February 13, 2013
29 mins read

UEFA Champions League 2013: በቻምፒየንስ ሊጉ የእንግሊዝ ክለቦች ወደ ሩብ ፍፃሜው መግባት ይችሉ ይሆን?

የቻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ድልድል ለእንግሊዛዊያን ክለቦች አስጨናቂ ይመስላል፡፡ ከ1995/96 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድም የእንግሊዝ ክለብ በሩብ ፍፃሜው ላይታይ ይችላል፡፡ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ቼልሲ፣ ሊቨርፑል እና አርሰናል በግማሽ ፍፃሜ ደርሰው ተሸንፈዋል፡፡ ቼልሲ ዋንጫውን በ2012 ቢያነሳም የቦሩሲያ ዶርሙትድ፣ ጁቬንቱስ እና ሻክታር ዶኔትስክ ዋነኛ ተፎካካሪ መሆን እና የባርሴሎና፣ ሪያል ማድሪድ እና ባየርን ሙኒክ አንሸራትቷቸዋል፡፡ ዘንድሮ ማንቸስተር ሲቲ እና ቼልሲ ከምድባቸው እንኳን ማለፍ አልቻሉም፡፡ ማድሪድ እና ባየርን ከአውሮፓ ሶስት ምርጥ ክለቦች መካከል ከተመደቡ የዩናይትድ እና አርሰናል እጣ ፈንታ ከወዲሁ የተወሰነ ይመስላል፡፡ እስኪ የእንግሊዝ ክለቦች ወደ ሩብ ፍፃሜው መግባት ይችሉ እንደሆነ እንመልከት፡፡

ማን.ዩናይትድ- ሪያል ማድሪድ Real Madrid vs Manchester United – World War III

በአውሮፓ ለመጨረሻ ጊዜ ዩናይትድ እና ሪያል ማድሪድ የተገናኙት በ2003 ነበር፡፡ በግጥሚያው በሳንቲያጎ ቤርናቢዩ ራኡል ጎንዛሌዝ በኦልድትራፎርድ ደግሞ ሮናልዶ ድንቅ ሆነው አመሹ፡፡ የጋላክቲኮዎቹ ተሰጥኦ እና ጥራት የታየበት ጨዋታ ነበር፡፡ ዚነዲን ዚዳን፣ ልዊስ ፊጎ፣ ሮቤርቶ ካርሎ እና ፈርናንዶ ሄዬሮ የነበሩበት ቡድን ለማየት የሚያስደንቅ ነበር፡፡ ግጥሚያው ድንቅ በመሆኑም ሮማን አብራሞቪች የእግርኳስ ክለብ ለመግዛት ወሰኑ፡፡ ከዚያ በኋላ ማድሪድ በቻምፒየንስ ሊግ የዋንጫ ድርቅ ተመትቷል፡፡ የቅርብ ተቀናቃኙ ባርሴሎና ለሶስት ጊዜያት ባለትልልቅ ጆሮዎቹን ዋንጫ ሲያነሳ ሪያል ማድሪድ በታሪኩ 10ኛ ዋንጫውን ለማንሳት ዳገት የመውጣት ያህል ከብዶታል፡፡ ስለዚህ ፕሬዝዳንቱ ፊዮሬንቲኖ ፒሬዝ ከባርሴሎና ጋር ለመፎካከር ከፍተኛ ገንዘብ አወጡ፡፡ ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ካካ፣ ካሪም ቤንዜማ፣ አንሄል ዲ ማሪያ፣ ፋቢዮ ኮኤንትራኦ እና ሉካ ሞድሪችን የመሳሰሉ ተጨዋቾችን ለመግዛት ማለት ነው፡፡ ለፒሬዝ የስኬት ቁልፉ ገንዘብ ማውጣት ነው፡፡ ሆኖም አልተሳካላቸውም፡፡ ባርሴሎና ማሸነፉን ቀጠለ፡፡ በዚህም ሪያልን ወደ ክለቦች ቁንጮነት ይመልሱት ዘንድ ጆዜ ሞውሪንሆን አመጡ፡፡ ተሳካላቸው? ባለፈው የውድድር ዘመን ላ ሊጋውን አሸንፈዋል፡፡ እጅግ ተፈላጊውን የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ወደ ነጩ ቤት ለማምጣት ቢቃረቡም በሁለት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ተሸንፈዋል፡፡ ይህ የውድድር ዘመን ደግሞ ያለጥርጥር የፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ መጨረሻ ነው፡፡ የሮናልዶና ማድሪድ ፍቺም እውን የሚሆንበት ዓመት ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ በአውሮፓ ለመንገስ የመጨረሻ ሙከራቸውን ያደርጋሉ፡፡ ለክለቡ፣ ለፕሬዝዳንቱ፣ ለአሰልጣኙ፣ ለኮከብ ተጫዋቹ ለሁሉም ትኩረታቸው 10ኛው የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ወደ ማድሪድ ማምጣት ነው፡፡ በላ ሊጋው የካታላኑ ክለብ ለብቻው እየሮጠ በመሆኑ ብቸኛው የሪያል አማራጭ ቻምፒየንስ ሊግ ነው፡፡

ቁልፍ ፍጥጫዎች ሮናልዶ ከራፋኤል ዳ ሲልቫ

ሮናልዶ ባለፉት ስድስት ዓመታት ምርጥነቱን ያሳየ ልዩ ተጨዋች ነው፡፡ ከባለተሰጥኦ ታዳጊነት ተነስቶ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ያደረሱት ሰር አሌክስ ፈርጉሰን እና የተጫዋቹ ከሁሉም በላይ ምርጥ የመሆን ጥማት ናቸው፡፡ ዩናይትድ ተጫዋቹ ምን መስራት እንደሚችል ያውቃል፡፡ ለክለቡ የቅርብ ዓመታት ስኬት የሮናልዶን ሚናም አይዘነጋም፡፡ አሁን ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቀድሞ ቤቱ ተመልሷል፡፡ ለራፋኤል ይህ ትልቅ ስጋት ነው፡፡ ዩናይትድ ወደ ሩብ ፍፃሜው መግባት ከፈለገ ሮናልዶን የሚያቆምበትን ዘዴ መቀየስ አለበት፡፡ በማድሪድ እና ሲቲ ግጥሚያ ሮቤርቶ ማንቺኒ የታክቲክ ስህተት በመፈፀማቸው የማንቸስተሩ ክለብ እጅግ ባሳፋሪ ሁኔታ ተሸንፎ ይመለስ ነበር፡፡ ሮናልዶ አራት ወይም አምስት ማስቆጠር ሲችል እድሎችን አመከነ እንጂ፡፡ የፖርቹጋላዊው እና ራፋኤል አንድ ለአንድ መገናኘት የዩናይትድ ጋፊዎችን ማስጨነቁ አይቀርም፡፡ ከብራዚላዊው ይልቅም ፊል ጆንስ ቢሰለፍ የተሻለ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ጆንስ እጅግ የተረጋጋ እና በአየር ላይ ኳሶች ከራፋኤል የተሻለ በመሆኑ ሮናልዶን ሊያቆመው ይችላል፡፡ ነገር ግን ቁልፍ የሚሆነው ፉል ባኩን መደገፍ እና ክርስቲያኖን ለሁለት መያዝ ነው፡፡ አንቶኒዮ ቫሌንሲያ ወሳኝ የሚሆነው እዚህ ላይ ነው፡፡ ኢኳዶራዊው ለቡድኑ ሲል ራሱን እንደሚሰዋ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ እርሱ በግጥሚያው የሚኖረው አቅም ሮናልዶ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች እንዳይጠቀም ያደርገዋል፡፡ ከዓለም ምርጥ ተጨዋቾች አንዱን ማቆም ከባድ ቢሆንም ዩናይትድ ከሌሎች ቡድኖች የተሻለ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ በውድድር ዘመኑ ማድሪድ ችግር ውስጥ ቢገኝም የቀድሞው የዩናይትድ ልጅ በቻምፒየንስ ሊግ ስድስት ጎሎችን በማስቆጠር በደርሶ መልስ ግጥሚያዎቹ ለእነ ራፋኤል ፈተና መሆኑ አይቀርም፡፡

አማካይ ክፍል ይህ ክፍል የጨዋታውን ውጤት ሊወስን ይችላል፡፡ ባርሴሎናን የመሳሰሉ ቡድኖች አማካይ ክፍሉን በማጨናነቅ ዩናይትድን ከውድድር ውጭ አድርገውታል፡፡ ለደጋፊዎች ራስ ምታት የሚሆነው ደግሞ ፈርጉሰን ችግሩን በትክክል አለመቅረፋቸው ነው፡፡ ማድሪድ ሶስት የአማካይ ክፍል ተጨዋቾችን ሊጠቀም ይችላል፡፡ ዣቢ አሎንሶ፣ ሳሚ ኬዲራ እና ሞድሪችን፡፡ ክሮኤሺያዊው ከቶተንሃም የመጣው ከሜሱት ኦዚል የበለጠ በአማካይ ክፍሉ ለቡድኑ ስለሚጠቅም ነው፡፡ ይህን ችግር ባለፈው የውድድር ዘመን ባየርን በሚገባ ተጠቅሞበታል፡፡ ቶኒ ክሩስ ወደ ኋላ በማፈግፈግ የሙኒክን የአማካይ ክፍል በሶስት ተጨዋቾች የተያዘ በማድረግ ከሪያል ሁለት አማካይ ተጫዋቾ የቁጥር ብልጫ እንዲኖረው አስችሏል፡፡ ስለዚህ ሞድሪች የመጣው ማድሪድን በአማካይ ክፍሉ ጠንካራ ለማድረግ እና ኳስን የበለጠ እንዲቆጣጠር ለማስቻል መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ዩናይትድ ዌይኒ ሩኒ የሞድሪችን ሚና እንዲወጣ ማድረግ እና ኳስ ሲቆጣጠር አሎንሶን ሰው ለሰው መያዝ አለበት፡፡ ታክቲኩ በአርሰናል ግጥሚያ በሚገባ ተተግብሯል (ሚኬል አርቴታን ኳስ እንዳይደርሰው ማድረግ)፡፡ ይህ የማድሪድን ማጥቃት ከምንጩ ማድረቅ ማለት ነው፡፡ የማድሪድ 4-2-3-1 ከዩናይትድ 4-4-1-1 ጋር የሚገናኝ ቢሆንም ወሳኙ ፍልሚያ የሚኖረው መሀል ሜዳው ላይ ነው፡፡ ሩኒ እና ሞድሪች ለየቡድኖቻቸው የሚኖራቸው ውጤታማነትም የግጥሚያውን አሸናፊ ሊወስን ይችላል፡፡

ደካማ ተከላካይ ክፍሎች? በማጥቃቱ በኩል ምርጥ እንዲሁም በአማካይ ክፍሉ ፍልሚያ ተመጣጣኝ ሊሆኑ ቢችሉም የተከላካይ ክፍላቸው ጥንካሬም ወሳኝ መሆኑ አይቀርም፡፡ ያለምንም ጥርጥር ሁለቱ ቡድኖች በአውሮፓ ምርጡን የተከላካይ ክፍል አልያዙም፡፡ ለጎሎች እና ለማጥቃት ሲባል የዘነጉት የተከላካይ ክፍላቸውን ችግሮች አለበት፡፡ ነገር ግን ማድሪድ እና ዩናይትድ በግጥሚያው የሚያሳየው የመከላከል እና በመልሶ ማጥቃት የመጫወት ችሎታ የሚያስመዘግቡት ውጤት ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ዘንድሮ ዩናይትድ በአውሮፓ ስኬታማ የማይሆነው በተከላካይ ክፍሉ ችግር ሳይሆን አይቀርም፡፡ የኔማኒያ ቪዲች አለመኖር ለሚቆጠሩበት በርካታ ጎሎች እንደምክንያት ቢቆጠርም እውነታው በተከላካይ ክፍሉ ላይ ወጣት እና ልምድ የሌላቸው ክሪስ ስሞሊንግ፣ ጆንስ እና ራፋኤል እንዲሁም ምርጥ ጊዜያቸው ያለፈባቸው እና በዕድሜ የገፉት ሪዮ ፈርድናንድ እና ፓትሪስ ኤቭራ መኖራቸው ነው፡፡ ዩናይትድ እስካሁን ድረስ ተጋጣሚያቸው ካገባባቸው በቁጥር የበለጡ ጎሎችን በማስቆጠር ሲያሸንፍ ቆይቷል፡፡ የማድሪድ አይነት ጥራት ያለው ቡድን ላይ ግን ተመሳሳዩን መድገሙ አጠራጣሪ ነው፡፡ ሪያል በበኩሉ እንደዩናይትድ አይነት ምርጥ የአጥቂ ክፍል ያለው ቡድን አያጋጥመውም፡፡ የሮቢን ቫን ፔርሲ መፈረም ሮናልዶ እና ካርሎስ ቴቬዝ ከኦልድ ትራፎርድ ከለቀቁ በኋላ ለሩኒ ምርጥ አጣማሪ አስገኝቶለታል፡፡ ቫን ፔርሲ ለፔፔ እና ሰርጂዮ ራሞስ ጭንቀት መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ በማድሪድ ተከላካይ እና አማካይ ክፍል የሚዋልለው ሩኒ ወደ ሳጥኑ ለመግባት የሚያደርጋቸውን ጊዜያቸውን የጠበቁ ሩጫዎች በማሻሻሉ የዩናይትድ ጎል የማስቆጠር እድል ሰፊ ይመስላል፡፡ ነገር ግን ማድሪድ ከዩናይትድ የበለጠ ጎል የሚያስቆጥር ይመስላል፡፡ ሞውሪንሆ ይህ እንዲፈጠር ያደርጋሉ? አሰልጣኙ ቡድናቸው ወደኋላ አፈግፍጎ ተከላክሎ በመልሶ ማጥቃት የዩናይትድን ተከላካይ ክፍል በቤንዜማ እና ሮናልዶ ፍጥነት እንዲያስቸግሩ የሚያደርጉ ይመስላል፡፡

ማድሪድ ሊቸገር? ሪያል ከዩናይትድ የተሻለ ቡድን ይዟል? መልሱ ‹‹አዎ›› ሊሆን ይችላል፡፡ የተሻለ አሰልጣኝስ? በተወሰነ መልኩ የዚህም መልስ ‹‹በትክክል›› ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይ በአውሮፓ ሞውሪንሆ በታክቲኩ በኩል ከፈርጉሰን የተሻሉ ናቸው፡፡ ለዩናይትድ ጥሩው ዜና ግን ዘንድሮ የቻምፒዮንስ ሊግን ለማሸነፍ እንደ ግዴታ አለመታየቱ ነው፡፡ ከማድሪድ እና ሞውሪንሆ በተቃራኒው ፕሪሚየር ሊጉን ማሸነፍ ትኩረቱ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በስፔኑ ክለብ ላይ ጫናውን ከፍ ያደርገዋል፡፡ የሞውሪንሆ ያለፉት የአውሮፓ ስኬቶች ሲታዩ ሰውየው ሻምፒዮን የሆኑት ግምት ያልተሰጣቸውን ቡድኖች ይዘው ነው፡፡ ፖርቶን ይዘው ከዩናይትድ ጋር በኢንተር ሚላን ደግሞ ከባርሴሎና ጋር ሲጫወቱ የእርሳቸው ቡድኖች እንደሚያሸንፉ ይጠበቅ ነበር፡፡ ወደ ፍፃሜው ሲጓዙ ምንም አይነት ጫና አልነበረባቸውም፡፡ በቼልሲ ዋንጫውን እንደሚወስዱ ሲገመቱ ግን ተቸግረዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታትም ማድሪድ ተመሳሳዩን ፈፅሟል፡፡ ይህ ሞውሪንሆ ዋንጫ እንደሚያነሱ ከሚጠበቁ ይልቅ ግምት ባይሰጣቸው እንደሚሻል ያሳያል፡፡ ምንም እንኳን ትልቅ ተፎካካሪ ቢሆንም ከማድሪድ ያነሰ ግምት ተሰጥቶት የሚመጣውን ዩናይትድን እንዲያሸንፉ ሲጠበቁ ይፍረከረኩ ይሆን? ከዚህ በተጨማሪ በቤርናቢዩ ይፋ የወጡ ሌሎች ችግሮች አሉ፡፡ ሊጉ የተበላ እቁብ ሆኗል፡፡ ከመጋረጃ በስተጀርባም ተጫዋቾቹና የቦርድ አባላት የእርስ በርስ ሽኩቻ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ይህ ደግሞ በቡድኑ አቋም ላይ ተፅዕኖው ታይቷል፡፡ የቡድኑ ትኩረት ሙሉ ለሙሉ ቻምፒየንስ ሊግ መሆኑን ተከትሎ የሞውሪንሆ የተጨዋቾቹን እምነት እና አንድነት በመመለስ ለፌብሩዋሪ መዘጋት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ግን ረዥም መንገድ መጓዝን ይጠይቃል፡፡ የቡድኑ የላ ሊጋ ውጤት በዚህ መልኩ ከቀጠለ ዩናይትድን በትክክለኛ መንፈስ ሆኖ መግጠሙ ያጠራጥራል፡፡ ፈርጉሰን አንድ ቡድን የሚሰሩት በየአራት ዓመት ልዩነት ነው፡፡ የአሁኑ ቡድን ደግሞ ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ምናልባት ይህ የውድድር ዘመን ለሰር አሌክስ የአሰልጣኝነት ህይወት ማብቂያ ሊሆን ስለሚችል ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የአውሮፓን ዘውድ ለመጫን ይሞክሩ ይሆናል፡፡ ቡድኑ ግን ለቻምፒየንስ ሊጉ ዋንጫ ዝግጁ አይመስልም፡፡ የዩናይትድ አላማ በሲቲ የተነጠቀውን የፕሪሚየር ሊግ የሻምፒዮንነት ክብር ማስመለስ ነው፡፡ ወደ ማድሪድ ሲያመራም ጫና አይኖርበትም፡፡ የአውሮፓ ድል እንደ ‹‹ቦነስ›› መታየቱ ለዩናይትድ በራስ መተማመንን ይፈጥርለታል፡፡ ለማድሪድ ግጥሚያው ሁሉም ነገሩ ስለሆነ ግፊቱ የትየለሌ ይሆናል፡፡ ግጥሚያው በታላላቆቹ አሰልጣኞች መካከል ትልቅ የታክቲክ ፍልሚያ ይታይበታል፡፡ የዓለም እግር ኳስ ሁለቱ ትልልቅ ክለቦች ምናልባትም በምንጊዜም ምርጥ አሰልጣኞች እየሰለጠኑ እና ከዓለም ምርጥ ተጨዋቾች መካከል የተወሰኑት ይዘው ፌብሩዋሪን በጭንቀት እና በጉጉት ይጠባበቃሉ፡፡ የሁለቱን ግጥሚያ ተመልክቶ ክለብ የሚገዛ ሌላ ባለሀብትም ሊመጣ ይችላል፡፡

አርሰናል – ባየርን ሙኒክ

የማድሪድ እና ዩናይትድ ግጥሚያ እንደሚያሳየው ከምድቡ አንደኛ ወይም ሁለተኛ ሆኖ መጨረስ የትኛው የተሻለ እንደሆነ አከራካሪ ነው፡፡ አርሰናል በድጋሚ ለውድድሩ የጥሎ ማለፍ ዙር መድረሱ ጥሩ ስኬት ነው፡፡ የመድፈኞቹ ጉዞ ግን እንደ አጋጣሚ ሆኖ እዚህ ላይ የሚያበቃ ይመስላል፡፡ አርሰናል ‹‹ከደካማ›› ቡድኖች ጋር ሲጫወት በአውሮፓም ሆነ በሊጉ የሚያቆመው ያለ አይመስልም፡፡ የአጨዋወት ዘይቤው እና የማጥቃት ተሰጥኦው በተደጋጋሚ ጎሎችን እና ድሎችን ያስገኛሉ፡፡ ቡድኑ ከአውሮፓ ምርጦች ጋር ሲገናኝ ግን ‹‹ደካማ›› ይሆናል፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን በሚላን በመጀመሪያው ግጥሚያ 4-0 መሸነፉ ሁለተኛውን ጨዋታ ከባድ አድርጎበታል፡፡ በመልሱ ግጥሚያ ለማሸነፍ ጫፍ ቢደርስም አልተሳካለትም፡፡ በ2010/11 በሜዳው ጥሩ ቢጫወትም በካምፕ ኑ ቫን ፔርሲ ቀይ ካርድ በተመለከተበት ጨዋታ በባርሴሎና ተረታ፡፡ በ2009/10 በካታሉ ክለብ 4-1 ተሸንፏል፡፡ በ2008/09 ግማሽ ፍፃሜ ቢደርስም በዩናይትድ በድምር ውጤት 4-1 ተረትቷል፡፡ እነዚህ ውጤቶች ከምርጦች ጋር ሲጫወቱ የቬንገር ልጆች እንደሚከብዳቸው ማሳያዎች ናቸው፡፡ ለድክመቱ ተጠያቂ የሚሆኑት ደግሞ ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ናቸው፡፡ የታክቲክ አረዳዳቸው አናሳ መሆን ቡድናቸውን ለጥቃት ተጋላጭ አድርጎባቸዋል፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን አርሰናል በሳንሲሮ ያሳየው አቋም የደጋፊዎቹን አንገት ያስደፋ ነበር፡፡ ሊዮኔል ሜሲ ለብቻው አራት ያስቆጠረበት ግጥሚያም እንዲሁ፡፡ ቡድኑ በተከላዮቹ መካከል እና ጀር ብዙ ጥፋቶች ይፈጥራል፡፡ ትንንሾቹ ቡድኖች ይህን ባይጠቀሙበትም የተሻሉት ለውጤት ያውሉታል፡፡ አርሰናል ጥሩ ቡድን ነው፡፡ ከምርጦቹ አጠገብ ግን የደረሰ አይመስልም፡፡ ስለዚህ ከዓለም ምርጥ ቡድኖች አንዱ የሆነው ባየርን ጨዋታውን በቀላሉ ሊያሸንፍ ይችላል፡፡

ባየርን ችግሮቹን ቀርፏል ባለፈው የውድድር ዘመን ሙኒክ በተካፈለባቸው ውድድሮች ሁሉ ሁለተኛ ሆኖ አጠናቅቋል፡፡ በቻምፒየንስ ሊጉ በሜዳው በቼልሲ የደረሰበት ሽንፈት ደግሞ ከሁሉም አስከፊው ነው፡፡ ተጨዋቾቹ እና ቡድኑ ያላቸው ችሎታ ግን የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ባየርን ሙሉ ለሙሉ ለውጥ ባያስፈልገውም የተወሰኑ ቀዳዳዎችን መድፈን ነበረበት፡፡ ስለዚህ ባለፈው ክረምት የተወሰኑ ግዢዎችን ፈፅሟል፡፡ በተከለካይ ክፍሉ ዳንቴን ጨምሯል፡፡ በአማካይ ክፍሉ ሀቪ ማርቲኔዝን በአጥቂው ላይ ደግሞ ማሪዮ ማንዘኪችን ቀላቅሏል፡፡ ባየርን ምርጥ ተጨዋቾችን ያካተተ ሲሆን የፕሄይንከስ ለአጨዋወቱ ሚዛናዊነትን ፈጥረዋል፡፡ የሚከተለው ግን ተመሳሳይ አጨዋወትን ነው፡፡ ዘይቤው አለመለዋወጡ አጨዋወቱን እንዲተነብይ ያደርገዋል፡፡ ነገር ግን ባየርን ከአርሰናል የተሻለ ነው፡፡ በሜዳው የትኛውም ክፍል አርሰናል የተሻለ መሆን አይችልም፡፡ የባየርን አማካይ ክፍል እንዳሻው ሊፈነጭ ይችላል፡፡ የመድፈኞቹ ተከላካዮችም ማሪዮ ጉሜዝ፣ አርየን ሮበን እና ፍራክ ሪቤሪን መቆጣጠር የሚችሉ አይመስሉም፡፡ ክሩስም በአማካይ እና ተከላካይ መሀል ላይ ክፍተትን ሊያገኝ ይችላል፡፡ ቬንገር ታክቲካቸውንም ሆነ ዘይቤያቸውን የሚቀይሩ አይመስልም፡፡ አርሰናል ምርጥ ለመሆን የሚያስፈልገው ጥቂት ተጨዋቾች ብቻ ወደ ቡድኑ መጨመር እንደሆነ የሚከራከሩ አሉ፡፡ ቡድኑ ግን አሁን ካለው የተሻለ እና ልምድ ያለው በረኛን ይሻል፡፡ የተከላካይ መስመሩ በብልህ ተጨዋቾች እንቅስቃሴ ሲቸገር ይታያል፡፡ ሶስቱ አማካዮችም ተመሳሳይ አጨዋወት ይከተላሉ፡፡ በተለያዩ ሚናዎች የሚጫወቱ ተመሳሳይ ተጨዋቾች ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በመከላከሉ በኩል ችግር ፈጥሯል፡፡ በማጥቃቱም በኩል ሳንቲ ካዞርላ እና ጃክ ዊልሼር ተመሳሳይ ስራ መስራትን ይሻሉ፡፡ ቡድኑ አቡ ዲያቢን ቢያጣም ፈረንሳዊው አርሰናልን በአውሮፓ እንዲፎካከር አያስችለውም፡፡ የአጥቂ ክፍሉም ጥራት ይጎድለዋል፡፡ ሉካስ ፓዶልስኪ እና ኦሊቪዬ ዢሩም ይህ ጥራት የላቸውም፡፡ በአርሰናል ሀይል የበላይነት እና ከፍተኛ ስሜት ከጠፋ ቆይተዋል፡፡ ይህ የቡድኑን አምበል የሚገልፅ ዘይቤ ይመስላል፡፡ ቶማስ ቬርሜሌን ወደ እንግሊዝ ሲመጣ የነበረውን ችሎታ ያጣው መስሏል፡፡ አርሰናል በድጋሚ ክጥሎ ማለፉ የሚያልፍ አይመስልም፡፡ ይህ ውድቀት አርሰናልን በመሰለ ክለብ ተቀባይነት እንደሌለውም ደጋፊዎቹ መጠየቅ አለባቸው፡፡

አውሮፓ ያለ እንግሊዝ ሁለቱ ግጥሚያዎች ሲታዩ የእንግሊዝ ተወካዮች ከውድድሩ እንደሚወጡ ይገመታሉ፡፡ ቼልሲ እና ሲቲ ገና ከወዲሁ ተመሳሳዩ እጣ ስለደረሰባቸው ስለቡድኖቹ እና ስለ ፕሪሚየር ሊጉ ደረጃ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ በቅርብ የውድድር ዘመናት የተከሰቱት ችግሮች የመከላከል ወሳኝነትን በመዘንጋት የመጡ ናቸው፡፡ ከጅምሩ ከውድድር የወጡት የሚያፈስ የተከላካይ ክፍል በመያዛቸው ነው፡፡ ይህን አሻሽለው በአውሮፓ በድጋሚ ለመንገስ ደግሞ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ያለፉት 10 ዓመታት የእንግሊዛዊያን ቆራጥነት እና ስሜት ከውጭ ሀገር ተጨዋቾች ችሎታ እና ፈጣሪነት ጋር ተዋህደው ይታዩበት ነበር፡፡ ነገር ግን የእንግሊዝ መንገድ በስፔናዊያን የኳስ ቁጥጥር እና በጀርመናዊያን ውጤታማነት ተተክቷል፡፡ በሁለቱ መንገዶች ተጨዋቾች ችሎታ ቢኖራቸውም ለመከላከል እና ቅንጅትም ትኩረት ይሰጣቸዋል፡፡ የትኛውንም አጨዋወት ይከተሉ የእንግሊዝ ክለቦች በዘንድሮው ቻምፒየንስ ሊግ ፈተና ገጥሟቸዋል፡፡

02/12
Celtic
vs
Juventus
‎-1:45 PM (CT)
02/12
Valencia
vs
PSG
‎-1:45 PM (CT)
02/13
Real Madrid
vs
Man. United
‎-1:45 PM (CT)
02/13
Shakhtar Do.
vs
Dortmund
‎-1:45 PM (CT)
02/19
Porto
vs
Málaga
‎-1:45 PM (CT)
02/19
Arsenal
vs
Bayern
‎-1:45 PM (CT)
02/20
Milan
vs
Barcelona
‎-1:45 PM (CT)
02/20
Galatasaray
vs
Schalke
‎-1:45 PM (CT)
03/05
Man. United
vs
Real Madrid
‎-1:45 PM (CT)
03/05
Dortmund
vs
Shakhtar Do.
‎-1:45 PM (CT)

Latest from Blog

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop