ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያዉያን ትሆን ዘንድ የመልካም ምኞት መግለጫ የምንሰጣጠዉ መቸ ይሆን ፤ ከማን ……..? ለምን እና እስከመቸ ይሆን በየዓመቱ ፲፫ኛዋን ወር በሚቀደድ እና በሽድድ ስያሜ የምን…የምን…ቀን ከምንል አገር ሰርተዉ አገር ሆነዉ ባኖሩን ቀደምት ቅድመ አያቶቻችን በከተማዋ አዲስ አበባ እና እንዲሁም ፲፫ኛዋን ወር የሚገልፅ ዕዉነተኛ እና ዘላቂ መታሰቢያ እንዲኖር ለማድረግ የምንተጋዉ ፡፡
በጋራ እና ምድር ላይ በሚገኝ ዕዉነተኛ ታሪካችን ላይ ሳንስማማ እንዴት በደራሽ እና ፈራሽ በሆነ ሀሰተኛ ፤መናኛ ጉዳይ ላይ ተስማምተን ልንዘልቅ ይቻላል ፡፡
ኢትዮጵያ ጠላቶቿ ጠላት ፤ ወዳጇ ወዳጂ ለማለት ኢትዮጵያ ፤ ኢትዮጵያ ማለት ሳይሆን ሰይጣንም ከወጥመድ ለማምለጥ በስመዓብ እንደሚል ሁሉ አስመሳዮች ድብቅ የኢትዮጵያ ጠላቶች ከመሆን እንደማይለዩ ዕዉነት ከሀሰት ፤ ምርት ከግርድ የሚለይበት ይሆን ዘንድ እንዲለይ መጪዉ ዓዉደ ዓመት በብሩህ ተስፋ ይጠበቃል ፡፡
የቀደሙት ኢትዮጵያዉያን መሪዎች በኢትዮጵያ አንድነት እና በህዝቦች ህልዉና መናጋት ስጋት የሚባሉትን አደብ በማስገዛት በፍፁም ህዝባዊ እና ብሄራዊ ስሜት እና ኩራት አገልግለዋል ፡፡
ዛሬ ላይ ፀረ -ህዝብ እና ፀረ-አንድነት የጥፋት ኃይሎች እንደ ሙጃ እየተስፋፉ እንደ ብሄራዊ ጀግና ሲታቀፉ እና ሲደገፉ የኢትዮጵያ እና ህዝቧ ባለዉለታዎች እና የቁርጥ ቀን ልጆች መቋሚያ ፤መቀመጫ የሚያሳጣ አካሄድ እይቶ እንዳላዩ ለሚያልፉትም ሆነ ይህን ፀረ-ኢትዮጵያዊነት ለሚያቀነቅኑ ለራሳቸዉም ሆነ ለሚመስሏቸዉ የደም ዉርስ እያቆዩ መሆኑን ከትናንት ዕድለቢሶች መማር አልቻሉም፡፡
በኢትዮጵያ ለኢትዮጵያዉያን ሁሉ የሚበጀዉ ዕዉነተኛ መግባባት እና መተማመን እንጂ ብይድ ታሪክ መነሻ ሁነኛ መሰረት ስለማይኖረዉ ሳይፀና ፈራሽ ነዉ፡፡
በዕዉነተኛ ታሪክ ላይ የሚደረግ ክህደት እና ማምታት የዕምቧይ ካብ መሆኑን ካለፉት የታሪክ ስብራቶች ተምረን መጪዉ ዘመን የቆየዉን እና ነባሩን ታሪካችንን በማደስ እና ማጎልበት የምንችልበት ይሆን ዘንድ የሁላችን መልካም ምኞታችን ነዉ ፡፡
መጪዉ አዲስዘመንኢትዮጵያ ኖሩላት እና የሞቱላት የሚከበሩባት፤ የኖሩባት እና የገደሏት የእጃቸዉን(ምሳቸዉን ) የሚያገኙበት ይሁን፡፡
በምንቀበለዉ አዲስ ዓመት ዘመነ ሉቃስ ኢትዮጵያ አገራችን ለታመሙት ፤ ምህረት ፤ ለወጡት መግባት ፤ ለተጣሉት ዕርቅ ፤ ለታሰሩት ምህረት፣ ለሞቱላት ገነት፤ ለገደሏት መርገምት …ትሆን ዘንድ እንመኛለን ፡፡
“ዘመነ ሉቃስየነፃነት እና ዕድገት ይሁንልን፡፡”
መጪዉ አዲስ ዘመን የጤንነት፣ ደህንነት፣ ነፃነት እና ዕድገት ይሁንልን