April 7, 2013
3 mins read

ከየት ነው ያመጣት?!? (ግጥም ለአርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ)

የሠራዊት እናት..በምናቡ የፈጠራት..
በፍቅረ ንዋይ ሰክሮ የሠራት
ከሌሎቿ ልጆቿ ጋር..
…በፍቅር ተብትቦ ያስተሳሰራት
ምነዋ ምድረ ከብድ ደራሲያኑን..
አዝማሪያኑን..ተዋንያኑን..
በገዛ ልጆቿ አንደበት..
…በክብር ሲያስጠራት
ምነዋ “ከልጅ ልጅ ቢለዩ…”
…ትለውን ብሒል አስረሳት
ምነዋ የኮሚኮቿ ነገር..
…አላንገበገባት እንደ’ግር እሳት::
ሳትል ‘ይማር ነፍሱን’
የአክሊሉ አድማሱን::
የጌጡ አየለን..
የሥዩም ባሩዳን..ያብቢለው ካሣን..
የሀብቴ ምትኩን..የእንግዳዘር ነጋን..
የተስፋዬ ካሣን..የአለባቸው ተካን..
‘ነፍሳቸውን ይማር!’..ማለቱ ተሳናት
የሠራዊት እናት::
የሠራዊት እናት..ከምናቡ የወለዳት
ምነዋ እስከነደንገጠሮቿ ከበዳት
ስለኮሚክ ልጆቿ..
…ላፍታም ቢሆን ማንሳት::
‘እንደቀለደ ያበደ’ተብዬውን..
…’ልመንህን’ እንኩዋን አስረሳት!!
ወይስ…
እንደሌሎች ልጆቿ..
ኮሚኮቿ..
…ከሀገር ወጥተው ቢሰደዱ
እትብታቸው ከተቀበረበት..
…ከፍቷቸው ርቀው ቢሔዱ
…ጨርቃቸውን ጥለው ቢያብዱ
…ወደ ሀገርም ቢመለሱ
እነርሱ…
…ከልጆቿ ሁሉ ሲያንሱ
…እንደሌላው እንደዘመድ አዝማዱ
…እናታቸውም ልትል ነወይ..”ሲቀልዱ”
ወይንስ…ኮሚኮቿን..
…አምጣ ያልወለደች
…በኮሚኮቿ ያልከበደች
ሆና ነወይ?!?
…በችግር ተጠብሳ ያላሳደገች
እንደቀሳውስቱ መጥራት የተሳናት
…የኮሚኮቿን ስም ያልፈለገች
ለዝክረ ሞታቸው መጠሪያ..
…የክብር ቦታን የነፈገች
እኮ!…የሠራዊት እናት..ሌላ ናት?
የሆነችው…ለኮሚኮቿ የእንጀራ እናት::
የሠራዊት እናት..ሌላ ናት?!?
ሥራ ጠፍቶ..ኑሮ ንሮ..ጤፍ ተወዶ
ባይበሉ እንኩዋን..ሆዳቸው ቢሆን ባዶ
አዕምሯቸውን አስጨንቀው..ተጨናንቀው..
እያነቡ..እሚኖሩ..እሚያኖሩ..አሳስቀው..
ኮሚኮቿን መርሳቷ ነው..
…እሚገርመው!..እሚደንቀው!..
ምነዋ የኮሚክ ልጆቿ..
…ሕመም ሥቃይ ያላመማት
አይ ሠራዊት¡..
ከየት ነው ያመጣት?..
…የእምዬን ስም የሸለማት
ያለ ግብሯ..ያለ አንጀቷ..
“ኢትዮዽያ” ሲል የሰየማት::
* * *
~ይህ ግጥም የኪነጥበብ ሰዎች ከቀድሞው ጠ/ሚ ጋር የምክክር ጉባኤ ባደረጉበት ወቅት ቀርቦ ለነበረ ተውኔት መታሰቢያ ነው::
__ፋሲል ተካልኝ አደሬ__
Go toTop