በኢዜማ እምነት አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ባለበት እስከቀጠለ ድረስ እንኳን ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን መገንባት ይቅርና እንደ ሀገር የመቀጠል ህልውናችንም ቢሆን አደጋ ላይ የወደቀ ነው!!

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሀገራችን ላይ እውን እንዲሆኑ ከሚታገልላቸው የፖለቲካ መሠረቶች አንዱ እና ዋነኛው የዜጎች እውነተኛ የስልጣን ባለቤትነትንና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ነው!!

ፌደራሊዝም “የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ ሕዝብ ነው” የሚለውን ትልቅ የዴሞክራሲ መርህ ሰፋ ያለ ትርጉም በመስጠት “ሕዝብ በሚኖርበት አከባቢ ራሱን በራሱ ማስተዳደር አለበት” የሚለውን መርህ ተግባራዊ የሚያደርግ የአስተዳደር መዋቅር ነው።

ፓርቲያችን ኢዜማ ኢትዮጵያ ካላት ሰፊ የቆዳ ስፋት፣ ከአንድ ቦታ ሁሉን ማስተዳደር የማይመች መልከአ ምድር፣ በተለያየ ደረጃ ያለ ኢኮኖሚ በየአካባቢው ባለበት፣ ብዝኀ ማንነት ማለትም ብዙ ዘውግ፣ ቋንቋ፣ ባህልና ሃይማኖት አንፃር ያልተማከለ ሥርዓት ያስፈልጋል ብሎ ያምናል። ካልተማከሉ የፖለቲካ ሥርዓቶች ውስጥ ደግሞ የመጀመርያው ምርጫ ፌደራሊዝም ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች ፌደራሊዝም ተመራጭ የሚሆነው በሁለት ዋነኛ ምክንያቶች ነው። አንደኛው ሕዝብ በአካባቢው ራሱን በራሱ ማስተዳደር እንዲችል ሙሉ መብትና ስልጣን የሚሰጥ የመንግሥት ሥርዓት ስለሆነ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ፌደራሊዝም ከአሐዳዊ መንግሥት በተሻለ ብዝኀነትን ማስተናገድ መቻሉ ነው።

ኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት የተከተለችው የፌደራሊዝም ሥርዓት፤ ፌደራል ሥርዓቱን የፈጠረው ሕገመንግሥት ሥራ ላይ ከመዋሉ አስቀድሞ በነበሩ ሂደቶች ብዙኃኑን ያላሣተፈ መሆኑ ዴሞክራሲያዊነቱን አሳጥቶታል። ከዚያ በተጨማሪ የፌደራሊዝም ዋና ጥቅም ለሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በመስጠትና በዘውግና በቋንቋ ልዩነቶች ላይ ተመስርተው የሚነሱ ግጭቶችን ማስወገድ ሆኖ እያለ፤ የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ግን ራሱ የተመሠረተው በዘርና በቋንቋ ልዩነቶች ላይ ስለሆነ ማስወገድ የሚገባውን ችግር ጭራሹኑ አባብሶታል። በተለይ የፌደራል ሥርዓቱ ማንነትንና የመሬት ባለቤትነት በሕገ መንግሥት ደረጃ እንዲያያዝ በማደረጉ ከዚህ ቀደም በመካከላቸው የሚለያያቸው ወሰን ባልነበረ ኩታ ገጠም በሆኑ ወረዳዎች በሚኖሩ የዘውግ ማህበረሰቦች መካከል ደም ያፋሰሱ በርካታ ግጭቶች እንዲካሄዱ ምክንያት ሆኗል። አሁንም መሆኑን ቀጥሏል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አራት ኪሎ ከፍተኛ እሳት ተነሳ | አብይ ባህር ዳር ሊገባ ነው | ዶ/ር ይልቃል እምቢኝ አሉ

በኢዜማ እምነት አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ባለበት እስከቀጠለ ድረስ እንኳን ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን መገንባት ይቅርና እንደ ሀገር የመቀጠል ህልውናችንም ቢሆን አደጋ ላይ የወደቀ ነው ብሎ ያምናል።

ይህንን አደጋ ለማስወገድ የፌደራል ሥርዓቱ እንዴት መመሥረት አለበት? ክልሎች እንዴት መዋቀር አለባቸው? በክልሎችና በፌደራል መንግስቱ መካከል ያለው ግንኙነት ምን መምሰል አለበት? የሚሉና ከፌደራል መንግሥትና ከክልል መንግሥታት ማን የበለጠ ስልጣን ይኑረው? ለሚሉት ጥያቄዎች እና ሌሎች ሀገሪቱን አደጋ ላይ ጥለዋታል የሚባሉ የሕገ መንግሥቱ ክፍሎችን አንድ በአንድ ነቅሶ በማውጣት ከፊታችን ሀገራችን ታደርገዋለች ተብሎ በሚጠበቀው ሀገራዊ ምክክር ላይ ማቅረብ የግዴታ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን።

ኢዜማ ለዚህ ምክክር ጠንካራ አማራጭ ሀሣቦችን ይዞ ለመቅረብ ሀገራዊ ምክክሩ ላይ ብቻ ትኩረትን ሰጥቶ የሚሰራ ኮሚቴ በማዋቀር እየሠራ ሲሆን ዝግጅቱንም አጠናቆ የመድረኩን መጀመር እየተጠባበቀ ይገኛል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የ “ክልል ወይንም ዞን እንሁን” የሚሉ ጥያቄዎች በስፋት እየተደመጡ ነው። ይህንንም ተከትሎ ሁለት ሕዝበ ውሳኔዎች ተደርገው ሕገ መንግሥቱ ሲጸድቅ ከነበሩት ዘጠኝ ክልሎች ሁለት ተጨምረው የክልሎች ቁጥር ወደ 11 ከፍ ብሏል።

አንዳንዶቹ የክልልነት ጥያቄዎች የሚቀርቡት ሕዝብ በወከላቸው እንደራሴዎች ሳይሆን ስልጣን ላይ ባሉ አካላት የግል የፖለቲካ እና ሌሎች ጥቅሞችን የማግበስበስ ፍላጎት መነሻነት መሆኑን ፓርቲያችን በተደጋጋሚ ገልጾ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ጥሪ አስተላልፏል። አሁንም በዚህ ተግባር የተጠመዱ ስልጣን ላይ ያሉ አካላት ከዚህ ተግባር እንዲቆጠቡ እናሳስባለን።

ማህበረሰቡም ለነዚህ ጥቅመኛ ግለሰቦች የግል ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሣርያ ከመሆን ይልቅ ከታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ጀምሮ ያጋጠሙትን አስተዳደራዊ በደሎች ለመፍታት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይደረጋል ተብሎ በሚታመነው የአካባቢ፣ የቀበሌ እና የወረዳ ምርጫ በንቃት በመሣተፍ በአግባቡ ሊያስተዳድሩት የሚችሉ ግለሰቦችን እንዲመርጥ ጥሪ እያስተላለፍን፤ የሀገራዊ ምክክሩንም ሂደት በተመሣሣይ እንዲሁ በአንክሮ እንዲከታተል እንጠይቃለን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ትኑር ኢትዮጵያ - ዘሪቱ ከበደ || Tinur Ethiopia - Zeritu Kebede (Official Lyric Video)

ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት የፌደራል ሥርዓቱ ያሉበት እንከኖች ሳያንስ ያለ ሕዝብ ፈቃድ እና ይሁንታ እንዲሁም አማራጭ ሐሣቦችን ሣይመለከት “የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግስትን በክላስተር ለማዋቀር” ብቸኛው አማራጭ አድርጎ ይዞ መምጣቱ ፈጽሞ ትክክል አለመሆኑን እና ሀገራዊ ምክክሩ ላይ አጀንዳ ሆኖ ይቀርባል ተብለው ከሚታመንባቸው አንዱ የሆነውን የፌደራል አወቃቀር ከወዲሁ በመነካካት ሀገራዊ ምክክሩ ላይ እምነት እንድናጣ ከማድረግ ሊቆጠብ ይገባል።

ኢዜማ ፌደራሊዝም ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር የተያያዘ በመሆኑ፤ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሕዝቡ ራሱን ለማስተዳደር መፈለጉ በራሱ ችግር አለመሆኑን ይገነዘባል፡፡

የዞን እና ክልል የመሆን ጥያቄ ያላቸው ማኅበረሰቦች ምንም እንኳ አሁን ሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47(2) መሠረት ጥያቄዎችን የማንሳት ሕገ መንግሥታዊ መብት ቢኖራቸውም፤ ክልል የመሆን ጥያቄዎች ከዘውግ ይልቅ ዜግነትን መሠረት ያደረገ እና ሁሉንም ማህበረሰብ ባቀፈ መልኩ መቅረብ እንዳለባቸው ኢዜማ ማስገንዘብ ይወዳል፡፡ ይህም ለጋራ የወደፊት ዘላቂ ሰላም እና ልማታችን ቁልፍ መሆኑን ያምናል፡፡

ኢዜማ በአራቱም አቅጣጫ ላለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘላቂ ሰላም እና ልማት የሚጠቅመው በጥናት ላይ የተመሰረተ እንዲሁም የህዝብን ከታች እስከ ላይ ባሉ መዋቅሮች ራስን በቀጥታ የማስተዳደር መብት የሚያጎናጽፈው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም መሆኑን ያምናል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ከፍተኛ በጀት ፈሰስ ተደርጎበት በአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን የተጠናው የአስተዳደር ክልሎች እንዴት ይዋቀሩ የሚለው የጥናት ውጤት ለሀገራዊ ምክክሩ እንደ ግብአት ሆኖ እንዲቀርብ እንጠይቃለን።

የዞን እና ክልል የመሆን ጥያቄ ያላቸው አካላት ቀጣይ ሀገራችን ታካሂደዋለች ተብሎ የሚጠበቀው ሀገራዊ ምክክር ላይ ተነስተው መፍትሄ ያገኛሉ ተብለው የሚጠበቁ ጉዳዮች ላይ ከወዲሁ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ማድረግ ምክክሩ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ መሆኑን ተረድተው ከጊዚያዊ አካባቢያዊ ጥቅም ይልቅ የትልቋን ኢትዮጵያ ምስል በማየት ለነገ የጋራ ጥቅማችን አስቦ አጀንዳውን በማሳደር፤ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ በሰከነ እና የሀገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታ በተረዳ መልኩ ከተለያዩ አካላት የሚቀርቡ ሀሳቦችን ከመመዘን እስከ ሕዝባዊ ውሳኔዎች ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አንድነት ፓርቲ የሰኔ አንድን ሰማእታት ዘከረ

ሀምሌ 28፣ 2014 ዓ.ም

#ኢዜማ

3 Comments

  1. ኢዜማ በአብይ አህመድ ተጠልፏል ፣የብልጽግና ቅርንጫፍም ነው እየተባለ የሚነገረው እውነት ወይንም ውሸት ስለ መሆኑ መግለጫ ከማውጣት ሌላ እስካሁን ተጨባጭ እርምጃን አልወሰደም፡፤ ምሳሌ ፦እራሱን ከመንግስታዊ መዋቅር አባልነት ማግለል፣ ህዝቡን ለሰላማዊ ተቃውሞ እንዲወጣ ማድረግና “ያሻግሩናል” ያላቸው አብይ አህመድም ሆነ ታከለ ኡማ እንዳላሻገሩን አምኖ ህዝቡን ስለማሳስቱ በይፋ ይቅርታ መጠየቅ የመሳሰሉትን ሲያደርግ አልታየም፡፡
    አሁንስ ቢሆን ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ ነው ህዝቡ ኢዜማን የሚያምነውና የሚከተለው?? “”ይህ እንደዚህ ይሁን””‘ እና “””ያ ደግሞ እንደዚያ አይሁን””” ስላለ ብቻ???
    ተግባር!!ተግባር!!!

  2. ብርሃኑ ነጋ ይህንን አስተያየት ደፍሮ ከሰጠ ብልጽግና ተዳክሟል ማለት ነው እጁን ቀድሞ ሲያወጣ ነው፡፡

  3. ድንቁ ሞላ ብሬን አታውቀውም መሰል በዘመነ ትግሬ ቅንጅት ምድር አንቀጥቅጥ ሰልፍ እንዲወጣ ትእዛዝ ሰጥቶ ሌሊቱን በውድቅት እንድብር እንሰት መሃል ቁጭ ብሎ ያንን የመከራ ጊዜ አሳለፈ እሱ ስለፉን መርቶ ለድል ያበቃኛል ያለ 230 ወጣት በትግሬ አልሞ ተኳሾች ረገፈ አሁን ደግሞ ትንሽ ቢሮ ገብቶ እንዲወጣ ሚኒስተር ነህ ብለውት ከብልጽግ ና በላይ ኢትዮጵያን የሚያሻግራት የለም ይልሃል ብሬና አረጋው በርሄ እንዲህ ያሉ ጩሉሌዎች ናቸው ብሬ በዚህ አሰራሩ ጥርሱን ነቅሎበታል አንድ ንግግር ሳያደርግ ሳይከራከር አንዷለምን ዘርሮ የድርጅቱ መሪ ሲሆን ትንሽ አይገባህም? አልታሰረ አልተገረፈ ባገር አልነበረ ብሩን ረጭቶ የፈለጋት ቦታ ቁጭ ብሏል ሰውዬው አብይ ሆነ እንጂ እሱና አረጋዊ ህልማቸው ሌላ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share