እሺ የጉራጌ ዞን ክልል ሆነ እንበል:: ከዛስ? – ብርሃኑ ዘርጋው

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ስብሰባ

ወድቆ ተጋጭቶና ተላልጦ ሰላማዊ ሰልፍ አድርጎ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር የጉራጌ ክፍለ ሐገር እንዲመሰረት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት በጎ ፈቃድ አገኘ እንበል:: ፈንጠዝያው በጉንችርየና በጉብርየ ከአገና እስከ እምድብር ከወልቂጤ እስከ ቡወዠባር እነሞርና ሙህር እዣ በሙሉ ጉመርና ቸሃ ሳይቀር መስቃንና ማረቆንም ጨምሮ ታላቁን የሶዶና የዶቢንም ህዝብ አስነስቶ በመላው የጉራጌ ዞን ርችት በርችት ሲሆን ብናይ አይፈረድብንም:: ብዙ ቆስለናል ተወግተናል ተዘርፈናል ሞተናል እንደ ጠላት ኢላማ ተደርገናል:: ይህን በትንሹ ለማካካስ ፈንጠዝያው ቢያንስ እንጂ የሚበዛ መቀናጣት አይሆንም:: እሰየሁ ለመጀመሪያው ሳምንት::

ከሁለትና ከሦስት ሳምንታት በሁላ ቁጭ ብለን ሰከን ብለን ማሰብ ስንጀምር ታድያ ይህን በእጄ ያለውን ክልል ምን ላድርገው ብለን መጠየቃችን ይቀራል?
ለዚህ ነው ከአሁኑ ምን አይነት ዴሞክራሲያዊ መንግስት ያስፈልገናል? ምን አይነት ህገ መንግስት ያስፈልገናል? ምን አይነት የትምህርት የጤና የማህበራዊ አገልግሎት የቴክኖሎጂ የከፍተኛ ትምህርት የአውራ ጎዳና ያየር ማመላለሻ የባቡር መንገድ የጸጥታና ደህንነት ኃይል የፍርድ ቤቶች የህግና የአስተዳደር ፖሊሲ ያስፈልገናል የሚለው ጥያቄ እስካሁን ካልተነሳ አሁኑኑ መነሳት የሚገባው::
አለበለዚያ ጊዜ በሰጠው ኃይል ተነጥቆ የጉራጌ ህዝብ እከክ እያከከ ያዲሱ ጉራጌ አስተዳዳሪዎች ከደቡብ ክልልና ከዞኑ የተሸጋገሩ የበለጠ የሚቆራረስ ዳቦ ወደሚገኝበትና ማገልገል ወደለመዱበት የብልጽግና ጎራ ብቅ ማለታቸው አይቀርም:: ውርድ ከራሴ ብያለሁ:: ጆሮ ያለው ይስማ:: ይህ ልማድ ከዚህ በፊት ያየነው ስለሆነ አዲስ አይደለም:: ህገ መንግስቱም በሽ በሽ ነው:: የኦሮሞን የአማራን ወይ የትግሬን ወይም የቤኒ ሻንጉልን ካልሆነም የአፋርና የሶማሌ ወይም የቅርቦቹን የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያና የሲዳማን ወስዶ ስም ለውጦ ያንኑ ያልቦካ ሊጥ መጋገር ይቻላል:: ይህ ግን በጭራሽ የጉራጌን ሕዝብ ማክበር አይደለም::

የጉራጌ ሕዝብ በክፍለ ሐገሩ በፍፁም የአንድ ወይም የሁለት ፓርቲዎች አምባ ገነንነት የሚያራምድ ስርአት ውስጥ መታሰር የለበትም:: ይህ ከሆነ የሕዝቡን ሉአላዊነት መናቅና መሻር ነው:: ሸንጎው ወይም ምክር ቤቱ የአንድ አይነት እይታና ተማክረው እንትን ያሉትን እንትን እንዲያሸቱን ሳይሆን የተለያየ አመለካከት ያላቸው የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት የሕዝብ ተወካዮች ተፋጭተው የሚስማሙባቸውን ብቻ መሆን ይኖርበታል:: ከላይ የወረደውን ከሚያፀድቅ የኢትዮጵያ ምክር ቤት ስህተት ይህን መማር እንችላለን:: አይ አይሆንም ተብሎ ብልፅግና ወይ ሞት የሚባል ከሆነ ሰላም ወዳዱና ጀግናው የጉራጌ ሕዝብ ለሌላ ዙር ትግል መዘጋጀት ይኖርበታል:: ያ እንዳይሆን ግን ካሁኑ ጊዜያዊና የሽግግር መሪዎቹን ሊመርጥና ለሚቀጥለው የታላቁ ጉራጌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ የተወካዮች ምክር ቤት ዝግጅት ሊያደርግ ይገባል::

እኔ ግን ከአንድ እስከ ሁለት አመት የመዘጋጃ ጊዜ ሆኖ በሁለተኛው አመት መጨረሻ የሕዝብ ተወካዮች ምርጫ ቢደረግ የሚል ምልከታ አለኝ:: በዚህ የዝግጅት ወቅት ሰላምና እርቅ ከየቦታው ቅሬታ ያለባቸው ጥርጣሬ ያደረባቸው ከቀቤና ከወለኔ ከመስቃን ከማረቆ ከቡታጅራ ከተለያዩ ቦታዎች በተለያየ ሰበብ አስባቦች ልባቸው ያዘነባቸው ብቻ ሳይሆን ልባቸው ከጉራጌ ህዝብም የሸፈተባቸውን ወገኖቻችንን ሰብስቦ ይቅርታና አዲስ ጉርዳ መገባባት ለነገ ማደር የሌለበት ስራ መሆን ይኖርበታል:: የሽማግሌዎቻችን ዋና ስራም ይህ መሆን አለበት:: ይህም በሰላምና በፍቅር በመግባባትና በመተማመን ፅኑ መሠረት ላይ የተገነባ ክልልን ይሰጠናል:: በተባለው ሁለት አመት ውስጥም ከእርቅና ሰላም ውጭ:-
 1. የአሸጋጋሪ ቴክኒካዊ አካል ማለት የህግና የአስተዳድር በተለያየ ሙያ የተመሰከረላቸው ሰዎች ምርጫ በሁለት ወር ውስጥ ቢጠናቀቅ
2. የአስመራጭ ኮሚቴ ተቋቁሞ በክልሉ ውስጥ መሳተፍ የሚፈልጉ ክልላዊና አገር አቀፍ ኢትዮጵያዊ ፓርቲዎችም እንዲሳተፉ ብቻ ሳይሆን እንዲመሰረቱ ማበረታታት ቢደረግ
3. ህግና ደንብን ለማስከበር ከዘመኑ ህግ አዋቂዎች ጋር በመተባበር የጆካና በሌሎችም የጉራጌ ክልል ውስጥ ያሉ ባህላዊ ደንብ አስፈፃሚ ደንቦችና ሽማግሌዎቻችን የክርስትናና እስልምና አባቶቻችንን እንዲሁም አዛውንት እናቶቻችንን እንዲጨመሩ ቢደረግ
4. የጉራጌን ሕዝብ ጸጥታና ሰላም እንዲያስከብሩ አሁን ባሉት የጸጥታ አካላት ላይ በተጨማሪ አባላት እንዲሆኑ ዘርማዎችን ከመላው ክልል ቢቀጠሩና ሌሎችም ያስፈልጋሉ የሚባሉ ነገሮች ቢካተቱ
5. የተለያዩ ክልላዊም ይሁኑ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመበረታታቸው ያክል የመፃፍ የመናገርና ሃሳብንና ልዩነትን በጋዜጣ በራድዮና በማንኛውም ሶሻል ሚድያ የማንጸባረቅ መብት እንዲኖር ቢደረግ የሚል ሃሳብ አለኝ:: እንግዲህ ይህ ከብዙ ሃሳቦች በጥቂቱ ቢሆንም በሂደት ሌሎች ተጭማሪ ሃሳቦች ከሌሎች እንደሚቀርቡ አልጠራጠርም::
አስቀድመን የቤት ስራችንን ካልሰራን ዳቧችንን እንደምንቀማ እንወቅ:: ጥፋቱም የእኛው ነው የሚሆነው:: መንገዳችን ሩቅ ጉዞአችንም ረጅም ስለሆነ ካሁኑ በጥንቃቄ የሕዝባችንንና የክልላችንን ደህንነት ሊያስጠብቁ የሚችሉ ከኔ በፊት ሕዝብ የሚሉ በፍርደ ገምድልነትና በአድልዎ ያልተወቀሱ መሪዎችን ለይተን እንድናወጣ ይገባናል:: ክልል የምንሆነው የእባብ እንቁላል ለመቀፍቀፍ ከሆነ ጎመን በጤና ማለት አይሻልም ይሆን? እንቁላሉ ተቀፍቅፎ ዶሮ አይሆንም:: የበለጠ እንነደፋለን::
ብርሃኑ ዘርጋው
ተጨማሪ ያንብቡ:  “አንተ የኔ ጀግና ነህ፡፡ ብትሞትም በእውነትህ ኮርተህ ሙት!” ሰርካለም ፋሲል

2 Comments

  1. ብርሀኑ ዘርጋው ብርሀኑ ነጋ ምነው ዝም አለ በዚህ ጉዳይ ጉራጌን የሚፈልገው ለመደበቂያነት ነው?

  2. ወዳጄ ክልል ከሆነ አቶ ርስቱ አጼ ርስቱ ይባላሉ ክልል እንዲሆን የደከሙት ካድሬዎች በደረጃቸው የሚገባቸውን ይመነትፋሉ ሌላ ሌላው ትያትር ነው ህዝቡም ሲያለቅስ ኑሮውን ይገፋል ክልል፡፡ ለህዝብ ሳይሆን ክልል እንዲሆን ለታገሉት ወሮበላዎች ኑሮ ማመቻቻ ነው እንግዲያዉማ ኑሮው በዉህድ ኢትዮጵያ ላይ የተመሰረተው የጉራጌ ህብርተሰብ ትግሉ መሆን የነበረበት ክልል ይፍረስ ብሎ መሆን ነበረበት፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share