ማሪዮ ባሎቴሊ ከቀድሞ ክለቡ ኢንተር ጋር በነበረው ግጥሚያ ተዳክሞ ቢስተዋልም እስካሁን የኤሲሚላን ጅማሮው አስደሳች ነው፡፡ በሚላኑ ፕሬዝዳንት ሲልቪዮ ቤርሎስኮኒ በአንድ ወቅት በዙሪያው ያሉትን ሊያበላሽ የሚችል የበሰበሰበ ፖም (አፕል) የተባለው አወዛጋቢው አጥቂ ከወር በፊት ወደ ሴረአው በመመለስ ምርጥ ብቃቱን ያገኘ ይመስላል፡፡ በጃንዋሪው ዝውውር ለአዲሱ ቡድናቸው ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳረፉ አምስት ተጨዋቾችን እንቃኛለን፡፡
ማሪዮ ባሎቴሊ – ኤሲሚላን
ጣልያናዊው ተጨዋች የዘንድሮውን የውድድር ዘመን በማንቸስተር ሲቲ በሚያስደስት መልኩ አልጀመረም፡፡ ከሮቤርቶ ማንቺኒ የቋሚ ተሰላፊነት እድል ተነፍጎት ከርሟል፡፡ ማሪዮ ከሜዳ ውጭ ከማንቺኒ ጋር የነበረው ንትርክ በመጨረሻ መቋጫውን አግኝቷል፡፡ ሚላን ለዝውውሩ ከ20 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ማውጣቱ በተጨዋቹ ላይ ያለውን እምነት ያሳያል፡፡ ባሎቴሊም ገና ከአሁኑ ቡድኑን እየጠቀመ ይገኛል፡፡
የ22 ዓመቱ አጥቂ በአራት የሴሪአ ግጥሚያዎች አራት ጎሎች በስሙ አስመዝግቧል፡፡ ጎል ሳያስቆጥር የወጣበት ግጥሚያ ቢኖር የሚላን ደርቢ ብቻ ነው፡፡ የኢንተሩ ግብ ጠባቂ ሳሚር ሃንዳኖቪች ምርጥ ብቃት ባይሆን ኖሮ ባሎቴሊ ሀት-ትሪክ በሰራ ነበር፡፡ በቀደሙት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ላይ ያስቆጠራቸው ጎሎች ግን ሚላን ነጥብ እንዲያገን አስችለውታል፡፡ ማሪዮ በመጀመሪያው ጨዋታ ዩዴኔዚ ላይ ያገባቸው ሁለት ጎሎች የማሲሚሲያኖ አሌግሪ ቡድን ሶስት ነጥብ እንዲያገኝ አስችለውታል፡፡ ካግሊያሪ መረብ ላይ ያሳረፋት ኳስ ቡድኑ አንድ ነጥብ እንዲያገኝ ረድታለች፡፡ ፓርማ ላይ አንድ ጎል በማስቆጠር ቡድኑ በአሸናፊነት እንዲወጣ አስችሏል፡፡ ባሎቴሊ ዘንድሮ በፕሪሚየር ሊጉ አንድ ጎል ብቻ ቢያስቆጥርም ከግብ ፊት የራስ መተማመኑ ከፍተኛ ነው፡፡ በሚላን እስካሁን በአማካይ በጨዋታ የሚሞከረው ኳስ 6.3 በሴሪአው ከእርሱ ቀጥሎ የሚከተለው ኤዲሰን ካቫኒ (4.2) ነው፡፡ ማሪዮ በአማካይ በጨዋታ ሶስት አየር ላይ ኳሶች ዘሎ በበላይነት ይጨርሳል፡፡ 1.6 ድሪብል ያደርጋል፡፡ 1.3 ቁልፍ ኳሶችን ያቀብላል፡፡ እንዲሁም በጨዋታ በአማካይ አንድ ጊዜ ሸርተቴ ይወርዳል፡፡ ለቡድኑ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ጉልህ ሲሆን ጎሎቹ ግን የበለጠ ወሳኞች ናቸው፡፡
ዳኒኤል ስተሪጅ-ሊቨርፑል
ስተሪጅ ለቀዮቹ እያበረከተ ያለው ውጤታማነት በስታምፎርድ ብሪጅ ዴምባ ባና ፈርናንዶ ቶሬስ ስኬት አልባ መሆን የቼልሲ ደጋፊዎችን ፀጉር ማስነጨቱ አይቀርም፡፡ እንግሊዛዊው ተጨዋች በፊት አጥቂነት የመጫወት ፍላጎት ቢኖረውም በሰማያዊዎቹ ቤት እድሉን ማግኘት አልቻለም፡፡ የቼልሲ ማጣትም የሊቨርፑል ማግኘት ሆኗል፡፡ ዳኒኤል በአምስት ጨዋታዎች (አንዱን ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር በነበረው ግጥሚያ ተቀይሮ በመግባት) አራት ጎሎች አስቆጥሯል፡፡ ስትሪጅ ቼልሲን ከለቀቀ በኋላ ዴምባ ባ እና ቶሬስ በሊጉ ማስቆጠር የቻሉት አንድ ጊዜ ብቻ ወን፡፡
የ23 ዓመቱ አጥቂ እንደ ባሎቲሊ ሁሉ እርሱም ባለው ችሎታ እምነቱ የላቀ ነው፡፡ ስተሪጅ ለመርሲሳይዱ ቡድን በጨዋታ በአማካይ 4.8 ሙከራ ያደርጋል፡፡ ይህ አሃዝ ከልዊስ ሱአሬዝና በምርጥ አቋም ላይ በሚገኘው ጋሬት ቤል ብቻ ይበለጣል፡፡ ስተሪጅ ከሱአሮዝ ጋር የፈጠረው ጥምረት ሊቨርፑል በሊገ የማረ ጉዞ እንዲያደርግ አስችሎታል፡፡ በአንፊልድ በዌስትብሮም የተሸነፈበት ግጥሚያ ስትሪጅ ያልተለሰፈ በመሆኑ የተጨዋቹን ተፅዕኖ ያሳያል፡፡ በቅርቡ ስዋንሲን 5-0 ሲያሸንፉ ዳኒኤል ጎል በማስቆጠርና ጎል የሆኑ ኳሶችን በማቀበል ለአዲሱ ቡድኑ መልካም ብቃቱ ያሳየበት ጨዋታ ማለት ይቻላል፡፡ በአማካይ በጨዋታ 2.2 ቁልፍ ኳሶችን ያቀብላል፡፡ በአማካይ በጨዋታ 2.2 ቁልፍ ኳሶችን ያቀብላል፡፡ የማቀበል ስኬቱ 89 በመቶ ሲሆን ለብሬንዳን ሮጀርስ ቡድን የሚያበረክተው አስተዋፅኦ የላቀ ነው
ሙሳ ሲሶኮ-ኒውካስል
ኒውካስል ሳይታሰብ ሲሶኮን በማምጣቱ ቅፅበታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳርፍ የተነበዩ ጥቂቶች ናቸው፡፡ በሊግ 1 ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የነበረው ሙሳ ባለፉት ጠቂት የውድድር ዘመናት እድገቱ ተገድባ ተስተውሏል፡፡ አዲስ ፈተና ያስፈለገው አማካይ በፕሪሚየር ሊጉ ያገኘውን እድል በሚገባ እተጠቀመበት ነው፡፡ አለን ፓርዲው ወጣቱን አማካይ የኒውካስልን የማጥቃት ሄል እንዲመራ ኃላፊነት በመስጠታቸው ትልቅ ሙገሳ ይገባቸዋል፡፡ ሙሳ በአዲሱ ሚናው እየጎመራ ይገኛል፡፡
የቀድሞ የቱሉዝ አማካይ በሊጉ በተሰለፈባቸው አራት ጨዋታዎች ሶስት ጊዜያት ኳስና መረብን አገናኝቷል፡፡ (የሳምንቱ መጨረሻ ጨዋታ አይጨምርም) ሁለት ጎል የሆኑ ኳሶችን ያቀበለ ሲሆን አንዱ ለማግፓይሶች የመጀመሪያ ግጥሚያውን ከአስቶንቪላ ጋር ባከናወነበት ወቅት የተገነች ነበረች፡፡ ያስቆጠራቸው ሶስት ጎሎች ከ10 ሙከራዎች መካከል የተገኙ ናቸው፡፡ በአንፃሩ ለቱሉዝ በበርካታ ጨዋታዎች 19 ጎሎችን ብቻ አስቆጥሯል፡፡ ስምንት ቁልፍ ኳሶችን የቀበለ ሲሆን ስድስት ስኬታማ ድሪብሎችን አድርጓል፡፡ ሶስት የተሳኩ የመሀል ለመሀል ኳሶች በመቀበል እስካሁን ዴምባ ባን ላጣው የማጥቃት ክፍል ነፍስ ዘርቶበታል፡፡
ሉካስ ሙራ – ፓሪ- ሰን- ዠርመ
ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ብራዚላዊ በስድስት የሊግ 1 ጨዋታዎች ኳስና መረብን ማገናኘት አልቻለም፡፡ ሙራ ከወጣበት ወጪ አንፃር ጎል አለማስቆጠሩ የሚያስጨንቅ ነው፡፡ አብዛኞቹ ሉካስ ተለዋዋጭ ተጨዋች በመሆኑ በአውሮፓ ስኬታማነቱ ላይ ትርጣሬ ነበራቸው፡፡ እስካሁን እነርሱ የፈሩት እውን አልሆነም፡፡ የ20 ዓመቱ ተጨዋች በሊጉ ሶስት ጎል የሆኑ ኳሶችን ማቀበል ችሏል፡፡ ይህ አስተዋፅኦው መልካም የሚባል ነው፡፡
ሙራ የግል ክህሎቶቹን እያሳየ ይገኛል፡፡ በጨዋታ በአማካይ 2.2 ስኬታማ ድሪብሎችን ያደርጋል፡፡ ፈጣሪ ተጨዋች መሆኑን እያስመሰከረ ነው፡፡ በአማካይ በጨዋታ 2.2 ቁልፍ ኳሶችን በማቀበል በቡድኑ ከፍተኛው ነው፡፡ ካርሎ አንቼሎቲ በሰጡት ነጻ ሚና እየተጠቀመ የገኛል፡፡ በሊጉ ካደረጋቸው 12 የጎል ሙከራዎች አንዱም ውጤታማ ባለመሆኑ አጨራረሱ ላይ መሻሻል ያስፈልገዋል፡፡ ነገር ግን ካሻገራቸው 11 ኳሶች ስድስቱ ስኬታማ ናቸው፡፡ በአስገራሚ መልኩ በአማካይ በጨዋታ 1.8 ሸርተቴዎች ማስመዝገቡ ወጣቱ ተጨዋች በውቧ ከተማ እየተደላደለ እንደሆነ ያመለክታል፡፡
ሚሼል ባስቶስ-ሼልክ
ባስቶስ ወደ ጀርመን ያቀናበት ጊዜ መልካም ባይሆንም በሼልክ ጎልቶ መታየት ችሏል፡፡ የቡንደስሊጋው ክለብ ደጋፊዎች በልዊስ ሆልትቢ መልቀቅና በአሰልጣኝ ሁብ ስፔቨንስ ስንብት ስሜታቸው ተጎድቶ ነበር፡፡ በሊዮን የሬሚ ጋርድ ቋሚ ተመራጭ ያልነበረው ብራዚላዊ የክንፍ አማካይ በሼልክ አንገቱን ቀና በማድረግ ውጤታማ እየሆነ ነው፡፡
የ29 ዓመቱ ተጨዋች በመጀመሪያ ጨዋታው ጎል በማስቆጠር ፈጥኖ እንዲላመድ አስችሎታል፡፡ ሼልክ በሜዳው በግሩተር ፋርዝ ቢሸነፍም ከሜይንዝ ጋር አቻ ሲወጣ ኳስና መረብን አገናኝቷል፡፡ በውሰት ውል የፈረመው ባስቶስ ሶስት ጎሎችን ከማስቆጠሩ በዘለለ ጎል የሆኑ ኳሶችን ማቀበል ችሏል፡፡ በቅርቡ ሼልክ ከስድስት ግጥሚየዎች በኋላ የመጀመሪያ ድሉን ሲያስመዘግብ ባስቶስ ጎል የሆነ ኳስ አቀብሏል፡፡ ሚሼል በአማካይ በጨዋታ 3-5 ሙከራዎች ያደርጋል፡፡ ይህ አሃዝ በሊጉ ከፍተኛ ከሆነው አንድራ ሹርል ጋር በእኩል ደረጃ ላይ አስቀምጦታል፡፡ ሁለት ስኬታማ ድሪብሎችና በአማካይ በጨዋታ ሁለት ሸርተቴዎቹ በደጋፊዎቹ ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ S
በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ቁጥር 49 ላይ ታትሞ የወጣ