ማሳመኛ ንግግር ዓይነቶች ሲፈተሹ  (ዶ | ር ፀጋዬ ደግነህ ጉግሳ)  

14.07.2022

ለተከበራችሁ ወገኖች

ጭምቅ ገለፃ

ዶ | ር ፀጋዬ ደግነህ ጉግሳ

ከዚህ በፊት የበይነ መረብ ስነምግባርን በተመለከተ ካወጣሁት ፅሁፍ በመቀጠል፣ ለውቅረ ሃሳብ እይታ እንዲረዳ በመገመት እና ከዓመታት በፊት ለፕሮጄክት ማኔጀሮች ሶፍት ስኬል እንዲያግዝ ከፃፍኩት በመቆንፀል እና በማሻሻል ይህን አጭር ፅሁፍ ለማቅረብ ወሰንኩ።

ቃላት ምስል ወልደው ድርጊት የመፍጠር ኃይላቸው ከባድ ነው። ማሳመኛ አባባል / ክርክሮች (arguments) ውጤታም የሚሆኑት፥ ክስተቶችን፣ ቀመሮችን፣ ቅደም ተከተሎችና ትንታኔዎችን አስመርኩዘው ጠለቅ ባለ ነጥብ ሲቀርቡ ነው፥ ንግግር ማቅረብ መቻል (rhetoric) ግን አንድን ሰው ስለ አንድ ነገር የጠለቀ እውቀት ሳያስፈልገው ሰዎችን በቃል አጣጣሉና ቅላጼው በመሳብ፣ ማሳመን ማስተባበር መቻል ነው። ይህን በተለይም ፖለቲከኞች፣ ማኔጀሮች፣ ሰባኪዎች፣ ተዋናዮች የሚማሩት ወይንም የሚችሉት ነው። መነጋገር ለብዙ ችግሮች መፍትሄ ነው። ይህም የተወሰነ ደንብ እና ስዓት ሲኖርው ውጤታማ ይሆናል። ለዕለት ተዕለት የመግባቢያ ንግግሮች እንዲረዳንም ሆነ ነገሮችን በቀላሉ ለመወሰን እንድንችል መሰረታዊ የመረጃ ልውውጥ አባባሎች፣ ዓይነቶችንና ደንቦችን መመርመር መልካም ነው። ለማሳየት እንዲረዳ ሲባል፤ አጠቃላይ (ይዘታዊ) እና ስሜታዊ የማሳመኛ መንገዶች በሚል እንደሚከተለው ማየት ይቻላል።

አጠቃላይ ማሳመኛ

  1. መሠረታዊማሳመኛ (Argumentum a priori)

ይህ ከአጠቃላዩ ወደ ውስኑ የሚተነትን ነው።

ምሳሌ፦ ሰው ሟች ነው። ሶቅራጥስ ሰው ነው። ሶቅራጥስ ሟች ነው። ደካማ መሰረተ ልማት የኋላቀርነት ምንጭ ነው፣ መንገድ አንዱ መሰረተ ልማት ነው። የመንገድ አለመኖር ኋላቀርነት ነው።

  1. ቀመር ተኮር ማሳመኛ (empirical argument)

ምሳሌ፦ አዲስ የተከፈተው ክሊኒክ በቀን 50 ሰው ቢያስተናግድ፣ በሳምንት 350 ሰዎችን ያስተናግዳል። | ኢትዮጵያ 12 ተፋሰስ ወንዞች ያሏት፣ በአንጻራዊነት ትልቅ መጠን ያለው በዓመት 122 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር የዝናብ መጠን እና እስከ 6.5 ቢሊዮን  ኪዩቢክ ሜትር የሚገመት የከርሰ ምድር ውሃ ቢኖራትም በሰፊው የዝናብ ልዩነት፣ በማከማቻ እጦት እና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ 3 በመቶው ብቻ ነው ጥቅም ላይ የሚውለው።

  1. ዳዊማሳመኛ (inductive argument)

ከልማድ እና ከታሪክ የተነሱ የማሳመኛ አባባሎች

ምሳሌ፦ ወደ ቆላ አካባቢ ሄዶ መስራት ለወባ በሽታ ሊዳርግ ስለሚችል መከላከያ መድኃኒት ሊዘጋጅልኝ ይገባል።

  1. ቀጥተኛ ያልሆነ ማሳመኛ (Argumentum e contrario)

ይህ በተለይም በተቃራኒው የሚያሳምን ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ማዕከላዊ ምክር ቤት የአራተኛ መደበኛ ስብሰባ የአቋም መግለጫ

ምሳሌ፦ የወባ መከላከያ መድኃኒት የሚወስድ ሰው በተለይም አካባቢው የወባ ትንኝ የሌለበት ደረቅ ከሆነ ስጋት የለውም እና ይህ ከተሟላ የወባ ስጋት ቢኖርም እንኳ ወደ ቆላ አካባቢ ሄዶ መስራት ይቻላል። |
ህጉ ለውጭ ዜጋ በመደበኛነት ተቀጥሮ መስራትን ይከለክላል፣ ስለዚህ በጊዜያዊነት መስራት ይቻላል።

  1. ከፍ ያለ ኃይልን፣ የታወቀን ሰው በመጥራት ማሳመን (Argumentum ad verecundiam)

መፅሐፍን በመጥቀስ፣ የታወቀ ሰውን ወይንም የነብያቶችን ስም በመጥራት ማሳመን

ምሳሌ፦ ማሀተመ ጋንዲ ጥንካሬ ከአካላዊ ብቃት ሳይሆን ከውስጣዊ ብርታት የሚመጣ ነው እንዳሉት፣ ጡንቻ መኖሩ ብቻ ሳይሆን የማይበገር የአዕምሮ ብርታት ነው የሚያስፈልገው እና በስፖርት ትይዩ ስነልቦናችሁን አጠንክሩ።

  1. ማህበረባዊማሳመን (Argumentum ad populum)

ሰው በብዛት የተቀበለውን ነገር እውነት ሆነም አልሆነ ወይም ከወቅቱ ሁኔታ አኳያ ቢያጠራጥረም እውነት አድርጎ መወሰድ።

ምሳሌ፦ ሰኔ እና ሰኞ  |  ፈሪ ውሃ ውስጥ ያልበዋል | ጸሀይ ሳለ ሩጥ፣ አባት ሳለ አጊጥ | ሰው ሁሉ ወጥቶ በዓል እያከበረ ነው፣ ኑ እኛም አብረን እናክብር።

  1. ሞራማሳመኛ (ethics argument)

ይህ በአብዛኛው ከሐይማኖት፣ ከህግ እና ማህበራዊ ሞራል በመነሳት  የሚሰጥ አባባል ነው።

ምሳሌ፦ ይህ ቤት ሁለት መቶ ዓመት ዕድሜ አለው፤ ስለሆነም ታሪካዊና ዕድሜ  ጠገብ በመሆኑ አይፈርስም። የሚሰራው መንገድ በቤቱ ዙሪያ አልፎ እንዲሄድ መደረግ አለበት። | ልጅ ወላጆቹን ማክበር አለበት። | መምህር ተማሪዎችን መምታት አይችልም።

  1. መላምታዊ ስሜታዊ ማሳመኛ (Hypothecal argument)

የገዛ ራስን ወይንም የሌላን ልምድ እና መላ ምቶችን በሶስተኛው ሰው በራሱ ላይ እንደደረስ አድርጎ ማሳመን። ይህ ማለት ግን የግድ አባባሉ ትክክል ነው ማለት አይደለም።

ምሳሌ፦ ሲጋራ ማጨስ ለካንሰር እንደሚዳርግ በጓደኛህ ላይ ዓይተህዋል። ስለዚህ ማጨስ አቁም።

  1. በተገላቢጦሽ ማሳመን ወይም ባለማወቅ ማወቅ (Argumentum ad ignorantiam |  vice versa)

ምሳሌ፦ ፈጣሪ እንደሌለ ማሳመኛ ማስረጃ እስካልቀረበ ድረስ ፈጣሪ አለ ማለት ነው።

  1. ከጥሩ ውጤት የሚነሳ ማሳመኛ (Argumentum ad crumenam)

ምሳሌ፦ አቶ እገሌ ባህላዊ ስዕሎችን በመስራት ሀብታም ሆነ። ስለዚህም ባህላዊ ስዕሎችን መስራት ሀብታም ያደርጋል።  | ወ/ሮ እከሊት በአትክልት ልማት ከራሷ አልፋ ለአካባቢዋ ነዋሪዎች አዲስ የስራ እድል ፈጠረች።

  1. የድግግሞሽ ማሳመኛ (Argumentum ad nauseam)

ይህ የሚጠቅመው በተለይ በመደጋገም ማሳመን ሲያስፈልግ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:   ፖለቲካ እንደ ዕምነትና እንደ መርህ ከመታየቱ በፊት መቅደም የሚገባቸው ነገሮች! - ክፍል አንድ!! - ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

ምሳሌ፦ የቶዮታ መኪና ሰራተኞች ጠዋት ጠዋት ስራ ሲጀምሩ እኛ በአለም አንደኛ ነን፣ ተፎካካሪዎቻችንን እናሸንፋለን! በማለት መፈክር ያሰማሉ። እዚህ ላይ ደጋግሞ በማለት የማሳመን ባህል በአገራችን ረዥም እድሜ ያለው ነው።

  1. ዝም በማለት ማሳመን (Argumentum ex silentio)

ጠቃሚ መረጃን አውቆ በማለፍ፣ ጥርጣሬ የሚያስከትሉትን ጥያቄዎች ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ በመተው ንግግርን ማቋርጥ፣ ዝም በማለት ወይም ምክንያት ሳይሰጡ አሉታን መግለጽ እና የማይመጥን ጥያቄን ማለፍን ይይዛል።

ምሳሌ፦ ይህንን ያህል ጊዜ ወስጄ የተከታተልኩት፣ በትዕግስት ያዳመጥኩት ምንም የሚጠቅም ነገር አላገኘሁበትም።

በስሜት ላይ የሚደረጉ ማሳመኛዎች

ይህ የማሳመኛ ጽንሰ ሐሳብ ከነገሩ ጋር በአብዛኛው ባልተገናኘና በምክንያታዊነት ላይ ያልተመረኮዘ ነው። ተናጋሪው በደመነፍስ ወይም አውቆ ይፈርጃል (unconscious / conscious bias)። ነገሩን ከዋናው እይታ አቅጣጫ በማስቀየስ፣ ግለሰብን በማጥቃት እና በማስፈራራት፣ እንዲሁም ለብቀላ በማነሳሳት፥ በዚህም የሰዎችን ስሜት በመቀስቀስ እና አንድን ሐሳብ ለማሳመን ወይንም ያላቸውን አቋም ለማስቀየር ይጠቀሙበታል። የይስሙላ ማሳመኛ Red Herring በመባል የሚታውቀውን ያጠቃልላል።

 

  1. የስህተት ማጠቃለያ አነጋገሮች (false conclusion, sophismus)

ትክክለኛ ጥቅስን ወይንም እውነትነት ያለውን አባባል ሆን ብሎ ለተሳሳተ ማስረጃና ማጠቃለያ መጠቀም

ምሳሌ፦ እያንዳንዱ ሰው ፍጥረት ነው፣ ፍጥረት ሁሉ ሰው ነው። | ናዚዎች ጀርመኖች ናቸው፣ ጀርመኖች ናዚዎች ናቸው።

  1. የማስተዛዘኛ ማሳመን (Argumentum ad misericordiam)

ስሜትን በመንካት ማሳመን

ምሳሌ፦ ሰውየው ስራውን መስራት ያቃተው ሚስቱ በመታመሟ በጭንቀት ስለተወጠረ ነው። | የምጠጣው ስራዬን በተንኮለኞች ስላጣሁ ነው።

  1. የስጋት፣ የጥላቻ ወይም የፍራቻ ማሳመኛ (Argumentum ad invidiamArgumentum ad metum)

ምሳሌ፦ ከአንተ እኩል የተቀጠሩት እኮ ዛሬ ከአንተ ያነሰ ስራ እየሰሩ ብዙ ይከፈላቸዋል እና ለምን መስሪያ ቤቱን ከሰህ መብትህ አታስከብርም? | ስራ ያጣነው ስደተኞች ቅድሚያ ስለተሰጣቸው ነው፣ እየባሰበት ነው፤ ስለዚህ ስደተኞች ከአገራችን ይውጡ።

  1. ግለሰብን በማጥቃት ማሳመን (Argumentum ad hominem) (Argumentum ad personam)

ምሳሌ፦ የተናጋሪውን ማንነት በመጥቀስ፣ ከዚህ በፊት የነበሩ ስህተቶች ካሉ ከነገሩ ጋር ባይያያዝም እየጠቀሱ፣  ሃሳቡን በመሰነጣጠቅ (sophistry)፣ ሌላ ትርጉም በመስጠት ተቀባይነት እንዳይኖረው ማድረግ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የብርሃን አካል በሆኑ ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት የአንድነት፣ ነጻነትና ፍቅር ፍሬዎች ይጎመራሉ - ሚኪያስ ግዛው

ይህ ጥሩ ነው ብለው ያቀረቡት ሃሳብ ቀድሞ ሲሰሩ የነበሩበት መስሪያ ቤት ለምን አልሞከሩትም። | አናምነውም፣ የሰውየው ዘመድ ገንዘብ አባክኖ የተፈረደበት ሰው ነው። | እኛ ስንሯሯጥ አንተ የት ነበርክ? | ለምን ይህንን አሁን ማድረግ ፈልክ? የሆነ ተንኮል ከጀርባው ቢኖር ነው። | ውጭ ሆኖ በርገር እየተበላ ስለሀገር ቤት ችግር መናገር አይቻልም። | አገርህ ሰው ተርቦ አንተ እዚህ አሜሪካ፣ አውሮፓ ተዝናንተህ መኪና ትነዳለህ፣ ቤት ትሰራለህ።

  1. በማስፈራራት ማሳመን (Argumentum ad baculum)

ምርጫ በማሳጣት ይህ ካልሆነ ይህ ይደርጋል የሚል እና ማዕቀብን ለመጣል የሚያስፈራራ ማሳመኛ ነው።

ምሳሌ፦ ጆርጅ ቡሽ በኢራቅ ጦርነት ወቅት ወይ ከእኛ ጋር ናቹህ ወይም ከጠላቶቻችን ጋር እንዳሉት ማለት ነው።

ወይም አብረህን ሰልፍ ካልወጣህ ደጋፊያችን አይደለህም።

  1. ጎጂ፣ የንቀት፣ ተራና ስድብ መሰል ተስፋ አስቆራጭ ማሳመኛ (K.O. Argument)

ይህ በተለይ ሌላውን ሰው በማጥላላት፣ በማናናቅ፣ ንግግሩን በማቋረጥ፣ በመረበሽ እና በማደናገር የሚሆን ነው።

ምሳሌ፦ አቁም! | አንተን ብሎ መካሪ | እኛ ብዙ ዓመታት ሰርተናል እናውቀዋለን | አንተን አሁን ማን ወከለህ | ማንም አይሰማህም | ምንም መቀየር አያስፈልግም | አሁን ጊዜው አይደለም | ጥቅም ፈላጊ | ውሸት ነው | አይመለከተንም | ሰዉ ይህንን መስማት አይፈልግም ሰልችቶታል ወዘተ…

ርዕሱ ሰፊ ቢሆንም በአጭሩ ለዛሬው ይህንን ይመስላል። ከምሳሌዎቹ ገላጭነት በመነሳት አንባቢው የራሱን ምሳሌ ሊያስቀምጥ ይችላል። ይህንን የሚያሻሽል እና የሚገነባ ሃሳብ ቢኖር መልካም ነው።

ከመልካም የጤንነት እና የሰላም ምኞት!

“ውጤታማነት ማንኛውም ዓይነት አባባልን ይተካል”  – ሳልቫዶር ዳሊ

____________■
ዶ | ር ፀጋዬ ደግነህ ጉግሳ
ሐምሌ ፯ ፪ሺ፩፬ ዓ∙ም∙ (Berlin, 14th July 2022)

2 Comments

  1. ደመቀ መኮንን ድርድሩን ይምራው ማለት ቁማሩን አስበልቶ ጣጣችሁን ቻሉት ለማለት ነው ማለት ነው? በጓዳ አብይ ደመቀን ያዛል ጥሩ ታዛዥ ነውና በገሃድ እኔ ምን ላድርግ የናንተው ሰው ነው ይለናል፡፡ ኧረ ጎበዝ የዚህ ትያትር ምስጢሩ ይገለጽልን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share