የወልቃይት ስትራቴጅክ ጠቀሜታ – የተከዜ ዘቦች


በዚህ ትንታኔ ለአንባቢን መሰረታዊ ግንዛቤ ያመች ዘንድ ‹ወልቃይት› እያልን የምንጠራው አካባቢ ጠገዴንና ሰቲት ሁመራን ያካትታል፡፡ በዚህ ቀጠና እንደአማራ ቀዳሚ ፍላጎታችን የተነጠቀ ማንነታችንን ማስመለስ ሲሆን፤ አማራ በመሆናቸው ብቻ በትህነግ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸምባቸው የኖሩ ወገኖቻችን ከቀጥተኛ የህልውና አደጋ ተጋላጭነት ነጻ ማድረግ፣ እንዲጠፋ ሲሰራበት የኖረውን አማራዊ ማንነታቸው ዳግም አብቦ፣ የተጎዳ ስነ-ልቦናቸው ተጠግኖ አማራዊ የአስተዳደር ነጻነታቸው እውን ሁኖ ማየትና ለሠላሳ ዓመታት ለተፈጸመው ግፍና በደል የፍትሕና የካሳ ጥያቄ ያለን መሆኑ እንደተጠበቀ ሁኖ፤ በዚህ ጽሁፍ የአካባቢውን ስትራቴጅካዊ ጠቀሜታ እንመለከታለን፡፡

ጉዳዩ ከርስት በላይ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉአላዊነት የማስጠበቅ ጉዳይ ስለመሆኑ በማስረጃዎች እንፈትሻለን፡፡ ወልቃይት የቀጣናዊ ፖለቲካዊ መስፈንጠሪያ ማዕከል እና የብሔራዊ ደህንነታችን አስኳል ስለመሆኗ በዝርዝር እንመለከታለን፡፡

የወልቃይት ጉዳይ፣ ተለዋዋጭ የሆነውን የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካን የመወሰን አቅም አለው፡፡ ትልቁ ጉልበቱ ለጂኦ-ፖለቲክሱ ያለው ጠቀሜታ ነው፡፡ የተከዜ-አጥባራ ንዑስ ተፋሰስ ድንበሮች ይህን አካባቢ በሰፊው ያካልላሉ፡፡ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሱዳን በዚህ ተፋሰስ በርካታ ከተሞቻቸውን ያደርሳሉ፡፡ ዋናው መነሻና ማዕከሉ ግን ወልቃይት ነው፡፡ በሰብል ምርት አቅሙ የአፍሪካን የግብርና ታሪክ የቀየረ አካባቢ ስለመሆኑ ምሁራን በጥናቶቻቸው መስክረዋል፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን፣ የኢትዮጵያን ግብርና ልማት ለማምጣት ሲካሄድ ከነበረው ጥረት አንዱ ‹Comprehensive Package Project (CPP)› የተሰኘው ፕሮጀክት ነበር፡፡ ይህ ፕሮጀክት በተመረጡ የኢትዮጵያ ለም አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ የግብርና ልማት ሥራን በማከናወንና ትርፍ እህል በማምረት በምግብ እህል ራስን መቻል፣ ለውጭ ንግድ ማቅረብና   ለሌላው መማርያ መሆን በሚል ዓላማ የተጀመረ ነበር፡፡

እነዚህ የልማት ፕሮጀክቶች በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እንዲካሄዱ ከተመረጠበት ቦታ አንዱ የበጌምድሩ ሁመራ (Humera Agricultural Devt Unit)፤ በዛሬዋ ኤርትራ ጋሽ ባርካና ታህታይ አዲያቦ  (GBADU, TARDU) ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከፍተኛ የሆነ የመንግሥት ና የብድር ገንዘብ ወጭ ተደርጎበት ሲካሄድ የነበረው የግብርና ልማት ፕሮጀክት  አንዱና ዋነኛው የወልቃይት ሁመራ ፕሮጀክት  ነበር፡፡ በዚህ ፕሮጀክት የተነሳ ነበር የአፍሪካን የግብርና ታሪክ የቀየረ ሰፊ ምርት ማግኘት የተጀመረው፡፡ ይህ እንድምታ በነጻነት ራሷን ችላ በቆመች ሀገር፣ በመኪና (ትራክተር) በማረስ የሰፊ ግብርና ምርት ባለቤት የመሆን ተምሳሌት ለሆነችው ኢትዮጵያ ወልቃይት ትልቅ የግብርና አቅም ሊሆናት ችሏል፡፡

ከዚህ የምርት አቅሙ በተጨማሪ ወደጎረቤት ሀገር ሱዳን ለመሻገር ወሰኝ አካባቢ በመሆኑ ከዘውዳዊው ሥርዓት ማክተም በኋላ በአካባቢው መንቀሳቀስ የጀመሩ ኃይሎች ዐይናቸውን ሲጥሉበት ታይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኀብረት (EDU)  በተቀናጀ ሁኔታ ትግል ሲጀምር ወልቃይትን የትኩረት ማዕከሉ ለማድረግ ሞክሯል፡፡ አንድም አካባቢው ሰፋፊ የእርሻ ልማት ያለበት በመሆኑ ከመንግሥታዊ ኃይሎች የዕለት ተዕለት ቁጥጥር አንጻራዊ ነጻነት ለማግኘት፤ አንድም ደግሞ ከጎረቤት ሀገር ሱዳን ድጋፍ ለማግኘት ወሳኝ ስትራቴጅካዊ ቦታ በመሆኑ ወልቃይትን መርጧል፡፡ በዚህም ከወቅቱ የሱዳን (ኒሜሪ) መንግሥት የሎጀስቲክስ ድጋፍ ለማግኘት አግዟቸዋል፡፡ በወቅቱ ሱዳን ውስጥ የሬዲዮ ጣቢያና የካድሬ ትምህርት ቤት ከፍተው ማስተማር የቻሉት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኀብረት አመራሮች፣ ወልቃይት ዋና መንቀሳቀሻው እንደነበረ የዘመኑ ወታደራዊና አብዮታዊ ታሪክ ጥናቶች  (John Young 1997, Christopher Clapham 1998) ያመለክታሉ፡፡

ከኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኀብረት (EDU) መዳከም በኋላ ደግሞ የግዛት ተስፋፊው ትህነግ አካባቢውን ለመቆጣጠር ብርቱ ጥረት አድርጓል፡፡ በተለይም ከሱዳን ድጋፍ ለማግኘት ተከዜን መሻገርና አካባቢውን መቆጣጠር የግድ አስፈላጊ ሁኖ ስላገኘው ትግሉን የሞት ሽረት ለማድረግ ተገድዷል፡፡ ከ1972 ዓ.ም እስከ 1976 ዓ.ም ባሉት አመታት ውስጥ ትህነግ ከደርግ ጋር ስያካሂድ በነበረው ጦርነት ምክንያት አካባቢውን በቁጥጥር ስር ቢያደርገውም፣ የወልቃይት አማራ ግን አልተቀበለውም ነበር፡፡ በወቅቱ ሕዝብ ከማስተዳደር ይልቅ ወደሱዳን መመላለሻ ኮሪደሩን ለወታደራዊ ዓላማ መጠቀም የመረጠው ትህነግ የደርግን ወታደራዊ ውድቀት ወደዕድል ለመቀየር አካባቢውን ተጠቅሞበታል፡፡ በመጨረሻም ከደርግ መንግሥት ውድቀት በኃላ በ1984 ዓ.ም. ህጋዊ ባልሆነ መንገድ፣ ያለሕዝቡ ይሁንታ ወልቃይትን የትግራይ አካል አደረገው፡፡ ይሄም ማለት አሁን በስራ ላይ ያለው የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ከመጽደቁና ሥራ ላይ ከመዋሉ ከሦስት ዓመት በፊት መሆኑ ነው፡፡

እዚህ ላይ ዛሬም እንደገና መነሳት ያለበትና በደንብ ሊታይ የሚገባው አንድ መሰረታዊ ነገር አለ፡፡ ይሄውም ‹ትህነግ በታሪክ የትግራይ አካል ሁኖ የማያውቀውን ‹ወልቃይት› ከ (በጌምድር-ጎንደር) አማራ ህዝብ በጉልበት ነጥቆ ለምን የትግራይ አካል አድርጎ መቀጠል ፈለገ?› የሚለው ነው፡፡ በመግቢያችን ላይ እንደተመለከትነው ጉዳዩ በዋናነት ከጂኦ-ፖለቲካው ጋር ይገናኛል፡፡

እንደሀገርም ሆነ እንደሕዝብ ከተጋረጠብን አደጋ አኳያ በዚህ ጉዳይ ላይ የጠራ ግንዛቤ ለመፍጠር ወሳኙን አጀንዳ ደግሞ ደጋግሞ ማጤንና ማስታወስ አስፈላጊ ሁኖ አግንተነዋል፡፡ ስለሆነም ትህነግ የወልቃይትን ጉዳይ የሞት ሽረት ትግል ያደረገባቸውን አራት ዋነኛ ምክንያቶች ተለይተው እንደሚከተለው ቀርበዋል፡-

  1. ወልቃይትን የትግራይ አካል ማድረግ፤ ኢትዮጵያን በተለይም አማራን የማዳከም አንዱና ዋነኛው የትህነግ ስትራቴጅ ሁኖ መገኘቱ ቀዳሚው ምክንያት ነው!

መላው የአማራ ህዝብ እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍ ሲል ደግሞ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደሚያውቀው፤ ትህነግ የኢትዮጵያና የአማራ ህዝብ ቀንደኛ ጠላት ነው፡፡ ትህነግ ኢትዮጵያን በመበተን ‹ታላቋ ትግራይ›ን ለመመስረት አቅዶ የተነሳና ዛሬም ድረስ በዚሁ መርህ እየተመራ ያለ ጸረ-ኢትዮጵያ ኃይል ነው፡፡ በተለይም ደግሞ አማራን በቀዳሚ ጠላትነት ፈርጆ የተነሳና የታገለ፤ በተግባርም ዓላማውን ለመፈጸም ብዙ ርቀት የተጓዘ፣ ዛሬም ግማሽ አካሉ መቃብር በወረደበት በዚህ ዘመን ከቀደሙት ጥፋቶቹ ሳይታረም በአውዳሚ መስመሩ ላይ የቆመ ድርጅት ነው፡፡ ስለሆነም ሁሌም ቢሆን የተዳከመች ኢትዮጵያንና አማራን ማየት የትህነጋዊያን ያደረና ዛሬም ያለ ህልም ነው፡፡ የትሕነግ ስሌት እጅግ በተዳከመችና በተከፋፈለች ኢትዮጵያ፤ ግዛቱን አጥቶ በተበታተነው አማራ መቃብር ላይ ‹የታላቋ ትግራይ ሪፐብሊክ አጀንዳችንን እውን እናደርጋለን› የሚል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያን ማዳከም፤ አማራውን መበተን የግቡ ማሳለጫ መንገድ አድርጎ ቆጥሮታል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግስት አንኳር ስህተቶች - አንድነት ይልቃል

የወልቃይት ጂኦ-ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ኢትዮጵያ በቀጠናው ላይ ለሚኖራት የበላይት እጅግ ወሳኝ ስትራቴጅካዊ አካባቢ ሲሆን፤ ለአማራ ህዝብ ደግሞ ሁለመናው ናት፡፡ ትህነግ ይህን በሚገባ ከተገነዘበ ውሎ አድሯል፡፡ ‹ወልቃይት ለአማራ ህዝብ ሁለመናው ናት› ስንል እንዲሁ ሳይሆን፤ እጅግ ዘርፈ ብዙ አገራዊና ክልላዊ ፋይዳ ያላት ከመሆኑም በላይ ለአማራ ህዝብ የማንነቱ መገለጫውና ኩራቱም በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ ስለሆነም ወልቃይትን ከአማራ መንጠቅ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአማራ ህዝብ ጉዳቱ ከፍተኛ ሲሆን፤ ለትህነጋዊያን ደግሞ የደደቢት ቅዠታቸው የሆነውን ‹ታላቋ ትግራይ›ን እንዲመሰርቱ ትልቁን በር ይከፍትላቸዋል፡፡ ለዚህ ነው ትህነጋዊያን ወልቃይትን የሞት ሽረት ጉዳይ አድርገው የሚመለከቱት፡፡

  1. ትህነግወልቃይትና አካባቢውን ዳግም በመቆጣጠር ኢትዮጵያንና አማራን ለማዳከም ሌላ እድል ያገኝበታል!

ትህነግ ወልቃይትን በመቆጣጠር ከሱዳን ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር፤ ያልተገደበና በራሱ የሚመራ የውጭ ግንኙነት በመፍጠር፤ አገር የመሆን ህልሙን እውን ለማድረግ ይጠቀምበታል፡፡ ከሱዳን ወታደራዊ ኃይል ጋር በመሻረክ ከሁመራ እስከ ቤንሻንጉል ያለውን የኢትዮጵያ መሬት የመቀራመት ፍላጎት እንዳለው በሀገር ክህደት ተግባራቱ አሳይቶናል፡፡ በተጨማሪም በአባይ ውሃ ጉዳይ የኢትዮጵያ ባላንጣ የሆነችውን ግብጽን ለሀገራዊ ቀውስና ብጥብጥ እጇን በሰፊው እንድታስገባ እየመራ ለማምጣት፣ በእነርሱ የመሳሪያ ድጋፍ ማዕከላዊ መንግሥቱንና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን በመውጋት ኢትዮጵያን ወደፍርስራሽነት በመቀየር ግብጽ በአባይ ፖለቲካ የነበራትን የበላይነት በቋሚነት ለማስቀጠል የባንዳነት ተልዕኮውን ለመወጣት፣ በወኪሎቹ በኩል የካይሮን ደጅ ደጋግሞ ረግጧል፡፡ የትህነግ ጭፍራዎች ከግብጽ ሚዲያዎች እኩል ጸረ-ኢትዮጵያ የሆኑ ፕሮፖጋንዳዎችን ሲነዙ የሚውሉት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የጋራ ውል ያላቸው በመሆኑ ነው፡፡

በዚህ ሂደት ትህነጎች ቢሳካላቸው እስከ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ያለውንና በምናብ ካርታቸው ላይ ያሳዩንን መሬት አካተው የ‹‹ታላቋ ትራግይ››ን ምስረታ እውን ሲያደርጉ፤ የሱዳን ወታደራዊ ኃይል ደግሞ ባልተጨበጠ የታሪክ ዳራ እና የሕግ ማዕቀፍ ከኢትዮጵያ ‹‹አለን›› የሚለውን መሬት በቀላሉ ይረከባል፡፡ ምኞታቸው ይህ ነው፡፡ በዚህ የተቀናጀና የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች ባሳተፈ የወረራ ተግባር የተዳከመች ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የተበታተነች ኢትዮጵያ እንድትፈጠር አልመው ይሰራሉ፤ እንደሕዝብ ጨርሶ የሚጠፋ አማራ እንዲኖር ይፈልጋሉ፡፡ በጠቅላላ ሂደቱም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከመኖር ወደአለመኖር በመቀየር የኢትዮጵያ ጠላቶችን ማስደሰት የትህነግ ፍላጎት ስለመሆኑ ገሃድ ወጥቷል፡፡ ለዚህ ስኬት ደግሞ ወልቃይትንና አካባቢውን ዳግም መልሶ መቆጣጠርን የሞት ሽረት ጉዳይ አድርጎታል፡፡

 

  1. ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር እንዳትገናኝ የማድረግ ሴራ!

ትህነግ ኢትዮጵያ በተለይም በአማራ በኩል ከኤርትራ ጋር በድንበር እንዳይገናኝ በማድረግ የኢትዮ- ኤርትራን ግንኙነት ለመገደብ ከመፈለጉም በላይ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ወንድም ሕዝብ ጋር በማህበረ-ኢኮኖሚውም ሆነ በጋራ የጸጥታ ጉዳዮች መልካም መስተጋብር እንዳይኖራት ይፈልጋል፡፡ እንደሚታወቀው ኤርትራዊያን ከትግራይ ልሂቃን ይልቅ ከኢትዮጵያዊያን ጋር በተለይም ደግሞ ከአማራ ጋር የቀረበ ቀረቤታና ፍቅር አላቸው፡፡ ይሄን እውነታ የሚያውቀው ትህነግ ኤርትራዊያን ከመላ ኢትዮጵያዊያን ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳይኖራቸው አድርጎ ቆይቷል፡፡ ይሄ የቆየ የፖለቲካ መሰናክል አሁንም እንዲቀጥል በትህነግ በኩል ብርቱ ፍላጎት አለ፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ ወልቃይት በትህነግ እጅ በጉልበት መልሶ ሲገባ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ወልቃይትን ላለማጣት ትህነግ የሞትሽረት ትግል ማድረጉ ይጠበቃል፤ እየሆነ ያለውም ይሄው ነው፡፡

  1. ወልቃይትለትህነጋዊያን ትልቅ የሀብት ምንጭ፤የገዥ መደብ መሰረት መሆኑ!

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በአንድ በኩል የሀገርን ኢኮኖሚ በሚያቆረቁዝ ደረጃ የኮንትሮ ባንድ ንግዱን በመጠቀም፤ በሌላ በኩል ደግሞ በመቶ ሽህዎች የሚቆጠሩ የወልቃይት አማራ ተወላጆችን በማፈናቀልና ለም መሬታቸውን በመንጠቅ በሰፋፊ የእርሻ ልማት በመሰማራት በርካታ የትህነግ ባለሥልጣናትና ባለሟሎቻቸው የለየላቸው ከበርቴዎች ሁነዋል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ተወላጁ ወልቃይቴ አማራ የበይ ተመልካች ሁኖ ሦስት አስርታትን አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ዘመናት ሲከፋም ዘሩ እንዲጠፋ በጅምላ ተገድሏል፤ ታስሯል፣ ሀገር ለቆ እንዲሰደድ፣ ወደ መሀል ጎንደርና ሌሎች አካባቢዎች በግፍና በገፍ እንዲፈናቀል ተደርጓል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወደለውጥ የማያመራው የትግላችን ጉዞ መሰናክሎች!

ትህነጋዊያን የእነሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ያስችለናል ያሉትን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ ታጋዮቻቸውን በማስታጠቅ እንዲሁም የሰብል ምርት እጥረት ካለበት  የትግራይ አካባቢዎች ያልታጠቁ ሲቪሊያንን በአንድ ላይ በማዋሃድ ከመሀል ትግራይ አምጥተው ወልቃይት ላይ አስፍረዋል፡፡ ይህ የሆነው ግን ተወላጁን አማራ ከኖረበት ቀየው በማፈናቀል ነው፡፡ በዚህ ሂደትም በርካታ የወልቃይት አማራዎች ዘራቸው ሲጠፋ፤ በአንጻሩ በርካታ የትህነግ ባለስልጣናትና የነሱ ጥቅም አስጠባቂዎች በልጽገዋል፡፡ ራሳቸውንም ወደገዥ መደብነት ለመቀየር ወልቃይት የሀብት ኮረቻ፣ የብልጽግና ማማ ሁናቸዋለች፡፡ በዚህም ምክንያት ትህነጋዊያንና ጥቅመኛ ማህበራዊ መሰረቱ ወልቃይትን ማጣት የሞት ያክል ከብዷቸዋል፡፡

 

የውጭ ኃይሎች የጣልቃ ገብነት ፍላጎትና ሴራ

የአለምአቀፉ ማህበረሰብ በዋናነት በጥቂት የምዕራቡ ዓለም ሀገራት የሚዘወሩ ተቋማት ስለምን በወልቃይት ጉዳይ አብዝተው እንደሚጮኹ እንመለከታለን፡፡ የውጭ ኃይሎችን የፖለቲካ ሴራም እንፈትሻለን፡፡

እዚህ ላይ ‹በጥቂቶች የበላይነት የሚዘወሩ አንዳንድ አለማቀፍ ተቋማት እንዲህ በተደጋጋሚ መግለጫ የሚያወጡትና የሚጮኹት ወልቃይት ላይ ምን ጉዳይ ስላላቸው ነው?› ‹የራያና አካባቢውን ጉዳይ ለምን በሁለተኛ ደረጃ አዩት?› የሚል ጥያቄ አንስቶ መመልከት እጅግ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን፡፡

በእኛ እምነት በጥቂት ሀገራት የሚዘወሩ የአለምአቀፉ ማህበረሰብ ተቋማት በወልቃይት ጉዳይ እንዲህ የሚጮኹትና የራያን ጉዳይ በሁለተኛ ደረጃ የሚመለከቱበት ምክንያት፤ እነሱም ልክ እንደ ትህነግ ከወልቃይት ጋር በተያያዘ ስትራቴጅካዊ ፍላጎት ስላላቸው ነው ብለን እናምናለን፡፡ ወልቃይት ኢትዮጵያን ከሱዳን በተለይም ደግሞ ከኤርትራ ጋር ያገናኛል፡፡ ይሄ ሁኔታ ደግሞ የኢትዮ-ኤርትራን ግንኙነት በእጅጉ እንደሚያጠናክረው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

ጥቂት የሚባሉ ግን ደግሞ በነጻ-ሀገራት ላይ ጫና የማሳደር አቅም አለን ብለው የሚያምኑ የምዕራባዊያን ሀገራት የኢትዮ-ኤርትራን የጠነከረ ግንኙነት በበጎ ይመለከቱታል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ከመጀመሪያውም  ‹እኛ በሽምግልና የሌለንበት ዕርቅ እንዴት ይፈጠራል› በሚል በኢትዮ-ኤርትራ ዕርቀ ሠላም እምብዛም ደስተኛ ያልሆኑት አካላት፤ ይህ ግንኙነት እያደር ተቋማዊ ቅርጽ ይዞ ወደኢኮኖሚያዊ ውህደት ካመራ በቀይ-ባህር ፖለቲካና በቀጣናው ላይ ያለንን ተጽዕኖ ያሳጣናል የሚል ስጋት ውስጥ የገቡ ይመስላል፡፡ በዚህ ምክንያት ወልቃይትና አካባቢው በትህነግ አገዛዝ ስር እንዲቆይ አይፈልጉም ማለት አይቻልም፡፡ ፍላጎታቸው ጠባብ የቡድንተኝነት ጥቅሞቹን እያስጠበቀ የብዙሃኑን ኢትዮጵያዊያንና የወንድም የኤርትራ ሕዝብን የጋራ ሁለንተናዊ የብልጽግና ህልም የሚቀብር ተላላኪ ኃይል ዳግም አቅም ፈጥሮ እንዲሰነብት ማድረግ ነው፡፡

ሌላው የእነዚህ የውጭ ኃይሎች ፍላጎት  የግብጽን ፍላጎት ከማሳካት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ የሱዳን ወንድም ሕዝብ መቼም ቢሆን የኢትዮጵያ ጠላት ሊሆን እንደማይችል ነው፡፡ ይሁንና በሥልጣን ጥም የናወዘው ወታደራዊ ኃይል ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ‹‹የመሬት ይገባኛል›› ጉዳዩን በማጦዝና ወደግጭት በመውሰድ በሥልጣን ላይ የመቆየት ፍላጎቶችን አሳይቷል፡፡ ይህ አደገኛ ፍላጎቱ ለወንድም የሱዳን ሕዝብ ችግር ከመሆኑም በላይ የሦስተኛ ወገን ፍላጎት ማስፈጸሚያ ሆኗል፡፡ ይህም ሆኖ ነገ በሱዳን ሕዝባዊ መንግሥት ሲመሰረት ከላይ የተመለከትነውን ስጋት ጨምሮ ሌሎች የተስፋፊነትና ጠብ አጫሪነት ፍላጎቶች ይቀረፋሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በዚህ አጋጣሚም ለወንድም የሱዳን ሕዝብ ወደዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲያመሩ መልካሙን እንመኛለን፡፡

ከውጭ ኃይሎች አደገኛ ፍላጎት አኳያ ዋናው ችግር የሚታየው፤ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ በጋራ ተጠቃሚነት የማያምነውን ግብጽን ለማስደሰት የሚሰሩ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ነው፡፡ እነዚህ የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ትህነግን እንደምርኩዝ ሊጠቀሙ ሲሞክሩ ታይቷል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት በይበልጥ ደግሞ የግድቡ አንደኛ ዙር የውሃ ሙሌት ከመጀመሩ በፊትና በኋላ (2012-2013) ትህነግን በመጠቀም የህዳሴ ግድቡን ለማሰናከል ፍላጎታቸውንና  የእጅ አዙርና ይፋዊ ድጋፋቸውን አሳይተውናል፡፡ አሁን ላይ እነዚህ ጥቂት ግን ደግሞ ተጽዕኖ እንፈጥራለን የሚሉ የውጭ ኃይሎች ትህነግን ለማጠናከር፤ በተለይም የጦር መሳሪያና ሎጅስቲክስ ለማቅረብ ወደ ትግራይ መግቢያ በር ይፈልጋሉ፡፡ ይሄ በር ደግሞ ወልቃይት ነው፡፡

ራያና አካባቢው ለትህነጎች እና ‹አቅመ-ቢስ መንግሥት› (Banana Republic)  የመትከል ፍላጎት ላላቸው ለውጭ ኃይሎች የወልይቃትን ያኽል አስፈላጊና ምቹ ስላልሆነ በሁለተኛ ደረጃ ይዘውታል፡፡ በዚህም ምክንያት የግብጽ ደጋፊ ውስን የምዕራቡ ዓለም ሀገራት ከራያ ይልቅ ወልቃይትን የቅድሚያ ቅድሚያ (Prioritize) ሰጥተው እንታመንለታለን የሚሉትን መርህ ለመጣስ ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ ይህም (የወልቃይት አማራ) ‹[አንድ ሕዝብ] ራሱን በራሱ እንዲያስተዳደር፤ በአፍ መፍቻ ቋንቋው እንዲማር፣ በቋንቋው ችሎት እንዲሰየምለት፣ የቤተ-እምነት አገልጋሎት እንዲያገኝ› የሚያስችለውን መሰረታዊ መብቶቹ ተጨፍልቀው፤ ለትህነግ ተላልፎ እንዲሰጥ ጸረ-ዴሞክራሲና ጸረ-ሉዓላዊነት ዘመቻዎች ላይ ተጠምደዋል፡፡ ይህ ቢሳካላቸው የጦር መሳሪያዎችንና ሌሎች አስፈላጊ የጦርነት ሎጀስቲክሶችን ወደ ትግራይ በማስገባት፣ የተዳከመች ኢትዮጵያን በመፍጠር ቀጣናዊ የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ ይጠቀሙበታል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  እናስራችኋለን? ለካንስ የነአጅሬ ጀግንነት ከድንበርም ተሻግሯልና!

በጠቅላላ ሂደቱ ‹ለእኛ ታዛዥ አልሆነም› ያሉትን የኢትዮጵያ መንግሥት  ከቻሉ በትህነግ በኩል ማስወገድ፤ ካልሆነም አቅመቢስ እንዲሆን ለመድረግ ይሞክራሉ፡፡ ይሄን እኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት ደግሞ ከትህነጎችም በላይ ትህነግ ሆነው ወልቃይት በጸረ-ኢትዮጵያ ኃይሉ (ትህነግ) እጅ ለማስገባት ወሳኝ ስትራቴጅካዊ አጀንዳቸው አድርገው ወስደውታል፡፡

ከአሁናዊ ፖለቲካችን አንጻር ወልቃይት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን እንደ አይን ብሌን ሁኖ መታየት ያለበት ቦታ ነው!

ከፍ ሲል ለማንሳት እንደተሞከረው፤ ትህነጋዊያን እና አሻንጉሊት መንግሥት የመፍጠር ፍላጎት ያላቸው የውጭ ኃይሎች ክሳቸው ከታሪክና ከነባራዊ ሁኔታ የሚመነጭ ሳይሆን፤ ከጊዜዊ ጥቅምና ከጂኦ-ፖለቲክሱ ስትራቴጅካዊ ጠቀሜታ አንጻር ነው፡፡ ለዚህም ነው ወልቃይትን እጅግ አስፈላጊ ቦታ አድርገው የወሰዱት፡፡ እነዚህ የውጭ ኃይሎች ወልቃይት የበጌምድር ታሪካዊ አካል የአማራው ግዛት ስለመሆኑ ባይጠፋቸውም፤ እውነታውን ለመሻር ከፍ ሲል በኢትዮጵያ መንግሥት  ላይ፤ ዝቅ ሲል ደግሞ በአማራ ክልል መንግሥትና ህዝብ ላይ የቻሉትን ያኸል ተጽእኖ ለማድረግ እየሞከሩ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎቻቸውን ደግመው እስካልፈተሹና ከነባራዊው ሁኔታ ጋር አጣጥመው ለመጓዝ እስካልፈለጉ ድረስ (ሩቅ ሊያሻግራቸው ባይችልም) ከጊዜዊ ጥቅም አንጻር ሲታዩ ወልቃይት ጸረ-ኢትዮጵያ ለሆነው ኃይል ተላልፎ እንዲሰጥ ጫና መፍጠራቸው በራሳቸው መንገድ ልክ ሊመስል ይችላል፡፡ እነዚህ ኃይሎች ትህነግን መርዳት ሽብርተኝነትን ማበረታታት ስለመሆኑ ሊጠፋቸው ባይችልም አሁናዊ ሚናቸው በውጤቱ ለቀጣናው አውዳሚ ስለመሆኑ ገሃድ ወጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ደግሞ፤ ወልቃይትን ከእጃቸው እንዳይወጣ፤ ቀጠናውን የመቆጣጠርና በሕግ ለሚገባው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የማፅናት፤ ከማንም በላይ ምክንያትና ጥቅም አላቸው፡፡ ኢትዮጵያን በመካድ በሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ላይ ክህደት ለፈጸመው፤ እንዲሁም ‹‹ታላቋ ትግራይ›› የመመስረት ፍላጎቱን ገሃድ ላወጣው ትህነግ ወልቃይትን ማስረከብ ማለት፤ በኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ሉአላዊነት ላይ እሳት የመለኮስ ያህል አደጋ አለው፡፡ አልፎም ድርጊቱ ሀገርን ለባዕድ አሳልፎ ከመስጠት አይተናነስም፡፡

በኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች የጋራ ሀብት የተገነባው የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ፍጻሜውን እንዳያገኝ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር የሚሰራው ትህነግ፣ ወደጎረቤት ሀገር በነጻነት የሚንቀሳቀስበት የመልክዓምድር አመችነት አገኘ ማለት ኢትዮጵያን ለመበተን ተጨማሪ ጉልበት፣ ዕድልና ሁኔታዎችን እንደማመቻቸት ይቆጠራል፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ሉአላዊነት የማይደራደሩት መላ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ከአማራ ህዝብ ጎን እንዲቆሙ ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡ በአሁናዊውና በመጭው ዘመን ፖለቲካችን የወልቃይት ጉዳይ ከኢትዮጵያ የግዛት አንድነት እና ከሀገር ሉአላዊነት ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ አካባቢውን በንቃት ሊጠብቁ፣ የሀገር ውስጥ ባንዳዎችንና የውጭ ጠላቶችን ሊመክቱ ይገባል፡፡

ሌላው የወልቃይትን ጉዳይ እንደ አይን ብሌን የምንመስልበት ጉዳይ፤ ወልቃይት ለኢትዮጵያ ሌላኛው አማራጭ የባህር በር መስመር መሆን የሚያስችል መልክዓምድራዊ ዕድል ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ይኼም ማለት የምጽዋ ወደብ ከሁመራ በ400 ኪ.ሜ የሚገኝ ሲሆን፤ ሰፊ የገበያ ፍላጎትና አቅም ላለው የሰሜን ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍል የወጭ ገቢ ንግድ ፍላጎቱን ያሟላል፡፡ ይህ የወደብ አማራጭ ከኤርትራ ጋር የሚኖረንን ሁለንተናዊ ግንኙነት ያጠናክርልናል፤ የጋራ ሠላምና ደህንነታችን የምናስጠብቅበት ተጨማሪ እድል ይፈጥርልናል፡፡

በሌላ በኩል በትህነግ የአፓርታይድ አገዛዝ ስር የቆየው ወልቃይትና አካባቢው፣ በቀጣይ  ወደዚህ አካባቢ ከመላው ኢትዮጵያ ለሚመጡ ወጣቶች ሰፊ የስራ እድል የሚያገኙበት ቦታ ይሆናል፡፡ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት እንደነበረው አግላይና ዘረኛ አካሄድ፣ ትግረኛ ቋንቋ መናገር የሀብት ምንጭ መሆኑ አብቅቶለት ኢትዮጵያዊያን በጥረታቸው ልክ ሀብት የሚፈጥሩበት በገበያ ሕግ የሚመራ አካባቢ እንዲሆን የሚያስችል ፖለቲካዊ ሥርዓት ይፈጠራል፡፡ በዚህም ወልቃይትና አካባቢው በወንድማማችነት ስሜት የጋራ ብልጽግናችን ምንጭ በመሆን የኢትዮጵያ ቀጠናዊ የበላይነት ማረጋገጫ የልማት ኮሪደር ይሆናል፡፡

በአካባቢው የሚመረተውን ሰፊ የሰሊጥ፣ ጥጥ፣ ማሽላ፣ የዱር ሙጫ፣ ወዘተ… ለመሰብሰብ  የሚመጡ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ከመላ አገሪቱ የተውጣጡ በመሆናቸው፣ ይህ የሚያመለክተው ወልቃይትና አካባቢው የመላ ኢትዮጵያዊያን እንጅ የአንድ አካባቢ/አማራ ብቻ አለመሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም የወልቃይትን ጉዳይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደአይን ብሌኑ ሊያየው ይገባል፡፡

ትህነግ በየትኛውም አማራጭ ወልቃይትን ዳግም መልሶ ካገኘ ኢትዮጵያን በትኖ ‹‹ታላቋ ትግራይ››ን ለመመስረት መነሳሳቱ አይቀርም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች የጋራ ብሔራዊ ደህንነት አደጋን ለማስተናገድ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ወልቃይት የጋራ ቀይ መስመራቸው ሊሆን ይገባል፡፡

የተከዜ ዘቦች

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share