ፀሀይ ውጪ ውጪ! – ገለታው ዘለቀ

ጎህ ሳይቀድ ማለዳ የአማሮች መርዶ

ጎህ ሳይቀድ ማለዳ የትግራዋይ መርዶ

ደግሞ ማልዶ ማልዶ የኦሮሞ መርዶ

ደግሞ ማልዶ ማልዶ የኮንሶዎች መርዶ

ደግሞ ማልዶ ማልዶ ያገሬ ልጅ መርዶ

አዘን ደረበባት ኢትዮጵያ አይኗ ጠፋ

ልቧ ተሰበረ ውሰጥ አንጀቷ ከፋ

በቃ በይ እባክሽ ፀሀይ ውጪ ውጪ

የመልካሙን ዜና እቅፍ ነዶ አምጪ

ጎህ ቅደጂ ፀሀይ አ’ዋፍት አሰማሪ

የደስታን ዜና የሰላም አዝማሪ

ማልዶ መርዶ ቀርቶ የሀሴት ሆኖለት

አበሻ በሙሉ እንጀራ ይውጣለት….. ሰላም ይሁንለት…. ደሰታ ይሁንለት…..

እባክሽን ፀሀይ ዛሬ ለታ ውጪ

እባክሸን ፀሀይ

እባክሽ እባከሸ

እባክሽን ሰልሽ?

ሀምሌ 7 ቀን 2014

ገለታው ዘለቀ

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኮሽታ (ዘ-ጌርሣም)

1 Comment

  1. ወንድሜ ገለታው – የችግራችን ሁሉ ምንጭ እኛው ነን። የ3 ሺህ ዓመት ታሪክ አለን እያለን የአንድ ቀን ሰላም የሌለን። በሃበሻዋ ምድር ስቃይና ሰቆቃ የሚያየው ሰው ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮም ጭምር ነው። የቤትና የድር አራዊቶች ሁሉ በእኛ ጭካኔ ተጨፍጭፈዋል። አሁንም ጫካዎች ሳይቀሩ በመመንጠር ላይ ናቸው። ለዚያም ነው በወሎ፤ በጎንደር፤ በሽዋና በአፋር የወያኔ አጥፊ ሃይል እንስሳትን ሳይቀር አርዶ የበላውን በልቶ ሌሎችን በጥይት የገደላቸው። በመሰረቱ የታህሳስ ግርግር እየተባለ ከሚጠራው መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ክሽፈት እንኳን ብንነሳ በጣሊያን ወረራ ለሃገራቸው የተዋደቁትን አንድ ላይ ሰብስቦ በመትረጌስ የፈጀ ሃይል ነው ለውጥ ይሻ የነበረው። ከዚያ በህዋላ የሆነውን ሁሉ እዚህ ላይ መጥቀሱ አላስፈላጊ ነው። ግን በነጮቹ የዘመን መቁጠሪያ በ1980 ስንዴ ስትመጸወት የነበረች ሃገር ዛሬም በሰሜን፤ በደቡብ፤ በምስራቅና ምዕራብ የድረሱልኝ ኡኡታ የሚያሰሙት አርሰው መብላት ጠፍቷቸው ሳይሆን የጠበንጃ አንጋቾች ሃበሳ በሚያደርስባቸው ገመና እንደሆነ ቁልጭ ብሎ ይታየናል። ጉዳዪ የጸሃይ መውጣትና መግባት ሳይሆን በወጣው ጸሃይና በዘነበው ዝንብ በሰላም አርሶ ለመኖር ህዝባችን አለመቻሉ ነው። ነፍጥ (ጠበንጃ) ማንገትና ሰውን ማንገላታትና መዝረፍ እንደ መኖሪያ ብልሃት በሚቆጠርባት ምድር ላይ ማን በልቶ ማን ተርቦ እንደሚያድር ህዝባችን ጠንቅቆ ያውቃል። ይህን ዘመን አመጣሽ የብሄር ሽንሸናውን ገደል ግፋውና እንዳለ ሃገሪቱን በአንክሮ ለተመለከተ ባርነት እንጂ ነጻነት አይታይባትም። ትላንት የታሰረው በዛሬ የብልጽግና (የድህነት) መንግስት ዞሮ የሚታሰርባት፤ የሚገረፍባት፤ የሚሰወርባት ሃገር ላይ ነገን አስቦ ለመኖር ያስቸግራል። በትግራይ ለ 50 ዓመታት ጠፍሮ የያዘው የወያኔ ሃርነት (ባርነት) ትግራይ አገዛዝ መላ ኢትዮጵያን ለ 30 ዓመት ገደማ ከገዛ በህዋላ ይኸው እንሆ ዛሬ ትግራይም ሌላ ሃገር ነኝ እያለች ኑና ግጠሙኝ እናሳያችሁ ጀግንነታችን ማለታቸው እላፊ ነገር እንጂ ጤነኛ ጭንቅላት ያለው በተራቆተ ህዝብ መካከል ቆሞ አይፎክርም። ለዚህም ነው የመከራችን ሁሉ ምንጩ እኛው ነን የምለው።
    ጊዜው ቆየ እንጂ አንድ መጽሃፍ አንብቤ ነበር። ጸሃፊው Blair Thomson ሲሆን የመጽሃፉ አርዕስት Ethiopia: The Country That Cut Off Its Head: A Diary Of The Revolution ካላነበብከው ፈልገህ አንብበው። ህይወት ስንክ ሳሯ የበዛ ነው። እንደ ሃበሻው አይነት ፓለቲካ ግን በማንም ምድር ላይ የለም። ቅድመ አያት፤ አያት፤ ወላጆችና ልጆችን ሲያስለቅስ የሚኖር የገማ ፓለቲካ። ዛሬ ያለችውን ደቡብ አፍሪቃ ማንዴላ በህይወት ኑሮ ቢመለከት ምን ይል ይሆን? ያኔ በአፓርታይድ ጊዜ አይዞአቹሁ በማለት የረዷቸውን ሃገር ዜጎች ነው ዛሬ የደቡብ አፍሪቃ ጥቁሮች እያደኑ የሚገድሉት። እውቁ ገጣሚ ጸጋዬ ገ/መድህን እሳት ወይ አበባ በተሰኘው መጽሃፉ ላይ እንደሚያመላክተን ሚስጢሩ “እኔ ለእኔ ኑሬ አላውቅም” ነው። ሁሌ አቤቱታ፤ ሁሌ ኡኡታ፤ መቼ ይሆን በራስ አስበን፤ ለራስ ቆመን፤ ለብሄራችን ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች መብትና ነጻነት ከሃገር አልፈን በአህጉርና በዓለም ላይ ድምጻችን የምናሰማው? ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ የሆኑትን ጋዜጠኞች፤ ጸሃፊዎችና ገጣሚዎች በምታፍንና በምትገርፍ ሃገር ውስጥ የሚቀጥለውን የፓለቲካ ምዕራፍ ለማየት ቢያስቸግርም ያዘው ጥለፈው በለው ማለቱ ይቀጥላል። በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share