March 15, 2022
84 mins read

ጦርነቱ የአሜሪካንና የአውሮፓውያን ነው ! ጦርነቱ ራሺያን ለማውደም የታለመና ይህንን ዕቅድ ለማክሸፍ የሚካሄድ ጦርነት ነው!

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
መጋቢት 15 2022

መግቢያ

የቀዝቃዛው ጦርነት ካከተመ፣ እስከ 1989 ዓ.ም በሁለቱ ኃያላን መንግስታት መሀከል የነበረው ፉክክርና ፍጥጫ ካበቃና፣ የሶቪየት ህብረት ፈራርሳ ራሺያ ሌሎችን በሶቪየት ህብረት ስር የተጠቃለሉትን አገራት እንደ ፈለጋችሁ ሁኑ ብላ ካሰናበተቻቸው በኋላና፣ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚመራው የምዕራቡ የካፒታሊስት ዓለም በአሸናፊነት ከወጣ ወዲህ  የዓለም ህዝብ ወደ ሰላምና ወደ ነፃነት ያመራል የሚል ተስፋ ተጥሎ ነበር።  የታሪክ ግዴታ ሆኖ ግሎባላይዜሽን የሚባለው በዓለም አቀፋዊ የምርት ክንውን፣ የንግድ እንቅስቃሴ፣ ዕዳ፣ እንዲሁም በኤንተርኔትና በሌሎች የማህበራዊ ሚዲያዎች የሚገለጸው ነገር የዓለምን ህዝብ ማስተሳሰር ከጀመረ ወዲህና የዓለም ህዝብም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በቀላሉ የመንቀሳቀስ ዕድሉ ከፍ እያለ ለመምጣት በመቻሉ በዓለም ህዝብ ዘንድ ከጦርነት ይልቅ ሰላም፣ ከድህነት ይልቅ ወደ ተሻለ ኑሮ መሸጋገር፣ ከጥላቻ ይልቅ ወንድማማችነት ይሰፍናል ተብሎ ከተማነ በኋላ አሁን እንደምናየው ዓለማችን ወደ ሶስተኛው ዓለም ጦርነት ወደሚጠጋ ሁኔታ ውስጥ እያመራች ነው።

275810408 3272390083033823 909932275083388205 nበአብዛኛዎቻችን ዕምነት እስክ 1989 ዓ.ም ድረስ ለነበረው ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የኢኮሎጂያዊ፣ የፖለቲካና የሚሊታሪ ቀውስ ተጠያቂው የኮሙኒስቱ ብሎክ፣ ወይም ደግሞ በሁለቱ ኃያላን መንግስታት መሀከል የነበረው ፍጥጫና ፍክክር ነበር። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ ግለሰባዊ ነፃነትን የሚያፍን፣ ነፃ ንግድንና የገበያ ኢኮኖሚን የሚቀናቀን፣ ለሊበራሊዝም አስተሳሰብ መስፋፋት እንቅፋት የሆነ፣ የህግ የበላይነትንና የፓርሊያሜንታሪ ዲሞክራሲን አጥብቆ የሚጠላው የኮሙኒስቱ ርዕዮተ-ዓለም ከተወገደ በኋላ በሁሉም አገሮች ዘንድ እኩልነት፣ በገበያ ኢኮኖሚና በነፃ ንግድ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ በዚህም አማካይነት ረሃብና ድህነት ይወገዳሉ፣ የዓለምም ህዝቦች በሰላምና በደስታ ይኖራሉ የሚል ዕምነት ነበር።

ይሁንና ግን ይህ ከመሆኑ ይልቅ  በአለፉት ሰላሳ ዓመታት የዓለምን ፖለቲካ፣ የጦርነትን ጉዳይ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውስን፣ እንዲሁም በአገሮች መሀከል ብቻ ሳይሆን፣ በተለይም ደግሞ ደካማ ናቸው በሚባሉት አገሮች ውስጥ የሰፈነውን በጎሳና በሃይማኖት ስም ተሳቦ የሚካሄደውን ግጭት ስንመለከት በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን የነበረው ፍጥጫ መወገዱ በሌላ መልክ ተከስቶ እንደመጣና የዓለምም ህዝብ በቀላሉ ሊወጣው የማይችለው ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ እንደወደቀ ለመገንዘብ እንችላለን። ይህ ብቻ ሳይሆን በአለፉት ሰላሳ ዓመታት የዓለምን ህዝብ በአንድ ወጥ አስተሳሰብ ለመጠቅለል በሚል አስተሳሰብ፣ ይሁንና ደግሞ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በሚመራው የምዕራቡ የካፒታሊስት ዓለም በተለይም “አደገኛ ናቸው” በሚባሉ አገሮች ላይ የተለያዩ ምክንያቶችን በመፈለግና ጦርነት በማወጅ መንግስታት እንዲወድሙ፣ አገሮች እንዲፈራርሱ፣ ህዝቦች እንዲሰደዱ፣ የታሪክ ቅርሶች እንዲጠፋና፣ ህዝብም ወደ ኋላ መለስ ብሎ የነበረበትን ሁኔታና የነበረውን ታሪክ እንዳያስታውስ ለመደረግ በቃ። የአሜሪካን ካፒታሊዝም ነፃ ገበያንና ሊበራሊዝምን ሽፋን በማድረግ፣ በመሰረቱ ዕውነተኛ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የገበያ ኢኮኖሚን መገንባት ሳይሆን ታዛዥ አገዛዞችን በማስፈን እንደፈለገው አገዛዞችንና ፖሊሳቸውን የሚጠመዝዝበትና ተግባራዊ የሚያደርግበትን ሁኔታ ለመተገበር አመቺ ሁኔታን ፈጠረ። በአንዳንዶች ዕምነት አሜሪካንና የተቀረው የምዕራቡ ዓለም ከኢራቅ ጀምሮ እስከ አፍጋኒስታን ድረስ፣ እንዲሁም በሶሪያና በሊቢያ ላይ ጦርነትን ያወጀው አሸባሪ ኃይሎችን ለመዋጋትና የዘይት ሀብትን ለመቆጣጠር የሚል ነው። ይህ አንደኛው ምክንያት ቢሆንም፣ ሌላውና ዋናው ምክንያት አሜሪካና የተቀረው የምዕራቡ ዓለም በእነዚህ አገሮች ላይ ጦርነትን የከፈቱት በመሰረቱ ከእነሱ አስተሳሰብ ውጭ የሆኑ አገሮችን ለማውደምና የታሪክ ቅርሳቸውን በማጥፋት ህዝቦቻቸው ብዥ ብሎባቸው እንዲኖሩ ማድረግ ነው። በአሜሪካን የካፒታሊስቱ ኦሊጋርኪ ዕምነት መሰረት ዋናው የሰው ልጅ ዕድል በገንዘብ ዙሪያ መሽከርከር አለበት፤ ባህልና ሃይማኖት፣ እንዲሁም ባህላዊና ማህበረሰበአዊ ግኑኝነቶች ቦታ የላቸውም። ሁሉም ነገር በግለሰብ ደረጃና በገንዘብ ዙሪያ የሚሽከረከርክር መሆን አለበት። ስለሆነም ማህበረሰብና ህብረተሰብ የሚባሉት መሰረተ-ሃሳቦች ቦታ የላቸውም። የቀድሞዋ የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስተር የነበሩት ወይዘሮ ቴቸር “የማውቀው ህብረተሰብን ሳይሆን፣ ግለሰብን ብቻ ነው” የሚለው አነጋገር በአሜሪካኖችና በአውሮፓ ኤሊቶች ተቀባይነትን አግኝቷል።

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ ከሶስት ሳምንት ጀምሮ በዩክሬይን የሚካሄደው ጦርነት በመሰረቱ የውክልና ጦርነት ሲሆን፣ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና  ግብረ-አበሮቿ ራሺያን ለማዳከምና የመጨረሻ መጨረሻም ለመበታትን ከረጀም ጊዜ ጀምሮ ያቀዱት ዕቅድ ነው። ስለሆነም ቀደም ብሎ ጆርጂያን፣ አሁን ደግሞ ዩክሬይንን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ስምምነትና የአውሮፓ አንድነት አባል መሆን ትችላላችሁ እያሉ በማባበል እነሱን ተገን አድርገው ራሺያን በመክበብና የመጨረሻ መጨረሻ  ጦርነት ውስጥ በመክተትና በወራሪነትና በጨፍጫፊነት ስም በመወንጀል፣ በአንድ በኩል በዲፕሎማሲ መነጠል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ኃይሏን በጦርነት እንድትጨርስ ማድረግ ነው። ይህንን የአሜሪካንን ኢምፔሪያሊዝምንና የግብረአበሮቿን ሴራ ለመረዳት እንዳንድ መሰረታዊ ነገሮችን ጠጋ ብለን እንመልከት። ክዚያ በፊት አንድ መሰረታዊ ነገር እንመልከት።

ሀቁ የሚነግረን ነገር ምንድነው?

በ1989 ዓ.ም ሶቭየት-ህብረትና በእሷ የሚመራው የኮሙኒስቱ መንደር ሲፈራርስ ይህንን ጉዳይ የታሪክ ግዴታ አድርገው የቆጠሩና፣ የኮሙኒስት ማህበረሰብ ተፈጥሮአዊ ያልሆነና፣ የነፃ ገበያን ወይም ካፒታሊዝምን እንደተፈጥሮአዊና ማንኛውም አገርና ማህበረሰብ የግዴታ መከተል ያለበት የዕድገት ፈለግ አድርገው የሚቆጥሩ፣ በተለይም ተማርን የሚሉ ጥቂት የማይባሉ ስዎች የሚጋሩት ሀቅ ነው። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ አመላካከት ከሳይንስ አንፃርና ከህብረተሰብና ከባህል ዕድገት አኳያ ሲመረመር ትክክል አይደለም።

በመጀመሪያ ደረጃ የካፒታሊዝምን ዕድገት ወይም ደግሞ በአብዛኛዎቻችን አነጋገር የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ በመባል የሚታወቀውን የዕድገት ሂደት ለመረዳት አንዳንድ መሰረታዊ ነገሮችን እናንሳ። ምናልባት ለአብዛኛዎቻችን ግልጽ ያልሆነው ነገር ካፒታሊዝም ታቅዶና ታልሞ እዚህ ዐይነቱ ደረጃ ላይ የደረሰ ሳይሆን የተለያዩ አጋጣሚ ነገሮች በመገናኘት ለካፒታሊዝም ዕድገት አመቺ ሁኔታን የፈጠሩ በመሆናቸው ነው። እስከ አስራአራተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ አብዛኛው የአውሮፓ ማህበረሰብ በእርሻ የሚተዳደርና የፊዩዳሉ ስርዓት ከካቶሊክ ሃይማኖት ጋር በመቀናጀት የብዝበዛን ስርዓት ያሰፈነበትና በጨለማ ዓለም ውስጥ ይኖር እንደነበር ይታወቃል። ቀስ በቀስ የግሪክ ፍልስፍና ሲገባና ወደ ላቲን ሲተርጎም አንዳንድ የተገለጸላቸው ምሁራን ከዚህ አዲሱ የግሪክ ፍልስፍና፣ የተፈጠሮ ሳይንስና ማቲማቲክስ፣ ድራማና ስነ-ጽሁፍ ጋር ሲገናኙ ለካ እንደዚህም ነገር አለ በማለት በዚያ ላይ ርብርቦሽ በማድረግ ቀስ በቀስ ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ በመቀጣጠል ከፊዩዳሉ ስርዓትና ከካቶሊክ ሃይማኖት ጋር በመጋጨት አዲስ ምሁራዊ እንቃስቃሴ እንዲፈጠር ይደረጋል። ይህ ዐይነቱ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ሲዳብር በጊዜው ብቅ ማለት ከጀመረው የንግድ እንቅስቃሴና የዕደ-ጥበብ ሙያ መስፋፋት ጋር በመዳበል አዲስ የሆነ የኢኮኖሚያዊ ኃይል አሰላለፍ ብቅ እንዲልና ቀስ በቀስም በፖለቲካው ላይም ግፊት የሚያደርግበት ሁኔታ ሊፈጠር ቻለ። ቀጥሎ በሃይማኖት አካባቢ የተደረገው ለውጥና ከዚያም በኋላ እየዳበረ የመጣው የፍልስፍና እንቅስቃሴ ዲስፖታዊ አገዛዞች በሚባሉት ላይ ከፍተኛ ግፊትና ተፅዕኖ ማድረግ ቻለ። በእግሊዝ አገር በመጀመሪያ ደረጃ በፖለቲካው መስክ ዙሪያ የህግ የበላይነትን አስመልክቶ የተደረገው ትግልና፣ ግለሰብአዊ ነፃነትን ማወቅና የሪፖብሊካን አስተሳሰብ ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግ በኢኮኖሚው መስክ ላይም የራሱን አዎንታዊ ተፅዕኖ ማሳደር ቻለ። እስከ አስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ አብዛኛዎቹ የአውሮፓ መንግስታት ይከተሉ የነበረው የኢኮኖሚ ፍልስፍና የውስጥ ገበያን ማስፋፋት በሚለው ላይና፣ በተቻለ መጠን በማደግ ላይ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች(Infant Industries) ከውጭ በሚመጣ ዕቃ እንዳይጎዱ የታሪፍ ዕገዳ ማድረግ ወይም የውጭው ንግድ ልቅ እንዳይሆን ማድረገ ነበር። ይሁንና ግን የኋላ ኋላ ለተነሱት እንደ አዳም ስሚዝና ሬካርዶ ለመሳሰሉት ኢኮኖሚስቶች ይህ ዐይነቱ አካሄድ በተለይም ለእንግሊዝ የኢኮኖሚ ዕድገት አመቺ አለመሆኑን በመረዳት የግዴታ የነፃ ንግድን ጥቅም ማስፋፋት ጀመሩ። ከዚህም በመነሳት አገሮች ገበያዎቻቸውን ለውጭ ዕቃዎች ክፍት እንዲያደርጉና በዚህም አማካይነት እያንዳንዱ አገር በሰለጠነበት የምርት ዘርፍ የበለጠ አትኩሮ ቢያደርግ በአንድ በኩል የምርት ዋጋን መቀነስ ሲቻል፣ በሌላ ወገን ደግሞ በተካፋይ አገሮች ውስጥ ተመሳሳይ የሆነ ዕድገት ሊመጣ ይችላል የሚል አስተሳስበ ማስፋፋት ጀመሩ። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ለጊዜው ተቀባይነትን ቢያገኝም፣ በተለይም በጊዜው ኋላ-ቀር በሚባሉ እንደ ጀርመን በመሳሰሉ አገሮች ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ አለተቻለም። የኋላ ኋላ ብቅ ያሉት የጀርመን ምሁራን የነፃ ገበያን ፍልስፍና መቀበል ወይም መከተል እንግሊዝን ብቻ ነው የሚጠቅመው ብለው በመቃወማቸውና የራሳቸውን ቲዎሪ በማዳበራቸው መጀመሪያ የውስጥ ገበያን ማስፋፋት ያስፈልጋል፣ ለዚህ ደግሞ የግዲታ በማኑፋክቸሪንግ ላይ ማትኮር ያፈልጋል የሚለው ተቀባይነትን በማግኘት ጀርመን ይህንን መንገድ በመከተሏ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንግሊዝን መወዳደር ቻለች። አዲስ የባንክ ስርዓትም በመፍጠርና በትምህርት ዘርፉም አብዮታዊ የሆነ ለውጥ በማድረግና፣ በተለይም ለሳይንስና ለፍልስፍና አትኩሮ በመስጠት ሰፋ ላለ ህብረተሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አመቺ ሁኔታ ሊፈጠር ቻለ።

ይህ እንደኛው ሲሆን፣ ከምሁራዊ እንቅስቃሴ መዳበር፣ ከፖለቲካው መድረክ መስፋትና ሳይንስና ቴክኖሎጂ የዕድገት ሞተሮች መሆናቸውን ተቀባይነትን ከማግኘት ባሻገር የአውሮፓው ካፒታሊዝም ቀስ በቀስ ማደግና መስፋፋት፣ የኋላ ኋላ ደግሞ የዓለምን ኢኮኖሚ መቆጣጠር የቻለው በተለይም የአፍሪካን የጥሪ-ሀብት በመበዝበዝ፣ የባሪያ ንግድና የቅኝ-ግዛት ሰተት ብለው እስከመግባታቸው ድረሰ የነበረውን አስተዳደርና የስራ-ክፍፍል በማውደም ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር፣ የአውሮፓው ካፒታሊዝም ዕድገት ዕምርታን ማግኘት በፍጹም ካለጥሬ-ሀብትና አፍሪካን ከመበዝበዝና ከማቀጨጭ ውጭ ሊታስብ በፍጹም አይችልም። አሁንም በሌላ አነጋር፣ የአውሮፓው ካፒታሊዝም ዕደገትና የአፍሪካ ወደር ኋላ መቅረት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ማለት ይቻላል። ከዚህ ስንነሳ የተገለጸለትና በሊበራል አስተሳሰብ መንፈሱ ታንጿል የሚባለው የአውሮፓው ካፒታሊስት መደብ፣ የኋላ ኋላ ደግሞ የአሜሪካኑ ካፒታሊስት መደብ በመሰረቱ የተገለጸላቸውና የሊበራሊዝምን አስተሳሰብ በሁሉም አገሮች በእኩልነት ለማስፋፋትና አገሮችን በተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ላይ ለማምጣት የታገሉ ሳይሆን የታሪክ አጋጣሚ የፈጠረላቸውን ሁኔታ በመጠቀም በሌሎች ኋላ-ቀሩ በሚባሉ አገሮች ላይ ጦርነትን በማወጅ ከኢኮኖሚና ከማህበረሰብ ዕድገት አንፃር ኋላ እንዲቀሩና፣ እስከዛሬም ደረስ ከዚህ ዐይነቱ መዘዝ እንዳይላቀቁ መርዝ ረጭተውባቸዋል ማለት ይቻላል። ዕውነተኛውን በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚደገፈውንና ሰፊውን ህዝብ ሊጠቅም የሚችለውን ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዳያደርጉ መንገዱን ሁሉ ዘግተውባቸዋል። ዘራፊ አገዛዞችን ስልጣን ላይ በማውጣትና ጥሬ-ህበትን በመዝረፍ በየአገሮቹ ውስጥ ያለው ህዝብ ህይወቱ ሁሉ ጨልሞበት እንዲኖር ለማድረግ በቅተዋል። አብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮች ነፃ ወጡ ከተባለ በኋላም ወደ እጅ አዙር የቅኝ-አገዛዝነት ሁኔታ ውስጥ ነው ለመለወጥ የበቁት። አሁንም ቢሆን አብዛኞዎቹ የአፍሪካ አገሮች የራሳቸውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የማውጣት መብት የላቸውም። የፈለጉትንም የህብረተሰብ ሞዴል መከተል አይችሉም። ሌላ አስተሳሰብ ያለው መሪና ሌላ የኢኮኖሚ ሞዴልን እከተላለሁ የሚል በአፋጣኝ ከስልጣን እንዲወገድ ይደረጋል፤ አሊያም ደግሞ ጦርነት ይታወጅበታል። ሀቁ ይህ ነው።

ወደ ሶቭየት ህብረትና ወደ ተቀሩት የድሮ ምስራቅ አውሮፓ አገሮች ስንመጣ እንደ ተቀሩት የአውሮፓ አገሮች በሬናሳንስ፣ በሬፎርሚሽንና በኢንላይተንሜንት የሚገለጽ ህብረተሰብ አልነበራቸውም። እነሌኒን እስከተነሱበት ጊዜና የሶሻሲት ርዕዮተ-ዓለም ቀስ በቀስ መስፋፋት እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ በተለይም ራሺያ በአብዛኛው መልኩ ወደ ኋላ የቀረች አገር ነበረች። ነገስታቱ በድሎት ዓለም ውስጥ ሲኖሩ አብዛኛው ህዝብ ደግሞ በድህነት ዓለም ውስጥ ይኖር ነበር። በታላቁ ፔተርና በታላቋ ካታሪና የጥገና ለውጦች ቢካሄዱም፣ ይህ ዐይነቱ የጥገና ለውጥ የማይናቅ ምሁራዊ እንቅስቃሴን ቢፈጥርም በኢኮኖሚው አኳያ መሰረታዊ ለውጥ ሊታይ አልቻለም። ስለሆነም የ1917 ዓ.ም የሶሻሊስት አብዮት መካሄዱ የታሪክ ግዴታ ነበር ማለት ይቻላል። እንደሚባለው አብዮትን የሚፈጥሩት ራሳቸው አገዛዞች ናቸው። አፍጦ አግጦ የሚታይን የተውሳሰበ ችግር ለመፍታት በማይችሉበት ጊዜ አብዮት የሚባለው ነገር የታሪክ ግዴታ ይሆናል ማለት ነው። እነሌኒን ስልጣንን ሲይዙ የገጠማቸው ችግር አያሌ ነበር። ራሺያ በተለይም በአንደኛው ዓለም ጦርነት በጣም ተጎድታ ነበር። ስለሆነም ሰፊውን ህዝብ የሚመግብ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለማውጣትና ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ዘዴዎችን ሞክረዋል። የኋላ ኋላ ስታሊን የተከተለው የግዳጅ የህብረት እርሻና የኢንዱስትሪ ፖለቲካ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረስ ይታወቃል። ይህ በእንደዚህ እንዳለ በሶቭየት-ህብረት ላይ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ይታወጅባታል። በዚህም የተነሳ ራሺያ ብቻ ከ20 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ልታጣ ችላለች። ትላልቅ ከተማዎቿ ሊወድሙ ችለዋል። ይሁንና እነስታሊን በአገር ወዳድ ስሜት በመነሳትና በጦር መሳሪያ ምርት ላይ በማተኮርና በማምረት የሂትለርን ጦር በመግጠም የመጨረሻ መጨረሻ በድል አድራጊነት ይወጣሉ። ከዚያ በኋላ ነው እነስታሊን ቀስ በቀስ ኢኮኖሚያቸውን መገንባትና ህዝባቸውን መመገብ የቻሉት። ከተማዎቻቸውንም በመገንባት ህዝብቻውን ማስተዳደር ችለዋል። ከዚህ ስንነሳ የኮሙኒስቱ ብሎክ በመባል የሚታወቀው እስከ 1989 ዓ.ም ድረስ የአፍሪካን የጥሬ-ሀብት በመቀራመትና አፍሪካን ወደ ኋላ በማስቀረት በፍጹም አልተሳተፈም። ራሳቸው በፈጠሩት የስራ-ክፍፍልና የንግድ ልውውጥ አማካይነት ነው ለህዝቦቻቸው አስፈላጊውን መሰረታዊ ነገሮች ማሟላት የቻሉት። ስለሆነም እስከ 1989 ዓ.ም ድረስ በኩሙኒስቱ መንደር አንድም ህዝብ የተራበ አለነበረም። በዕውቀት ደረጃም ከፍተኛ ቦታ የያዙና ማንኛውም ሰው የመማር ዕድል ነበረው። ስለሆነም ማንበብና መጻፍ የሚችለው ህዝብ ቁጥር ከፍ ያለ ነበር ማለት ይቻላል። የኮሙኒስቱ ብሎክ ከፈረሰ ከረጅም ዐመታት በኋላ ጋሉፕ በሚባለው የአሜሪካን የምርምር ተቋማት ባደረገው ጥያቄ መሰረት አብዛኛዎቹ በምስራቅ አውሮፓ አገሮች የሚኖሩ ህዝቦች  በኮሙኒስት ዘመን የነበረውንና ከለውጥ በኋላ ያለውን ሁኔታ እንዲያመዛዝኑ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ ኮሙኒስት ይባል በነበረው ስርዓት ውስጥ አብዛኛው ህዝብ በእርግጠኝነት ይኖር እንደነበር፣ የስራ ቦታ ችግር እንዳልነበረበት፣ ልጆቹን በነፃ ያስተምር እንደነበር፣ ህክምና ለሁሉም ይዳረስ እንደነበር፣ የቤት ችግር እንዳልነበረበትና፣ የሚከፍለውም የቤት ኪራይ ርካሽ እንደነበር.፣ በአጭሩ በነፃ የገበያ ኢኮኖሚ አማካይነት መሻሻልን ሳይሆን ድህነትንና፣ እርግጠኝነት አለመሰማቱን ነው የተናገረው። በእርግጥም የኮሙኒስቱ ብሎክ ከፈራረሰና የነፃ ገበያ የሚባለው ፈሊጥ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ጀምሮ በተለይም ወጣቶች አገራቸውን ጥለው እንዲወጡና ለከፍተኛ አደጋም እንደተጋለጡ ይታወቃል። በተለይም ከቡልጋሪያ፣ ከዩክሬይንና ከሩሜኒያ እንዲሁም ከፖላንድ የሚመጡ ለአቅመ-አዳም ያልደረሱ ሴት ልጆች በየመንገድ በመቆም ሰውነታቸውን እንዲሸጡ ነው የተገደዱት። ይህም ማለት እነ አሜሪካና የተቀሩት የምዕራብ አውሮፓ አገሮች በእነዚህ አገሮች የሰለጠነ ስራ ከመስራትና ኢኮኖሚው ቀስ በቀስ ከታች ወዳላይ ኦርጋኒካሊ እንዴት እንደሚገነባ ከማሳየት ይልቅ ወደ ዘረፋ ነው ያመሩት። በዚህም ምክንያት የተነሳ ከራሺያ ጀምሮ እስከ ዩክሬይንና ሌሎችም የቀድሞውም የኮሙኒስት አገሮች ዘራፊ ኦሊጋሪኪዎችና የአሜሪካን ተላላኪዎች ነው ቦታውን መያዝ የቻሉትና በሙስና በመጠመድ ህዝቦቻቸውን ማራቆት የጀመሩት።

አንድ መሰረታዊ ሃሳብን በጭንቅላት ውስጥ ለመቋጠር የኮሙኒስቱ ብሎክ ወይም በእዝ ኢኮኖሚ የሚመሩት አገሮች ሊፈራርሱ የቻሉት 1ኛ) በተለይም በኢኮኖሚው መስክ ላይ የጥገና ለውጥ ለማድረግ ባለመቻላቸው፤ ሁሉም ነገር ከላይ ወደ ታች በዕቅድ እንዲመረት በመደረጉ፣ በተለይም የየግለሰብ ፈጠራና ተሳትፎ እንዳይዳብር መንገዱ በመዘጋቱ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ኢኮኖሚው ፍሌክሲቭል እንዲሆንና የህዝቡን ፍላጎት ሰፋ ባለመልክ ለማዳረስ በሚችል መንገድ የግል ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ ከመንግስት ጋር የሚቀናጅበትና አጋዥ እንዲሆን ለማድረግ አልተቻለም። አንድ ዐይነት ርዕይና አሰራር በመለመዱም ከዚህ ፍቅቅ ማለት አልተቻለም። በ2ኛ) ደረጃ በተለይም ሶቭየት-ህብረት ከአሜሪካን ጋር ለመወዳደር ስትልና አሜሪካንም በዚህ አማካይነት ሶቭየት-ህብረትን ማዳካም ይቻላል ብሎ ስላመነ የግዴታ የሶቭየት-ህብረት መንግስት የጦር መሳሪያ ውድድር ላይ እንዲገባ አስገደደው። ለኢኮኖሚው የሚውለው ኢንተለጀንስ፣ ሪሶርስና ገንዘብ በሚሊታሪ መሳሪያዎች ምርት ላይ እንዲውል በመደረጉ ኢኮኖሚውን ሰፋ ባለ ቴክኖሎጂያዊ መሰረት ላይ እንዲመረኮዝ ማድረግ አልተቻለም። ተከታታዮቹ የሶቭየት-ህብረት አገዛዞችም በሚሊታሪ ቴክኖሎጂ መጥቀው ለመሄድና አሜሪካንንም ለመወዳደር ቢችሉም በዚህ መስክ ላይ ያላቸውን ዕውቀትና ችሎታ በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች፣ ለምሳሌ በማሽን ኢንዱስትሪ፣ በኤሌክትሮኒክስና በመሳሰሉት፣ እንዲሁም የህዝቡን የረጅም ጊዜ ፍላጎት ሊያረኩ በሚችሉ እንደ ማቀዝቀዣና ሌሎች ቁሳቁሶች ላይ ማዋል አልቻሉም። በአጭሩ ኢኮኖሚው ከጊዜው ሁኔታ ጋር እንዲሄድ ታቅዶ የጥገና-ለውጥ መካሄድ ባለመቻሉ የግዴታ ስርዓቱ ቀስ በቀስና የኋላ ኋላ እነ ጎርቫዦብና ዬልሲን በሰሩት የፖለቲካ ስህተት ሊፈራርስ ችሏል ማለት ይቻላል። አካሄዳቸውም የዋህነት የተሞላበትና የምዕራቡን የካፒታሊስት ዓለም የሽፍጠኝነት ወይም የሽወዳ  ፖለቲካና አገሮችን የማዳከምና የማፈራረስ ፖለቲካ የሚሉትን ፈሊጥ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ አልነበረም።

 

የሶቭየት-ህብረት መፈራረስ የፈጠረው አዲሱ የፖለቲካ ሁኔታና

የተፈጠረው የኃይል አሰላለፍ!

የሶቭየት-ህብረት ወይም የኮሙኒስቱ ብሎክ መፈራረስ ከእንግዲህ ወዲያ በርዕየተ-ዓለም ዙሪያ ይደረግ የነበረው ትግል አክትሟል ተብሎ የታወጀበት ጊዜ ነው። ከእንግዲህ ወዲያ የምዕራቡ የነፃ ገበያ ፍልስፍናና የሊበራሊዝም አስተሳሰብ አሸናፊ ሆኖ ሆነው ስለወጡ የሚቀጥለው ትግል ደግሞ በተለይም በሃይማኖት ዙሪያ የሚደረግ የባህል ጦርነት ነው። ሰልሆነም ትግሉ ርዕዮተ-ዓለማዊ መሆኑ ቀርቶ በእስልምና ሃይማኖትና በምዕራቡ የክርስትና ሃይማኖት መሀከል ነው። ይህ ዐይነቱ አንዳንድ የአሜሪካን ሶስዮሎጂስቶች የፈጠሩት አዲስ የትግል ዘዴ ሆን ተብሎ የተፈጠረና የዓለምን ህዝብ አትኩሮ በእዚህ ላይ እንዲያተኩር ለማድረግና ከረጅም ጊዜ አንፃር ጦርነትን ለመክፈት ነው። በሌላ ወገን ግን ነገሩን ጠጋ ብለን ስንመለከት የእስልምናንም ሆነ የክርስትናን ሃይማኖት እናስፋፋለን ወይም እንከተላለን የሚለት ድርጊታቸው ሁሉ በቁራንም ሆነ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩትን አስተሳሰቦች የሚጻረሩ ናቸው። ሁለቱም አመጽን የሚያስቀድሙና የሌላን ሰው አስተሳሰብ ለመቀበል የማይፈልጉ ናቸው። ዋናው ቁም ነገር ይህ ሳይሆን ከእንግዲህ ወዲያ ፓክስ አሜሪካንን ወይም ደግሞ በአሜሪካን የበላይነት የሚመራን ዓለም መፍጠርና፣ አሻፈረኝ የሚሉትን ደግሞ ማስንበርከክ አሊያም ደግሞ ጦርነት አውጆ ድምጥማጣቸውን ማጥፋት ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄድ በመሰረቱ የሊበራሊዝምንና የዲሞክራሲን መሰረተ-ሃሳቦች የሚጻረር ነው። አንድን ህዝብ አንድን ርዕዮተ-ዓለም ወይም ሃይማኖት ብቻ እንዲያምን ወይም እንዲቀበል ማድረግ የሚቻለው ጦርነት በማወጅ ሳይሆን በጥሞናና በውይይት ብቻ ነው። ሌላው መያዝ ያለበት ቁም ነገር ደግሞ የዓለምን ህዝብ መንፈስ በአንድ ወጥ አስተሳሰብ መቅረጽ በፍጹም አይቻልም፤ የተፈጥሮን ህግ የሚጥስም አካሄድ ነው። ተፈጥሮ የልዩ ልዩ ነገሮች ውጤት እንደመሆኗ መጠን፣ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥም የተለያዩ ሃይማኖቶችና፣ የአኗኗርና የአመራረት ስልቶች መኖራቸው ተቻችሎ ለመኖር የሚያመቹና መደገፍም ያለባቸው ናቸው። አንድን ህብረተሰብ ወጥ አድርጎ መቅረጽ ዕድገት እንዳይኖር ማድረግ ብቻ ሳይሆን የሰውን ልጅ ውስጣዊ ፍላጎትና ነፃነት የሚፃረር ነው።

ያም ሆነ ይህ በተለይም ራሺያንና የተቀሩትን የምስራቅ አውሮፓ አገሮች ለማዳከም አሜሪካና የአውሮፓው አንድነት አገሮች የተከተሉት ስትራቴጂ የነፃ ገበያ ፖሊሲ ወይም ኒዎ-ሊበራሊዝም በመባል የሚታወቀውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲቀበሉና ተግባራዊ እንዲያደርጉ ማሳመን ነበር። ስለሆነም ኤክስፐርቶች ናቸው የሚባሉ የአሜሪካንና የአውሮፓው አንድነት የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ አቀንቃኞች ወደ ራሺያና ወደ ተቀሩት የምስራቅ አውሮፓ አገሮች በመላክ በጥገና ለውጥ ስም ከዚህ በፊት ያልተለመደና የሰፊውንም ህዝብ ፍላጎት የማያሟላ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ነበር። ለዚህ ደግሞ ቀድሞ ወጣት ኮሙኒስቶች ከነበሩት ውስጥ በመመልመል የአሜሪካና የተቀሩት አውሮፓ አገሮች አፈ-ቀላጤና አገልጋይ ማድረግ ነው። በሊበራሊዝም ስም የተካሄደው ኢንዱስትሪዎችንና የጥሬ-ሀብት መስኮችን በርካሽ ዋጋ መቸብቸብና የውጭ ኃይሎች ተጋሪ እንዲሆኑ ማድረግ ወደ ውስጥ አዲስ የህብረተሰብ ክፍል እንዲፈጠር ያደረገ ሲሆን፣ በዚያው መጠንም በተለይም ራሺያ በኢኮኖሚው የጥገና ለውጥ አማካይነት በአጭር ጊዜ ውስጥ በዕዳ መተብተብ ቻለች። አሜሪካና የአውሮፓ አንድነት አገሮች በተለይም ራሽያን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር ለማዋልና ጥሬ-ሀብቷንና፣ ማለትም የዘይትና የጋዝ ክምችት፣ የዲያመንድና የወርቅ ክምችቶችን፣ እንዲሁም ስትራቴጅክ የጥሬ-ህብቶችን በመቆጣጠር ለዝንተ-ዓለም የበላይነታችንን ለመቀዳጀት እንችላለን ብለው ያመኑበት ጊዜ ተፈጠራልቸው። በየቢሮክራሲው ውስጥ ተሰግስገው በመግባት የስለላ ድርጅቱን እስከመቆጣጠር የደረሱበት ጊዜ ነበር። ፕሬዚደንት ፑቲን ስልጣንን እስከተረከቡበት ጊዜ ድረስ የራሺያ ህዝብ አጋሬና መሬዬ ብሎ የሚመካበት መንግስትና አገዛዝ አልነበረውም። ለድህነትና ለበሽታም በመጋለጡ ምክንያት የተነሳ የሚሞተው ህዝብ ቁጥር ከፍ እያለ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ የሴቶች የመውለድ አቅም በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰበት ጊዜ ነበር። በአጭሩ ራሺያና ህዝቦቿ እየፈረካከሱና፣ በዚያውም መጠንም አንዳንድ የራሺያ ተንታኞች እንደሚሉት በተለይም በዘረፋ መደለብ የጀመረው የህብረተሰብ ክፍል በግማሽ ወደ አውሬነት፣ በግማሽ ጎኑ ደግሞ ሰው የሚመስልበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሎ ነበር። ስለሆነም እንደ ሞስኮውና ፔተርስበርግ በመሳሰሉት ከተማዎች ውስጥ ግድያ የጦፈበትና ቢሮክራሲውና ፖሊስ አዲሱን ሁኔታ መቆጣጠር ያልቻሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ቻለ። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ለምዕራቡ የካፒታሊስት ዓለም አመቺ ነበር። በዚህ መልክ አንድ ህዝብ መሪ ሲያጣና ሁኔታው ሲዘበራረቅበት የበለጠ ሁኔታውን ማባባስ ይቻላል። በዚያውም መጠንም የተቀደሰ አስተሳሰብን ሳይሆን የብልግና ኢንዱስትሪን ማስፋፋት ይቻላል። ወደ ሴተኛው አዳሪነት የተለወጠን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊት በማፍራት ሀብትን መዝረፍ ይቻላል፤ ህዝብንም የባሰ አቅመ-ቢስ ማድረግ ይቻላል። ይህ ነው የአሜሪካንና የተቀረው የምዕራቡ ዓለም የሊበራሊዝምና የዲሞክራሲ ፍልስፍና። በመሰረቱ ይህ ዐይነቱ ሂደት ዕውነተኛውን የሊበራሊዝምን አስተሳሰብምና የዲሞክረሲን መርሆችን የሚቃረን ነው፡፡ ግለሰብአዊና ብሄራዊ ነፃነትን በመግፈፍ አንድን ህዝብ ባሪያ የሚያደርግ ነው። ከውስጥ የተስተካከለና በመጀመሪያ ደረጃ የሰፊውን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎት የማያሟላ አካሂድ ነው።

የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ፕሪዜደንት ዬልሲን በፈቃዳቸው ስልጣኛቸውን ለፕሬዚደንት ፑቲን ሲያስረክቡ ለራሽያ ህዝብ ጥሩ የታሪክ አጋጣሚ ነበር። ይሁንና ሁኔታውን ሀ ብለው መጀመር ነበረባቸው። ቢሮክራሲው ከቁጥጥር ውጭ ወጥቷል። ብዙ ሀብት ወደ ውጭ እንዲሸሽ ተደርጓል። ከቁጥጥር ውጭ የወጣና አደገኛ የሆነ ኦሊጋርኪ መደብ ተፈጥሯል። የራሱ የሆነ የገዳይ ቡድን የፈጠረ ኃይል ትላልቅ ከተሞችን ተቆጣጥሯል። ሀብቱን ለማስጠበቅ ሲል እስከግድያ ድረስ የሚሄድ ኃይል ነበር  በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊፈጠር የቻለው ማለት ይቻላል። ይህንን ሁሉ ኃይል በአንድ ጊዜ ማስወገድ በፍጹም አይቻልም። በጣምም አደገኛ ስለነበር ሁኔታውን በጥንቃቄ መያዝ ነበረበት። በሌላ ወገን ደግሞ የውጭው ፖለቲካ አስተማማኝ አልነበረም። የሰሜን አትላንቲክ የጦር ስምምነት(NATO) የቀድሞዎችን በሶቭየት ህብረት ውስጥ የነበሩትንና ኋላ ላይ ነፃ የሆኑትን አገሮች በማባበልና አባል እንዲሆኑ በማድረግ በየአገሮች ውስጥ የጦር ሰፈሩን ዘርግቷል፤ ሚሳይሎችም ተክሏል። በአጭሩ ራሺያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሁሉም አቅጣጫ ለመከበብ በቅታለች። የዋርሶው ፓክት የሚሉት የጦር ቅንጅት ከፈረሰ በኋላ ደግሞ ለምን የስሜን አትላንቲክ እንዳልፈረሰ፣ ይባስ ብሎ ለመጠናከር እንደቻለ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነበር። ይህ ከመሆኑ ይልቅ እየተስፋፋና ለአዲስ ጦርነት የተዘጋጀበት ሁነታ ነው የተፈጠረው። ይህንን ሁኔታ በጥብቅ የተከታተሉት ፕሬዚደንት ፑቲን ነገሩ በጣም እያሳሰባቸው መጣ። በፕርቶኮል የተያዘውን፣ ኔቶን ወደ ተቀሩት የቀድሞው የሶቭየት ሪፑብሊክ አገሮች አናስፋፋም ብለው የተናገሩትን በመካድ የእነዚህን አገሮች ወጣትና ህዝቦቻቸውን የማይወክሉ አዳዲስ የፖለቲካ ተዋናዮችን በመደለልና የኔቶ አባል እንዲሆኑ በማድረግ ቀስ በቀስ ራሺያን መክበብን ተያያዙት። ይህ ሁኔታና አሜሪካን የሚሆነውን የማይሆነን ሰበብ እየፈለገች አገሮችን የማዳከምና በጦር መውረር የተመለከቱት ፕሬዚደንት ፑቲን ስትራቴጂያቸውን ማስተካከል ነበረባችው። በተለይም በ2007 ዓ.ም ሙኒክ በሚባለው አንዱ የጀርመን ከተማ ላይ በየዓመቱ በሚደረግ የሴኩሪቲ ስብሰባ ላይ ፕሬዜደንት ፑቲን ያደረጉት ንግግር “እስካሁን ድረስ አምነናችሁ ነበር፣ ከእንግዲህ ወዲያ አናምናችሁም” በማለት ነው በግልጽ የተነገሩት። ቀደም ብሎም ሆነ በኋላ ላይ በመሳሪያ ምርትና ፈጠራ ላይ ከፍተኛ መሻሻል እንዲኖር በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሚሳይል አፋኝ የሆኑ እንደ S 400ና S 500 የመሳሰሉትንና ሌሎችንም አንድን አገር በአንድ ጊዜ ውስጥ ድምጥማጡን የሚያጠፋ መሳሪያ በመስራት ከእንግዲህ ወዲያ በቀላሉ ሊበገሩ እንደማይችሉ ለማረጋገጥ ቻሉ። ይሁንና ግን ፕሬዚደንት ፑቲን በዚህ መስክ ከፍተኛ መሻሻል እንዲደርግ ቢያስችሉም፣ በሌላው ወገን ግን አሁንም ራሺያ የጥሬ-ሀብቶችን በብዛት በማምረትና በመሸጥ ነው ኢኮኖሚዋን የምታንቀሳቅሰው። በተለይም አዲስ የፍጆታ አጠቃቀምንና የአኗኗር ስልትን የለመደው አዲሱ የኦሊጋርኪ መደብ ከጥሬ-ሀብት ማውጣት ተላቆ ኢንዱስትሪዎችን ወደ መትከልና ወደ ፈጣሪነት አላመራም። ፓዮኔር ስፕሪት በፍጹም ማዳበር አልቻለም። በሌላ ወገን ደግሞ ፕሬዚደንት ፑቲን እንደሚሉት ከሆነ እሳቸው ከሚሰጡት ትዕዛዝና ስምምነት ከተደረሰበት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውስጥ ተግባራዊ የሚሆነው ከ25% አይበልጥም እያሉ ነው የሚናገሩት። አሁንም ቢሆን በቢሮክራሲው ውስጥና በፖሊሲ አስፈጻሚዎች መንፈስ ውስጥ የሶስተኛው ዓለም ሜንታሊቲ እንዳየለ ነው መገንዘብ የሚቻለው። በመሰረቱ ራሺያ ባላት ኢንተለጀንስና የተትረፈረፈ የጥሬ-ሀብት በሁሉም መስክ ራሷን በቻለች ነበር። ከጥሬ-ሀብት አምራችነት ብቻ ተላቃ በቴክኖሎጂ መስክ የማይናቅ ዕድገት ማሳየት በቻለች ነበር። ሌላው የራሺያ ችግር በዓለም ላይ በስፋት ሌሎችን አገሮች የምትበልጥ ብትሆንም ከዚህ ስፋት ጋር የሚመጣጠን የህዝብ ቁጥር የላትም። የሶቭየት-ህብረት ከፈረሰ በኋላ ህዝቧም በግማሽ ቀነሷል። በዚህ ላይ ደግሞ በበሽታና የተወሰነው ወደ ሌላ አገር በመሄዱ ያንን ትልቅ አገር ሊሸፍን የሚችል የሰው ኃይል የላትም።

ለማንኛውም ወደ ኃይል አሰላለፍ ለውጥ ስንመጣ በአካባቢው አገሮችም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በአሜሪካን የሚመራው የካፒታሊስት ዓለም የዓለምን ህዝብ እንዳሻው የሚነዳበት ሁኔታ ሊፈጠርለት ችሏል ማለት ይቻላል። በተለይም እንደኛ አገር የመሳሰሉ የበሰለ ምሁራዊ እንቅስቃሴና ትችታዊ አመለካከት ባልዳበረበት አገር አንድን አገር ወደ ሽንት መሽኛነት መለወጥ ቀላል ነው። በወያኔ የአገዛዝ ዘመንና በአሁኑ በአቢይ አህመድ የሚመራው የኦነግ ሸኔ አገዛዝ ዘመን የምንመለከተው ይህንን ዐይነቱን የባህል ዝቅጠት ነው። ወደ ቀደሞው ሶቭየት ሪፑብሊክ አገሮች ስንመጣ፣ እንደባልቲኩም የመሳስሉት አገሮችና ወደተቀሩ የምስራቅ አውሮፓ አገሮች፣ ማለትም ወደ ቡልጋሪያ፣ ሩሜንያና ፖላንድ ስንመጣ ፖለቲከኛ ነን ባዮች ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም መንፈሳቸውን እንዳለ ነው መሸጥ የጀመሩት። የሰሜን አትላንቲክ የጦር ስምምነትና የአውሮፓው አንድነት አባል መሆንን ልክ ገነት ውስጥ እንደመግባትን ነው የቆጠሩት። ባህላችንና እሴታችን ከአሜሪካንና ከተቀረው የምዕራብ አውሮፓ ጋር የሚመሳሰል ነው በማለት ወደ ውስጥ መስራት ያለባቸውን ነገሮች እንዳይሰሩ የታገዱና በሙስና የዘፈቁ ናቸው። በዚህም ምክንያት የተነሳ በተፈጠረው የኃል አሰላለፍና አሜሪካን በየአገሮች ውስጥ ጣልቃ በመግባት በምታካሂደው ጦርነት የተነሳ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የውጭው ፖለቲካ ለራሺያ አመቺ አልነበረም። ስለሆነም የውጭ ፖለቲካውን ማረምና የጦር መሳሪያቸውን ማሻሻል የግዴታ ነበር። ስለሆነም ፈራረሰች፣ ከእንግዲህ ወዲያ ማንሰራራት አትችልም የተባለችው ራሺያ በተለይም ሶሪያ ውስጥ ጣልቅ በመግባት በሶሪያ ላይ ከአሜሪካን፣ ከእንግሊዝና ከፈረንሳይ የተሰነዘረባትን ጦር ከሜድትራኒያን ባህር እንዳያልፉ በዘመናዊ የማፈኛ ወይም የማኮላሻ መሳሪያ በምደገፍ 95% የሚሆነውን የተተኮሰውን ሚሳይሎች ለማክሸፍ ችላለች። በዚህ ዓይነቱ ጦርነት ላይ በአንድ ጊዜ ሶስትና አራት አገሮችን ለመቋቋም እንደምትችል አረጋግጣለች።

ይህ በእንደዚህ እያለ በተለይም ባለፉት ሃያ ዓመታት ቻይና በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካና በሚሊታሪ ተወዳዳሪ እየሆነች በመምጣቷ ተዝናንቼ ዓለምን እንደፈልግሁት መበወዝ እችላለሁ፣ በተለይም የአፍሪካን የጥሬ-ሀብት እንደፈለግሁት መበዝበዝ እችላለሁ ብሎ ለሚሯሯጠው የምዕራቡ ዓለም ከፍተኛ እንቅፋት ነው የተፈጠረባቸው። እስካሁን ድረስ የምዕራቡ ዓለም ባልተሳተፈበት የባቡር ሃዲድና መንገድ፣ እንዲሁም ህንፃን በመስራት መሳተፍ የምዕራብ ካፒታሊስቱን የበላይነት እየተቋቋመችና ወደፊት ደግሞ ብቸኛዋ ኃያል መንግስት ሆና የማትወጣበት ምክንያት አይኖርም ማለት ነው። ይህ አዱሱ ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ ለአሜሪካንና ለተቀረው የካፒታሊስቱ ዓለም አላፈናፍንም ያለበት ሁኔታ ነው። ከዚህ ስንነሳ ራሺያ አጋር አግኝታለች ማለት ነው። እራሷም በበኩሏ በሶሪያ፣ በሊቢያ፣ አሁን ደግሞ በማሊ በመግባት ፈረንሳይንና ሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገሮችን መፈናፈኛ እያሳጣቸው ነው። የፕሬዚደንት አሳድ መንግስትና የቬኔዙዊላው ፕሬዚደንት ማዶሮ ከስልጣን መባረር የዳኑት በራሺያ ጠልቆ ገቢነት ብቻ ነው። በተለይም በማዕከለኛው ምስራቅ የኢራን አይሎ መውጣትና እስራኤልንና አሜሪካንን መቋቋም፤ እንዲሁም አልበገሬነትም ማሳየት ይህ ሁሉ ለአሜሪካንም ሆነ ለተቀረው የካፒታሊስቱ ዓለም ትልቅ የራስ ምታት ነው ለመሆን የቻለው። ስልሆነም ለአሜሪካንም ሆነ ለተቀሩት የካፒታሊስት አገሮች የተለያዩ ምክንያቶችን በመፈለግ ጦርነትን ዓለም አቀፋዊ ማድረግ የማይታለፈው ስትራቴጂ ነው። ምክንያቱም ካፒታሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም ካለጦርነት ስለማይኖሮኑ ስለማይደልቡ። የዓለምን ህዝብ አትኩሮ በጦርነትና በፍርሃት ላይ በምዳረግ ብቻ ነው የበላይነታቸውን ለማቆየት የሚችሉት። ከዚህ በመነሳት ነው ከሶስት ሳምንት ጀምሮ በዩክሬይንና በራሺያ መሀከል የሚካሄደውን ጦርነት መመልከት የምንችለው።

 

ጦርነቱ የውክልና ጦርነት ነው!

በተለይም አንዳንድ ክሪቲካል አመለካከት ያላቸው የአሜሪካ የፖለቲካና የሚሊታሪ ጦር ተመራማሪዎችና ምሁሮች እንደሚሉትና ትክክልም እንደሆነው አሁን በራሽያና በዩክሬይን መሀከል ለሚካሄደው ጦርነትና ለብዙ ሰዎች መሞት ምክንያት ለሆነው ዋናው ተጠያቂ ራሺያና ፕሬዚደንት ፑቲን ሳይሆኑ በተለይም አሜሪካ ነች  በማለት ነው የሚነግሩን። አሜሪካን ራሽያን ለማዳከምና ቀስ በቀስም እንደዩጎዝላቪያ ለመበታትን ስትል የምትከተለው ስትራቴጂ በአካባቢው ያሉ አገሮችን የኔቶ አባል እንዲሆኑ በማድረግ፣ የጦር ሰፈር በመመስረትና ሚሳይሎችን በመትከልና እነሱንም በማስታጠቅ ነው። ስለሆነም ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ቀደም ብሎ ጆርጂያ ላይ ለመከተል የፈለገችው ስትራቴጅ በፕሬዚደንት ፑቲንና በአገዛዛቸው ስለከሸፈባት ቶሎ ብላ ሌላ አማራጭ በመፈለግ ዩክሪይንን እንደመሳሪያ በመጠቀም በራሺያ ላይ ጦርነት ማዋጅ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ የሚያሳዝነው ነገር ሁሉም የባልቲኩም አገሮች ህዝቦችና፣ የጆርጂያና እንዲሁም የዩክሬይን ህዝቦች የራሽያን ቋንቋ ይናገራሉ። አብዛኛዎችም የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ዕምነት ተከታዮች ናቸው። በባህልም የሚመሳሰሉና ስላቮች ናቸው። በዚህ ላይ ደግሞ ሰባ ዓመታት ያህል በአንድነት ኖረዋል፤ ተጋብተዋልም፤ ተዋልደዋልም። ከዚህ ስንነሳ ያለው ችግር በህዝቡ ዘንድ ሳይሆን ፖለቲከኛ ነን ባዮች በሚባሉት ዘንድ ነው። ችግሩን የሚፈጥሩትና አገሮቻቸውንም የጦር አውድማ የሚያደርጉና የውክልና ጦርነት እንዲካሄድ አመቺ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩት የፖለቲካ ኤሊት ነኝ የሚለው ደንቆሮ የህብረተሰብ ክፍል ነው። ህብረተሰብን በስርዓት ማስተዳደርና ለህዝብ አለኝታ መሆን ሳይሆን ዋናው ተግባራቸው እንደምንም ብሎ የአሜሪካንና የተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊስት አገሮች አገልጋይና አሽከር በመሆን ሁኔታውን ማዘበራረቅ ነው።

ይህንን ሁኔታ የሚረዳውና ሰፋና ጠለቅ ያለ ዕውቀት የሌላቸውን፣ እንዲሁም አንድ ህብረተሰብ ማለት ምን ማለት ነው? የታሪክስ ሂደት እንዴት ነበር ብለው ወደ ኋላ ዞር በማለት ለመጠየቅ የማይችሉ የፖለቲካ ኤሊቶች፣ በመሰረቱ ፖለቲካ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የማይገባቸውን በመመልመልና በመደለል በቀላሉ የአሜሪካንና የግብረ-አበሮች መሳሪያ በመሆን ህዝቦቻቸውን የጦር እራት እያደረጓቸው  ነው። አገሮቻቸውን የፈጠራና የመኖሪያ ቦታ ከማድረግ ይልቅ ወደ ጦነት አውድማነት እንዲለወጡ አመቺ ሁኔታዎችን እየፈጠሩ ነው። የፖለቲካ ትርጉምን በአፍጢሙ በመድፋት የህዝቦቻቸውን ሰቆቃ እያራዘሙና ህዝቦቻቸውም ወደ ውጭ እንዲሰደዱ አመቺ ሁኔታዎችን እየፈጠሩ ነው። ቀጥታ ወደ ጦርነቱ ከመምጣታችን በፊት የቀድሞው የዩክሬይን ፕሬዚደንት የነበሩት ፕሬዚደንት ቪክቶር ያኑኮቪትሽ በ2013 ዓ.ም ከአውሮፓው አንደነት ጋር የድርጅቱ አባል ከመሆን በፊት አብሮ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ለማድረግ ለመፈራረም ሲሉ ጉዳዩ በፕሬዚደንት ፑቲን ግፊት እንዲቋረጥ ይደረጋል።  ከዚያ በኋላ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር በማፍሰስና ፋሺሽቶች በማስታጠቅ እንደኩዴታ የሚመስል ነገር ያካሂዳል። ፕሬዚደንቱም አምልጠው ወደ ሞስኮው ይገባሉ። የአሜሪካን አቀንቃኝ የሆነ ኃይል ስልጣንን በመያዝ የበለጠ የቀኝ አዝማሚያ ፖለቲካ በመከተልና ፀረ-ራሺያ ፖለቲካ በማካሄድ የማያስፈልግ የፖለቲካ ውዝግብ ይፈጥራል። ይህ ሁኔታና የአሜሪካን አደገኛ ፖሊሲ ያሰጋቸው ፕሬዚደንት ፑቲን  ሶሺ በሚባለው ቦታ የክረምት የኦሎምፒክ ውድድር በሚካሄድበት ጊዜ ውድድሩ ካለቀ በኋላ ራሺያ ክሬሚያን ወም ክሪምን እንድትወር ያደርጋሉ። ራሺያ ደግሞ የመርከብ ጦር ሰፍሯ እዚያ ስለሆነ በዩክሬይንና በራሺያ መሀከል ያለው ስምምነት ጊዜው ሲያልቅ አሜሪካኖች ያንን ባህር ይቆጣጠራሉ ብላ በመፍራት ቀደም ብላ ይህንን ዐይነቱን ስትራቴጂ መከተል ነበረባት። ይህ በእንደዚህ እንዳለ በተለይም በምስራቅ ዩክሬይን የራሺያን ቋንቋ በብዛት በሚነገርበት አካባቢ የሚኖረው ህዝብ አውቶኖሚ እንደሚፈልግ በግልጽ ያውጃል። ኪቭ የሚገኘው በፕሮሼንኮ የሚመራው አገዛዝ ከእነሱ ጋር አንዳች ስምምነት ላይ ከመድረስ ይልቅ ፀረ-ራሺያ ፖለቲካ በመከተልና፣ መብታቸውንም በመርገጥ ጉዳዩ ወደ ጦርነት ውስጥ እንዲያመራ ያደርጋል። በምስራቅ ዩክሬይን የሚኖረው የራሺያ ተናጋሪ ህዝብም ከራሺያ አስፈላጊውን የጦር መሳሪያ ዕርዳታ፣ ምክርና ልዩ ልዩ ድጋፎች በማግኘት ጦርነቱን ያፋፍማል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ከሁለቱም በኩል እስካሁን ድረስ ከአስራ አራት ሺህ በላይ የሚቆጠር ህዝብ ህይወቱን እንዲያጣ ይደረጋል። በመሀከሉ አሜሪካኖች ኪቭ የሚገኘውን ቅምጥ አገዛዝ በዘመናዊ መሳሪያ በማስታጠቅ የልብ ልብ እንዲሰማው ያደርጋሉ። በቀላሉ የራሺያን ወታደር እንደሚያሽንፍ ያስባል። ቀደም ብሎ በጀርመንና በፈረንሳይ መሪዎችና መንግስታት ተነሳሺነት የዩክሬይኑ የምስራቅ ክፍል አንድ መቋጠሪያ እንዲያገኝ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ። ይህ የሚንስክ ስምምነት በመባል የሚታወቀውና በህሉም ወገን ተቀባይነትን ያገኘው በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ኪቭ በሚገኘው የዩክሬይን መንግስት ይጣሳል፤ ወይም ተግባር ላይ ሊውል አልቻለም። እንዲያውም ይባስ ብሎ ክሬሚያን ማስለቀቅ አለብኝ በማለት ስሌንሲክ የሚባለው  አዲሱ የዩክሬይን ፕሬዚደንት ቅስቀሳቅ ያካሂዳል። ይህ በእንደዚህ እንዳለ  በምስራቁ ክፍል የሚገኙት የራሺያ ተናጋሪ ህዝቦችና መሪዎቻቸው የፕሪዚደንት ፑቲን መንግስት ሬፑብሊክ መሆናቸውን እንዲያውቅላቸው ይወተውታሉ። ስለሆነም ዱማ የሚባለው የተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩን በመቀበልና ለፕሬዚደንት ፑቲን እንዲተላለፍ በማድረግ ፕሬዚደንት ፑቲን ሬፑብሊክ ነን ብለው የሚጠሩትን ነፃ መንግስት መሆናቸውን እንዲያውቁ ይገፋፉቻዋል። ከጥቂት ቀናት ማቅማማት በኋላም ፕሬዚደንት ፑቲን ዕውቅናን ያገኛሉ። ቀደም ብሎ ለረጅም ሳምንታት ያህል ወደ መቶ ሺህ የሚጠጋ ወታደር በአካባቢው በማስፈርና ልምምድ በማድረግ አስፈላጊውን ዝግጅት ያደርጉ ነበር። ይሁንና ግን ዩክሬይንን ለመውረር ሳይሆን ይህ ዐይነቱ ልምምድ የተለመደ ነው በማለት ለማስተባበል ይሞክራሉ። ቀደም ብሎ ሲአይኤ ፕሬዚደንት ፑቲን ዩክሬይንን ለመውረር ተዘጋጅተዋል ብሎ በተደጋጋሚ ቢናገርም፣ በተባለው ቀን ግን ወረራው አልተካሄደም። ይሁንና ግን ሁኔታው በሰላም እንዲቋጭ በመሀከሉ ፕሬዚደንት ፑቲን ከአሜሪካኑ ፕሬዚደንት ጋር በመገናኘትና በመደዋወልም ጆን ባይደንና መንግስታቸው ፕሬዚደንት ፒቱን ያቀረቡትን ቅድመ-ሁኔታዎችን ለስምምነት የሚያመቹ ነጥቦች ተቀባይነት እንደሌላቸው ያረጋግጡላቸዋል። ፕሬዚደንት ፑቲን ያቀረቧቸው ነጥቦች 1ኛ) ዩክሬን በምንም ዐይነት የኔቶ አባል መሆን የለባትም የሚል ሲሆን፣ 2ኛ) ደግሞ ዩክሬን ኒውትራል የሆነች አገር ወይም ከማንኛውም ጎን የማትሰለፍ የሚል ነው። 3ኛ) ደረጃ ደግሞ ወደ ሌላ አካባቢዎች ኒቶን አለማስፋፋት የሚሉ ናቸው። እነዚህና ሌሎች ለሰላም የሚያመቹ ነጥቦች በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ተቀባይነትን አላገኙም። አሜሪካን የግዴታ ጦርነቱን ትደግፈዋለች። ለዚህ ደግሞ ሌላው ዋና ምክንያት ከራሺያ በቀጥታ ወደ ጀርመን የሚመጣ የጋዝ የመተላለፊያ ቧንቧ ተዘርግቷል። ይህ የሰሜኑ የመተላለፊያ ቧንቧ የሚባለውና በቀጥታ ከጀርመን ጋር የተያያዘውና ያለቀለት ግንባታ ስራውን ለመጀመር ማህተም ብቻ ነበር የሚያስፈልገው። ስለሆነም ይህ የጋዝ ስርጭት ስራውን ከጀመረ አሜሪካን ወደ ጀርመንና ወደ ተቀሩት የአውሮፓ አገሮች የምትሸጠው ጋዝና ዘይት መጠኑ ይቀንሳል፤ አሊያም ደግሞ እንዳለ ይቋረጣል። ሌላው ምክንያት ደግሞ ከረጅም ጊዜ አንፃር ጀርመን ከራሺያ ጋር የጠበቀ ግኑኝነት ስለምትመሰርት ይህ አካሄድ የአሜሪካንን የጄኦ ፖለቲካ ተጽዕኖ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሰዋል። ስለሆነም በዚህ መልክ ጦርነትን በመቀስቀስ የአውሮፓ አገሮችን ጦርነት ውስጥ መዝፈቅ ነው። በዚህ ዐይነቱ ጦርነት የመጨረሻ መጨረሻም የአውሮፓ አገሮች ናቸው የሚጎዱት። ይህም ማለት ጦርነቱ በአሜሪካን ምድር የሚካሄድ ሳይሆን በአውሮፓ ምድር የሚካሂድ ነው ማለት ነው። በዚህ ጦርነትም ጋዝ በቀጥታ በሰሜኑ ቧንባ እንዳይተላለፍግ ማህተም ተከልክሏል። አሜሪካንም ለጊዜው የምትፈልገውን ነገር አግኝታለች ማለት ነው።

ለማንኛውም ጦርነቱ መካሄድ ከጀመረ ሶስት ሳምንትን አስቆጥሯል። የራሺያ ወታደር በአየር ጥቃት የዩክሬንን የራዳር መቆጣጠሪያዎችን እንዳለ አውድሞባቸዋል። የጦር መሳሪያ ክምችት ያለበትንና የተዋጊ አውሮፕላኖች የሚኑስባቸውን ማረፊያዎች እንዳለ አውድሟል። አንዳንድ ከተማዎችም እንዳልነበሩ ሆነዋል። በራሺያ ወታደር ቁጥጥር ስር የወደቁ ከተማዎች እንዳሉም ይታወቃል። እንደማርዮፖል የመሳሰሉት የባህር አጠገብ ከተማዎች በራሺያ ወታደሮች ተከበዋል። ኗሪው የሆነው ህዝብም ከተማዎችን ለቆ እንዲወጣ እየትደረገ ነው። ራሺያኖች እስካሁን ድረስ ዩክሬይንን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ያልቻሉት የብዙ ሰው ህይወት ሊቀጠፍ ይችላል በማለት ነው። ምክንያቱም ጨቅላ የሆነው በሴሌኒስኪ የሚመራው አገዛዝ ለተራው ህዝብ መሳሪያ ሳለደለና የቤት ለቤት ውስጥና የሽምቅ ውጊያ ሊካሄድ ይችላል ብሎ በማሰብና፣ በዚህም የተነሳ ከሁለቱም ወገን በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ሊሞት ይችላል ብሎ በመገመት ነው። ይህ አካሄድ ደግሞ ትክክል ነው። በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብን ከገደልክ በኋላ ጤናማ ፖለቲካ ማካሄድ ስለማይቻል ነው። የሚያሳዝነው ነገር ግን ምስኪኑ ህዝብና ህፃናት በዚህ ዐይነቱ በአሜሪካኖችና በተቀረው የምዕራቡ ዓለም በታለመውና በተለኮሰው ጦርነት ህይወታቸውን እንዲያጡ መደረጋቸው ነው።  በዚህ ዐይነቱ ጦርነትም የአሜሪካን ካፒታሊስቶችም ፈንድቀዋል። የጦር መሳሪያ ፋብሪካ የአክሲዮን ገበያ ዋጋው በከፍተኛ ዋጋ ከፍ ብሏል። ጦርነቱን ማን ማን እንደሚደግፈው ጥያቄ በተካሄደው መሰረት በአሜሪካን አገር ብቻ ከተጠየቁት ውስጥ ሀብታም የሚባሉት 70% ጦርነቱ ሲደግፉና፣ አሜሪካንም ጣልቃ እንድትገባ ሲገፋፉ፣ ሰራተኛ የሆነውና ተራው ህዝብም 26% ብቻ የሚሆነው ነው ጦርነቱን የሚደግፈው። ጀርመንም ጦርነቱን የሚደግፈው የሚዲያው ዓለምና አካዴሚሺያን የሚባሉት ናቸው። ፖለቲከኞች ነን የሚባሉት ሁሉ ጦርነቱ እንዲበርድ ስትራቴጂ ከመቀየስ ይልቅ ጦርነቱ እንዲባባስ ለዩክሬይን ወታደሮች መሳሪያ እያቀበሉ ነው። ፈሺሽቶች እየሄዱ በመዋጋት ላይ ናቸው። የራሺያ ወታደርም በፖላንድ በኩል የሚገባውን ጦር እንዳለ ከሰማይ በመሆን በማውደም ላይ ነው። ብዙ ፋሺሽቶችንም ገድሏል።

ራሺያ ያደረገቸውን ራስን የመከላከል ወረራ አስመልክቶ በራሺያና በመንግስቷ እንዲሁም በእነ ፕሬዚደንት ፑቲን ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ተጥሏል። አንዳንድ ስትራቴጂክ የሆኑ ማሽኖችንና ለምርት የሚያገለግሉ እንዳይወጡ ታግደዋል። ከራሺያ ደግሞ ማዳበሪያና እንደ ስንዴ የመሳሰሉትና ለዘይት የሚያገለግል የጎመን ዘር እንዳይገቡ ተከልክለዋል። በተጨማሪም ራሺያ ስዊፍት ከሚባለው የገንዘብ መተላለፊያ ስርዓት ውስጥ እንድትወጣ ተገዳለች። በዚህም ምክንያት የተነሳ አስመጪና ላኪዎች ገንዘባቸውን ማስተላለፍና መቀበል አይችሉም። በተለያዩ የአውሮፓ ውስጥ የሚኖሩ የራሺያ ኦሊጋርኪዎችም ሀብቶቻቸው ታግዶባቸዋል። ታላላቅ የሙዚቃ ሰዎችም አቋም ካልወሰዳችሁ እየተባሉ ከፍተኛ ግፊት እየተደረገባቸው ነው። በአጠቃላይ ሲታይ ራሺያን ለመጉዳት ሲባል የተጣለው የኢኮኖሚ ማዕቀብ የቤንዚንን ዋጋ በከፍተኛ ዋጋ እንዲናር አድርጎታል። ስንዴና ሌሎች የስትራቴጅክ ጥሬ-ሀብቶች ከራሺያ እንዳይገቡ በመደረጋቸው በጀርመንና በሌሎች የአውሮፓ አገሮች ከፍተኛ እጥረት እየታየ ነው። የዋጋ ግሽብት በተለይም በአሜሪካን ንሯል። በተለይም የቢንዚንና የጋዝ ዋጋ መናር የአሜሪካንን ሰራተኛ እያስመረረው ነው። ይህን አስታኮ የፕሬዚደንት ጆን ባይደን መንግስት ከቪኑዙዌላና ከኢራን ተጨማሪ ጋዝ ለማስመጣት ጥረት ቢያደርግም እንደማይቻል ነግረውታል። ሳውዲ አረቢያና ካታርም ተባባሪ እንደማይሆኑ የስልክ ጥሪ ባለማንሳት የአሜሪካንን አካሄድ አጣጥለዋል። በአጭሩ የኢኮኖሚ ማዕቀቡ የአንድ ወጥ መንገድ ወይም ራሺያን ብቻ የሚጎዳ ሳይሆን ራሳቸውንም የምዕራብ አውሮፓ አገሮችንና አሜሪካንንም እየጎዳ ነው። ከዚህም በላይ ከዩክሬይን ወደ ጀርመን በመምጣትና ወደ እንግሊዝ በመሄድ በተለይም ዕቃዎችን በትላልቅ መኪናዎች በማመላለስ ተቀጥሮ የሚሰራው አገሬን ከራሺያ ወራሪ ኃይል መከላከል አለብኝ ብሎ በመሄዱ በከፍተኛ ደረጃ ትላልቅ መኪናዎችን የሚነዳና የሚታዘዙ ዕቃዎችን በየቤቱ የሚያደርስና ለኢንዱስትሪዎችም የመለዋወጫ ዕቃዎች የሚያቀርበው የስራ ኃይል በመጉደሉ የተነሳ በኢንዱስትሪዎችና በአገልግሎት መስኩ ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው። ጦርነቱ ሁሉንም እያዳረሰ ነው ማለት ነው።

ያም ሆነ ጦርነቱ ቢያሳዝነም፣ ራሺያን ለማዳከምና ለመበታተን የታቀደው ህልም በፍጹም ተግባራዊ ለመሆን አልቻለም። ከራሺያ ጎን እንደ ቻይና የመሳሰሉ አገሮች ቆመዋል። እንደ ህንድ፣ ፓኪስታን፣ ሜክሲኮና ሌሎች የደቡብ አሜሪካ አገሮች  ድምጻቸውን በመያዝ የአሜሪካንን ግፊት ውድቅ አድርገዋል። እንደ ኪዩባና ቬኔዙዌላ የመሳስሉት፣ ኢራንም ጭምር ከራሺያ ጎን የቆሙ ናቸው። በአጭሩ ራሺያን በኢኮኖሚም ሆነ በዲፕሎማሲ ለመጉዳት የተደረገው ሙከራ የተጠበቀውን ውጤት ያመጣ አይደለም። በራሳቸው በአውሮፓ አንድነት ውስጥም መከፋፈል እየታየ ነው። የጀርመን መንግስት ከራሺያ የሚመጣውን ጋዝ እንዳማያቋርጥ በግልጽ ተናግሯል። ራሺያም ያለውን ሁኔታ በመጠቀም የጋዝንና የዘይትን ዋጋ አልጨመረችም። የአሜሪካን መንግስት ግን ግፊት ከማድረግ አልተቆጠበም። ስለሆነም ፕሬዚደንት ፑቲን ጠንካራ መንፈስና ትክክል የሆነ የዲፕሎማሲ አካሂድ እያሳዩና ኃይሎችንም እየከፋፈሉ ነው። ወደ ውስጥም አብዛኛው ህዝብ ከጎናቸው የቆመ ነው።

በዚህ አጋጣሚ ወደ አገራችን ስንመጣ የሚያስፈልገን አገዛዝ ህዝብን የሚበታትንና ለጠላት የሚያጋልጠን፣ ወይም በውጭ የሚደገፍ የውስጥ ኃይል እንደዚያ የመሰለ ጭፍጨፋና የአገር ውድመት ሲያካሂድ ዝም ብሎ የሚመለከትና፣ በቆራጥነት የሚታገለውንና ደሙን የሚያፈሰውን ትጥቁን የሚያስፈታ መሆን ያለበት አይደለም። የሚያስፈልገን አመራር አገር ወዳድና የበሰለ መሪ ነው። ከውስጥ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚችልና ህዝቡን በመሰብሰብ ወደ ውጭ ደግሞ የምትፈራና የምትከበር አገር እንድትመሰረት የሚያደርግ መሆን አለበት። በዛሬው ወቅት አገራችን በጮርቃዎችና በዝቅተኛ ስሜት በተወጠሩ በተራ ተንኮለኞች የምትመራ አገር ነች። ጠቅላላውን አገራችንን ወደ ጦርነት አውድማ ውስጥ በመጣል ህዝባችን በጭንቀት ዓለም ውስጥ እንዲኖር የሚያደርግ አገዛዝ ነው በአገራችን ምድር የሰፈነው። ከዚህ አሳፋሪ ድራማ ለመላቀቅ የግዴታ አዲስ ስትራቴጂ መቀየስ ያለበት ይመስለኛል። አንድ አገር በጮርቃዎችና በዱርዬዎች ተመርታ እንደ አገር ልትኖር ስለማትችል የግዴታ በከፍተኛ ዕውቀት የተካኑና በራሳቸውና በህዝባቸው ላይ የሚተማመኑ፣ እንዲሁም ደግሞ ህዝብን የሚያስተባብሩና ለስራና የሚያነሳሱ የህብረተሰብ ኃይሎች ብቅ ማለት አለባቸው። መልካም ግንዛቤ!!

 

[email protected]

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከቴዎድሮስ ሐይሌ ትግል ዘርፈ ብዙ ጎኖች አሉት:: ዲፕሎማሲ ሚድያ የፖለቲካ ; ካድሬዎች ; ወታደራዊ ባለሙያዎች ;የሕዝብ አደረጃጀት እና ሌሎችም ተጏዳኝ ዘርፎችን እና ሌላም ብዙ ተቋማዊ ባህሪያት እንደ ትግሉ ጸባይና ሁኔታ ሊያካትት ይችላል::

የአማራ ሕዝባዊ ድርጅት ያደረገው ውይይት ወይስ ድርድር?

January 27, 2025
ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)  ጥር 19፣ 2017(January 27, 2025) ሰሞኑን እስክንድር ነጋ “እመራዋለሁ የሚለውን የፋኖ ክንፍ” በመወከል ከአቢይ አህመድ አገዛዝ ጋር፣ እሱ እንደሚለው ውይይት፣ በመሰረቱ ድርድር እንዳደረገ በተለይም እነ ሀብታሙ አያሌው በሚቆጣጠሩት የኢትዮጵያ 360 ዲግሪ ሚዲያ ሰምተናል። ከመንግስት ጋር

እስክንድር ነጋ በታዛቢዎች አማካይነት ከአቢይ አህመድ ጋር የሚያደርገው ድርድር የአማራውን ህዝብ የተሟላ ነፃነት የሚያጎናፅፈው ወይስ ለዝንተ-ዓለም ኋላ ቀር ሆኖና ኑሮው ጨልሞበት እንዲቀር የሚያደርገው ?

ትግላችንን ለዳግም ባርነት ለሚያመቻቹን የብልጽግና እሳቤ አራማጆች አሳልፈን አንሰጥም!!! ቀን፦ ጥር 18/2017 ዓ.ም ትግላችን የኅልውና፣ የፍትሕ፣ የነጻነት፣ የሰብዓዊ ክብር ሆኖ እያለ ከፋፋይነት፣ ብልጣብልጥነት፣ አወናባጅነት፣ ከምንም በላይ በሕዝባችን ላይ የፖለቲካ ቁማርተኝነት እሳቤዎችን ከጀርባቸው

በወቅታዊ ጉዳይ ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ መግለጫ

January 26, 2025 ጠገናው ጎሹ ከቅኝ አገዛዝ (colonial rule) ነፃ መሆንን ከማወጅ ያለፈ የውስጥ ነፃነት ፣እኩልነት፣ ፍትህ እና እደገት/ልማት እውን ማድረግ ባለመቻል ምክንያት በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም የኋላ ቀርነት እና ለመግለፅ

አህጉራችን እና እኛ

ከሰሞኑ ታዛቢዎች በተገኙበት ከመንግስት ጋር ውይይት እንዳደረገ እና ለድርድር ዝግጁ እንደሆነ የገለፀው በእስክንድር ነጋ የሚመራው የፋኖ ክንፍ ድርድሩ በውጭ ሀገራት እንዲሆን እየጠየቀ መሆኑ ታውቋል። የመሠረት ሚድያ ምንጮች እንደተናገሩት ታጣቂ ክንፉ ድርድሩ በአውሮፓ

በእሰክንድር ነጋ የሚመራው ፋኖ’ ከመንግስት ጋር ለመደራደር ተዘጋጅቷል

January 26, 2025
Go toTop