ሰው እና ጀምበር – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ሰው ነኝ።  ፈጣሪ ፍቃዱ ከሆነ በወግ ልክ እንደ ጀንበሯ ፣ ጥዋት   ወጥቼ ማታ ልጠልቅ እችላለሁ ። ይኽ የሰው ልጅ ዕጣ ፈንታ ነውና !   አዳም እና ማቶሣላ ሺ ለመድረሥ ጥቂት ቁጥሮች የቀራቸው ዘመናትን ኖረው ፣ ዕድሜ ጠግበው መሞታቸውን ሣሥብና የዛሬው ሰው ዕድሜ ከ 70 ከዘለለ ድካም እንጂ ተርፍ የለውም ተብሎ በድጋሚ በፀሐፍ ቅዱስ መጠቀሱን ሣሥተውል እግዜሩ ለምን የዕድሜ ሥሥታም ሆነ እላለሁ ? ( ወይሥ ራሣችን ነን በምድራዊ ጥበብ የተነሠሠ ዕድሜዬችንን በየሚሊኒየሙ እያሣጠርነው የመጣነው ?)

ሰባን የማይሻገሩ የሰው እድሜዎች፣ ከጀንበር ፍንጥቀት እስከ ሥርቀት ያለውን ጉዞ ገላጭ ናቸው   ። ይሁኑ እንጂ ሰው እነዚህን የጤዛ ያህል ቆይታ ያላቸውን ቀናትን ሰው ፣ ሰው ሆኖ እንዳይኖርባቸው ተረግሟል ። በተለይም በአፍሪካ ። በባሰ መልኩ ደግሞ በኢትዮጵያ ።

በኢትዮጵያ    “ የሱም ሆነ የኔ ሰው መሆን ነው  እንጂ ዋናው ቁም ነገሩ  ሌለው  በዘመን ውስጥ ሰዎች የፈጠሩት ኮተትና ቆዳ ማዋደድ  እኔን አይመለከተኝም ። … ቋንቋ  ፣ዘር፣ጎሣ ኃይማኖት፣ ወዘተ ። ከሰው ተራ አያወጡኝም ። አማራ ፣ ትግሬ ፣ ኦሮሞ እያሉ በከፋፍለህ ግዛ እና ሽጥ ዘዴ ፣ የሌሎች የጋለ  የእንጀራ ምጣድ አያደርገኝም ። “ የሚል ሰውነቱን በቅጡ የተገነዘበ ፣ ከተሜ በብዛት የለም ። በአርሶ አደሩ ቀዬ ደግነትና ርህራሄ ትላንት ሞልቶ ተትረፍርፎ ነበር ። ዛሬ ግን ዕድሜ  ለሥግብግብ  እና ዘረኛ  ሊሂቃን እና ለመብላት ተቧድነው ለሚያሤሩ ፖለቲከኞች በባላገሩም ቀዬ ጥርጣሬ ና ሰው ጠልነት ለመንገሥ እያኮበኮበ ነው ። ለአገዛዝ እና ለምዝበራ ሲባል የመለሥ ዜናዊ እና የአሜሪካው ሲአይኤ የፈጠረው በቋንቋ ፣ በጎሣ ና በነገድ ላይ የተመሠረተ የዘመነ ከፋፍልቲ አገዛዝ “  የገሃነም  እሣት ነው ። “ ለባለአገሩ ።

ይኸንን “ የገሃነም እሣት “   ኢሳያስ አፈወርቂ ያልወደደው ሰው የተባለውን የጋራ መጠሪያ እና ሰውነትን እራሱን የሚያሥክድ በመሆኑ ለአንድነት ና ለፍቅር ፀር በመሆኑ መተላለቅን በሰዎች ዘንድ በእጅጉ የሚያበዛ መሆኑንን አሥቀድሞ ሥለተገነዘበ ነው ። ይኽ የዘመነ ከፋፍልቲ መንገድም  ፤ ጂቡቲን እና እራሷን  ኤርትራን እንዳሳጣትም  “ ከኢሱ “ የተሰወረ አይደለም ። በእንጊሊዝ መንግሥት ሥውር ሴራ ፣ በሲአይኤ ና በሞሳድ እሥፖንሰርነት ነው ፣ ቀኃሥ በቀላሉ ፍርክስክስ ያሉት ።   መንጌም አገር ጥሎ ሀራሬ የገባው በእነዚህ አገራት “ ነጭ ለባሾች “ ታላቅ ሴራ ነው ።

ሲጀመር ፣ መንጌ  ሥልጣንን ያገኛት ሻሞ ተብላ በአየር ላይ ሥንትሣፈፍ ነው ። ይኽንን ሃቅ  ሥንቶቻችሁ ታውቃላችሁ ?የጦር ክፍሉ ከሚገኝበት  ከሐረር ጦሩ ከእነ ሃምሣ አለቃ ለገሰ አሥፋው ጋር ጦሩ የላከው ሌላውን ተራ ነገር ተውትና “ ነውጠኝነቱን እና አንደበተ ርዕቱነቱን “  በማሥተዋል ነው ፣ ጦር ሠራዊቱ ብሶቱን እንዲያሰማለትና መፍትሄ እንዲያመጣለት መርጦ የላከው  ። እርሱም ፣ ድንገት ነው ሥልጣንን ጠቅልሎ መያዝ እንደሚቻል የተገለፀለት ። በሴራ እና ለምሣ ያሠቡትን ቁርሥ በማድረግ ለንግሥና መብቃት እንደሚቻል የተከሠተለት በወቅቱ በወታደራዊው ኮሚቴ ውሥጥ ለሚከሰቱ ችግሮች ፈጣን የመፍትሄ ሃሳቦችን ሲያቀርብ የጦሩን ቀልብ በመግዛቱን በማሥተዋሉ ነው ። ከእርሱ የተሻለ አንደበተ ርዕቱ በወታደራዊው ደርግ ውሥጥ ያለመኖሩን ሲረዳማ በልቡ “ የኃይሌ ዙፋን የእኔ ናት  ። “ ሣይል እንዳልቀረ ገምቱ   ። የአፍሪካ መንግሥታት ሥልጣን እንዲህ እንደዋዛ በብልጣ ብልጥነት ና ለምሣ የሚያሥቡህን ያለርህራሄ ለቁርሥ በማድረግ የምታገኛት ናት ። በአፍሪካ እነ ሙጋቤ እንደመሠከሩልን ፣   ደፋር ፣ ቆራጥ አብዮታዊ መሪ ከሆንክ ከአርባ ዓመት በላይ ሁላ መግዛት ትችላለህ ።   ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በፖለቲካ ቋሚ ጠላትና ቋሚ ወዳጅ የለም!!!

ተርታው ህዝብ በዕውቀት እና በጥበብ ባለመበልፀጉ ፣ በተራራ ፣ በዛር ፣ በቃልቻ ፣ በደብተራ ፣ በመፀሐፍ ገላጭ ፣ በጠንቋይ ፣ ወዘተ ። ከማመኑም በላይ ዛሬም ፈጣሪ ደሃ እንዳደረገው በማሰብ ኃላፊነቱን ለእርሱ ሰጥቶ ፣ “  አንተ  ታውቃለህ “ ። … የአርባ ና የሰማኒያ ቀን እድሌ ነው ። ይኽ የእኔ ዕጣ ፈንተ ነው ። … ባይ  ነው ። ህዝቡ   ፣ በመሠረታዊ ፍላጎቶች እጦት የሚሰቀይ እና ያለ ንቃተ ህሊና የሚኖር በመሆኑም ለመገዛት ምቹ ነው   ። ( ይኽንን ሃቅ አለማየሁ ገላጋይ “ በየተጠላው እንዳልተጠላ “ መፀሐፉ በጥልቀት ገልፆታል ። ብራቮ ! አሌክስ ። ፈጣሪ ሰው ያለመሆኑንን እና በዚህ የተነሣም  ሐሜት ፣ ሰብቅ ፣ አሽሙር ወዘተ የመሣሠሉትን ተንኮሎች ብቻ ሣይሆን የንፁሐኖችን ግድያ በተመለከተ እጁን በምድራዊ ፍርድ እንደማይከት ለማሣየት ብዙ እርቀት ሄደሃል ። እኔም ምድር ጥረን ግረን እንድንበላ እንጂ ተቀምጠን አበሣ እንድንቆጥር አልጋበዘችንም ። እላለሁ ። ሰው የምድር እንግዳ ነውና ።   ደሞም ለሐጢያት የሚመጣ ለፃድቃንም እንደሚደርስ አሥቀድሞ በቅዱስ መፀሐፍ የተፃፈውን አንብቡ ።   የሰው ጠላት ራሱ ሰው ነው ። ጠላትነቱም ከሥግብግብ ባህሪው ና መሞቱን በቅጡ ካለመገዘቡ ይመነጫል ።  አንዴ የቋንቋና   ከሁሉም ሰው ጋራ ተግባብቼ  ለመኖር የቻልኩትም  በተአምር አይደለም ።  ሰውን በሰውነቱ ብቻ በመቅረቤ እንጂ ነው።    የዓለም ሰው ሁሉ  በሰውነቱ  አንድ ነው ። ቆዳው ይለያይ እንጂ የወል መጠሪያው ሰው ነው ። ይህ ሰው በመባል የሚታወቀው፣የተለያየ የቆዳ ቀለም ከፈጣሪ የተለገሰው ፣ የዓለም ህዝብ በሙሉ ፣ ወንድሜና እህቴ ነው ። ብዬ የማምን  ነኝ ። አምኜም ቋንቋው ሣይገድበኝ በወዳጅነት ቀርቤ ና ቀርቦኝ ፣ቋንቋውን ባልችል  እንኳ በምልክት ቋንቋ ፍቅሬን ና አክብሮቴን ገልጬ ከተግባባው ምን እፈልጋለሁ ???  ሲጀመርም የዓለም እውነት ይኸው ነው ። …ከምልክት ቋንቋዋ ነው የመላው ዓለም ቋንቋዋ የመነጨው ፡፡ በየሀገሩ የተለያየ ባህል ቋንቋ ና ሀይማኖትን በዘመን እርጅና ውስጥ የፈጠሩትም የትላንት እህትማማችና ወንድምማች ሰዎች ከምልክት ቋንቋዋ ተነስተው ነው ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሞቴ ተሰውሮ - ከዶ/ር ፍቅሬ ቶለሳ

በኢትዮጵያ አማርኛ ብቻ አንደበቱ የሚናገር ሆኖም ኦሮምኛ ቋንቋ ከሚናገሩ የተወለደ ግለሰብ  “እኔ እኮ… ! ” ብሎ ኦሮሞነቱን  በአማርኛ ማስረዳት ቢጀምር ሰሚ የሚያጣው የቋንቋን ጅማሮ እና የተለያየ መሆን ደማዊ የሆነ መስሎ በመገኘቱ ነው ግን አይደለም ፡፡  በእውነቱ ይኽ ያልተገባ  አፍቅሮተ ቋንቋ  ነው ። ቋንቋ ሰው ከተፈጠረ በኋላ የሚለማመደው ፣ የሚኮርጀው እና የሚማረው እንጂ በደሙ ውስጥ ፣ በአንጎሉ ውስጥ ከመወለዱ በፊት ያለ አይደለም ፡፡

ፀሐፊው ይኽንን  ጽሑፍ የፃፈው ሰዎች፣ ቋንቋ ሳይሆኑ ፣ ሰው መሆናቸውን ተገንዝበው ከሁሉም ሰው ጋር በፍቅር እንዲኖሩ ጥቂት የብርሃን ፍንጠቂ በጨለመው መንገዳቸው ላይ ለማኖር አስቦ ነው ፡፡ሰው ሁሉ ምሥኪን ተራ ሟችነቱን ተገንዝቦ ፣ እስከ መቃብር  ከአምሳያው ጋር ያለውን ትስስር እና ንሮውን ለማሸነፍ የሚደርገው ጥርት እንዳይስተጓጓል በሰውነቱ እንጂ በቋንቋው ሌ እነዳይሟዘዝ ትሁት ምክሩን በመለገስ   በማስተዋል እንዲሞላ ለማድረግ ነው ፡፡

ከራሴ ሰውነት ተነስቼ እውነት ልናገር ፡፡ በበኩሌ ፤  አማራ፣ኦሮሞ፣ ትግሬ ፣  ኢትዮ ሱማሌ ፣ደቡብ  ውስጥ ካሉትም ጎሣ ነኝ ከሚሉት የአንዱም ነገድ አይደለሁም ።   ዘግይቶም ሆነ ፈጥኖ ወደመቃብር የሚገባ ጠፊ ሰውነት ይዢ ለግዜው በህይወት የምንቀሳቀስ ተራ ሰው ነኝ ።  የህይወት  ጉዞዬም እንደሁሉም ሰው  ከጀንበር ፍጥቀት  እሥከ ሥርቀት ነው ። ዘግይቶም ሆነ ፈጥኖ  ከአፈር በመሠራቴ ወደአፈር የምመለሥ ።  ሰው ሁሉ  እንደ እኔ ተራ ሟች እንደሆነም አምናለው ። ዛሬ ሲሞት ነገ በሚሞተው ተራ ሞች ታሪኩ ቢነገርም ተስካርና ዘካ ቢወጣለትም ፤  በምድር ቆይተው ከአፈር የተገኘውን ሲበላ እንደኖረ ሁሉ ፣ በተረው ደግሞ በአፈር ይበላል ፡፡ ሁሉ ከአፈር የተገኘ ነውና ሰው በቁሙ የሚንቀሳቀስ አፈር አይደለሁም ለማለት አይችልም ። …

“…ምንም ብንጓጓለት ብንስገበገብለት፣ይፈርሳል በግዜይቱ ሥጋ ነውና ከንቱ።…” ብላ እንዳዜመችው አፈር የሆነችው ብዙዬ ነገ ሁላችንም አፈር፣ወይም አመድ እንሆናለን። (አሥከሬን አቃጣዮች ሥላሉ ነው – አመድ ያልኩት።!)     ጥላሁን ገሠሠም    “ሀብቴ ተርፎ በዝቶ ብዙ ቢያደረጀኝ፣ሥሞት ሥንቅ አይሆነኝ ኋላ ምን ሊበጅኝ??? ” በማለት   ” እራቁታችንን ወደዓለም መጥተናል ከዓለምም አንዳች ይዘን አንሄድም ። ” በማለት አዚሟል ። እነዚህ በድምፃቸው ወርቅነት የማንረሳቸው የኪነት ሰዎች ፣እውነቱን በውብ ዜማ  ቢያሳውቁንም ፣ ሁሌ የሚሞተው በሬሣ ሣጥን ውሥጥ ያለው አሥከሬን ሥለሚመስለን ዛሬ እንደምንሞት ለማሰብ አንፈልግም ። ሞትን ለማሰብ ባንፈልግም ሞት ሁሌም አብሮን ይጓዛል ፡፡ መሞታችንን ሳናምንም ወደመቃብር  እንወርዳለን ፡፡ አብዛኞቻችን ከሰው ይልቅ ለቁስ ትልቅ ክብር በመስጠት እየኖርን ነው ሞት በድንገት የሚወስደን ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ቅራኔን መፍታት በብልሃት፣ (ከጆቢር ሔይኢ)

“…ሰው ሞኝ ነው ተላላ፣ይጨነቃል ለሀብቱ— ነገ ትቶት ለሚሄደው  ወደ ማይቀረው ሞቱ። “ የሚባለውም ለዚህ ይመስላል ፡፡

ሰው ልጅ አበክሮ  መጨነቅ የሚገባው ፣ለሀብቱ ሳይሆን ከሱ ሞት በኋላ ሀብትና ንብረቱን ለሚረከበው ትውልድ መሆን ነበረበት ። ትውልዱ የሱን ንብረትና ሀብት ከነበረው አልቆ የማያስቀጥል ከሆነ ልፋቱ ከንቱ ፣ ከንቱና የከንቱ ከንቱ ነው ፡፡ ባክኖ ነው የሚቀረው ። የሰው ደም፣እንባና ሰቆቃን በውሥጡ ያከማቸ የግፍ ሀብት ከሆነ ። ትውልዱም የሀብቱን ምንጪ  ሥለሚያውቅ ለዛ ሀብት ና ንብረት ደንታ ቢስ ነው የሚሆነው ፡፡ ሀብቱና ንብረቱም   የኋላ፣የኋላ ላለፋበት ባዳ ሰው  ሲሳይ ሆኖ ያርፈዋል ።

እናም   ሰዎች ሆይ አንዘናጋ ፡፡   ህይወት አጭር ናት ። በዚች አጭር ህይወት ፣የግፍ፣የሥርቆት ና የዘረፋ ሐብት ፣በማከማቸት ለልጆቻችን መከራን አናውርሳቸው ። … ህይወት  እንደ ጠዋት  ጀምበር   ፈንጥቃ ፡፡ በረፋድ ሞቃ ፡፡ በቀትር ደምቃ ። በማታ አዘቅዝቃ ። በመጨረሻም በጨለማ ተውጣ ፤ አካላዊውን  ሥጋ በምድር ጥላ  ፣ በነፍሥ ተመስላ ወደ ሠማያዊው ሠማይ ትነጉዳለች  ። እንደ እምነታችን ፡፡

 የጀንበር ጉዞ  ህይወት

ያ -የጀንበሪቱ፣የስርቀት ውበት

ያፈዘኛል ያ -ልዩው ፍካት

የከሰል ፍም አይነት…

ልብን የሚያሞቅ ድምቀት ፡፡

—————————— ይመስጣል

የማታ ጀንበር ውበትዋ

ስትጠልቅ የምናስተውለው ..

ደም ግባትዋ ፡፡

ህሊናን የሚያሸፍተው …

ማራኪ ብርሃኗ …

እንድናያት ግድ የሚለን …

ወርቃማ ጨረሯ ፡፡

” የአትሸኙኝም ወይ? “ የማታ ግብዣዋ ፡፡

የታጀበው በውብ ፈገግታዋ ፡፡…

ፍዝዝ አድርጎኝ እባባለሁ

በሀሳብ ባህርም  እመሰጣለሁ ።

በጀምበር ውስጥም ጠልቄ እገባለሁ ።

ለአፍታ ከሥጋዬ አለያለሁ ።

ህይወት እንደዚች ጀምበር ናት እላለሁ ።

 

………………………………………..

“ጀንበር ለእኛ ብርሀኗን ስትነፍገን

ለሌሎች ደግሞ እንደምታበራ

ህይወትም ከህይወት ተጎዳኝታ

ሌላ ህይወት እንደምታፈራ

እንዲሁ ነው……….

እዛኛው ቤት ፣ ልጅ ሲወለድ

እዚህኛው ቤት ፣ እናት ሞታ …

እዚህኛው ቤት ፣ የሠርግ ድግስ …

እዛኛው ቤት ፣ ለቅሶ እሪታ…

እዚኛው ቤት ፣ እፍኝ ቆሎ

እዛኛው ቤት ትልቅ ቅልጥም

ሁሌ ቡፌ…”ዶሮ ፋንታ ! “

ህይወት ሁሌም እንዲሁ ነች …

በተቃራኒ እውነታ የተሞላች ፡፡

እስቲ ለአንድ አፍታ ፣ እናስተውላት

ለደቂቃ ቆም ብለን ፣ እንመልከታት ፡፡

” ሞትና  – ህይወት …… ”

የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ !

በጨለማና በብርሃን ይመሰላሉ

በተቃራኒ እውነታ !

ጨለማን ማንም አይወደውም

ተንኮልና ሸርን መጠንሰሻ…

በመሆኑ የሞት ጓዳ ፡፡

በጨለማ ተሸሽጎ እኮ ነው …

ሰው ለጥፋት የሚሰናዳ ፡፡

እርግጥ ነው ፡፡ …

ሰው ጨለማ ለብሶ አምሳያውን ቢያጠፋ

እርሱም ፀሐይ ሳትጠልቅ ነው ፤

በአፍጢሙ  የሚደፋ ፡፡

ሰው ቢያልም በግፍ ለመክበር

ህይወቱ  እንደሆን አጭር ናት

ከጀንበር ፍንጥቀት –እሥከሥርቀት

አጭር  የዝንጋታ ፤ የጉዞ ፍታት ።

በሐዘን፣ በደስታ ፤ በፍቅርና በጥላቻ…

ደምቃ የምናያት ።

ከፀሐይ ፍንጥቀት እስከ ሥርቀት …

ጧት ተጥዳ ፣ ማታ የምታከትም ናት ።

የኛዋ ህይወት ፡፡

አንድ ቀን እኮ  ናት  የኛ ህይወት

ጣፋጭ ሆና ሥቃይ ያየለባት ፡፡

የቀዝቃዛ ፣የለብታ፣ የግለት …

የሞቅታ ፣ የስከነት …

የሥክነት ፤ የእረጋታ ፤ የአንቅልፍ ፤ የእፎይታ ፡፡

እንደዛች ጀንበር ፣አጭር ጉዘት ፤

ከጎህ መቅደድ ፣ እሰከ ጀንበር ሥርቀት ፡፡

 

1983  ( በደሌ _ ኢሉባቦር )

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share