መንደርደርያ
የአማራ ሕዝብ ቤዛ ፋኖ፣ የአማራን ሕልውና ለማስቀጠል ከኦነግና ከወያኔ ጋር የሞት ሽረት ትግል እያደረገ ይገኛል፡፡ በዚህ የሞት ሽረት ትግል ላይ ደግሞ ሁሉም ፋኖ አማራ ሁሉም አማራ ፋኖ በመሆን እንደክሂሎቱ የበኩሉን ተጋድሎ ማድረግ አለበት፡፡ ከነዚህም ተጋድሎወች ውስጥ ደግሞ አንዱና ዋናው የአማራን ሕዝብ ተፈጥሯዊ የጦርነት ጥበብ በጦርነት ሳይንስ ማዳበር ነው፡፡ (ሁሉም ፋኖ አማራ ያልኩት ለወያኔና ለኦነግ አማራ ብቻውን ከበቂ በላይ ስለሆነ እንጅ፣ የነ ክቡር ታዴወስ ታንቱን ታላቅ አርበኝነት ዘንግቸው አይደለም፡፡)
ጎጠኛው መለስ ዜናዊ አገር ወዳድ ጦቢያውያንን ከመከላከያ አመራር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አስወግዶ በወያኔወች ተካቸው፡፡ ወያኔወችን ውጭ አገር ድረስ እየላከ በከፍተኛ ወጭ ከፍተኛ ወታደራዊ ትምህርት እንዲማሩ በማድረግ ወታደራዊ ክሂሎትን የወያኔወችና የወያኔወች ብቻ ለማድረግ የተቻለውን ያህል ጣረ፡፡ ለማስመሰል ያህል ደግሞ ወታደራዊ እውቀታቸው መናኛ የሆኑትን፣ እነ ባጫ ደበሌንና አበባው ታደሰን የመሳሰሉትን ሆዳደሮች በጀነራልነት እያንበሸበሸ፣ አልትግሬወችን (ትግሬ ያልሆኑ ጦቢያውያንን) በመደለል ለማታለል ሞከረ፡፡ እነ ጀነራል ተፈራ ማሞንና አሳምነው ጽጌን ደግሞ ዓለም በቃኝ አጎረ፡፡ ኦነጋዊው ዐብይ አሕመድ ደግሞ የነፍስ አባቱ መለስ ዜናዊ ያደረገውን እጅግ በከፋ ሁኔታ በማድረግ የአማራ ሕዝብ ወታደራዊ መሪ እንዳይኖረው የተቻለውን ያህል አደረገ፣ ጀነራል አሳምነውን ገደለ፣ ጀነራል ተፈራን አፈነ፡፡
የአማራ ሕዝብ ግን ካብናቶቹ (ማለትም ካባቶቹና ከእናቶቹ፣ forebears) ሲወርድ ሲዋረድ በቀሰመው፣ ባያሌ የጦር አውድማወች ላይ ተፈትኖ ፍቱንነቱን ባስመሰከረ፣ አድዋን ጨምሮ አያሌ አሸብራቂ ድሎችን ባጎናጸፈ ዘመን ጠገብ አራት ማዕዘናዊ የጦርነት ጥበብ (ፊታውራሪ፣ ጃዝማች፣ ግራዝማች፣ ደጀን) የተካነ ነፍጠኛ ነው፡:
ፊታውራሪው ጠላትን በግንባርጌ እንደ ተርብ እየተወረወረ ሲነድፈው፣ ቀኛዝማቹና ግራዝማቹ ደግሞ በቀኝጌና በግራጌ እየተገተጉ መፈናፈኛ ያሳጡታል፡፡ የደጃዝማቹ ሚና ውጊያውን ማስተናበር ሲሆን፣ የደጀኑ ሚና ደግሞ ፊታውራሪውን፣ ቀኛዝማቹንና ግራዝማቹን ለመርዳት የደጃዝማቹን ሚና በተጠንቀቅ መጠባበቅ ነው፡፡
ነፍጠኛው የአማራ ሕዝብ በነፍጠኛነቱ የተካነውን የጦርነት ጥበብ በሌሎች አገሮች (በተለይም ደግሞ በቻይናና በሩሲያ) የጦርነት ጥበቦች ካዳበረው፣ ማናቸውንም ጦርነት ባሸናፊነት የመወጣት እድሉ ከፍተኛ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡ የቻይናው የጦርነት ሊቅ ሰንሹ (Sun Tzu) የጦርነት ጥበብ (Art of War) በተሰኘው ድንቅ መጽሐፉ ላይ በስፋት እንዳብራራው ደግሞ፣ የጦርነትን ጥበብ የተካነ፣ ትጥቁ እጅግም የሆነ ሠራዊት፣ እስካፍንጫው የታጠቀን ሠራዊት በቀላሉ ድል እንደሚመታ ነው፡፡ የዚህ ጦማር ዓላማ ደግሞ ከሰንሹ የጦርነት መርሖች ውስጥ አንዱ የሆነውን የማጥቃትና የመከላከል መርሕ መዘርዘር ነው፡፡
የኦነግ ሠራዊት ጨለማን ተገን አድርጎ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉትን ሕጻናትን፣ አረጋውያንና ደካሞችን ከማረድ በስተቀር፣ በዕድሜ ዘመኑ አንድም ቀን ድል ማድረግ ቀርቶ በቅጡ ተዋግቶ የማያውቅ፣ በትንሽ ብትር የሚንኮታኮት እንኩቶ፣ በፍንጥቅ እሳት ዐመድ የሚሆን ገለባ ሠራዊት ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን ጠላት አይናቅምና ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ባልተጠነቀቀበት ቦታ ላይ በድንገት ከተፍ ብሎ መከታተፍ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም ደግሞ ማንም አይነካኝም ብሎ በመተማመን ተኮፍሶ በሚንጎባለልበት ቦታ ላይ ቅንብቻውን ማስተንፈስ የግድ ነው፡፡ የዐብይ አሕመድ ጃንደረባወች ተመስገን ጡሩነህና ደመቀ መኮንን የሚያሰማሯቸውን የአማራ ለምድ የለበሱ ብአዴናዊ የመስመር መኮንኖች በማስወገድ፣ የዐብይ አሕመድን የግንኙነት መስመሩን መበጣጠስ ይዋል ይደር መባል የለበትም፡፡ የሰንሹ ትምህርት የሚያስተምረውም ይህንኑ ነው፡፡
የሰንሹ የማጥቃትና የመከላከል መርሖች
ድል ማድረግ በራስ ሁኔታ፣ ድል መደረግ ደግሞ በጠላት ሁኔታ ይወሰናል፡፡ ስለዚህም ጠቢብ የጦር አዛዥ በራሱ በኩል ሊያከናውናቸው የሚገባውን ሁሉ በጥንቃቄ አከናውኖ አመችውን ጊዜ ነቅቶና ተግቶ በትእግስት ይጠባበቃል፡፡ ታላቆቹ ጦረኞች ትዕግስትና ጊዜ ናቸው፡፡ ጊዜ የሰጠው ቅል ዲንጋ ይሰብራል፡፡
ኢተረችነት በመከላከል ችሎታ፣ ረችነት በማጥቃት ችሎታ ይወሰናል፡፡ ጠላት ሲበረታ ተከላከል፣ ሲደክም አጥቃ፡፡
ጠቢብ የጦር አዛዥ የሚያጠቃው መጠቃት ያለበትን እንጅ ለማጥቃት ሲል አያጠቃም፡፡
ጠቢብ የጦር አዛዥ የሚከላከለው መካላከል ያለበትን እንጅ ለመከላከል ሲል አይከላከልም፡፡
ጠቢብ የጦር አዛዥ ሲያጠቃ የሚከላከል፣ ሲከላከል የሚያጠቃ ያስመስላል፡፡
ጠቢብ የጦር አዛዥ ሲያስፈልግ እንደ እሳተ ገሞራ ከምድር ይፈነዳል፣ ሲያስፈልግ ደግሞ እንደ መብረቅ ከሰማይ ይበርቃል፡፡
ጠቢብ የጦር አዛዥ ሲያስፈልግ እንደ ንፋስ ይፈጥናል፣ ሲያስፈልግ ደግሞ እንደ ተራራ ይቆማል፡፡
ጠላት ሲረጋጋ ባሉባልታ አሸብረው፣ ሲያርፍ በትንኮሳ አዋክበው፡፡ ካጋም እንተጠጋ ቁልቋል ረፍት እየነሳህ፣ እዚህም እዚያም እየበሳሳህ፣ ዘላለም አስለቅሰው፡፡
ጠላትህ ትይዝብኛለህ ብሎ የማያስበውን፣ ከያዝክበት ደግሞ ባስቸኳይ ሊያስለቅቅህ የግድ የሚያስፈልገውን ቦታ ሳይስበው በድንገት ያዝበትና ሥራህን ቶሎ ሠራርተህ ሳያስበው በድንገት በመውጣት ትሄድበታለህ ብሎ በማያስበው መንገድ ትሄድበታለህ ብሎ ወደማይገምተው ቦታ በፍጥነት ሂድ፡፡
እንደ መብረቅ በድንገት በርቀህ እንደ አውሎ ንፋስ በድንገት ንፈስ ፡፡ መብረቅ ድንገት ይበርቃል እንጅ ከየት በኩል እንደሚበርቅ አይታወቅም፡፡ አውሎ ንፋስ በድንገት ይነፍሳል እንጅ ከወዴት እንደሚነፍስ አስቀድሞ አይታወቅም፡፡ ሲበርቅ ቢጨፍኑ ከመወጋት አይድኑ፡፡
ጠንካራ ስትሆን ደካማ፣ ደካማ ስትሆን ጠንካራ፣ ሩቅ ስትሆን ቅርብ፣ ቅርብ ስትሆን ሩቅ፣ ዝግጁ ስትሆን አልዝግጁ፣ አልዝግጁ ስትሆን ዝግጁ መስለህ ለጠላትህ ታይ፡፡ ጠላትህን እንቁ አሳይተህ እነቀው፡፡ ሲጠናከር ሽሸው፣ ሲዳከም ተጋፈጠው፡፡ በግንባርህ ሲመጣብህ በጀርባው፣ በቀኝህ ሲመጣብህ በግራው እየተዟዟርክ አዋክበው፡፡ አወይ አተኳኮስ ወይ ደፋር መሆን፣ ሲሄድ መቀለቻ ሲዞር ግንባሩን፡፡
ማጥቃትህ ስኬታማ እንደሚሆን እርግጠኛ ልትሆን የምትችለው ጠላትህ የማይከላከለውን ስታጠቃ ብቻ ነው፡፡ መከላከልህ ስኬታማ እንደሚሆን እርግጠኛ መሆን የምትችለው ጠላትህ የማያጠቃውን ስትከላከል ብቻ ነው፡፡ በማጥቃት የተካነውን መከላከል፣ በመከላከል የተካነውን ማጥቃት ትርፉ ትልቅ ሽንፈት ነው፡፡
መስፍን አረጋ