March 15, 2022
20 mins read

የአማራው” ፌስቡከኛ ለምን ይወቀሳል? (ጌታቸው ሽፈራው)

(በፌስቡክ ስለታገድኩ የደረሳችሁ ብታጋሩት አልጠላም)

አክቲቪስቲም ፖለቲከኞቹም በፌስቡከኛው እያማረሩ ነው። ብዙዎቹ እየተሳቀቁ ነው። በርካቶች እየታዘቡ ነው። ቀሪው ግራ ይጋባል። ለምን ግን ይሄ ሆነ? ለምን በአማራ ስም የሚፅፈው ፌስቡከኛ ይህን ያህል ወቀሳ በዛበት? አንዳንድ ጉዳዮች መጤን ያለባቸው ይመስለኛል።

1) ማሕበራዊ ሚዲያ አናንቋል:_

ፌስቡክ መልካም ነገር የፈጠረውን ያህል ብዙ ችግር አምጥቷል። “ለውጥ” ከመባሉ በፊት ደፍረው የሚፅፉትን ሰዎች ፅሁፍ በስህተት “like” ላለማድረግ የሚጠነቀቀው አሁን የቻለውን ይፅፋል። ከድሮው በበለጠ ከመሪዎቹ ጋር ይገናኛል። ድሮ በራዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በመፅሐፍ ወይ በጋዜጣ ያየው የነበረውን “መሪዬ” ብሎ የሚያከብረውን ሰው፣ አሊያም የተሻለ ሀሳብ የሚያቀርበውን አሁን ፌስቡክ ላይ ጓደኛው ነው። ቢፈልግ ከፍ ዝቅ አድርጎ ከስር አስተያየት ይፅፍለታል፣ በሜሴንጀር ይደውልለታል። መረጃ ይለዋወጣል። እዛው ፌስቡክ ላይ መልስ ይሰጠዋል። ወዘተ። አብረው ይውላሉ። ፌስቡክ ላይ “ጓድነት” አይከበርም። ዲስፕሊን የለም። መርህና ሕግ የለም። ሲፈልግ ሕዝብ ትክሻ ላይ ይሰቅለዋል። ሲፈልግ ይፈጠፍጠዋል። የፌስቡክ ጓድነት ሀሜት እንጅ መወያየት አይበዛውም። መነቋቆር እንጅ መማማር ብዙም አይደለም። “ትግላችን እልህ አስጨራሽ ነው” የሚል መፈክር ፌስቡክ ላይ እየደጋገመ ወቅታዊ ፖለቲካን የሚያስረዳ ረዥም ፅሁፍ ለማንበብ ወገቤን የሚል ይበዛል። የትግልን መራራነት እያወራ የራሱ ወገን ያጠፋ ሲመስለው “ምን ሆነህ ነው?” ብሎ በዝግ ለመጠየቅ አቅል አጥቶ ባለ በሌለው መረጃ ያወርድበታል። ጠላትም፣ ወዳጅም የሚውልበት ፌስቡክ ላይ። በዚህ ምክንያት ይህ መድረክ ለትግል ቀርቶ ለማሕበራዊ ሕይወትም ድብልቅልቁ የወጣ፣ አብዛኛው አጠቃቀሙንም የማያውቅበት ነው። ስለሆነም መናናቅ በዛው፣ አብሮ መዋል ጓድነትን አላልቶታል። እነ ፕሮፌሰር አስራት በህይወት ኖረው ፌስቡክ የሚጠቀሙ ቢሆን ዛሬ ሰማዕት የሚላቸው በገባውን ባልገባውም ሲዘልፋቸው ባየን ነበር። አጤ ምኒልክ፣ አጤ ቴዎድሮስም፣ በላይ ዘለቀም፣ ንጉስ ሚካኤልም በጎጥ ሲመተሩ፣ ፌስቡክ ከከፈተ ወር ባልሞላው ሰው ከመሰደብ አይድኑም ነበር።

2) ከዲስፕሊን ይልቅ የሴራ ትንተና ቀድሟል:_

ሴራ ፖለቲካ ውስጥ ያለ ነው። ሴራን መገንዘቡ ጥሩ ነው። ነገር ግን ሁሉም ባልተናበበ መልኩ፣ ዕዝ ሳይኖረው፣ እከሌስ ምን አለ ብሎ ሳይጠይቅ፣ ምን ለማለት ተፈልጎ ይሆን ብሎ ሳያወሳ ስጋቱን የሚያጋራው ብዙ ነው። ይህ ጉዳይ አማራ ከሚደርስበት ስቃይም ጭምር የመጣ ነው። ከፖለቲካ አለመተማመን የመጣ ነው። ግን ትግል ከራስ ወገን ጋር ዕዝ ሰንሰለት ከመመስረት ይጀምራል። ፌስቡክ ደግሞ እንዲያስብ እንዲያንሰላስል አይረዳውም። ድሮ አንድ ሰው ሀሳቡን ለመስጠት በየሳምንቱ የሚወጣ ጋዜጣ ይጠብቃል። ያውም እድል ካጋጠመው። እስከዛ ስሜታዊ ከነበር ይበርድለታል። ራዲዮ ጣቢያ ድረስ ይሄዳል። ያውም የሀሳብ ጥራት ካለው። አሁን ፌስቡክ መጠጥ ቤትም ሆኖ (ሰክሮ)፣ ንዴቱ ሳይበርድለት እንዲፅፍ እድል አመቻቸለት። ሳይረጋጋ ሀሳቡን ይሰጣል። የመጣለትን ያሰፍራል። ፌስቡክ ለግለሰብ ማተሚያ ማሽንም፣ ቴሌቪዥን ጣቢያም፣ ራዲዮም በሆነበት በዲስፕሊንና በብስለት ከሚሰጠው ይልቅ የመጣለትን ይፅፋል። በወገኑ ላይ የሴራ ትንተና ላይ ይጠመዳል። ስሜቱን በረድ ለማድረግ ጊዜ ሳያገኝ እጁ ላይ ያለውን ሞባይል ላይ ያሰራጫል። በፌስቡክ ብቻ ሳይሆን በአካል የተጋጨን ሰውምኮ ገላጋይ ወደሆነ ቦታ ወስዶ፣ መክሮ ብስጭቱ እንዲበርድለት ያደርጋል። ፌስቡክ ለገላጋይ አይመችም። የትም ሆኖ እንደመጣለት ወንድሙ ጋር መቀነዳደሽ ተለምዷል።

3) የበርካታ ኃይሎች ተሳትፎ:_

ፌስቡክ ላይ ከሚያጠፋው መካከል አብዛኛው በየዋህነትና በቀናነት ነው። ችግር የሚፈጥረው ወይ ጠላት፣ ወይ በጣት የሚቆጠሩ የራስ ወገኖች ናቸው። በተለይ በዚህ ወቅት በአማራ ስም በርካታ ኃይል እጁ አለበት። አማራን በራሱ ልጆች መምቻው ደግሞ ፌስቡክ ላይ ሆኗል። ጠላት በርካታ የሀሰት ገፆች አሉት። አንዳንዱ የዋህ አንድን ጉዳይ በእውነታው ከሚዘገብ ጠላት አጩኾ የሚዘግበው ትክክል ይመስለዋል። ከትክክለኛው መረጃ ይልቅ የሀሰት አስደንጋጭ ፎቶ ይስበዋል። በሕይወት ያሉ ወንድሞችን “ሞቱ” ብሎ በየዋህነት የሚያለቅስ ፌስቡከኛ ያጋጥማል። በሀሰት ድል የሚቦርድ ሞልቷል። የተወሰኑት ግን ይጠቀሙበታል። ፓርቲዎች ይጠቀሙበታል። ከአንደኛው ወንድማቸው ጋር የተጋጩ ይጠቀሙበታል። ፌስቡከኛው የተቃዋሚም፣ የገዥውንም አመራሮች ያገኛል። ሀብታሙንም፣ ወታደሩንም፣ ፋኖውንም፣ ዳያስፖራውንም ያገኛል። መጥፎም ይሁን መልካም ለፖለቲካው የራሳቸው እይታ፣ የራሳቸው ተቃውሞ፣ የራሳቸው ፍላጎት አላቸው። የእነዚህን አካላት ስሜትና ፍላጎት ሳይጨመቅ በየፊናው ፌስቡከኛ ሲያንፀባርቀው ጫጫታ ነው። ግጭት ይፈጥራል። አሁን አሁን ዝናን የሚፈልጉም ሞልተዋል። ሌላ ቦታ ሳንሄድ ራሱ ፌስቡከኛው በየሰፈሩ “ታዋቂ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ” ነኝ ባይ ነው። ራሱን የሚያይበት፣ ሌላ ወገኑን የሚያይበት አይታረቅለትም። መንግስትም በርካታ የሀሰት አካውንት አለው። ይህ ሁሉ ድብልቅልቅ ፈጥሯል። ቋንቋውን የሚችለው ብዙ መሆኑ በአማራ ስም ፌስቡኩ መደባደቢያ ሆኗል። በትንሹ በእነ ሙስጦፌ ሞሃመድ፣ በእነ ጄኔራል ተፈራ፣ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ወዘተ ስም የሚፃፍባቸውን የሀሰት አካውንቶች የእውነት አስመስሎ ሲያጋራ የሚውለው የዋህ ፌስቡከኛ ብዙ ነው። “ምን ይፈልጋል?” ብለው ያጠኑ አካላት የሚመቸውን ይሰጡታል። ወስዶ ይዘራዋል። ይጨቃጨቃል። ለአንድ አፍታ ሳያረጋግጥ አጀንዳ ያደርገዋል።

4) የፍላጎትና ተግባር አለመመጣጠን:_

ፌስቡክ ላይ ያለው ሌላኛው ችግር እውነታውን ያላገናዘበ ፍላጎት ነው። በአንድ ቀን ተአምር የሚፈልግ ሞልቷል። አብን በተመሰረተ በነጋታው ሱዳን በቋራ በኩል ወርሮን “አብን ምን እየሰራ ነው?” ብሎ የፃፈ ሰው አስታውሳለሁ። ገና የእግሩን ስር ሳይሰራ፣ የሰማይ የሚጠብቁ ሞልተዋል። በዚህ እይታ ሚዲያ ቢመሰረት፣ ባንክ ቢመሰረት፣ ወዘተ ቢመሰረት መጀመርያ ጨፍረው፣ በነጋታው የሚያለቅሱ ሞልተዋል። የአማራ ተቋማት አልበረክቱ ያሉት ነባራዊ ሁኔታውን ከሚረዳው ይልቅ ውጤቱን እያየ የሚያባክን ብዙ ሰው መኖሩ ነው። ለምሳሌ ያህል ሰኔ 15 አንደኛው ምክንያቱ የሚመስለኝ የአማራ ብሔርተኝነት አቅምና ፍላጎት ለየቅል መሆኑ ነው። አንድ ህፃን መራመድ ይፈልጋል። የፍላጎቱን ያህል መራመድ ሲፈልግ ግን ይወድቃል። የአማራ ብሔርተኝነት የገጠመው ችግር ፍላጎትና አቅሙን አለማወቁ ነው። አቅሙን ሳያውቅ አጣድፎ፣ ጎትቶ፣ ገፍትሮ መጣል የትግል አካል ሆኖ ወይኔ የሚለው ካለፈ በኋላ ነወወ። ከኋላ ሆኖ የሚገፋው ብዙ ነው። ያለውን አቅም አያውቅም። በመሃል መደናቀፉ፣ ተሰላችቶ መቆሙ የሚመጣው ምን አለን፣ ምን ያንሰናል፣ በአቅማችን የት መድረስ እንችላለን የሚል በመጥፋቱ ነው። ገና የፖለቲካ አካባቢውን በደንብ ያልቃኘ፣ በወገኑ ስቃይ የነደደ ብሔርተኝነት ከዚህም ከዛም አባካኙ ሲበዛ ውድቀቱ ቅርብ ነው። ስክነት ውድ ሆኗል። ማሰላሰል፣ ስሜትን ዋጥ አድርጎ ከወገን ጋር መምከር፣ የራስን ወገን መቻል እጅግ ውድ ነገር ሆኗል።

5) ሚና መለየት አለመቻል:_

በዚህ ወቅት የሆነ አጋጣሚ ያሳወቀችው ሁሉ በነጋታው የፋኖ ወይንም የልዩ ኃይል ምረቃ ላይ ይገኛል። ሌላ ቦታ ላይ ፊት አውራሪ ይሆናል። በሆነች አጋጣሚ መታወቁን ተጠቅመው በቀናነትም “ቅረብ” ሲሉት “የእኔ ቦታ አይደለም” አይልም። በፍፁም። የፖለቲካውን መንፈስ ያልተረዱ የዋሆች የሆነ አጋጣሚ ያሳወቀውን ሰው “መሪዬ” ይሉታል። ከፊት ይሰለፍና ከኋላው ያለውን የድጋፍ ጩኸት ሳያስበው ወደገደል ይከተዋል። መጥፎ ጩኸት ሲመጣ ያስደናግጠዋል። ከፊት ያለውን ችግር አዲሱ ነው። ሚና ባለመለየቱ ይናቃል። ሌላውን ተውት። ስለታወቀ ብቻ ስንቱ ሰው ዩቱዩበኛ እንደሆነ ተመልከቱ። ለሚዲያ የሚመጥን እውቀት ይኑረው አይኑረው። ፍሬ ነገር ይኑረው አይኑረው “ቀጥታ ስርጭት” ገብቶ ሚዲያ ላይ የሚደክመው ብዙ ነው። ሚና ባለመለየቱ ለመደነባበሩ፣ ያለ አቅም መንገድ ለመዝጋቱ፣ ለመጠላለፉ፣ ባለ በሌለ አጀንዳ ለመጠለፉ ምክንያት ነው። ሁሉም ፖለቲካው ላይ፣ ሁሉም ፌስቡኩ ላይ፣ ሁሉም ዩቱዩብ ላይ ተጠመደ። ዕዝ አልባ ዘመነ መሳፍንት በየፊናው ተጠመደ። ፌስቡክ ላይ ዘመነ መሳፍንት ተፈጥሯል። የጎበዝ አለቃ ሞልቷል። ማዕከላዊነት፣ አንድነት ተጠልቶ ሁሉም የጎበዝ አለቃ ነው።

6) ለፓርቲና ግለሰቦች ከሚገባው በላይ ግምት መስጠት:_

አንድ ጉዳይ ተጀመረ ሲባል እንደአማራው ፌስቡከኛ የሚያስጮኸው የለም። ባለፈው ክፉ አገዛዝ ምክንያት የእነዛ አገር ገንቢዎች ልጅ ገብጋባ፣ አይቶ አያውቅ ሆኗል። ከገዥውም ሆነ ከተቃዋሚው አንድ ሰው የተገኘ ሲመስለው ከፈጣሪ ቀጥሎ የማይሳሳት አድርጎ ይወስደዋል። ትንሽ የተሳሳተ ሲመስለው የቆየውን አስተዋፅኦውን ገደል ከትቶ አይንህን ለአፈር ይለዋል። በተቋም ደረጃም ተመሳሳይ ነው። ሁሉን ችግር የሚፈታ አድርጎ አትንኩብኝ ይላል። ትንሽ ያጠፋ ሲመስለው፣ ለጥጦ ያሰበውን ካላደረሰለት ጎትቶ ለመጣል ይሮጣል።

7) ማሕበራዊ ሚዲያ ለሀሜት እድል ሰጥቷል

ቀደም ሲል በአደራሽ ከሚደረገው ይልቅ አሁን በሜሴንጀር፣ በዋትሳፕ ወዘተ ስብሰባዎች ይደረጋሉ። እነዚህ ስብሰባዎች ከራስ ወገን መካከል ትንንሽ ህቡዕ ቡድኖችን ፈጥረዋል። ወጥ ከሆነ አመለካከት፣ ከጠቃሚ አጀንዳ ይልቅ ሀሜት ማሰራጫ፣ መጎሳሰሚያዎች ሆነዋል። ተገናኝቶ ከመናገር ይልቅ በየፊናው ተደባብቆ መጎሳሰምን አስለምዷል። ብዙ የድብቅ ሜሴጅ ግሩፖች ማሕበራዊ ሚዲያውን ለጎሪጥ የሚተያይ አድርገውታል። የተሻለ ነው ከሚሉት ጠይቆ ከመረዳት ይልቅ ሀሜት ከሚያመላልስ አካል ጋር መዶለት የጊዜው ትግል ሆኗል።

መልካም ነገር ሲሰሩ እውቅና፣ መጥፎ ነገር ሲሰሩ ኃላፊነት የሚወሰድበት አይደለም ማሕበራዊ ሚዲያ። ነፃነት እንጅ ግዴታ እምብዛም አይታወቅም። መርህ እምብዛም ነው።

ከሚደርስብን ሰቆቃ መፈወስ አልቻልንም:_

ፌስቡክ የጦር ሜዳ ነው። የሚፈናቀል ወገናችን ስቃይ እናይበታለን። የወገናችን አስከሬን ተሰጥቶበት ይውላል። ሕዝባችን ይዘለፍበታል። ሕዝባችን ላይ አጀንዳ ሲያዝበት እናስተውላለን። ለመበሳጨት፣ ስሜታዊ ለመሆን፣ ለማዘን ፌስቡክን የሚያህል አሰቃቂ ሜዳ የለም። ጦር ሜዳ ላይ ያለ ሰው የማያየውን አስከሬን ሁሉ የምናይበት ጊዜ አለ። ሴራውንም አስከሬኑንም በአንድ ላይ እናየዋለን። የሀሰት ፎቶና ዜና ሲጨመርበት ለማበድ የሚደርስ ሞልቷል። ይህም ሆኖ ሁሌም ፌስቡክ ላይ አለን። በየቀኑ እየታመምን፣ በየቀኑ እየተበሳጨን፣ ብስጭትን የዕለት ተዕለት ጉዳይ አድርገን፣ ተናደን ወገንን መዝለፍን ስራ አድርገን እንውላለን። ከዚህ ሰቆቃ የምናርፈው ወገን ስንዘልፍ የሚመስለን እንኖራለን። ከሁለት ሶስት አመት በፊት በሌላ ላይ የምንጠላውን ስድብና ዘለፋ በወገናችን ላይ እናደርገዋለን። ይህ ዘለን ከገባንበት ፖለቲካ፣ በተለይም የማሕበራዊ ውጥንቅ የያዘን ስሜታዊነት፣ ስድብ፣ ችኩልነትን የምናበርድበት መድረክም እድልም ሳናገኝ በላይ በላይ ስንጨምርበት እብደትን፣ ወገን መዝለፍን እንደ ትግል እንድንቆጥረው አድርጓል።

ለዚህ ሁሉ መፍትሄ:_

1) ሌሎች ላይ ብቻ ሳይሆን ራሳችን ላይም ጭምር ሂስ ማድረግን መልመድ ያዋጣል

2) ትልልቆችን ማየትና መስማት ይጠቅማል

3) ጠላትና ወገን ምን ይሉኛል የሚለውን ማዘውተር

4) መናበብ

5) የራስን ወገን ችግርን በአንድ ጀንበር የሚፈታ ወደር የለሽ አድርጎ ከመሳልም ሆነ የችግር ሁሉ ምንጭ አድርጎ ከመወንጀል መቆጠብ

6) ሚናችን መለየት

7) ትልልቆቹ በመድረክ ይውቀሱ። ቄስና ሸኩ እንዲወቅሱ ይደረግ

በአካል ተገናኝቶ ሂስና ግለሂስ መወራረድ ጠቃሚ ነው።

9) ተቋማት የተበተነውን ለመሰብሰብ ጥረት ቢያደርጉ ወዘተ የሚስተካከል ይመስለኛል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop