December 25, 2022
5 mins read

ከጠ/ምኒስትር ከዐብይ አህመድ: ለሌቦቻቸው የቀረበ ጥሪ !! (አሥራደው ከፈረንሳይ)

leflafiw abiy

ጠቅላይ ምኒስትር ዐብይ አህመድ፤ ይቅርታ ፓስተር ዐብይ አህመድ፤ ማለቱ ሳይሻል አይቀርም፤ ሰሞኑን በወላይታ ፤ የዳቦ መጋገርያ ፋብሪካ ለመመረቅ፤ ወደ ወላይታ ሄዶ ባደረገው ንግግር ፤ በኢትዮጵያ የህወሃትና  የብልጽግና፤ (ኦህዴድ/ኦነግ/ብአዴን) ሥርዓት የፈጠሯቸው ሌቦቻቸውን፤ የኢትጵያን ሕዝብ ሃብት በመዝረፍ በህግ ፊት እንዳይጠየቁ፤ ፤ ዳቦ ቤት፤ ትምህርት ቤትና ሆስፒታሎች….ወዘተ. እንዲከፍቱለት ተማጥኗል ::

ከአንድ አገር መሪ በማይጠበቅና፤ እጅግ በዘቀጠ መልኩ፤ እመራታለሁ በሚላት አገርና፤ በሚመራው ሕዝብ ፊት ቀርቦ፤ በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት ባለመኖሩ፤ ፍትህን ማግኘት እንደማይቻል፤ በገዛ አንደበቱ ለህዝብ አረጋግጧል ::

አጠያፊ ሌቦችን በመጠየፍ፤ በህግ የበላይነት፤ ለፍርድ በማቅረብ፤ እንዲጠየቁ በማድረግ ፈንታ፤  የአገር ሃብት በመዝረፍ፤ በንቅዘት (በሙስና)  የበሰበሱትን ሌቦች፤ ዳቦ ቤት ክፈቱልን፤ ት/ ቤት፤ ሆስፒታሎችን ሥሩልን  …. ወዘተ ብሎ ሲማጠን መስማቱ፤ የኢትዮጵያን ትንሳኤ  ለምንናፍቅ ዜጎች ፤ በእጅጉ የሚዘገንንና  የሚያበሳጭ  ሆኖ አግኝቸዋለሁ ::

ከዚህ በፊት « ከሠርቶ አደር: ወደ ሰርቆ አደር  ነገስ ?! » በሚል ርዕስ ባቀረብኩት መጣጥፌ : ሌብነትና ሌቦችን በመጠየፍ ለፍርድ ማቅረብ እንደሚገባ አመላክቼ እንደነበር ፤ አንባቢዎቼ በዚህ ማስፈንጠሪያ በመጠቀም ሊቃኙ ይችላሉ ::

https://www.goolgule.com/challenges-for-change-in-ethiopia/

« ዋልታ ረገጥ ! ጽንፍ የረገጠ !  የአማራው ሸኔ ! የኦነግ ሸኔ !  ……. ወዘተ. ለሚሉት  አባባሎቹ             ሰሞኑን ከአማራ ቆዳ በተሠራ  ከበሮ: ጭፋሮ !!  በሚለው የሁለተኛው ክፍል መጣጥፌ ስለምመለስበት  ለጊዜው ትቼዋለሁ ::

ወገኖቼ እስቲ እግዜር ያሳያችሁ ! በድሃው ሕዝባችን ስም፤ በብድርና በልመና ከውጪ አገራትና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች፤ የተገኘን ገንዘብ በመዝረፍ፤ ዓሣ ዓሣ የሚሸቱ ሌቦችን፤ ዳቦ ቤት ክፈቱልን፤                      ት/ ቤትና፤ ሆስፒታሎችን ሥሩልን  ብሎ ከመማጠን በላይ፤ ምን ዓይነት የፖለቲካ ክስረት ይኖራል ?!

እርግጠኛ ነኝ፤ ለህሊናው የሚኖር ኢትዮጵያዊ፤ ሌቦች ከከፈቱት ዳቦ ቤት፤ ገዝቶ ለመብላት ቀርቶ፤ በበሩ ደጃፍ ሲያልፍ እንዳይሸተው አፍንጫውንና አፉን በጭንብል ሸፍኖ፤ እንደሚያልፍ አልጠራጠርም ::

ደግሞስ፤ ቱባ ቱባ የሆኑ ሌቦች፤ ባሠሩት ት/ ቤት ውስጥ፤ የሌብነትን ሞያ ተምረው የሚመረቁት፤ አዳዲስ ወጣት ሌቦች፤ የሚሰማሩበት የሥራ ቦታ፤ ገንዘብ ሚኒስቴር ፤ ማዕድን ሚኒስቴር፤ ብሔራዊ ባንክ፤ ንግድ ባንክ፤ የመሬት ይዞታና ማዘጋጃ ቤት ሳይሆን ይቀራል ?!

ሌቦች በሚያሠሩት ሆስፒታል ውስጥ ገብቶ የሚታከም ዜጋ፤ አንድም እንደነሱው ሌባ የሆነ፤ ወይም የለየለት ጨርቁን ጥሎ ያበደ፤ አለያም ኑሮ አስከፍቶት እድሜዬን ላሳጥር ብሎ ፤ የሚገባ ካልሆነ በቀር፤ የሌቦች ሆስፒታል ውስጥ ገብቶ፤ ማንስ ታክሞ ድኖ ሊወጣ ?!

ይህ ጥሪ የቀረበው፤ ዐብይ አህመድ በቅርብ ለሚያውቃቸው ሌቦቹ፤ የቀረበ ጥሪ ቢሆንም፤ የትኞቹ ሌቦች ጥሪውን ተቀብለው፤ በሕዝብ ፊት ሌብነታቸውን ለማስተዋወቅ ብቅ እንደሚሉ ስናስብ፤ አስቂኝም፤ አሳዛኝም፤ ባዶ ኳኳታ መሆኑን እንረዳለን ::

 

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!

ነፃነት፤ እኩልነትና ወንድማማችነት ይለምልም !!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ !!

ታኅሣሥ 16 ቀን 2015 ዓ.ም (25/12/2022) እኤአ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop