ድርድር ወይስ ማደናገር!

እንግዲህ እንዳለመታደል ሆኖ የእኛኑ የኢትዮጵያውያን ዕጣ -ፈንታ ወሳኞቹ ምሕራባዊያኑና የምዕራባውያኑ አፍሪካዊያን መሪ ነን ባይ ቡችሎች ሁነዋል።

ለነገሩ የአባቶቻችን “እምቢ ለነጭ ነጫጭባ ፣ ለባንዳ” የሚለውን ትብዕል አውልቀን ከጣልን ቆይተናል። መሪዎቻችን የእትጌ ጣይቱን አስተዋይነት ፣ አርቆ አሳቢነት ፣ የዐፄ ምኒሊክን ደፋርነት ፣ የዐፄ ቴዎድሮስን ለነጭ ተንኮል አሻፈረኝ ባይነትን ካባ አውልቀው ከጣሉ ከራርመዋል። አንድ ሃገርን በመንግስትነት የሚያስተዳድር አካል ከተራ ሽፍታ ጋር እጁን ተጠምዝዞ ድርድር ማድረግ በማንም ሥርዓተ መንግስት ታይቶም ተሰምቶም አይታውቅም።

ይህን ስል በደርግ የመጨረሻ እስትንፋስ ወቅት “ደርግ ከወያኔና ከሻቢያ ጋር ድርድር አላደረገም ወይ?” ብላችሁ ልትጠይቁ ትችሉ ይሆናል። በዚያ ወቅት የተደረገው ድርድር ሳይሆን ሕወሃት፣ ኦነግና መሰል የኢትዮጵያን መፍረስ የሚያፋጥኑ ቡድኖቹ ወደ ሚኒልክ ቤተ – መንግሥት እንዲገቡ ለማድረግ የተከወነ የሸፍጥ መደላድል የተወጠነበት አካሄድ እንደነበር ማንም ሊዘነጋው አይገባም።

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት ተብሎ አራት ኪሎ በአሜሪካን ተንኮልና አቀነባባሪነት ለ 27 ዓመታት ተሰይሞ የነበረው የህወሃት ቡድን በጥቅም ግጭት  ከኤርትራው ሻቢያ ቡድን ጋር ሲፋለሙ እንደ አሁን በአፍሪካ ህብረት /OAU/ አስተባባሪነት በአልጀሪያ-አልጀርስ ድርድር ተደርጎ ነበር ። ነገርግን ድርድሩ ፉርሽ የሆነው የሁለቱ መሪዎች የስምምነት ፊርማ ሳይደርቅ እንደነበረና “ያለጦርነትና ያለለሰላም መኖር ‘ No war no peace’” በሚል የማይተገበር ትብዕል እንደተዘለቀ ታውቃላችሁ ። ይህን መሰረት አድርገን የዚህ ድርድር ዳፋ አማራውንና ትግሬ ውን በዚህ ጉንጭ አልፋ የሌለ መርኋቸው አፋጠውት የስልጣን ዘመናቸውን እያረዘሙ ሊዘልቁ ይሆን የሚል ፍራቻና ጥርጣሬ አለ። ኦነግ ተብየውን መሰል ተገንጣይ የእነ ሌጮ ለታ ቡድን “ ሥልጣንን ተከፋፍለን ኢትዮጵያን እንምራ “ በሚል ተደራድሮ ወደ ኢትዮጵያ ካስገባ በኋላ የአሁኑን አያድርገው እንጂ እንዴት ህወሃት ቡድኑን እንዳፈራፈረው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።   መቸም የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚደርስበት መከራ ምክንያት የማስታወስ ችሎታው እየቀነሰ ነው / Short memory/ እንደሚሉት ማለት ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያ ወይንስ የኦሮምያ ንግድ ባንክ? የኦሮምያ ወይንስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ?... ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ይህን ካልን ዘንዳ በደቡብ አፍሪካ -ፕሪቶሪያ ከኢትዮጵያ ተወካዮ በድን ብልፅግና እና ከህውሃት ጋር የተደረገውን ድርድርና የስምምነት ዳራ ከተሞክሮና ከድርድር ፅንሰ ሃሳብ ጋር አገናዝበን እንገምግመው። በመልካም ልቡና ፣ ሰላምን በመሻት ፣ ያለብልጣብልጥነትና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚከናወን ድርድር እሰየው የሚያሰኝ ነው። ህወሃት በታሪኩ የማይፈራውና የሚደፍረው ነገር ቢኖር ድርድር ነው። አቅሙ በደከመ ጊዜ ፣ እንደገና አፈር ልሶ ለመነሳት ሲያስብ ፣ ለጦርነት ዝግጅት ጊዜ ካስፈለገው ፣ ተፃራሪዎችን ለመሰልቀጥ ባሰበ ጊዜና በተለያየ መልኩ በተወጣጠረ ጊዜ ድርድር ካሉት “ ሰርግና ምላሹ” ነው።

እስኪ ከዚህ ቀደም ድርድር አድርጎ የሰራውን ጉድና ክህደት እንዘርዝር። ህውሃትን እንደ አማራ ሕዝብ በተለይ እንደ ጎንደር ሕዝብ የሚያውቀው የለም ለማለት እደፍራለሁ። ምክንያቱም በሰላምም ሆነ በጦርነት ወቅት እነዚህ ሕዝቦች አብረው በፍቅር ኑረዋል ፣ ተፋልመዋል ነገር ግን ህወሃት የአማራን ሕዝብ “ወጭት ሰባሪ”ና “በአጎረስኩ ተነከስኩ” እንዲሉ በተደጋጋሚ ክዶታል። ይህ እውነታ ለሌላው ኢትዮጵያዊ ብሔር ብሔረሰብ ( ሕዝቦች ብል ይሻላል) እንግዳ ሊሆን ይችላል።

አስኪ አጠር አጠር በማድረግ ከቅድመ ወያኔ መፈጠር ጀምሮና ወደኋላ የዘመናት ክህደታዊ ክስተቶችን እንከትብ ። ዐፄ ዮሃንስ እንደ ልጃቸው አርገው ያሳደጉትን ታላቁን የአንድነት ቀንዲል ዐፄ ቴዎድሮስ ከእንግሊዝ ጋር በመላላስ ክድዋቸዋል ፣ ለእለፈት ህይወታቸው ምክንያት ሁነዋል። ቀደም ያሉትን የክህደት መዝርዝሮች እናቆያቸውና በድርድር ስም የደርግን ስርዓት ለማስወገድ አብረው ተሰልፈው የነበሩትን እነ ኢዲዮን ፣  ኢሕአፓንናም ፣ ከፋኝና የወልቃይት ታጋዮችን ህውሃት እንዴት አድርጎ እንዳካደ እንመልከት።

ኢዲዮ የተባለው በድን በአርማጭሆ ፣ መተማ ፣ ወልቃይትና ጠገዴ ደርግን ለማስወገድ ይፋለም የነበረ ድርጅት ነበር። በተለይ የዚህ ቡድን መሪዎች ራስ አዳነ ስዮም የወልቃይትና ጠገዴ ገዥ ራስ መንገሻ ስዮም የትግራይ ገዥ ፣ ጄነራል ነጋ ተገኝ ወዘተ እንደነበሩ ታሪክ ያትታል። ኢዲዮ እየጠነከረ ሲመጣ ራስ እዳነ ስዮምን በድርድር ስም እንዴት እንደበሉ ፣ ኢሕአፓንና የወልቃይት ፣ ጠገዴ ተፋላሚዎቻቸውን በአብረን እንታገል ስም ከደርግ ጋር ተመሳጥረው እንዴት እንደ መቷቸው ሃገር ያወቀው ፀሃይ የሞቀው ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በቤተልሄም የወሲብ ጉዳይ ‹‹ዴሞክራት›› ለመባል የፈለጉት አቶ አብርሃም ደስታ

ይህን ለማስታወስ የሞከርነው “ ወያኔም ማመን ቀብሮ ነው። ለማለት ነው። እንግዲህ ወደ ሰሞኑ የደቡብ አፍሪካ – ፕሪቶሪያ ክስተት ስንመጣ ፣ ህወሃት ወደ ድርድር የመጣው አቅሙ ስለደከመ ፣ ድርድሩ አካታች አይደለም ምክንያቱም በዚህ ጦርነት በህወሃት የተጎዱት የአፋርና የአማራ ሕዝቦች አልተወከሉም ፣

ህውሃት ወደ ጦርነት የገባበት ዋነኛ ምክንያቶች በአጀንዳነት ተሰንደው ማለትም የማይገባውንና በታሪክ የትግራይ አካል ሆኖ የማያውቀውን “ የላም አለኝ በሰማይ ወተቷን የማላይ” የወልቃይት ፣ ጠገዴ ፣ ሰቲት ሁመራና የራያ ጉዳይ በድርድሩ ላይ ቢነሳም የተነሳው የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ግብረ መልስ ይፋ አልሆነም። በይደር የተቀመጠ አጀንዳ ለቀጣይ ጦርነት ስለሚዳርግ በኢትዮጵያ በኩል ተወክለው የሄዱት “ አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ “ እንዲሉ ጉዳዮን የአማራና የትግራይ ሕዝብ ለቀጣይ ጦርነት እንዲነሳ ፣ እርስ በእርስ እንዲፋጅና “እኛን አይመለከተንም” በሚል  በእጓጉል የግብር ይውጣ ስሜት አልፈውታል።

 

መላ የኢትዮጵያ ሕዝብም “ አለ ነገር የማይነገር” ብሎ እያጉረመረመ ነው ። በሕውሃት በኩል ተወክለው የስምምነቱን ፊርማ የፈረሙት በአማራነት የሚታሙት አቶ ጌታቸው እረዳ በመሆናቸው ፣ ህወሃት ይህን ያደረገው ነገ ስምምነቱን ለማፍረስ “ትክክለኛ ተጋሩ ትግራዊያን ፊርማችንን አላስቀመጥንም ፣ ድርድሩ አይመለከተንም” እንደሚሉ ከልምድ የሚታወቅ ነው። ለምን  ፃድቃን አልፈረመም?

ብልፅግና እና ሕውሃት እጅ ለእጅ ቢጨባበጡም ፣ እኛ ኢትዮጵያዊያን ፣ አማሮችና አፋሮች የምናስበው “ ሁለት የተነፋፈቁ አጋር ፓርቲዎች ፣ ተራርቀው በመቆየታቸው የተነሳ ቀን ደርሶ ናፍቆት አጋመዳቸው “ እንላለን እንጂ ሕዝብ እንደ ሕዝብ በይቅርታ ልቦና ስይታረቀ ፣ የእጅ መዳፋቸው እስካልተላጠ ድረስ “ ድሮም ወዳጆች ናቸውና” ቢተቃቀፉ አይደንቀንም፣

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከነመላኩ ፈንታ በኋላ የቆመ መርከብ የሆነው ፀረ - ሙስና ኮሚሽን

ብድርድሩ ይመለከታቸዋል የተባሉ ቡድኖች ፣ የሃገር ሽማግሌወች ፣ የታሪክ አዋቂወች ፣ የሃይማኖት መሪዎች ወ.ዘ.ተ. እካልተሳተፉ ድረስ ፣ ይሁንታቸውን ሆነ ቅሬታቸውን እስካልገለፁ ድረስ የድርድሩ ግልፅነትና አሳታፊነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባው ነው።

በአጠቃላይ እውነተኛው የጦርናቱ መነሻ ፣ የጉዳቱ መጠነ፣ የዚህ ሁሉ ሞት ፣ መደፈር ፣ የመሰረተ ልማት መውደም ፣ መፈናቀልና አጠቃላይ ለሃገሪቱ ምስቅልቅል ውስጥ መግባት ተጠያቂ የሆነው አካል ነጥሮ ሳይወጣ ፣ ለፍርድ ሳይቀርብና የካሳ ክፍያና የዕርቅ መድረክ ሳይመቻች እንደ ባልና ሚስት ጠብ “ እንተ ትብስ ፣ አንቺ ትብሽ “ በሚል መልኩ የሚቋጭ ድርድር ጉልበት መጨረስ፣ ገንዘብ ማጥፋት ፣ ጉንጭ ማልፋትና ዘላቂ መፍትሄ ያላስቀመጠ ፣ ይልቁንስ “በመርዝ የተለወሰ “ ድብቅ አጀንዳ ለመጭው ትውልድ አስቀምጦ ያላፈ ድርድር  እንደሆነ አስረግጠን እናሳስባለን።

ተዘራ አሰጉ

ከምድረ እንግሊዝ

4 Comments

 1. ወንድሜ ተዘራ – ልክ ብለሃል። ሰው የሚመዘነው በተራመደበት፤ በኖረበት፤ ባደረገው ተግባር እየተለካ ነው። ወያኔ በታሪኩ ለሰላም እጅን ሰጥቶ አያውቅም። በሰላም ስም ብዙዎችን አታሎ አፈር እንደመለሰባቸው ግን የራሳቸው ታጋዪች ሳይቀር የጻፉትን፤ የተናገሩትንና አሁንም የሚነግሩንን አበጥሮ ማወቅ ያስፈልጋል። ሲጀመር ወያኔ በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜም ሆነ አሁን ሰዎችን ለዝንተ ዓለም ደም የሚያቃባ ተግባርን ሲፈጽም የነበረው ለራሱ የህልውና መራዘም የረጅም ጊዜ እቅድ ነው። እኛ ስንናቆር እነርሱ ሊያምርባቸው። ኢትዮጵያን ሲኦል ድረስ ወርደን እናፈርሳታለን ያለው ጌታቸው ረዳ ዋና ተደራዳሪና የስምምነት ተብየው ፈራሚ መሆኑ በራሱ የሚነግረን የተንኮል ገመድ አለው። ይህ ስምምነት ተፈረመ ከተባለ በህዋላ የሚወጡ ዜናዎችን ለተመለከተ አሁንም የወያኔ የነጭና የሃገር በቀል ደጋፊዎች ጦርነቱ እንዲቀጥል እንደሚፈልጉ ያመላክታል። ለምሳሌ Alex De Wall በቢቢሲ ላይ የጻፈውን ላነበበ የጦርነቱ እሳት እንዳይጠፋ እሱና መሰሎቹ እንደሚሰሩ ያሳያል። ሌላው ጡሩንበኛና የተንኮል ሰው Martin Plaut ለፈረንሳዪ 24 ቴሌቪዥን በቅርብ ቀን የሰጠው ትንተና አስተዛዛቢ ነው። በዚህ ላይ በዓለም ዙሪያ በየስርቻው የተሸጎጡ የወያኔ የሩቅ አዋጊዎች አሁንም ጦርነቱ እንዲቀጥል በሚፈልጉ እብዶች የተሞሉ ናቸው። እብዶች ምእራብ ትግራይ ምስራቅ ትግራይ ይላሉ፡፡ እውነቱ ግን ሁሉም የኢትዪጵያዊያን ምድር ነው፡፡ ሰው በሰላም ወጥቶ የሚገባባት ምድር ብትሆን ኑሮ በአንዲት ሃገር ውስጥ ሰው በክልል ፓለቲካ ተሳክሮ በድንበር ጉዳይ ባልተጋፋም ነበር፡፡ የሚያሳዝነው የማያባራ የመከራ ዝናብ እንዲዘንብ ወያኔ ሆን ብሎ በቀበረው የሸር ፈንጅ ሁሉም ሰው እየተጎዳ መሆኑ ነው፡፡
  ባጭሩ ይህ የሰላም ፊርማ ሳይደርቅ ከአራቱም ማዕዘን በለመድነው መሰረት እየተገዳደልን የምዕራባዊያን ተመጽዋች እንድንሆን በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር የሚሰሩ ሃይሎች በሙሉ ሃይላቸው ተንኮል በመሸረብ ላይ ይገኛሉ። አንድ የቅርብ ጓደኛዬ የሆነ የመቀሌ ልጅ ጋር ትጥቅን በመፍታት ዙሪያ ስንጫወት በጣም ተበሳጭቶ እንዴት ትጥቅ ይፈታል በማለት ልቡ እስክትቆም ጮኽና ሲጨርስ እንዲህ አልኩት። እንኳን የወያኔ ሰራዊት ያለ ልቡ እየታፈነና እየተገፈፈ የገባው ቀርቶ፤ የጃፓን፤ የጀርመን፤ የጣሊያ ወዘተ ወታደር ትጥቅ ፈትቷል። የሃበሻው ጉራ ሰማይ ጠቀስ ስለሆነ እውነትን ለማየት ይከብደናል። ለዛ ነው ቡራ ከረዪ የምናበዛው እንጂ የወያኔ መታጠቅ ለህዝባችን ጥቅም የለውም፡፡ ለዘመናት ታጥቀው ያመጡትን አይተናልና ስለው ረገብ ብሎ ልክ ነህ በማለት ነገራችን በሌላ ወሬ ተለወጠ፡፡ የሰው ልጅ እስከ መቼ ድረስ ሲገዳደልና ገደል ለገደል እንደ አውሬ ሲሮጥና ሲያሯሩጥ ይኖራል? እህቱን ወንድሙን አባቱንና እናቱን ገድሎ ከሚፎክር የእብድ ጥርቅምስ እንዴት ሰላም ይመነጫል?
  ወያኔ በበረሃ ዘመኑ በትግራይ ህዝብ ላይ ያደረሰው በደል ቢመዘን ድርጅቱ እንኳን ትግራይን መምራት ቀርቶ መሪዎቹ በህይወት እንዲኖሩም ባልተፈቀደ ነበር፡፡ ግን የፈሰሰው የድሃ ልጅ ደም ነው፡፡ ዛሬም የሚፈሰው የድሃ አደግ ልጆች ደም ነው፡፡ መግደል መገዳደል ለማንም ለምንም አይጠቅምም፡፡ ወያኔ ግን ገና ከጅምሩ ሰው መግደልና ማሰቃየት በኩራት የለበሰው መለያው ነው፡፡ ከላይ እንደተባለው ከወያኔ በፊት ትግራይ በረሃ ውስጥ የነበሩ የትግራይ ተንቀሳቃሽ ሃይልን፤ ኢዲዪን፤ ሌሎችንም ሽፍታ ናቸው የሚባሉትን ሁሉ ኑ አብረን እንታገል በማለት በማታለል ነው የጨፈጨፋቸው፡፡ በሰሜን እዝ ላይ ያደረሰውን ግፍ በጭልፋ ለማየት ” የተካደው የሰሜን እዝ” የተሰኘውን ፈልጎ ማንበብ ያሻል፡፡ ሌላው ግፍ ሁሉ በሆያ ሆዬ እየተሸፈነ እየተረሳ ነው፡፡ ይህ ስምምነት ተግባራዊ ይሆናል አይሆንም ለምትሉ በእኔ እይታ 50% እድል እንኳን አልሰጠውም፡፡ የሰሜን ሰራዊት የወያኔን ጥቃት ቀልብሶ መቀሌ ከገባ በህዋላ በሰራዊቱ ላይ ህዝቡ ራሱ ገቢያተኛ መስሎ፤ እርጉዝ መስለው በርበሬና ሚጥሚጣ በመያዝ ነበር የወጓቸው፡፡ ለዛ ነው ሠራዊቱ ለቆ የወጣው እንጂ ለእርሻ ጊዜ ለመስጠት አልነበረም፡፡ ያኔ የትግራይ ህዝብ ከሰራዊቱ ጎን ሆኖ ታግሎ ቢሆን ኑሮ አሁን እልፎች በየጥሻው ወድቀው በትግራይ በአማራና በአፋር ክልል ባልቀሩ ነበር፡፡ ሰላምን ማንም አይጠላም፡፡ ግን ዝንተ አለም ሲገድልና ሲጋደል የኖረን ህዝብ የተለዬ ህይወት አለ እባካችሁ ይብቃ በማለት አማራጭ መንገድ ለማሳየት የክፋቱ ቋት ወያኔ መፈንገል አለበት፡፡ ወያኔ እያለ የትግራይ ህዝብ በራሱ አስቦ መኖር አይችልም፡፡ 1 ለ 5 የፓለቲካው እስራት ይቀጥላል እንጂ! Sor Juana Inés de la Cruz ” You Foolish Men” ከተሰኘው ግጥሙ የወሰድኩትን ልጥቀስና ይብቃኝ፡፡
  What kind of mind is odder
  than his who mists
  a mirror and then complains
  that it’s not clear.

 2. በእውነት ምን ይሻለናል?

  አገራችንን በዘር ፖለቲካ ተጠቅሞ ባልተጠበቀ የመከራ ጎርፍ ውስጥ የከተታት (በተለይ አማራውን) TPLF ትጥቅ ሊፈታ ተስማማ ሲባል የከፋቸው ሰዎች ዋና ዓላማ ምን እንደሆነ ፈጽሞ አልገባ አለኝ!

  ምናለ ሰውን በጥርጣሬ ላይ ተመስርተን ስምን ጥላሸት ቀብቶ በአሉባልታ ከማጥፋት ይልቅ ከሚጽፈውና ከሚናገረው ባለፈ ሚዛን በሥራው ውጤት ቢሆን? ይህን ብናደርግ በእውነት ስህተት ከመሥራት እንድናለን የሚል ጽኑ እምነት አለኝ!

  ሁሉም አዋቂና ሌላውን ነቃፊ በሆነበት ማህበረሰብ ውስጥ አዋቂና በሳል ሰው አለ ብየ አላምንም! አዋቂነትም የሁሉትና የሦስት ዓይነት ዲግሪ ባለቤት መሆን ወይም ጥሩ ጸሐፊ መሆን እንዳልሆነ ባልተማሩ ሰዎች የተሠሩ አስደናቂ ሥራዎችን የህብረተሰብ ታሪክ ዋቢ ጠቅሶ ያስረዳናል::

  ስለዚህ ለጋራ ሐገር ወቃሽና ተወቃሽ ወይም ጠርጣሪ እና ተጠርጣሪ ወይም ተቆርቁዋሪና ግዴለሽ እያልን ከመፈራረጅ እና ከመናቆር በሚታይ ሥራ እንመዛዘን???

 3. በእውነት ምን ይሻለናል?

  አገራችንን በዘር ፖለቲካ ተጠቅሞ ባልተጠበቀ የመከራ ጎርፍ ውስጥ የከተታት (በተለይ አማራውን) TPLF ትጥቅ ሊፈታ ተስማማ ሲባል የከፋቸው ሰዎች ዋና ዓላማ ምን እንደሆነ ፈጽሞ አልገባ አለኝ!

  ምናለ ሰውን በጥርጣሬ ላይ ተመስርተን ስምን ጥላሸት ቀብቶ በአሉባልታ ከማጥፋት ይልቅ ከሚጽፈውና ከሚናገረው ባለፈ ሚዛን በሥራው ውጤት ቢሆን? ይህን ብናደርግ በእውነት ስህተት ከመሥራት እንድናለን የሚል ጽኑ እምነት አለኝ!

  ሁሉም አዋቂና ሌላውን ነቃፊ በሆነበት ማህበረሰብ ውስጥ አዋቂና በሳል ሰው አለ ብየ አላምንም! አዋቂነትም የሁሉትና የሦስት ዓይነት ዲግሪ ባለቤት መሆን ወይም ጥሩ ጸሐፊ መሆን እንዳልሆነ ባልተማሩ ሰዎች የተሠሩ አስደናቂ ሥራዎችን የህብረተሰብ ታሪክ ዋቢ ጠቅሶ ያስረዳናል::

  ስለዚህ ለጋራ ሐገር ወቃሽና ተወቃሽ ወይም ጠርጣሪ እና ተጠርጣሪ ወይም ተቆርቁዋሪና ግዴለሽ እያልን ከመፈራረጅ እና ከመናቆር በሚታይ ሥራ እንመዛዘን???

 4. አልተግባብቶም ወዳጀ። የፅሁፉ ሃሳብ ” ኋላ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” የሚል ሃሳብ አለው እንጂ አንተ እንደምትፖተልከው ሰላምና ዕርቅን አጣጥሎ የቀረበ ክትብ አይደለም ፅሁፉ። አንተ ላይ ላዮን ስትከካ ልምድ ያላቸው ሰወች ደግሞ ” ሞኝነት በዛ” እያሉ ነው።

  ጥንቃቄ ካለ ደግሞ ድርድሩ ወደ ሰላም በር ያደርሳል ነገር “የነ ተሎ ተሎ ቤት ግድግዳው ሰምበሌጥ” እንዲሉ ፣ በቃ ሰላም መጣ ብቻ በሚል እሳቤ መኬድ የለበትም ነው እየተባለ ያለው። አንት ፍላጎትህን ነው የምትደረድረው ፣ ፀሃፉው ደግሞ ” እንደ ዕርግብ የዋህ ፣ እንደ እባብ ብልጥ ሁን” እያለህ ነው። መሪነት ውሳኔ መስጠት ፣ በቆራጥነት ፣ በብልሃትና በጥበብ ማሻገር ነው።
  እግዚአብሔር ይጨመርበትና ሁሉን በሰዓቱ እናየዋልን።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share