የኢትዮጵያ የፖለቲካ ለሂቃን በኔሽን ቢዩልዲንግ ዘዴ ላይ ሁለት የተለያዩ ትምህርቶችን የሚከተሉ ሲሆን የእነዚህ ትምህርቶች ግጭት የለሂቁን ክፍፍል እያሰፋ የረጋ ሃገረ መንግስት እንዳንመሰርት አድርጎናል። ዛሬ በዚህች በጣም ቁጥብና ምጥን ጦማር ስር የእነዚህን ግጭቶች መንስዔና ከግጭቶቹ መሃል የመውጫውን ዘዴ እንጠቁማለን።
ታዲያ ለመሆኑ እነዚህ ሁለት የተራራቁ የአስተምህሮ ቅራኔዎች ምን ምን ናቸው? ብለን ከጠየቅን፤ አንደኛው አስተምህሮ የፕራይሞርዳያሊዝም አስተምህሮ ሲሆን ሌላው ደግሞ የኮንስትራክቲቪዝም አስተምህሮ ነው። የፖለቲካ ለሂቃን ይህንን አርቲክል ሲያነቡ ወደ አንዱ የሚያዘነብሉ እንደሆነ ራሳቸውን ቀድመው ቢያዩ ለውይይት ይረዳናል። Am I primordialist or constructivist? ብለው ራስዎን እንዲጠይቁ እጋብዛለሁ።
ርግጥ ነው በብሄር ወይም በዘር ትምህርት ውስጥ ሶስት አይነት ንደፈ ሃሳቦች አሉ። አንደኛው አስተምህሮ ከፍ ሲል ያነሳነው ፕራይሞርዳያሊዝም የተባለው ንድፈ ሃሳብ ሲሆን ሁለተኛው ኮንስትራክቲቪዝም ሶስተኛው ኢንስትሩመንታሊዝም ይባላሉ።
ፕራይሞርዳያሊዝም የተባለውን አስተምህሮ የሚከተሉ ምሁራን ብሄር የማይነካ፣ ተፈጥሮአዊ ስብስብ ነው ይላሉ። አንዳንዴም የደም ትስስር አለው ይላሉ። ይህ ብሄር የተባለው የሰው ልጆች ጠገግ ጥንታዊ ስብስብ ሲሆን ይህንን ስብስብ ለማፍረስ መሞከር ኢሰባዊነት ነው፣ እንዴውም ይህ ስብስብ የራሱ መሬት ሊኖረው ይገባል፣ የራሱ አስተዳደርራዊ ክልል ሊኖረው ይገባል፣ የራሱን እድል በራሱ ሊወስን ይገባል ይላሉ። ብሄር ጥንታዊ ስለሆነ ሁል ጊዜም የራሱ መሬትና ግዛት አለው ይላሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት አርባ አመታት ገደማ የዚህ ትምህርት ተከታይ የሆኑቱ በዚህ ትምህርት አምሳል የተቀረጸ ህገ መንግስት ጽፈው ብሄሮችን በፖለቲካ ፓርቲነት አደራጅተው ይኖራሉ።
ከላይ የጠቀስነው ኢንስትሩመንታሊዝም የተባለው አስተምህሮ በራሱ የዘር ንድፈ ሃሳብ ሳይሆን በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የፕራይሞርዳያሊዝምን ትምህርት ተቀብሎ ነገር ግን ብሄር ማታገያ ነው የሚል እምነት ያለው ፍልስፍና ነው።
እነዚህ የፕራይሞርዳያሊዝምን ትምህርት የሚከተሉ የኢትዮጵያ ለሂቃን ይህንን ትምህርት ይዘው ወደ ፖለቲካ ሜዳ ሲገቡ ኢንስትሩመንታሊስት ይሆናሉ ማለት ነው። ብሄር ማታገያ ሲሆን ደግሞ የራሱን ቀለም እየለቀቀ እየለቀቀ እየለቀቀ እንደሚሄድ፣ ብሎም የብሄሩ ባህልና ልማዶች ሁሉ የፖለቲካ መሳሪያ ሲሆኑ እየተጎዱ እንደሚሄዱ በተግባር ቢረጋገጥም ኢንስትሩመንታሊስቶች ግድ የላቸውም። አንዱ የኢትዮጵያ ለሂቃን ጎራ ይህን እያደረገ ይኖራል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሃገረ መንግስትን ለመገንባት የተሻለ አስተምህሮ አለን ብለው የሚሉ ሌሎች ለሂቃን ደግሞ የኮንስትራክቲቪዝም ደቀመዛሙርት ናቸው። እነዚህ ለሂቃን ብሄር ስሪት ነው፣ ብሄር የሚባለው ጠገግ እግዚአብሄር የፈጠረው አይደለም። ቋንቋም ይሁን ወግ ልማድ ሰው የፈጠረው ስለሆነ ይህ የብሄር ጠገግ ያን ያህል ግዝፈትና ትኩረት አይሻም ይላሉ። እነዚህ ወገኖች የሚያምኑት ብሄራችን ዋናውን የጋራ ቤታችንን ወይም ኢትዮጵያዊነትን የሚገዳደር መሆን የለበትም እያሉ ይሟገታሉ። ብሄር ተፈጥሮአዊ ስላልሆነ አንድ እናትና አባቱ ኦሮሞ ተናጋሪ የሆኑ ሰው በአጋጣሚ ሲዳማ ተወልዶ ቢያድግ ይህ ሰው የሲዳማ ብሄር አባል ይሆናል የሚል ትንታኔ አላቸው። ቋንቋና ባህል የሰው ልጅ ውጫዊ ልምምዶች ስለሆኑ ማንም ሰው ለሆነ ቋንቋና ባህል ተጋላጭ ከሆነ ከዚያ ብሄር አባልነት ምንም ሊከለክለው የሚገባ ነገር የለም ብለው ይሞግታሉ። ስለዚህም ብሄር የራሱ መሬት ያለው፣ የራሱ አስተዳደር ያለው፣ ክልል ያለው የሚለው ትምህርት ሃገራዊ ህብረት ለመመስረት አስቸጋሪ ነው ይላሉ። ስለዚህ ፖሊሲዎች፣ አስተዳደሮችና ደንቦች ሁሉ ብሄር ማህበራዊ ስሪት ነው የሚለውን ትምህርት ከፍ አድርጎ የተቀበለ ሆኖ እንዲቀረጽ ይሻሉ። እነዚህ ለሂቃን ደጋፊዎቻቸውን ሁሉ “መጀመሪያ ሰው ነኝ” በሉ ከዚያ ነው ብሄር የሚመጣው እያሉ ይሰብካሉ። በተቻለ መጠን የብሄር ማንነትን እያኮሰሱ ግለሰብን በማጉላት የጋራ ማንነት ለመገንባት ይሞክራሉ። ስለሆነም የነዚህ ለሂቃን ተከታዮች እኔ ሰው ነኝ፣ መጀመሪያ ሰው ነኝ…….. እያሉ ከፕራይሞርዳያሊስቶች ጋር ሙግትና ብሽሽቅ ይዘው ይታያሉ።
ፕራይሞርዳያሊስቶች በበኩላቸው ሰባዊ መብት የሰውን ማንነት ማክበር አለበት፣ የሰው ልጅ ከቋንቋው ውጪ፣ ከባህሉና ከሃይማኖቱ ውጭ ከቶውንም ህልው የለውም የሚል ክርክር እያቀረቡ ኮንስትራክቲቪስቶችን ያበሽቃሉ። ኮንስትራክቲቪስቶች በበኩላቸው ባህላዊ ማንነቶች በሙሉ በትምህርት የሚገኙ ስለሆነና ብሄር የተፈጠረ፣ በመፈጠር ላይ ያለና ወደፊትም ሊፈጠር የሚችል በመሆኑ ፖለቲካችን ከፕራይሞርዳያሊዝም ወጥቶ በኮንስትራክቲዚዝም እሳቤ ላይ ሊቀረጽ ይገባል እያሉ የመልስ ምት ይልካሉ። በዚያም በዚህም ያለው ግትርነት አክራሪነት እያደገ እንዲሄድ የሚያደርግ ሁኔታ ፈጠረ።
እነዚህ ኮንስትራክቲቪስቶች ሊፈርስ የማይገባው ጠገግ ሃገራዊ ህብረት ነው፣ ብሄር ኮንስትራክትድ ስለሆነ በለውጥ ሂደት ውስጥ ነው። ሃገራዊ ህብረት ግን በዜጎች ፈቃድ ላይ ተመስርቶ ዘላለማዊ ሆኖ መዋቀር አለበት ይላሉ። ከዚህ ከኮንስትራክቲቪዝም ትምህርት አራማጆች መካከል በጣም አጥባቂዎቹ ደግሞ እንዴውም ብሄርን እያፈረስንም ቢሆን ሃገራዊ ማንነትን መገንባት የጥበብ መጀመሪያ ነው ይላሉ። እንግዲህ እነዚህ ኮንስትራክቲቪስቶች ማእከላዊ የፖለቲካውን ሜዳ ከያዘው ፕራይሞርዳያሊስቱ ለሂቅ ጋር የሚጋጩት የነሱን ትምህርት ለመምታት ብሄር ስሪት ነው በሚል መፈክር ስር የሚታገሉ መሆኑን ስናይ ሁለቱም ለሂቃን ብሄርን ለራሳቸው የፖለቲካ አላማ መሳሪያ ማድረጋቸውን በግልጽ እናያለን። ሁለቱም ጎራዎች ኢንስትሩመንታሊስት በሆኑበት ሃገር ደግሞ ብሄራዊ መግባባት አደጋው ይበዛል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ይህ የአስተምህሮ ግጭት አንዳንዱ ሰው ገብቶት ሌላው በደመ ነፍሱ የሚከውነው ሲሆን ለሂቁ ከነዚህ ትምህርቶች በአንዱ ጎራ ይሰለፍና ትግል ላይ መሆኑን ሲገልጽ እናያለን። ፕራይሞርዳያሊስቱ የራሱን የብሄር ትምህርት ይዞ ብሄር የራሱ መሬት ያለው የማይነካ ጠገግ ነው ብሎ ሲከራከር ኮንስትራክቲቪስቱ ሃገራዊ ማንነት ይበልጣል፣ ብሄር ሰው ሰራሽ ነው ብሎ ይሞግታል። በዚህ መሃል ሁለቱም ሃይሎች ብሄርን መሳሪያ አድርገው ነው ለሃገረ መንግስት ግንባታ የሚሟገቱትና ከፍ ሲል እንዳልነው ሁለቱም ወገኖች አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ኢንስትሩመንታሊስት ሆነዋል። ፕራይሞርዳያሊስቶች እምነታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ብሄርን ማታገያ እንደሚያደርጉት ሁሉ ኮንስትራክቲቪስቶች ደግሞ ብሄር ማታገያ ሊሆን አይችልም ይልቁን ዋናውን ቤት ለመገንባት ቢፈርስም ችግር የለውም አይነት ሃሳብ ስለሚያቀርቡ እነዚህ ሃይሎችም ሃገረ መንግስት ለመገንባት ብሄርን ፈርሽ አድርገው ወይ በብሄሮች ፍርስራሽ ላይ ብሄራዊ ማንነት ለመገንባት ስለሚፈልጉ ያው ኢንስትሩመንታሊስት ሆነው ተገኝተዋል። ዞሮ ዞሮ የከፋው ነገር ፕራይሞርዳያሊስቱም ሆነ ኮንስትራክቲቪስቱ ብሄርን ለገዛ አላማው መሳሪያ ስላደረገው የሃገራችን የሃገረ መንግስት ግንባታ በግጭቶች መሃል እንዲቆይ አደረገው። ከሁለቱም ጎራዎች ብሄርን በተለያየ ዘዴ ማታገያ ሲያደርጉት ከመቼውም ጊዜ በላይ የሃገራችን የቡድን መብት
ጥያቄ አደጋዎች በዙበት፣ ሃገራዊ ማንነታችንም በግጭቶች መሃል ስላለ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቀጥኖ ይታያል።
ታዲያ የለሂቁ ክፍፍል እንዴት ይቀንሳል?
የሃገራችን ፖለቲካ ከነዚህ ከሁለት አስተምህሮዎች በእውነት መራቅ አለበት። ብሄርን ማታገያ ማድረግ የረጋ ሃገረ መንግስት እንዳንመሰርት ያደርጋል። እነዚህ ከፍ ሲል የሚነሱ የብሄር ንድፈ ሃሳቦች በአካዳሚው ዘንድ መከራከሪያ ሆነው ይቀጥሉ። ነገር ግን ፖለቲካችን በነዚህ ላይ በሃይል መመርኮዝ የለበትም። መራቅ አለበት ። ኮንስትራክቲቪስቱ ብሄር የሚሰራ ስሪት ነው የሚል የፖለቲካ አቋም ይዞ ሲነሳ የለም በእኛ ብሄር ህይወት ውስጥ የመለኮት ፈቃድ አለበት ከሚሉ ቡድኖች ጋር ይጋጫል። የለም እኛ ጥንታዊ ነን ብሄራችን ሰው ሰራሽ አይደለም ያንተ ትምህርት አቃለለን ከሚሉት ጋር ይጋጫል። ኮንስትራክቲቪስቱ ፖለቲከኛ ደጋፊውን መጀመሪያ ሰው ነኝ በል፣ ከዚያም ስለብሄርህ አውራ ሲለው አንዳንዱ ሰው የለም ሰውነቴ ከቋንቋየ ጋርና ከባህሌ ጋር የተዋሃደ ነው ብሎ ይከራከራል፣ ስለሆነም ይህ ግጭት ለብሄሮች ህልውና የስጋት ምንጭ ይሆናል። ከማንነቶች በላይ ብሄራዊ ማንነት ይቀድማል ብሎ ሲከራከር በሃይማኖቴና በብሄሬ እንዲሁም በብሄራዊ ማንነቴ መካከል ግጭት አታምጡ አታሽቀዳድሙብኝ ከሚለው ዜጋ ጋር ይጋጫል። በሌላ በኩል ፕራይሞርዳያሊስቱ ብሄር ማንም ያልፈጠረው የጥንት ነው ሲል በብሄሩ ውስጥ ባሉ ዜጎች መካከል ደምና አጥንት ቆጠራ ሂሳብ ውስጥ ያስገባና በጠገጉ ስር በሰፈሩ ዜጎች መሃል ትርምስ ያመጣል። ይህ ለሂቅ ከኮንስትራክቲቪስቶች ጋር ግጭትና እልህ ውስጥ ስለሚገባ ሃገረ መንግስቱን ያናጋል። ስለሆነም ሁለቱም ትህምርቶች አደጋ አላቸው።
የሚሻለው ብሄር ራሱን እንደፈለገ ይመልከት ። የራሱን ትርክቶች ይጠብቅ። ነገር ግን ፖለቲከኛው አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበር ለመፍጠር መስራትና ብሄሮችን ማክበር ከሁሉም በላይ ማታገያ መሳሪያ ሳያደርጋቸው በራሳቸው ምህዋር ላይ እንዲዞሩ ማድረግ ተገቢ ነው። ብሔሮች ሁሉ በአንድ በኩል ከፖለቲካ ውጭ የሆነ የባህል አስተዳደር መስርተው የሚኖሩበትንና በሌላ በኩል የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉዳያቸውን የሚያካሂዱበትን የጋራ ስርዐት በመዘርጋት በጣምራ ፌደራሊዝም ሃገሪቱን ማስተዳደር የረጋ ሃገረ መንግስት ለመመስረትና ግጭት ለመቀነስ ይረዳል።
ከሁሉ በፊት ሃገሪቱ የግልንም የቡድንንም መብቶች እያከበረች የምትኖርባቸውን ሁለት የቃል ኪዳን ሰነዶች ማዘጋጀት የረጋ ሃገረ መንግስት ለመመስረት ይረዳል። የመጀመሪያው የሃገር
ቃል ኪዳን ሰነድ የጋራ እሴቶቻችንን በጽሁፍ የሚገልጽ ሰነድ ነው። ኢትዮጵያውያን የጋራ እሴቶች አሉን እንላለን። ነገር ግን እነዚህ እሴቶች ህቡእ ኪዳን (hidden covenant) ናቸው። በግልጽ ተጽፈው ስለሌሉ አስር ጊዜ የጋራ እሴት እያልን ብናወራም በግልጽ ጥርት አድርገን አናውቃቸውም። ስለዚህ እነዚህን ረቂቅ መተሳሰሪያ መርሆዎች ወይም የጋር እሴቶች አንድ ራሱን የቻለ ዶክመንት ሊኖራቸው ይገባል። ይህ ዶክመንት በሃገሪቱ ውስጥ ዘላለማዊ ሃገራዊ ሰነድ ተብሎ ለትውልድ የሚተላለፍ ይሆናል። ይህን ጉዳይ በተመለከተ ጣምራ ፌደራሊዝም በሚለው መጽሃፌ ላይ ተግልጾ ይገኛልና እንድታነቡት እጋብዛለ
እንደሚታወቀው ህገ መንግስት የሃገራት ከፍተኛ የቃል ኪዳን ሰነድ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ሰነድ ውሱን ከሆኑት ባህርያቶቹ መካከል ረቂቅ የሆኑ የህብረተሰብ መተሳሰሪያ መርሆዎችን ወይም እሴቶችን ይገድፋቸዋል። ለምሳሌ መረዳዳት፣ መተማመን፣ ፍቅር፣ ትጋት፣ ጀግንነት፣ መከባበር፣ ቃለ መሃላ……..። በህገ መንግስት ውስጥ ይገደፋሉ። እነዚህ ጉዳዮች ግን ከብዙ
የህገ መንግስት ህጎች በላይ ለህብረታችን መጽናት ጠቃሚ እሴቶች ናቸው። ስለሆነም እነዚህን ረቂቅ ጉዳዮች አንጥሮና አርቲኩሌት አድርጎ አውጥቶ የኢትዮጵያን እሴቶች በጽሁፍ በመቅረጽ የሃገሪቱ አንድ ብሄራዊ ከፍተኛ ዶክመንት ማድረግ ለህብረታችን ጥንካሬ ለኔሽን ቢዩልዲንግ ስራችን እንደ መልህቅ ሆኖ በዘመናት መካከል ይረዳል። ከዚህ ቀጥሎ የተለመደው ዶክመንት ህገ መንግስት ሲሆን ይህንን ዶክመንት የቡድንንም የግለሰብንም መብት እንዲያከብር አድርገን መቅረጽ ተገቢ ነው። በዚህ መሃል ቡድኖች የራሳቸውን ትርክቶች ይዘው ደግሞ ለሃገር የሚሆኑ መስዋእቶችን ከፍለው በነጻነት ይኑሩ። ኮንስትራክቲቪስቱ እየተነሳ ፈራሽ ነህ አይበላቸው። ፕራይሞር ዳያሊስቱ ተነስቶ የፖለቲካ ልብስ አልብሶ ማታገያ አያድርጋቸው። በአጠቃላይ ለሂቁ በነዚህ ሁለት ትምህርቶች ላይ ተመርኮዞ ጎራ ለይቶ የሚያደርገውን ፍትጊያ ያቁምና አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበር ለመፍጠር እንስራ በፌደራል ስርዐታችን ውቅር ላይ ለብሄር ፖለቲካዊ ያልሆነ ክፍል እንስጠው። የዚህን ሃሳብ ዝርዝር በመጽሃፌ ላይ ገልጫለሁ። በሌላ በኩል ከፍ ሲል እንዳልነው የጋራ እሴቶቻችንን እንጻፍና ኢትዮጵያን ዘላለማዊ ኪዳን እንሸልማት።
ስለሆነም በእነዚያ የብሄር ትምህርቶች ላይ የፖለቲካ ቤቶችን ሰርተን መናቆር እንተውና የረጋ ሃገረ መንግስት እንመስርት። ለሂቁ የክፍፍሉ ምንጭ እነዚህን ትምህርቶች ተግባራዊ ለማድረግ በሚደረግ ሽኩቻ መሃል የተፈጠረ ቅራኔ መሆኑን አውቆ ከነዚህ ትምህርቶች ወጥቶ የጸዳ ፖለቲካ ይስራ።
መጽናናት ለኢትዮጵያ ይሁን
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ
ገለታው ዘለቀ