የኢትዮጵያ መንግስት ቻይና አሰርቶ ያስገባው የጸረ ኤችአይቪ መድሃኒት ከፍቱንነት ይልቅ አቁስሎ እየገደለ ነው ተባለ

/

በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ ኤድስ ሰለባ ሆነው የመድኃኒት ተጠቃሚ የሆኑ ታካሚዎች መንግስት ከቻይና አስመጥቶ እያከፋፈለ ያለው መድኃኒት ከፍቱንነቱ ይልቅ በአሰቃቂ ሁኔታ አቁስሎ እየገደለ መሆኑን ምንጮቻችን በተለይ ለፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ገለፁ፡፡

እንደምንጮቻችን ጥቆማ ከሆነ ቀደም ሲል መድኃኒቱ ይመጣ የነበረው በተባበሩት መንግስታት የዓለም የጤና ድርጅት በሚደረግ ዕርዳታ እንደሆነ እና ደረጃውን የጠበቀ መድኃኒትም ከደቡብ አፍሪካ ይገባ እንደነበረ ተጠቁሟል፡፡ በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ለሙስና እንዲመቻቸው ደረጃውን ያልጠበቀ መድኃኒት በርካሽ ዋጋ ከቻይና በማስመጣት ተጠቃሚዎች ላይ ከፍተኛ የጤና ችግር መፈጠሩን ጨምረው ገልፀዋል፡፡  

አዲሱን ከቻይና የመጣውን የኤች አይ ቪ ኤድስ መድኃኒት የሚጠቀሙ ሰዎችም ሰውነታቸው ድንገት በመቆሳሰሉ ለአልጋ ቁራኛነት በመዳረግ ህይወታቸው እያለፈ በመሆኑ ጉዳዩን ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቢያመለክቱም እስካሁን ምላሽ ባለመገኘቱ ለአደጋ እንደዳረጋቸው ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ ምንጮች ለፍኖተ ነፃነት ገልፀዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑትን አቶ አህመድ ኢማኖን ሐሳብ ለማካተት ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም ስልካቸውን ሊያነሱልን አልቻሉም፡፡ ሌላው ጉዳዩ ይመለከተዋል የተባለው የኢትዮጵያ መድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የምግብና መድኃኒት ፈቃድ ዳይሮክተሬት ዳይሬክተር ተወካይ የሆኑት አቶ ብኒያም ቢተው የኤች.አይ.ቪ ኤድስ መድኃኒት ለኢትዮጵያውያን ተጠቃሚዎች ይመጣ የነበረው ከደቡብ አፍሪካ መሆኑንና አሁን ግን ከቻይና መምጣቱን አምነው የተቀየረበትና እያስከተለ ስላለው ጉዳት ሲጠየቁ ግን “የማውቀው ነገር የለም፤ እንደውም በህዝብ ግንኙነት በኩል ካልመጣችሁ የምሰጣችሁ መረጃ የለኝም ፤ እኔ ተወካይ እንጂ ኃላፊ አይደለሁም” ሲሉ ለፍኖተ ነፃነት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

 የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ወደ ህዝብ ግንኙነት ኃለፊ ብናመራም በቦታው ላይ ያሉት አቶ አበራ ደነቀ የሚባሉ ተወካይ በመሆናቸው መረጃው እንደሌላቸውና በይበልጥ በቀጥታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይተው ወደፊት መልስ ሊሰጡ እንደሚችሉ ከመጠቆም ውጭ ለማረጋገጥም ሆነ ለማስተባበል አልደፈሩም፡፡ ይሁን እንጂ የመድኃኒቱ ለውጥ የገባቸው ተጠቃሚዎች በስጋት ላይ መሆናቸውን በመናገር ላይ ናቸው፡፡

 

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሚኒስትሮች ምክርቤት ከስልጣኑ በላይ ያፀደቀው ሰነድ አወዛገበ

 

1 Comment

  1. Bengrchen laye derjawen yaltebke medhante aymrtem yamirca yechayena belo negre yelm bemdhanite derja

Comments are closed.

Share