጉያና በድብቅ የእናታቸው አካላት በመከራ ያድጋሉ፡፡ ሕጻናት ወንድ ዝንጀሮዎች አድገው የአባታቸውን ሚስት – ለነሱ እናታቸውን – ይቀሙናል ብለው ስለሚቀኑ አባት ዝንጀሮዎች ወንድ ሕጻናት ዝንጀሮዎችን ከመግደል እንደማይመለሱ ይነገርላቸዋል፡፡ የሴቶቹ እንደልብ እየፈነጠዙ ማደግ ግን ያው ‹እናትን አሣራፊዎች› በመሆናቸው ‹እነሱን ባረገኝ› ተብሎ የማይቀናበት እንስሳዊ ባሕርይ ነው፡፡
ወንዶች ሕጻናት ዝንጀሮዎች እንደምንም አድገው መጎርመስ ሲጀምሩ ታዲያ ከኋላ ከኋላ እየተከተሉ የአባታቸውን ኮቴ ወይም ዱካ ይለካሉ አሉ፡፡ ኮቴያቸው ከአባታቸው እኩል ሲሆን ነጻነታቸውን በራሳቸው ያውጁና ጎን ለጎን መራመድ ይጀምራሉ፤ ከዚያም ባለፈ ‹የፈሩት መድረሱ፣ የጠሉትም መውረሱ› አይቀርምና አባት ባሎች ሊፈነገሉ የሚችሉበት አጋጣሚም መኖሩ በስፋት እንደሚተስዋል ይነገራል፡፡ አያድርስ ነው መቼም፡፡ (አንዳንድ አንባቢያን እያሰባችሁ ያላችሁትን ዐውቃለሁ! ዘመኑ የመጨረሻ ነውና የፈለጋችሁትን ብታስቡ ከገሃዱ እውነት ባለመውጣታችሁ ኩነኔ የለባችሁም፡፡ አነጋገሬ ላቲን እንዳይሆንባችሁ ያህል – ‹ይሄ ነገር ኧረ በሰውም ሞልቷል› ብላችሁ ለምታስቡ በተለይ በውጪው ዓለም ለምትገኙ ምዕመናን ማለቴ ነው፡፡ አይድነቃችሁ – ሁሉንም ቅዱስ ወንጌል ጨርሶታል፤ አሮጌው ዓለም ተቀብሮ አዲሱ ዓለም እውን ሊሆን የቀረው የመጨረሻው ፊሽካ ብቻ ነው – በዚህን የአዲሱ ዘመን ዋዜማ የማይሰማና የማይታይ ሰቅጣጭ ነገር አለመኖሩ እንጂ መኖሩ አያስገርምም፡፡ ከአሁን በኋላ ከዚህ ቆሻሻ ዓለም ምን ሲቀርብን? የሚቀርበት ይቀርበታል እንጂ እኛ ከደሙ ንጹሕ ነን ብለን የምናምንና የምናስብ ምሥኪኖች የሚቀርብን አንዳችም ነገር የለምና በከንቱ አንጨነቅ፡፡ ከፈለገች ዓለም ለምን ዛሬ ሌሊት አታልፍም!)( በነገራችን ላይ – ቻይና፣ሰሜን ኮሪያ፣ኢራን፣ሦሪያ፣ ወያኔ፣ አልቃኢዳ፣ አልሻባብ፣ … ለየባለጉዳዮቻቸው እንደወንድ የዝንጀሮ ልጆች ዱካ ሲለኩ ቆይተው በመጨረሻ በቀላሉ የማይቆረጠሙ ያደሩ ባቄላዎች መሆናቸውን ልብ ይሏል …)
ይህን የዝንጀሮ ታሪክ በመግቢያነት ያመጣሁት ሰሜን ኮሪያን በጨረፍታ ለማንሳት ነው፡፡ ይህች ገና በቅጡ ባልባለቀ ሮጦም ባልጠገበ ወጠጤ እንደምተመራ የሚነገርላት የአንድ ቤተሰብ የወለድ አገድ ንብረት የሆነች ሀገር ሰሞኑን ‹ፍንዳታ› ሆናለች፡፡ አዲስ ፍንዳታ በሠፈር ውስጥ አላፊ አግዳሚን – በተለይ ወጣት ሴቶችን – አላስቆም አላስቀምጥ እንደሚል ሁሉ ይህች በተስፋ መቁረጥና ለዘመናት ሲንከባለሉ በመጡ ፖለቲካዊና ማኅበረሰብኣዊ ችግሮች የተቆላለፈች ዝግ ሀገር የታያትን እንጃ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይ አራስ ነብር ሆናለች – ከማስፈራራት ባለፈ ቁርጠኝነት፡፡ አሜሪካንን ያህል ዓለምን እያንቀጠቀጠች የምትገዛ የኃያላን ኃያል ሀገር እያንቆራጠጠቻት ትገኛለች፡፡ ‹አንዳንዴ ተስፋ መቁረጥ ለካንስ መጥፎ አይደለም› የሚያስብል ሁኔታ ተፈጥሯል – እንደኔ፡፡ ፈረንጆቹ – “Little temper settles the dust.” ይላሉ አሉ – ከፍርሀት ያልተለዬን ትግስት ለማንጓጠጥ፡፡
ሲያስቡት ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ እንደውነቱ ከሆነ ዛሬ ጊዜው የጦርነት አይደለም፤ ውድ አንባቢ ምዕመናን ሆይ! ጦርነት መግጠም ዱሮ ቀረ – በፋራዎች ዘመን፡፡ በዛሬ ዘመን ጦርነት መግጠም ማለት – ትክክለኛውን የ21ኛውን መቶ ክፍለ ዘመን ጦርነት ማለቴ እንደሆነ ግንዛቤ ያግኝልኝ – ልድገመው – በዛሬ ዘመን ጦርነት መግጠም ማለት እንደጥንት እንደጧቱ ስንቅ ሰንቁልኝ፣ ፈረሴን ጫኑልኝ፣ ጋሻየን ከተሰቀለበት አውርዱልኝ፣ ሞይዘሬን ወልውሉልኝ… የሚባልበት የሞኞች ዘመን አይደለም፡፡ በዛሬ ዘመን ዋናው ቀድሞ መገኘት ነው፡፡ አንድ የውጊያ ቴክኒሻን መኝታ ቤቱ ቁጭ ብሎ በዘመኑ ምዕራባዊ ቋንቋ ከሚመስለው ጋር በፍቅር ተቃቅፎ የድንች ጥብሱን ከሽ እያደረገ በሪሞት ኮንትሮል በሚንቀሳቀስ ዘመን አፈራሽ መሣሪያ ሚሊዮኖችን የዶግ አመድ በሚያደርግበት ዘመን ላይ ተቀምጠን የጥንቱን ኮንቬንሽናል የ‹ቆመህ ጠብቀኝ› መሣሪያ ጦርነት ማሰብ ቂልነት ነው፡፡ ይህን ብዙዎች ያውቃሉ – ለዚህም ይመስላል ቃታ ለመሳብ ከወዲህኞቹም ከወዲያኞቹም ድፍረት የጠፋው – ‹ድብድቡ ከተጀመረ ተጀመረ ነው› ፤ ድብድቡ ነፍስ እንዳላወቀ – አንቀልባ ውስጥ እንዳለ እርጥብ ልጅ ነው፡፡ የሚመርጠው የለም፤ የሚጠላውና የሚወደውም የለም፡፡ የሚመራው በሰው ፍቅርና ውዴታ ሳይሆን በኬክሮስና ኬንትሮስ የግሪድ ሪፈረንስ ቀመር ነው፡፡ ያ ሰው ሰራሽ ሪፈረንስ ደግሞ ክፉዎች ሰዎች በፈለጉት አቅጣጫ የሚመራ፣ ኃላፊነት በጎደላቸው ሰዎች ቁጥጥር ሥር የሚገኝ በመሆኑ ‹እግዜር ያውጣ› የሚለው ጸሎት ራሱ የሚሠራ አይመስልም – ፈጣሪ ቀደም ሲል የገባውን ቃል አይሽርምና፡፡ ቃሉም ‹ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም› በሚለው ነባር ሕግ የሚታዘዝ “ዓለም ታልፋለች” የሚለው ኅያው ቃል ነው፡፡ ለመቼነቱም የተሠጡ ምልክቶች ስላሉ ሁሉም በሚገባ ተሟልተዋልና ግፋ ቢል ‹ጥቂት ሣምንታት›ን እንጠብቅ ይሆናል እንጂ ‹ወራት›ና ‹ዓመታት› እንኳን አልቀሩም፡፡ ብሎም ቢሆን ያቺን እውነተኛ የጭንቅ ቀን ከአንድዬ በስተቀር ማንም እንደማያውቅ በመነገሩ የቻለ ተዘጋጅቶ ከመጠበቅ ውጪ ትክክለኛውን ዘመነ ኅልፈት ሊያውቅ የሚችል የለም – እንዲያ ቢሆን ደግሞ የሚጠፋ ባልኖረ፤ ሁሉም ለመዳን በተሯሯጠ፡፡ ትንሹዋን የገዛ ሞታችንን እንኳን ማወቅ ያልቻልነው ለዓላማ እንደሆነ የሚያውቁ ይናገራሉ፡፡(ለምሳሌ ‹በዐርባ ዓመት ዕድሜህ፣ በዕለተ ማክሰኞ ከቀኑ በአሥር ሰዓት ትሞታለህ› ተብሎ ቢነገርህ የምትኖረው የሰቀቀንና የፍርህት ኑሮ ይታይሃል? ለዚህ ነው የዓለም ማለፊያ ቀንም ከምልክቶቹ በስተቀር ስለእውነተኛዋ ዕለት እንዳናውቅ የተደረገው – ይሉናል የሥነ መለኮት ምሁራን፡፡)
ዓለም በሥልጣኔ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛው ጫፍ ላይ ደርሳለች፡፡ ይህ መጥፊያም መልሚያም የሆነ የሥልጣኔ ጫፍ ደግሞ መጀመሪያ እንደነበረው ሁሉ መጨረሻም አለው – ጅማሬ ያለው ሁሉ ፍጻሜም አለውና፡፡ ለዐይን ይበጃል ተብሎ የተቀቡት ኩል ዐይንን እንደሚያጠፋ ሁሉ ለዓለም ሕዝብ ይበጃል ተብሎ በግለሰቦችና ቡድኖች ብዙ የተለፋበትና የተደከመበት የሥልጣኔ ፍሬ በአብዛኛው ድኽነትን የሚያስፋፋና ዕልቂትና ውድመትን የሚያስከትል መሆኑን ስናጤን በሥልጣኔያችን ምክንያት እንዲህ ከምንሆን ከነጭራሹ ሥልጣኔው ሁሉ ባፍንጫችን በወጣ እንላለን፡፡ በተለይ ባለፉት አንድ መቶ ዓመታት በጣም በተለይ ደግሞ ባለፉት ሃምሣ ዓመታት የታዩ የሥልጣኔ ግኝቶች ደግሞ የመቃብራችንን ቁፋሮ በእጅጉ እያጣደፉት ናቸው፡፡ በስለላውና በወታደራዊው መስክ የተመዘገቡት አሉታዊ እመርታዎች ሲታዩ ምንም እንኳን በሺዎች ኪሎሜትሮች ከፍታ ላይ የምትበርን ድንቢጥ ወፍ በጨለማ አነጣጥሮ የሚበታትን ሥልጣኔ ላይ ብንደርስም ጎን ለጎን አብዛኛው የዓለማችን ሕዝብ ከሚማቅቅባቸው የበሽታና የርሀብ አለንጋዎች እንዲሁም እዬዬ ከሚልባቸው የፍትህና ርትዕ ጉድለቶች ልናላቅቀው አልተቻለንም – በዚህና በሌሎች ተዛማጅ ምክንያቶች ተነሣ ባወቀ መጠን የሚደድብ እንደሰው የለም ማለት እንችላለን፡፡ ዓለምን የሲዖልና የገነት ማሳያ መድረክ ለማድረግ ቆርጠን በመነሳታችን ሳቢያ ሰማይና ምድር ተጣልተውብን ይሄ ሁሉ በዓለም ላይ እያስተዋልነው ያለነው ችግርና ችጋር ሲሰለጥንብን ምንም ማድረግ አቅቶን ከልማት ይልቅ ጥፋት እየቀናን በዚያው ጎዳና እየተመምን እንገኛለን – ከማልማት ይልቅ ማጥፋት፣ ከመመገብ ይልቅ ማስራብ ከመፋቀር ይልቅ መጣላት ቀሎን ተገኝቷል እያልኩ ነው፡፡
ሌላው ቀርቶ ዛሬ ኢራን ውስጥ የተከሰተውንና በሠላሣዎቹ ገድሎ በመቶዎቹ ያቆሰለውን የመሬት መንቀጥቀጥ ከሌላ ነገር ጋር ማዛመድም እንደሚቻል መጠቆም አይከብድም – ሰው ሆኖ መጠርጠር አይከፋም፡፡ ዝናብን አለጊዜው መላክና ከማሣ ያልተነሣን እህል ማበላሸት ወይም በተቃራኒው ዝናብ በሚያስፈልግበት ጊዜ እንዳይዘንብ በልዩ የቴክኖሎጂ መሣሪያ መከልከልና የመኸርና የበልግ የዘር ወቅት እንዲጨነግፍ በውጤቱም ርሀብና ድርቅ እንዲስፋፋ ሕዝብም በርሀብና ርዛት እንዲያልቅ ማድረግ የሚችሉ የምድር ኃይላት መኖራቸውን የምንረዳ ወገኖች የዚህችን ዘመን የጦርነት መንስኤና አጠቃላይ መዘዝ አሳምረን እናውቃታለን፡፡ ለመሆኑ በመቶ ሺዎች የሚገመት ሕዝብ የፈጀው የሃይቲ የመሬት መናወጥ በርግጥ ተፈጥሯዊ ነበር ወይንስ በመሬት የውስጥ ለውስጥ የመሣሪያ ሙከራ የሰው ልጆች በሰው ልጆች ላይ ያካሄዱት የጭካኔ ተግባር ነበር?(ልብ አድርጉ፡- በዩኒቨርስ እንደሰው ልጅ ጨካኝ የለም!) በሌሎች ስንትና ስንት ሰው ሠራሽ ሊሆኑ እንደሚችሉ በሚጠረጠሩ ርዕደተ መሬቶች ምን ያህል ሰውና ንብረት ወደመ? በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በአውስትራሊያ እንዲሁም በሌሎች የመሬት ውስጥ፣ የመሬት ላይና የሕዋ ውስጥ የምርምር ጣቢያዎች በርካታ ምሥጢራዊ ጥናቶች እየተካሄዱ እንደሆነ ለአፍታ እናስብ – (እዚህ ላይ በምሕጻረ ቃል ‘CERN’ በመባል የሚታወቀውን አውሮፓ ውስጥ በስዊዘርላንድና ፈረንሣይ ድንበር አካባቢ የሚገኘውን ‹ሰላማዊ› የምርምር ማዕከልና ‘HAARP’ በመባል የሚታወቀውን አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ጥቁር መዝገበኛ ሀገሮችን በርዕደ መሬት የማጥፋት ዘመቻ አንግቦ የተነሣ የምርምር ማዕከል ማስታወስ ይቻላል)፤ በነዚህ የምርምር ማዕከላት ከሚከናወኑ አንዳንድ ፍሬ ፈርስኪ የጥናት ጭብጦች (ለምሳሌ ቢንግ ባንግን(Bing Bang) አስመስሎ የመፍጠር ቅዠታዊ ጥናት) በተጓዳኝ በረቂቅ መንገድ እንዲጠፉ የሚፈለጉ ሀገራትን የሚያወድም የምርምር ጥናት እንደሚደረግ እንሰማለን(ታያላችሁ! ‹ድብድቡ ሲጀመር› ሰው ሠራሽ የመሬት መንቀጥቀጥም አንዱ መሣሪያ ይሆናል! ሁሉም የየራሱን የማምለጫና የማጥቂያ መንገዶች ማዘጋጀቱ ሳይታለም የተፈታ ቢሆንም ቴህራን ወዮላት፣ ደማስቆስ ወዮላት፣ ኒውዮርክ ወዮላት፣ ሴዑልና ፒዮንግያንግ እንዲሁም ሌሎች ከተሞች ወዮላቸው…)፡፡
የሰው ልጅ ለጥፋት የሚያወጣውን ይህን ሁሉ ዕውቀትና ገንዘብ ለልማት ቢያውለው ታዲያ በአሁኑ ወቅት ዓለማችን ምድረ ገነት ሆና አልነበረምን? ዘርን፣ ቀለምንና አካባቢን መሠረት ያደረጉ የተናጠል ሩጫዎች ገታ ተደርገው አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ ሰውኛ ጥረቶች ቢደረጉ አሁን የትና የት ደርሰን አልነበረምን? ግን ቃል አላ! ያ ቃል ከሚታበይ ዓለም ብታልፍ ይቀላል ተብሏላ! ትንቢት መጥፎ ነው፡፡
‹ስለሆነም› እንበልና ሰሜን ኮሪያን እዚህ ላይ በድጋሚ አውስተን እዚቺው ላይ እንዘምዝማት፡፡ ስለሆነም የሰሜን ኮሪያን ሽሮ መሰል ድንፋታና ለያዥ ለገራዥ ማስቸገር በጎሪጥ ተመልክተን ‹ድብድቡ ሲጀመር› ወይም ሁኔታውን ልክ እንደወዲህኞቹ የጉዳዩ ባለቤቶች እንደነደቡብ ኮሪያና አሜሪካውያኑ ትንሽ ቀለል እናድርገውና ‹ድብድቡ ቢጀመር› የድንቡሼው ወጣት መሪ ሀገር ሰሜን ኮሪያ ከጎኗ የሚሠለፉ ወገኖች እንደማይጠፉ እንገምት፡፡ የጠላትህ ጠላት ወዳጅህ መሆኑ ጥንትም የነበረ በመሆኑ ከዚህች ሀገር ጋር በጎሣ፣ በነገድ፣ በዘርና በሃይማኖት እንዲሁም በርዕዮተ ዓለም ፍጹም የማይገናኙ ሀገሮች ‹ጅቡን ለመውጋት አህያን ተጠልለው› መነሣታቸው፣ ኃይላቸውንም አስተባብረው ከጠላታቸው ጠላት ጎን መሰለፋቸው የታመነ ነው፡፡ በማከያውም ይህን ሁኔታ በደስታ የሚጠባበቁና አጋጣሚውን ትንፋሽ ለመግዣነት የሚገለገሉበት ኃይሎች እንዳሉ ደግሞ በጣም ግልጽ ነው፡፡ በተጨማሪም ዓለም በአንዲት ራስዋን በራስዋ የዓለም ገዢ ነኝ ብላ በሾመች ሀገር መገዛቷ የእግር አሳት የሆነባቸው አገሮች አሉ – ገዢነትን የሚጠላ ስለሌለ የራሱን የዓለም ገዢነት ተራ ለማምጣት ወይም ቢያንስ ፍትህ በጎደለው መልክ መገዛትን የሚደግፍ ስለሌለ የዚያችን ሀገር ኢፍትሃዊ የበላይነት የሚቃወም ኃይለኛ ሀገር አይኖርም አይባልምና ድብድቡ ሲጀመር የራሱን ኩርኩም መሠንዘሩ አይቀርም – ባመቸው አቅጣጫ ወደፈለገው ሀገር፡፡ ነገሩ የኳሷ አበደች ቢጤ ስለሚሆን አታድርስ ነው፡፡ ጠያቂም ተጠያቂም የማይገኝለት የጨረባ ተዝካር ውስጥ ገብቶ ዕብዶች የደገሱትን የዕልቂት ድግስ መኮምኮም ነው የኛ ድርሻ የሚሆን – ‹የፓትርዮት ሚሣኤል ባትሪ› የሚሉትም ቀልድ ነው – ከምንም አያድንም፡፡ እነዚህ ከፍ ሲል በገደምዳሜ የተጠቀሱት ወዳጅ መሳይ የውስጥ ‹መሠሪዎች› ሁለቱንም ተጻራሪ ጫፎች እያጃገኑ ወይም ሁኔታዎችን እያመቻቹ በሚፈጠረው ልዩ አጋጣሚ የራሳቸውን ሚና ከመጫወት የሚመለሱ አይመስሉም፡፡ ያደፈጠም ያሸመቀም … ‹የቤተ ዘመዱ ይታያል ጉዱ› የሚባልበት ዘመን መባቱ አይቀርም – ወዮ ለኛ ይልቅንስ ምኑንም ሳናየው የመጨረሻው የጥፋት ማዕድ ተሣታፊ ለሆን፡፡
በዚህ በታቀደልን የጥፋት ዘመቻ ውጤት የዓለም ገዢዎች መፈራረቃቸው አይቀርም – ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ፤ የኃይል ሚዛን መለዋወጡ የግድ ይመስላል፡፡ የዝንጀሮዎቹ የዱካ መለካካት ታሪክ መታየቱ የማይቀር ነው – ደካሞች ይበረታሉ ፣ ብርቱዎች ይደክማሉ፡፡ የተሸሸጉ ይወጣሉ፤ እዩኝ እዩኝን ያበዙ ይሸሸጋሉ፡፡ የዓለም የእስካሁኑ አካሄድ እንዲህ ነበር – ዛሬ ድንገት ደርሶ አይለወጥምና ታሪክ በቅርብ ይደገማል፡፡ የነአክሱምና የነሜሶፖታሚያ ሥልጣኔ፣ የነግሪክና ሮማውያን ሥልጣኔም በአንድ ቀን አዳር ተጨናግፎ ወደታሪክ መዝገብነት አልተዛወረም፡፡ ‹እኔም ባንድ ቀን አልተቆመጥኩም› ብላለች አንዷ ብልህ ሴት፣ እጄን አሳከከኝ ላለቻት ሕጻን ልጇ፡፡ የእጅን ማግኘት ዛሬ የተጀመረ አይደለም፡፡ ዕድሜህን እንዲያረዝመውና ሁሉን እንድታየው መጸለይ ነው ይልቁንስ – ቀኑ ደርሷል፡፡
ለማንኛውም ሰሜን ኮሪያ ብቻዋን ናት ማለት አይቻልም፤ እኛም እሷም እነዚያም እነዚህም … ብቻዋን እንዳልሆነች እናውቃለን፡፡ ሁሉም ይተዋወቃል – የመረጃ ዕጥረት የለም፡፡ ‹አስቸጋሪ እንግዳ ተዘቅዝቆ ይተኛል› ይባላል፡፡ አሜሪካዎች፣ በመካከለኛው ምሥራቅ አስቸጋሪ እንግዳ ተዘቅዝቆ ተኝቶባቸው ተቸግረዋል፡፡ የናቁት እንትን እንዳያስረግዝም ሰግተዋል – ልብ እናድርግ የፈሩት ግን ወጠጤውን – በርሀብ አለንጋ የሚገረፍ ምሥኪን ሕዝብ የሚመራውን ወጣት የሰሜን ኮሪያ መሪ አይደለም፤ የፈሩት ጦሱን ነው፡፡ የፈሩት የታወቀውን ሣይሆን ያልታወቀውን ነው፡፡ ጉድ እየተንተከተከ ነው፡፡ በጌታዋ የምትተማን በግ ላቷን የት ነበር ታሳድራለች የሚባለው? ዳንስ ቤት መሄዱን ትቶ በጦር ሜዳ አጉል ማለቴ አጉሊ መነጽር የወታደሮቹን የጦር ልምምድ እየተመለከተ የሚዝናናው ኪም ኢል ኡንም የተማመነውን ቢተማመን እንጂ ይህች ሀገር ለአሜሪካ ጦር የቁርስ ማዳረሻ እንጂ ያን ያህል የምታሰጋ ልትሆን ባልቻለች ነበር፡፡ ለነገሩ ስለሰሜን ኮሪያ እኛን ምን ጥልቅ አደረግ? ችግራቸውን ጊዜ ይፍታው፡፡ በሀገራችን ስንትና ስንት የራሳችን ጉድ እየተፍለቀለቀ የምን በሰው ጓዳ ውስጥ ገብቶ መፈትፈት ነው!
የማርጋሬት ታቸርን ሞት ተከትሎ የታዘብኩት ነገር በምንም ነገር ተገርሜ የማላውቀውን ያህል በጣሙን ገረመኝ፡፡ ‹ዴሞክራሲ ለካንስ እንደዚህ ኖሯል?›ብዬ በእጅጉ ተደነቅሁ፡፡ ሴትዮዋ በመሠረቱ ዕድሜ ጠግባ ነው የሞተችው – ዕድሜ ባይጠገብም፡፡ ይሁንና ገሚሱ በሀዘንና በዕንባ ሲራጭ ገሚሱ ደግሞ ሻምፓኝ እየከፈተ – እውነቴን ነው – ያለ አንዳች ይሉኝታ ደስታውን በአደባባይ ሲገልጥ በታዋቂ ሚዲያዎች ማየቴ ‹ምድር ላይ ነው ያለሁት ወይንስ ሌላ ዓለም ውስጥ?› ብዬ እስክገረም ተደምሜያለሁ፡፡ ወዲያው የመጣልኝ ነገር መለስ ሲሞት መስቀል አደባባይ ወጥቼ ሻምፓኝ መክፈቱና በጊታር ባህላዊ ዘፈንን – እንደእንግሊዛውያኑ -‹በደስታ ሲቃ ተውጬ› ማቀንቀኑ ከሀበሻ ባህል አኳያ በነውረኝነት ስለሚያስፈርጀኝ ቢቀርብኝም፣ ‹እሰይ! ሞትም ሲያንሰው ነው! ክፉ ሰው ነበር፡፡› ብዬ በግልጽ ብናገር ኖሮ ይሄኔ የመቃብሬ ሥፍራም አይታወቅም ነበር፡፡ እንዲያውም ከናካቴው የመቀበርን መልካም ዕድል አላገኝም ነበር – ዘልዝለው ተቃርጠው ይበሉኝ ነበር እንጂ ጨክነው አይቀብሩኝም – እንዴ ወያኔዎች እኮ ከአውሬም የመጨረሻው ክፉ አውሬ ናቸው፡፡ የሚጠሉትን በፍጥነት በማደባየት ከዓለም ፍጡራን የሚስተካከላቸው የለም – በቀለኞች፣ ተንኮለኞች፣ አንድን ሰው ለማጥፋት በአንድ ቀን ሕገ መንግሥታቸውን ሳይቀር ከመለወጥ የማይመለሱ የእፉኝት ልጆች ናቸው – መጥኔ በወያኔ አገዛዝ ሥር ለምንማቅቅ ኢትዮጵያውያን – ደግነቱ ዘመኑ ቀረበ! ‹የነጻነት ዘመን ቀርባለችና ሃሤት አድርጉ› የሚለኝ አንዳች መንፈስ በውስጤ ይሰማኛል፡፡ ለማንኛውም የሚገርም የሰው ልጆች የአእምሮ ዕድገት ልዩነት ነው ዛሬ ከወደእንግሊዝ የታዘብኩት፡፡ ሰው ሞተ ተብሎ – ሊያውም አንዲት የጨረጨሰች አሮጊት – ያን ያህል ደስታና ፈንጠዝያ? ለነገሩ ይሄኛውስ ምን አገባን? እዚያው እንደፍጥርጥራቸው፡፡
ወግ ነው አሉ ሲዳሩ ማልቀስ፡፡ የዚያች የድኻይቱ መበለት የቀድሞ ባለቤት – አእምሮዋን የተነጠቀችው የማይሟ ባለድግሪ ጋለሞታ የአዜብ ባል መለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን ተቋቋመለት አሉ፡፡ ዘመኑ ጅብ እማያውቁት ሀገር ሄዶ ብቻ ሣይሆን በሚያውቁት መካከል ዐይኑን በጨው ታጥቦ የአህያ ጎድንና ፍሪምባ አንጥፉልኝ የሚልበት የድፍረት ዘመን መሆኑ በጄ እንጂ ይህ ነገር ኮረንቲ ያስጨብጣል – ሊያውስ ኮረንቲውስ በቅጡ ሲገኝ አይደል? (ዕድሜ ለትራንስፎርሜሽናችን የዕድገት ምጥቀት ኮረንቲና ውሃ የህልም ያህል እየሆኑብን መጥተዋል፤ የሚያገኛቸው የታደለ ብቻ ሆኗል – ለብዙዎቻችን በረጃጅም ወረፋ የሚገኙ የቅንጦት ነገሮች ከሆኑ ሰንብተዋል፡፡)
ይሄ በሙት መንፈስ እየገዛ የሚገኝ ሰውዬ መጨረሻው ናፍቆኛል፡፡ ዓለምን እያስደመመ ነው – ለነገሩ እኛኑ እንጂ የምን ዓለም አለና፤ ውሸታሟ ዓለምማ የማይነጋ መስሏት ከነርሱው ጋር ተባብራ የለምን? ሞቶም ዕረፍት የሚነሣ ልጅ የወለደች ኢትዮጵያ ብቻ እንደሆነችም ከተገነዘብን ቆየን – ዕረፍት የማይሰጥ የሲዖል ትል ሆኖብናል፤ ፎቶውና በቲቪና ሬዲዮ ነጋ ጠባ የሚወተወተው ስሙ፣ እየተፈበረከ የሚለጠፍለትም ‹ምሁራዊ› አስተዋፀዖው ብቻ ሳይሆን የሙት መንፈሱ አጠቃላዩን የሀሪቱን ድባብ ተቆጣጥሮታል፡፡ በየትም ሀገር በሌለ ሁኔታ ከሞተ አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት ብቻ የቀሩት ሰው አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እሱ ራሱ የሆነ ያህል ሀገር ምድሩ የሚምለውና የሚገዘተው በእርሱ ራዕይ ሆኗል – የቬንዞላዎቹ ሀዘናቸውን በአንድ ወር ውስጥ ወደጎን ትተው ለምርጫ ሲሰናዱ እነዚህኞቹ ቂሎች ሞት በነሱ ሠፈር የተጀመረና ብርቅም የሆነ ያህል መለስ በሞተ በአሥር ወሩ ደረት ጥለው፣ ጀንዲ አንጥፈው በመቀመጥ ገና ሙሾ በማውረድ ላይ ናቸው – ያልታደሉ፤ ግን ግን ለማስመሰያነት እንጂ ከጥንትም ቢሆን ከአንጀታቸው እንዳልሆነ ይታወቃል – ወያኔ ፍቅር አያውቅም – ሆዳም ፍቅር እንደማውያቅ ሁሉ፡፡ ኢትዮጵያ የይምሰልም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ያላት መሆኗ ተረስቷል፡፡ ያ ጉልቻ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና አምባሳደር ሸኚና ተቀባዩ ዘፍዛፋው ፕሬዚደንት መቶ አለቃ አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ስማቸው የሚነሣው ከስንት አንዴ ነው – የማስመሰል ድራማ ሲያስፈልግ ብቻ፡፡ እኚህ መናጆ የመሀል ሀገር የተጋቦት ወያኔዎች፣ ደንበኞቹ ወያኔዎች የራሳቸውን ሰዎች እስኪተኩ ድረስ ወንበር ለመጠበቅ የተቀመጡ መሆናቸውን ማናችንም እናውቃለን፡፡ አሰለጦቹም ያውቃሉ፡፡
ፋውንዴሽኑ ተቋቋመ፡፡ ለነርሱ የዚህ ፋውንዴሽን መቋቋም ልዩ ዓላማና ተልእኮ አለው፡፡ ለብዙኃኑ ኢትዮጵያውያን ግን የመለስና በሙት መንፈሱ የሚመራው የሕወሓት ጀምበር ለይቶላት እስክትጠልቅ ድረስ ብዙ ነገርን እንዘክርበታለን፡፡ ኑሯችን ከእጅ ወደ አፍ መሆንም አቅቶት በሚሊዮኖች የምንቆጠር ዜጎች ደመወዝም እያገኘን ወደለማኝነት የወረድንበትን ዘመን፣ በተወለድንባት የጋራ ሀገር ጥቂቶች ሲዘማነኑባት ብዙዎቻችን ግን እንደመፃተኛ ከየምንኖርበት ቀዬ በመንግሥት ጃዝ ባይነትና መሣሪያና መመሪያን ከማውረድ ጀምሮ ሌሎች ሁኔታዎችን በወያኔ አመቻችነት በሚቀለጣጠፍ የዘር ማጥፋት ዘመቻ እየተባረርን ለሞት፣ ለመፈናቀልና ለስደት የተጋለጥንበትን የአድልዖ ዘመን፣ አማራነትን በበጎ ፈቃድ ከፈጣሪ ተሠልፈን ያገኘነው ይመስል ‹ለምን አማራ ሆናችሁ ተፈጠራችሁ?› በሚል ከአቅማችን በላይ የሆነ ምክንያት እየተገደልንበትና እየተጋዝንበት የምንገኝበትን ልዩ የዘረኞች መፍለቂያ ዘመን፣ አንድ ላይ ቢሰባሰቡ አንድ ታላቅ ሀገር ሊፈጥሩ የሚችሉ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ሀገራቸው የገሃነም እሳት ስለሆነችባቸው በመላዋ ዓለም ተሰድደው በሁለተኛ ዜጋነት የሚኖሩበትን የግፍ ዘመን፣ በሀገር ውስጥ ለም መሬታችን ለወያ ሹምባሽ ባለሀብትና ለሕንድና ቻይና የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎች በርካሽ እየተቸበቸበ ኢትዮጵያውያን በዘውጋቸው፣ በሀገራዊ አቋማቸውና አንዳንዴም በሃይማኖታቸው ምክንያት ከመኖሪያና ከሥራቸው እየተፈናቀሉ ወደባሰ ድኸነትና ጎዳና ተዳዳሪነት የተዛወሩበትን የበቀል ዘመን፣ ጥቂቶች ጠግበው መሬት ሲጠብባቸውና ከድሃው የሚመዘብሩትን ገንዘብ ማስቀመጫ ሲያጡ ሚሊዮኖች በድኽነት የሚሰቃዩበትን የመከራና የበይ ተመልካችነት የማይረሣ ዘመን፣ ብዙዎች ለመኖር ሲሉ እምነታቸውንና አቋማቸውን እየለወጡ ከጎጠኛው ሥርዓት ጋር የሚሞዳሞዱበትን የክህደትና የአድርባይነት ዘመን፣ ፍርሀት ከላይ እስከታች ሠፍኖ ምሁራንና ዐዋቂዎች ለሆዳቸው አድረው ወይም በይሉኝታ ገመድ ታስረው እውነትን የሚናገርና ሕዝብን የሚያሰባስብ ኃይል ጠፍቶ ማይማን ጋላቢዎች ሀገሪቱን እንደፈለጉ ሽምጥ የሚጋልቡ የወያኔ ደናቁርት የነገሡበትን ዕኩይ ዘመን፣ ሀገሪቱ በጎሣና በዘር እንዲሁም በሃይማኖት ተሸንሽና ዜጎች እርስ በርስ እንዲተላለቁ ሁኔታዎች የተመቻቹበትን ነገር ግን ሕዝብ ከወንበዴው መንግሥት ተሽሎ ይህን መሠሪ ተንኮል ሙሉ በሙሉ ባይሆንም በተወሰነ ደረጃ ያከሸፈበትን አስገራሚ ዘመን… የምናስታውስበት ፋውንዴሽን ነው፡፡ ይህ ፋውንዴሽን ራቁቱን የወጣ የሕዝብ ድህነትንና በተስፋ መቁረጥ ማዕበል የተመታን የቀቢፀ ተስፋን ትውልድ የምናስታውስበት፣ ዕብደትና ሰካራምነት፣ ማጭበርበርና ማምታታት፣ በዛሬ ከምሞት ነገ ልሙት የአህያ ተረት የተጠለፉ ዜጎች አቅላቸውንና ኅሊናቸውን ስተው በሥልጣንም ይሁን በንግድ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ገንዘብ በመዝረፍ በአቋራጭ የሚከብሩበትን አጋጣሚ የምናስታውስበት፣ ከሞላ ጎደል አብዛኛው ዜጋ በአንድ ወይ በሌላ ምክንያት በችግርና በመከራ አብዶና ሰክሮ የምናይበትን ሁኔታ የምናስታውስበት የዘመነ ግርምቢጥ መታሰቢያ ሀውልት ነው፡፡ መፍረሱ ባይቀርም እስኪፈርስ ኅሊናችንን መቆጥቆጡ የሚጠበቅ ነው፤ መቻያውን ይስጠን፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ በትናንትናው ዕለት የኬንያው ኡሁሩ ኬንያታ ሢመተ በዓል በናይሮቢው ስቴዲየም ውስጥ የወያኔውን ቅን ታዛዥ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ መከናወኑ የሚታወስ ነው – ዋናው ጠ/ሚኒስትራቸው መለስ ዜናዊም በመንፈስ ሳይገኝ እንደማይቀር ይገመታል፡፡ ይህ ሰው – ኡሁሩ – በአንድ የምርጫ ወቅት አጠፋው በተባለ ጥፋት አይሲሲ የሚባለው ዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት – ይቅርታ – ዓለም አቀፍ ወንጀለኞችን የሚዳኝ ፍ/ቤት – የመያዣ ካርኒ ቆርጦበት ሲያበቃ የሀገሩ ፕሬዚደንት እንዲሆን ሕዝቡ በጠባብ ድምፅ መርጦታል(እዚህች ላይ ራይላ ኦዲንጋ ሽንፈቱን ላለመቀበል ማንገራገሩን በጎሪጥ ማየቴን ሳልጠቅስ ባልፍ ሌላ አጋጣሚ የማላገኝ ከሆነ ይቆጨኛል – የአፍሪካ ክፉ ዐመል ሆኖ ቀረ ልበል? ባይሆን 99.64 በመቶ ቢሸነፍ ኖሮ አንዳች ነገር አለ ብለን መጠራጠርና ለሰውዬውም ማዘን እንችል ነበር፤ ይችኛዋ ግን የሥልጣን ፍቅር ታስመስልበታለች! ይህች ሥልጣን ምን ዓይነት ክፉ ደዌ ናት ለካንስ! ለኔ ካልሆነ ይበጣጠስና ይጣል ይባላል?)፡፡ ስለክሱ ጉዳይ ወደፊት የሚታይ ሆኖ በአሁኑ ሁኔታ ግን ሕዝብ የፈለገውን መምረጡ በአንድ በኩል የሚቀበሉት ሆኖ በሌላ በኩል ይህ ዓለም አቀፍ የብይን ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ለስንትና ስንት ጊዜ ፍትህ ሲዛባ ዜጎች ከፍርድ ውጪ በጠራራ ፀሐይ ሲጨፈጨፉ… በጨረፍታም ቢሆን ለማየት አለመፈለጉ ‹ዓለም የማን ናት?› የሚያስብል ግርምትን መፍጠሩ አይቀርም – ቢያንስ በእኔ ጭንቅላት ውስጥ፡፡ ኔቶንና አይሲሲን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ አኮርባጆች መቼና የማን ጉዳይ ሲሆን ነው አለንጋቸውን የሚያነሱት? የሚለው ጥያቄ ሁሌ ይከነክነኛል(እዚህ ላይ – እነዚያ ወገኖች የሚያራምዱትን ‹ዳብል ስታንዳርድ› ለማመልከት ፈልጌ እንጂ ኡሁሩ ለምን ተከሰሰ የሚል ቅሬታ ኖሮኝ አይደለም – ካጠፋና ከተፈረደበትም ይታሰር)፡፡
ታስታውሱ እንደሆነ የፍልስጥኤም ሕዝብ አንድ ወቅት ይሻለኛል ያለውን ሃማስን በዴምክራሲያዊ መንገድ መረጠ፤ ‹ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ› ‹አይ፣ ሃማስን እኛ ስለማንፈልገው አንተ መምረጥ ያለብህ አንተ የምትፈልገውን ሳይሆን እኛ የምንፈልገውን አልፋታህን ነው› አሉትና አስገረሙት – አስገረሙን፤ የኛው የኛ ቅንጅትን መምረጥና የነሱ ወያኔን መምረጥ የቅርብ ትዝታችንም የሚዘነጋ አይደለም – ያ ሁሉ ሕዘብ ሲያልቅና እሥር ቤት ሲታጎር አይሲሲ የተባለው አለንጋቸው የት እንደነበር የሚያውቁት እነሱ ብቻ ናቸው(እግዜር ይይላቸው!)፡፡ እንግዲህ ይታያችሁ – ከላይ የተቀመጠው ፍርደ ገምድል እንዲህ ያለ የቁጭ በሉ ሥራ ከሠራ እታች ያሉት እነ ወያኔ ከዚህ የበለጠ ቢሠሩ ማን ሃይ ሊላቸው ይችላል? ዋናው የአለቆቻቸውን ትዕዛዝ ማክበራቸው እንጂ የሕዝብ ፍላጎት ከቁብ እንደማይገባ ብዙ አብነቶችን መቃኘት ይቻላል፡፡ የነፓናማ፣ ግሪናዳ፣ሆንዱራስ፣ ቬንዙዌላና ሌሎች ምሥኪን ሀገሮች ሕዝብ የሚያፈቅሯቸው መሪዎች በልዩ የጦር ጣልቃ ገብነትና በፈረደበት የ‹አውሮፕላን አደጋ› ሤራ እየተገደሉ ለሕዝብ ለማይጠቅሙ ነገር ግን ለታላላቅ ሀገሮች ኩባንያዎች በተለይም ለአሜሪካውያኑ የነዳጅ ቁፋሮ ኮርፖሬሽኖች አደግድገው ለሚያገለግሉ ወያኔን መሰል ድርጅቶችና ግለሰቦች ሥልጣኑ ይተላለፋል – የዚህች ዓለም ገመና መቼም የጉድ ነው ፣ ተወርቶም አያልቅ፤ ጊዜ ሲያልፍ ‹እቡና ላይ ቁጭ ብለን ለማውራት ያብቃን› እንጂ ይሄ ሆድና ሥልጣን የማይፈጥሩት ነገር የለም – ‹ሆድ እንኳን ከፊታችን ሆነ፤ እኋላችን ቢሆን ኖሮ ገፍትሮ ገደል ይከተን ነበር› የሚሉ ወገኖች ትክክል ናቸው፡፡
ሕዝብ የሚወዳቸው የሕዝብ ዕንባ ጠባቂዎች ተወግደው ሕዝብ የሚጠላቸው ይሾማሉ፤ የነዚህኞቹ ጥፋት ለከበርቴ ሀገራት አመራሮች እንደልማት ይቆጠራል፤ ሕዝባቸውን ለማስደስት የሚሠሩ ካሉ ግን ያ እንደትልቅ ጥፋት ይቆጠርና ሕይወታቸው ባጭር እንዲቀጭ ወይም ከሥልጣን እንዲወገዱ ሸር ይጎነጎንላቸዋል፤ ምድረ ታጣቂ ሰላይ ይከብባቸውና ወደተዘጋጀላቸው እንጦርጦስ ባፋጣኝ ይወርዳሉ፡፡ ዓለም የአስመሳዮች መድረክ ናት፡፡ ይህን ጉዳይ በሚመለከት ይበልጥ ለመረዳት ጆን ፐርኪንስ የተባለ ንስሃ የገባ የቀድሞ ሰላይ የጻፈውን ድንቅ የማጋለጫ መጽሐፍ ማየት ይጠቅማል – ርዕሱ Confessions of an Economic Hitman ነው፡፡
የመጽሐፎች ሁሉ ቁንጮ የሆነው ቅዱስ መጽሐፍ ‹ኩሎ አመክሩ፣ ወዘሠናየ አፀንዑ› ስለሚል ተበልቶ ለሚጠፋ ቂጣ ብለን እውነትን አንሽሽ – አንዳንዴ ለመንፈሳዊና ለአእምሮኣዊ ሕይወታችንም እንጨነቅ፡፡ አሥር ለማይሞላ ዓለም ዘወትር ቀና ደፋ ስንል ብዙ ነገሮችን ሳናውቅ ከዓለም እንለያለን፡፡ ማንበብ ደግሞ የተሸፈነ እውነትን ያወጣልና አንባቢም አስነባቢም በዚህ ረገድ ባይሳነፍ መልካም ነው፡፡ ይህን የምለው ከተለመደው ቅኝት ወጣ የሚል ነገር የምንጽፍ ሰዎች የሚደርስብንን ውግዘትና መድረክ ክልከላ ስለማውቅ ነው፤ በጣት ከሚቆጠሩ ድረገፆች በስተቀር – ለምሳሌ – ብዙዎች ድረገፆች ከኢትዮጵያ ፖለቲካና ከዚያም ውስጥ እነሱ ከሚፈልጉት ርዕሰ ጉዳይ ውጪ ሌላ ነገር የማስተናገድ ፍላጎታቸው እንደ ጋሪ ፈረስ ዕይታ በእጅጉ የተገደበ ነው፤ ስለዴሞክራሲ እየጻፉ ዴሞክራሲን እንደዶሮ አርደውና በልተው ሲጥሏት ቅር አይሰኙም፡፡
ከመብት አንጻር ይህን አካሄዳቸውን በበኩሌ አልቃወምም፡፡ እንዲያ ባይሆንና አስተሳሰባዊ የግዛት ‹ምኅዳራቸው› ጥቂት ሰፋ ቢል ግን ምርጫየ ነው – ከሙያና ለዓለማችን አሁን ከሚያስፈልጋት ሆደ ሰፊነት አኳያ፡፡ ለዚህ ግን የንባብ አድማስን ማስፋት፣ የመቻቻል ባህልን ማዳበር፣ የዴሞክራሲን ሥነ ተፈጥሮ መረዳትና(ተቃራኒ ሃሳቦችን በነጻነት የማንሸራሸርን በጎ ገጽታ) በረባ ባልረባው ሰዎችን ከመኮነን መቆጠብን መለማመዱ ገምቢ ይመስለኛል – ኩርፊያና የማይስማሙበትን ሀሳብ ገሸሽ ማድረጉ በሕጻናት ዘንድ ካልሆነ በዐዋቂዎች አያምርም፡፡ የሚስማሙበትን ሃሳብ ብቻ እየመረጡ መውሰዱና ማስተናገዱ በእነሱም ቤት አለ – በፈለግኸው የ‹እነሱ› ዐውድ መረዳት ትችላለህ፤ እኛ ከ‹እነሱ› የምንሻል መሆናችንን የምንገልጸው እኛ በምንም መንገድ ከ‹እነሱ› የማንሻል መሆናችንን በማሳየት ሊሆን አይገባም – አለበለዚያ የ‹እኛ›ና የ‹እነሱ› ልዩነት አይኖርም – በ‹እኛ›ና በ‹እነሱ› መካከል ያለው ድንበርም የማስመሰልና አንዲትን በየፊናችን የምንነታረክባትን ወርቃማ ዕድል የማግኘትና ያለማግኘት ጉዳይ ካልሆነ የአንጀት ወይም የምር አይደለም ማለት ነው፡፡ የኩርፊያና የሆደባሻነት ሰለባዎች ከሆንን በሥፍራ እንጂ በተግባር አንድ ነን፤ በሥልጣን ቦታ እንጂ በአፈጻጸም ተመሳሳይ ነን ማለት ነው፡፡
ከነዚህ ከጠቃቀስኳቸው ነጥቦች አንጻር እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ የሚቀረን ነገር እንዳለ ይሰማኛል፡፡ ባህላችን የሚቃወሙንን ለመደፍጠጥ – በምናብም ይሁን በገቢር ወይም እስከተቻለ በሁለቱም ድባቅ ለመምታት – በቅጽበት ውስጥ የሸሚዝ እጀታን ወደመሰብሰብ የሚመራን በመሆኑ በተለይ በአሁኑ ዘመን ግልፍተኞችና ሆደ ባሻዎች እየበዛን ሳንመጣ የቀረን አይመስለኝምና መግባባት ከፈለግን ይህን ቀላል ግን መሠረታዊ የሆነ የአስተሳሰብና የአመለካከት ችግር ለማስወገድ ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል፡፡ ይሄ ቱግ ቱግ ማለትና መገፈታተር አላዋጣንም – አያዋጣንምም፡፡ እንግሊዞችን እንመልከት – በአንድ ሰው ሞት አንዱ ያለቅሳል ሌላው የደስታ ጮቤ ይረግጣል – ልክ ነው ልክ አይደለም ሌላ ጉዳይ ነው፤ ግን ስናያቸው ይቻቻላሉ – ወደቡጢና ቁርቋሶ አልተጋበዙም፤ መሠረታዊ የአብሮነት ድርና ማጋቸውን የሚፈታተን እልህ አስጨራሽ ጠብና ፍትጊያ ውስጥ አልገቡም – ሲያስቀኑ! ማንም የሚያደርገው ነገር የሌላን ሰው መብት በኃይል እስካልተጋፋ ድረስ መብቱ መሆኑን ይረዳሉና ድንበር ዘለል ግጭትና እንደኛ ጎራ የለዬ መተላለቅ ጨርሶውን አይታይባቸውም፡፡ የነገር ቁርሾ እየያዙ መናቆርና በሞተ ጉዳይ ላይ መገዳደል ባህላችን የሆነ እኛና መሰሎቻችን ነን፡፡ በበኩሌ ትልቅ ትምህርት ቀስሜያለሁ፡፡ የመቻቻልን ትርጉም በጣሙን የተገነዘብኩበት አጋጣሚ ቢኖር የማርጋሬት ታቸር ሞት ነው፡፡ ከ87 ወይም 88 ዓመት ዕድሜ በኋላ ለሰው ሞት ማዘኑን ብዙም ስለማልቀበለው እንጂ የሴትዮዋ ሞት በርግጥ ያሳዝናል፤ ደረት የሚያስጥል ግን አይደለም፡፡ (ለማንዴላ ሰዎች ያን ያህል ሲጨነቁ ይገርመኛል፡፡ ማዘንስ አንዱንም ሳይጨብጠው ገና በለጋነት ዕድሜው ለሚቀጭ፡፡ የአንዳንድ ሰው ነገረ ሥራ ለእግዜሩም ለወይዘሪት ተፈጥሮም የሚገርም ሳይሆን አይቀርም፡፡ ለታዋቂ ሰው ፈጣሪ ስንት ዕድሜ ይስጥ? መለሳውያን እንዲህ ቢንገበገቡ አይፈረድባቸውም – የተጎዳው እርሱ ብቻ ሳይሆን በዋናነት እነሱ አልቃሾቹና በግድ አስለቃሾቹም ናቸው፤ በቀላሉ ሊተኩት ባለመቻላቸው እርሱም እንደሁጎ ሻቬዝ የሚመስለውን ወያኔያዊ ማዱሮ ተክቶላቸው ባለመሄዱ ተቆጩ፤ አዘኑ፤ አለቀሱ፤ እስከህልፈታቸውም በዚህ መልክ የሚኖሩ ይመስሉኛል፤ የማያገግሙበት ክፍተት ትቶባቸው ነው ድንገት የተሰናበተው – ማን? አትሉኝም? ሙት ወቃሽ አትበሉኝና ያ ባለጌ ሰውዬ፡፡)
ለመሰነባበቻ፡-
እዚያ ማዶ ሆኖ ክፉ ሰው ተጣራ፤
እዚህ ማዶ ሆኖ ክፉ ሰው ወይ አለው፤
ጎበዝ ተጠራጠር ይህ ነገር ለኛ ነው፡፡
የተባለውን የቀደመ ነገር ላስታውስና በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ የምትተነትነውን ጢስ ፈቃዱ ከሆነ ድንበር ሳትሻገር ባጭሩ እንዲያስቀራት እግዚአብሔርን እንለምነው፡፡