የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ስላሴ ኮሌጅ ከመጋቢት 30 ቀን 2005ዓ.ም. ጀምሮ መቋረጡን የሚገልፅ ማስታወቂያ በኮሌጁ ግቢ ውስጥ መለጠፉ ተገለፀ፡፡ የፍኖተ ነፃነት ምንጮች እንዳረጋገጡት ከሆነ ከመጋቢት 30 ቀን 2005ዓ.ም. ጀምሮ ትምህርት መቋረጡን የሚገልፅ ማስተወቂያው በይፋ በኮሌጁ ግቢ ውስጥ የተለጠፈ ሲሆን ማን እንደለጠፈው የሚያረጋግጥ የኃላፊ ስም አለመኖሩም ተጠቁሟል፡፡
የትምህርቱን ሟረጥ ማስታወቂያ የግቢው አስተዳደር አካላት እንደማያውቁት የተገለፀ ሲሆን የኮሌጁ ምክትል አስተዳደር ዲን የሆኑት ዶ/ር አባ ኃይለማርያምም ጉዳዩን ስለማያውቁት በክፍል ውስጥ ገብተው ማስተማራቸው ታውቋል፡፡ የኮሌጁ ትምህርት የተቋረጠበትን ምክንያት ለማጣራት ወደ ቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ወደ ሆኑት ብፁ አቡነ ህዝቄል ጋር ብንደውልም ስብሰባ ላይ ነኝ የሚል መልስ ሰጥተውናል፡፡ በኮሌጁ ከማጋቢት 2 ቀን 2005ዓ.ም. ጀምሮ ተማሪዎች ባነሱት ጥያቄ የምግብ አድማ ማድረጋቸውን ተከትሎ የተቋረጠው ትምህርት ከ2 ሳምንታት በኋላ ከምግቡ በቀር ትምህርቱ ቢጀመርም ተማሪዎቹም ሆኑ አብዛኛው የአስተዳደር አካላት ሳያውቁ በተለጠፈ ማስታወቂያ ትምህርት መቋረጡ ተጠቁሟል፡፡
ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ከአዲስ አበባ እንደዘገበው።