October 24, 2022
9 mins read

“ምነው ባልተወለድን እያልን በሞተ ሰው እየቀናን ኖረናል” የራያ አላማጣ ነዋሪዎች

311278404 422940713362723 2315275887077441253 n

311278404 422940713362723 2315275887077441253 nአሸባሪውና ወራሪው የህወሃት ቡድን በጥምር ጦሩ ተቀጥቅጦ ራያ አላማጣን ለቆ ከወጣ በኋላ የራያ አላማጣ ነዋሪዎች በአላማጣ ከተማ ከሰሜን ወሎ ዞን አመራሮችና ከፀጥታ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

አሸባሪውና ወራሪው የህወሃት ሀይል ካለፉት 27 የጭቆና ዓመታት በበለጠ በዚህ አንድ አመት ከአራት ወር ውስጥ ከአዕምሮ በላይ የሆነ ግፍና በደል ሲፈፅምባቸው እንደነበር ነዋሪዎቹ በውይይቱ ላይ አንስተዋል።

የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስና አማራን ለማንበርከክ በማለም ለሁለተኛ ጊዜ ወረራ ከፈፀመበት ሰኔ/2013 ዓ.ም ጀምሮ ከወትሮው በተለዬ አረመኔነት በተላበሰ ድርጊት በራያ አላማጣ ህዝብ ላይ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃትና በደል ሲፈፅም መቆየቱን ገልፀዋል።

እኛ የምንፈልገው መሬቱን እንጂ ህዝቡን አይደለም፤ ስለዚህ አካባቢውን ለቃችሁ ሂዱ፤ ካልሄዳችሁ ግን እንገድላችኋለን እያሉ ከማንገራገር ባለፈ ፀያፍ ስድብ ይሳደባሉ፣ ወጣቶችን በማንነታቸው ብቻ እያፈኑ ያስሯቸዋል፣ አስረው ይደበድቧቸዋል፣ መማሪያ ትሆናላችሁ እያሉ በጭካኔ ገድለው ይጥሏቸዋል ሲሉ ነዋሪዎች ጨምረው ተናግረዋል።

በተለይም ባለፉት አስራ አምስት ወራቶች “ምነው ባልተወለድን እያልን በሞተ ሰው እየቀናን ኖረናል” ሲሉ የተናገሩት ነዋሪዎቹ መንግስት ትግራይን ለቆ ከወጣ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ራያና አካባቢውን በወረራ ገብተው በመቆጣጠር ከመንግስት ጋር ሆናችሁ ተዋግታችሁናል በሚል ብዙዎችን እያፈሱ ድብደባ በመፈፀም በእስር ቤት ሲያማቅቋቸው እንደነበር ተናግረዋል።

ብዙዎች ከ20 እና 30 ዓመት በላይ በእስር እንዲቀጡ ተፈርዶባቸው ታስረው ሲሰቃዩ እንደከረሙ ተጎጅዎች የተናገሩ ሲሆን በሌሉበት ከ40 ዓመት በላይ የተፈረደባቸው እንደነበሩና እነርሱ እንዲመጡ በሚል ቤተሰቦቻቸውን አስረው ያሰቃዩዋቸው እንደነበርም ተናግረዋል።

ቄሶችና ሼኮች ጭምር በትግርኛ ብቻ ማስተማር አለባችሁ በሚል ታስረው ሲሰቃዩ እንደነበር ያነሱት የሀይማኖት አባቶች ከብዙ የሰቆቃ ጊዜ በኋላ በመከላከያ ሰራዊቱ የሚመራው ጥምር ጦር አላማጣ ከተማን ሲቆጣጠር ከእስር እንዳስፈታቸውም ገልፀዋል።

ፈጣሪ በአምሳሉና በክብር የፈጠረው የሰውልጅ ቀርቶ ሰይጣን ይፈፅመዋል ተብሎ የማይገመት ግፍና በደል እንደተፈፀመባቸው ያነሱት የሀይማኖት አባቶች በአሸባሪው ህወሃት የክፋት በትር ምክንያት እንኳንስ የሰው ልጅ በሰማይ የሚበሩ እና ዛፍ ላይ የተጠለሉ ወፎች ጭምር ሰላም አጥተው እንደነበር ነው የሽብር ቡድኑን አረመኔነት የገለፁት።

የአሸባሪው ቡድን አረመኔነት ከሰውኛ ባህሪ ፈፅሞ የወጣ እንደሆነ በምሬት ያነሱት የውይይቱ ተሳታፊዎች በማንነታቸው ብቻ አስረው ከሚያሰቃዩዋቸውና በግፍ ከገደሏቸው በተጨማሪ ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት ጀምሮ ያሉ ህፃናትን እና ወጣቶችን አድነው በመያዝ ወደ ውጊያ ወስደው የጥይት ማብረጃ አድርገዋቸዋል ብለዋል። በጥምር ጦሩ ተሸንፈው ራያ አላማጣን ለቀው ቢሄዱም ልጆቻችንን አስገድደው ወስደዋቸዋል ነው ያሉት።

ሰው ማንነቱን መርጦ አይወለድም ያሉት ተሳታፊዎቹ አሸባሪው እና ወራሪው የህወሃት ቡድን አማራነትን ወንጀል አድርጎ ነው የሚቆጥረው፤ በአማራነታችን ብቻ በምድር ላይ ያልተፈፀመ ግፍ ተፈፅሞብናል ሲሉ ጨምረው ገልፀዋል።

አያይዘውም “ማጣት በራሱ ወንጀል ሆኖብን ነው የባጀነው” ያሉ ሲሆን አረመኔው ቡድን አማራዎችን እየለዬ ከማሳደድ፣ ከማሰርና ከመግደል በተጨማሪ ለታጣቂ ሀይሉ የሚሆን የእርድ በሬ፣ ፍየልና ዱቄት እንዲሁም የበሰለ ምግብ አምጡ እያሉ ያሰቃዩናል፤ ቤታችን ውስጥ ያለውን ሁሉ አሟጠው ከወሰዱ በኋላ ደግመው አምጡ ይሉናል፣ የለንም ብለን የእንጀራ ሞሰብ ጭምር ከፍተን እናሳያቸዋለን፣ ከሌለን ደግሞ ወስደው ያስሩናል ሲሉ አንስተዋል።

ከብዙ ሲቃይና መከራ በኋላ የባርነት ቀንበር ተሰብሯል፤ በጥምር ጦሩ የጀግንነት ተጋድሎ ነፃ ወጥተናል፤ እርስ በርስ ለመተያዬትና ለመገናኘትም በቅተናል፤ ክብር ምስጋና ለጥምር ጦሩ ይሁን ሲሉም የነፃነት አየር እንዲያገኙ ላደረጋቸው ሰራዊታችን ምስጋና አቅርበዋል።

ወደፊትም አሸባሪው ቡድን ተቀብሮ ኢትዮጵያ ከአሸባሪ ነፃ እስከምትሆን ድረስ በእልህና በቁጭት ለሰራዊቱ ደጀን ሆነው እንደሚታገሉ አረጋግጠዋል።

አካባቢያቸው ነፃ ከወጣም በኋላ ከመንግስትና ከፀጥታ ሀይሎች ጋር ሆነው አካባቢያቸውን ከሰርጎ ገብ እየጠበቁ፣ የቤት ለቤት ፍተሻ እያደረጉ፣ ተደራጅተው ሮንድ እየጠበቁ እንደሆነ እና የመንግስትና የግለሰብ ንብረቶችን እየጠበቁ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

የሽብር ቡድኑ ሀብትና ንብረታቸውን እየዘረፈ ለታጣቂዎቹ ግብዓት ሲያደርግ በመቆየቱ ምክንያት ብዙ ህዝብ በችግር ላይ የሚገኝ በመሆኑ መንግስት አስቸኳይ የሰብዓዊ ርዳታ እንዲያደርግ ጥሪ ያስተላለፉ ሲሆን ውሃ፣ መብራት፣ የጤና ተቋማት፣ ባንክና ቴሌ የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉና ሥራ እንዲጀምሩም ጥያቄ አቅርበዋል።

ውይይቱን አቶ ጋሻው አስማሜ የሰሜን ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ፣ አቶ መለሰ ተሻለ የሰሜን ወሎ ዞን ከተሞችና መሰረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ፣ ኮሎኔል ኃ/ማሪያም አምባዬ የሰሜን ወሎ ዞን ሰላምና ደህንነት መምሪያ ኃላፊ እና አቶ ካሣ ረዳ የአላማጣ ከተማ ከንቲባ በጋራ መርተውታል።

ኃላፊዎቹ የመንግስት መዋቅሮች ፈጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው አስፈላጊው የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚደረግ እና ሁሉም መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢ ፕ ድ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

big stomach
Previous Story

ሆድ ስንቱን አስከዳህ! – በላይነህ አባተ

German Amhara Association
Next Story

የአማራ እጣ ፈንታ በራሱ ወኪሎች እንጂ በሌሎች አይወሰንም!! – የአማራ ኅብረት በሙኒክ (ጀርመን)

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop