ከዘካሪያስ አሳዬ ([email protected])
! … ወያኔና የወያኔ ጀሌዎች የመናገር ነፃነት አለ እያሉ የሚደሰኩርት እዛው ለገደል ማሚቱ ። አንሰማችሁም ….!
የመናገር መብት እኮ ተፈጥሮ በስጦታ የለገሰችን እንጂ የወያኔ ችሮታ አይደለም። ወይ የመናገር ነፃነት!
እንዲሁ ተነስተው ማስፈራራት፣ መደብደብ፣ ማሰር፣ፀረ_ሰላም ሐይል፣ሽብርተኛ፣ ኧረ ምኑን ብዬ ምኑን ልተወው። ወያኔ ከከባድ መሳሪያ ይልቅ ብዕርን ይፈራል !ሀቅ ነው። ትንሹን ሚዲያ እንኳን ሀሳብን ለመግለፅ የምንጠቀምባትን ጋዜጣና መፅሔት እገዳ መብዛትን፣ ለየት ያለ ሐሳብ መንግስትን የሚተች ፅሁፍ ሲፃፍ ጋዜጠኛው፣ አምደኛው ማሳደድና የፀረ_ ሰላም ሀይሎች ቡድን አነሳሽ እያሉ በውሸት ክስ መስርተው ሽብርተኛ አባል እያሉ ማሰር። እንዴት ነው ታዲያ በዚህ ሁናቴ መንግስት ጥሩ ነው የምትሉን! አንሰማችሁም። ለአገር ተቆርቋሪ ፣ አገር ወዳድ መሆን እኮ በአገር ላይ ጦርነት ማወጅ እኮ አይደለም! አንድ ሰው የፈለገውን የፖለቲካ ድርጅት አባል፣ ደጋፊ መሆን ይችላል ህገ_ መንግስት መብቱ ነው።ወያኔ እኔን አምልኩኝ ማለት አይችልም! አገር ዉስጥ ሆኖ የፈለገውን እየተናገረ ያለ ሰው እንዲሁም እየፃፈ ኢትዮዽያ ዉስጥ የመናገር መብት የለም ይላል የምትሉ ሁላ። ብንጽፍም መብታችን ነበር ግን ዋጋም እየተከፈለ እስከ እስራት፣ ድብዳባ ፣ሞት ድረስ። በነፃነት ጉዳይ ቢከፈልም አይቆጭም እውነት እንዲ ስለምታገበግብ መስዋትነት ይከፈልላታል። ደግሞ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 29 ዜጎች ዘርፈ ብዙ ከሆኑ የመገናኛ ብዙሀን መረጃን የማግኝት እና የመሰላቸውን አስተያየት የመያዝ መብታቸው ተረጋግጦላቸዋል። በተለይ ደግም በአንቀጽ 29 ንኡስ አንቀጽ 5 መሰረት በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙ መገናኛ ብዙሀንም እንኳ ቢሆኑ የአስተሳሰብ እና የአስተያየት ብዙሃነትን (Diversity of Expression and Opinion) ማረጋገጥ አለባቸው::
ጥሩ የሚባል አስተያየት ነው። ነገር ግን ለወያኔ/ኢህአዴግ የመናገር መብት ወይ ነፃነት በአግባቡ ካለመገንዘብ የመነጨ ሆን ብለው የሚያደርጉት ይመስለኛል።
የመናገር መብት በዌብ ሳይት እና በፌስቡክ ብቻ መፃፍ መቻል ማለት ነው? ስለ መናገርና ስለ መፃፍ መብት ስናገር፣ መናገር የምችልባቸው መድረኮች እንዲኖሩ እየጠየቅን ነው። ለምሳሌ በአገር ቤት ውስጥ እኔ በነፃ ሚድያ (የግል ቲቪ፣ ሬድዮ፣ ጋዜጣ፣ መፅሄት፣ ጦማርና የተለያዩ ዌብሳይቶች እንደፈለኩ መናገርና መፃፍ እችላለሁ ወይም እንችላለን? እነዚህ ሁሉ በገዥው መንግስት የተዘጉ አይደሉምን? በነፃነት እንዳንናገር አልታፈንም? የግል ሚድያ ሲታፈን የመናገር መብትም አብሮ እየታፈነ ነው።
ስለዚህ በፌስቡክ መፃፍ ስለቻልኩ የመናገር መብቴ ተከብሮልኛል ማለት አይቻልም። በኢንተርኔት ካፌ እንኳን ስንጠቀም እኮ ማን አለ አጠገባችን፣ከዛም አልፎ የመንግስት ሰላዮች እንደ ቤቱ ጠባቂ ቁጭ ብለው እንደሚውሉ ይታወቃል ይሄ ነው የፌስቡክ ነፃነት የሚባለው? አንሰማችሁም!! ፌስቡክ የኢትዮዽያ መንግስት የግል ስጦታ አይደለምና እድሜ ለፈልሳፊዎቹ! እኛ ነን እንዳትሉኝ መንግስት ተብዬዎቹ።
እንበልና እኔ በፌስቡክም በሌላም የፈለኩትን ነገር እንድናገር ተፈቅዶልኛል። እኔ የመናገር መብት አለኝ ማለት ሁሉም የኔ አምሳያ የመናገር መብት አለው ማለት እንችላለን? ብዙ ዜጎች እንኳን የመናገር መብታቸው ሊጠቀሙና ለህይወታቸውም ፈርተው ይኖራሉ አረል እንዴ። ብዙ ጓደኞቼ ህውሃት ( ወያኔን) ባለመደገፋቸው እንዳይጽፉ፣ የታሰሩ ፣ የተገደሉ፣ የተሰደዱ፣ከስራ ሁሉ የተባረሩ ሁሉ ቆጥረን የማንጨርሰው እራሳቸው ይቁጠሩት እንጂ እኛማ እንዴት? የፈለጉትን የተናገሩ ሰዎች ከገዢው ፓርቲ ማስፈራርያ፣ድብደባ ይደርሳቸዋል።ሃቅ ነው!
ባጭሩ የእኔ የመፃፍ መብት ተከበረ ማለት የሌሎች ሰዎች (የሁሉም ሰው) መብት ተከበረ ማለት አይደለም። ወይስ የራሴ መብት ካስከበርኩ ስለሌሎች ሰዎች መብት መናገር የለብኝም ነው ነገሩ?
“እንደፈለክ እየተናገርክ የመናገር መብት የለም ትላለህ” ለምትሉኝ ሁላ አንሰማችሁም። እኔ የመናገር መብቱ ስላለኝ፡ ዝም ብዬ ዝም ልበል? ምን እያላችሁኝ ነው? እዚጋ የመከራከርያ ሐሳባቹን ማወቅ እፈልጋለሁኝ። አማራጭ ልስጣቹ (እኔን ለምትቃወሙ የስርዓቱ ደጋፊዎች) እኔ መናገር ስለቻልኩ:
ገዢው ፓርቲ ዴሞክራሲ (የመናገር ነፃነት) አስከብሯል/ አስፍነዋልና፤ ፓርቲውን መውቀስ፣ መቃወም የለብህም እያላችሁኝ ነው? ፓርቲያቹ የመናገር (ሐሳብን የመግለፅ) መብት ከፈቀደ፣ እኔ በፌስቡክ ስፅፍም ይህንን ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቴ እየተጠቀምኩ ነው። ስለዚህ መብቴን መጠቀም እንጂ ዝም እንድል አይጠበቅም። መብቱ ስለተሰጠህ (ተስጥቶኝ ከሆነ) ዝም ማለት አለብህ ሊባል አይገባም፤አፃፍ ከተባለ ግን መብትን መስጠት ሳይሆን መከልከል ነው የሚባለው።
በኢትዮዽያ ዴሞክራሲ የለም (የመናገር ነፃነት ታፍነዋልና) አንተ ገዢው ፓርቲ የመንቀፍ ወይ የመቃወም መብት የለህም እያላቹ ነው? ሐሳባቹ እንዲህ ከሆነ ታድያ የኔ በፌስቡክ በመፃፍ ሰዎች ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እንዲኖራቸው ለምናደርገው ትግል አንድ አካል መሆኑ ነው። ስለዚህ የምፅፍበት ምክንያት ግልፅ ነው። እኛ ኢትዮዽያውያን የመናገር ነፃነታችንን የሚያከብርልን ዲሞክራሲያዊ መንግስት ያስፈልገናል። ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ መታገል ያስፈልጋል። ስለዚ መፃፌ ትክክል ነው።
በኢትዮዽያ ዴሞክራሲ የለም፣ ግን ዴሞክራሲ የራሱ የሆነ ገደብ (ሕግና ስርዓት) አለው። አንተ በምትፅፋቸው ነገሮች ስርዓት ሊኖርህ ይገባል እያላቹ ከሆነ እኔ የምፅፈው ሕገ መንግስት መሰረት ያደረገ መሆኑ ላረጋግጥላቹ እወዳለሁ። በኢትዮዽያ ሕገ መንግስት የሚጣሰው በተራ ዜጎች ሳይሆን በገዢው ፓርቲ ነው። ሕግ የጣሰ በሕግ ይጠየቃል። ነፃነት ገደብ አለው። ያ ገደብ ግን በተግባር በሚሰራበት ሕገ መንግስት ውስጥ የተደነገገ የጋራ የስምምነት ነጥብ እንጂ የገዢዎችን የግል ጥቅም መሰረት ያደረገ አይደለም።
በዚህ መሰረትም ሐሳብ የመግለፅ ነፃነት እስከመሳሳት ድረስ ይሄዳል። ሰው የመሳሳት መብት አለው። መሳሳት በራሱ ስሕተት አይደለም። አንድ ተግባር ስሕተት የሚሆነው የሌላውን ሰው መብት በአሉታዊ መልኩ መጉዳት ሲጀምር ብቻ ነው። ለዚህ መፍትሔም ጉዳዩ ወደ ሕግ (ፍርድቤት) ማቅረብ ነው። (ይቅርታ ነፃና ገለልተኛ የፍትሕ ኣካላት ሲቋቋሙ ማለቴ ነው)።
የመናገር መብት (ሐሳብን በነፃነት መግለፅ) ሲባል ስትጮህ ወይ ስትፅፍ አለመታሰር ወይ አለመከልከል ማለት ብቻ አይደለም። የመናገር መብት የመደመጥ መብትም ይጨምራል። ዜጎች የመናገር መብት አላቸው ስንል ለሚናገሩትን ነገር፣ ለሚጠይቁትን ጉዳይ መንግስት በሚገባ አዳምጦ መፍትሔ የመስጠት ሕገ መንግስታዊ ግዴታ አለበት። ዜጎች ተሰሚነት ሊኖራቸው ይገባል።
የመናገር መብት መጮህ (ወይ መፃፍ) ብቻ አይደለም። ለምሳሌ የኢትዮዽያ ሙስሊሞች ለአንድ ዓመት ያህል በሰለማዊ ሰልፍ መልክ ጥያቄያቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። ጥያቄያቸው ግን እስከኣሁን ድረስ መልስ አላገኝም። ሰልፍ መውጣት ስላልተከለከሉ ታድያ ሰለማዊ ሰልፍ የማድረግ መብታቸው ተከብሮላቸዋል ማለት አይቻልም። የሚመለከተውን አካል ጆሮ ማግኘት አለባቸው። መፍትሔ እስካላገኙ መብታቸው አልተከበረም። ስለዚህ መናገር ብቻ አይደለም የምንፈልገው፤ መደመጥም እንፈልጋለን።
በሚዲያ መረሳት ሞት ነው!ነጻ ሚዲያ የሌለበት አገር አደጋ ውስጥ ነው! ነጻ ክርክርና ነጻ ሚዲያ የሌለበት አገር ሰላምና መረጋጋቱ አስተማማኝ አይደለም።ነጻ ሃሳብና ነጻ ህዝብ መፈጠር አለበት።የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩም ሆነ በማንነቱ ለነፃነት አዲስ አይደለም።
የመናገር መብት ከሌለ ‘የነፃነት መብት የለም’ በተመሳሳይ የመኖር ህልውናም ያከትማል ። ስለዚህ ‘የመናገር መብት የለም’ ብዬ ግን! የመናገር መብት አለኝ።የገዥው መንግስትና ጀሌዎች አንሰማችውም የመናገር መብት ሳይኖር መብት አለ እያላችሁ ለምታቀነቅኑ! አሁንም እንላለን አንሰማችሁም!!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!