በነፃነት ቀን ነፃነት ማጣት !

ከይድነቃቸው ከበደ

ሰብአዊ መብቶች እያንዳንዳችን ሰው በመሆናችን ብቻ የሚገቡን ከሰብአዊነታችን ተለይተው ሊታዩ የማያችሉ መብቶች ናቸው፡፡ መንግስታት እነዚህን በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጣቸውን ሰብአዊ መብቶች ለማክበር ለማስከበርና ለማሟላት በቀዳሚነት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በዚህም መሰረት ኃላፊነት ከፈረሙ ቀደምት አገራት መካከል ኢትዩጵያ ትገኝበታላች፡፡
ይሁን እንጂ የሴቶች ሰብአዊ መብቶች በሚፈለገው መልኩ ተግባራዊ ካለመሆኑ ባሻገር ኢ-ፍትሃዊነት እጅግ የበዛ ነው፡፡ ይህም በመሆኑም እ.ኤ.አ. በ1908 በአሜሪካ ኒወርክ ከተማ በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ይሰሩ የነበሩ ላብአደር ሴቶች ‹‹ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያና የተመቻቸ የሥራ ሰዓት ለሴቶች›› በሚል መፈክር የሥራ ማቆም አድማ በማካሄድ የሴቶች ድምፅ እንዲስተጋባ አድርገዋል፡፡ ይህን ተከትሎ የዓለም ሴቶች በማህበር በመደራጀት ትግላቸውን በማጠናከራቸው የዓለም መንግስታትን አስተሳሰብ በመለወጥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል አገሮች የሴቶች መብት ስምምነት/ኮንቪክሽን/ እንዲፈራረሙ እብይ ምክንያት ሆነዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1910 በኮፕን አገር ከተማ በተደረገው ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የሴቶች ጉባሄ ላይ የመነሻ ሃሳብ በማቅረብ ማርች 8 በየዓመቱ እንዲከበር ያደረጉት ሴቶች ለመብታቸው ያደረጉትን አስታውጾ ለመዘከር ዓለም አቀፍ መድረክ ለማመቻቸት በመቻላቸው ስማቸው በአክብሮት ይነሳል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓሉን ያከበሩት ጀርመን፣አውስትራሊያ፣ሲውዘርላንድ እና ዴንማርክ ለመሆናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከዚሁ የአንድነት ተምሳሌትነት በመነሳት በዓለማ አቀፍ ደረጃ ማርች 8 የሴቶች ቀን በማድረግ ዓለም አቀፍ ስያሜዎችን በመስጠት አገራችን ኢትዮጵያ ጨምሮ በተለያየ መልክ ሲከበር አመታትን እቆጥሯል፡፡ የዘንድሮዉም ማርች 8 አለም አቀፍ የሴቶች ቀን እስከ ዛሬ በአገራችን በተከታታይ የኢትዮጵያ ሴቶች ካከበሩት በዓላት የሚለየው ሁሌም የምኮራባቸው የሰማያዊ ፓርቲ ሠላማዊ ታጋይ ሴቶች የፈፀሙት ገድል ነው፡፡
በአገራችን ኢትዮጵያ የዜጎች መብት በእኩልነት ተጠብቆ በሴቶች ላይ አጥልቶ የኖረው የጾታ ጭቆና እስከዛሬ ምላሽ ያላገኘ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡በተለይ በወያኔ/ኢህአዴግ መንግስት የስልጣን ዘመን የሴቶች ጭቆና እና የመብት እረገጣ በህግ ማቀፍ ውስጥ መሆኑ ይብልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ ይህን ለማለት የሚያስደፍረው የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ ነው በሚባለው ህገመንግሰት የፆታን አድልዎ የሚቀርፍ እና የሴቶችን መብት የሚያመላክት ድንጋጌዎች በውስጡ አካቶ የያዘ ቢሆንም ተግባሪዊነቱ ፕ/ር መስፍን እንዳሉት ‹‹የተፃፈበትን ወረቀት ያህል ዋጋ የማያወጣ ነው››፡፡ ዋጋ አለው እንኳን ከተባለ የትርፉ ተካፋይ የሆኑት የገዥው መንግሰት አጨብጫቢዎች እና የጡት ልጆች ብቻ ናቸው፡፡
በአገራችን መከበር ከጀመረ ከሦት አስርታት በላይ ያስቆጠረው ማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ለሴቶች በሴትነታቸው ከሚደርስባቸው ጾታዊ በደል እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ያስቀረላቸው አንድም ነገር የለም፡፡ በተለይ ከላይ እንደተገለፀው በወያኔ/ኢህአዴግ መንግሰት ሴቶች በህግ እና በመብት ጥላ ስር ከፍተኛ የሰብአዊና የዲሞክራሲ ጥሰት እየተፈፀመባቸው ይገኛል፡፡
እጅግ አስገራሚው ክስተት ደግሞ የኢህአዲግ ሴቶች ሊግ ፣ የሴቶች ፎረም ኢህአዲግ የሚያዘው እና አገዛዙ ያስተባበራቸው በርካታ የሴት ማህበራት ተጠሪነታቸው በቀጥታ ለወያኔ መንግስት ስርአት ነው፡፡ ስርአቱ ደግሞ የመላው ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እና ይሁንታ ያላገኘ መሆኑ ነው፡፡ ነገሩን ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ከመንግስት ድጋፍ ውጪ በራሳቸው ፍቃድና አቅም አንድም የተደራጀ ማህብር የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ እርግጥ ነው የሴቶች የፅዋ እና የእድር እንዲሁም የዕቁብ ማህበራት በአገራችን ለቁጥር የሚታክቱ ነው፤ግን እነዚህ ማህበራት የሴቶችን ሁለንተናዊ ችግሮችን የሚቀርፉ አይደለም፡፡
ለመደራጀት ሳይሆን ለማደራጀት ትኩረት እና ድጋፍ የሚሰጠው መንግሰት በሴቶች ላይ ማላገጥን ስራዬ ብሎ ተያይዞታል፡፡ለዚህም እንደማሳያ ከታችኛው የቀበሌ ባለስልጣን ጀምሮ እስከላይኛው የአገር መሪ የሴቶች እኩልነት እና የመደራጀት መብት በህግ የተጠበቀ እንደሆነ ሳይታክቱ የሚገልፁት ነገር ነው፡፡ይሁን እንጂ የሴቶች እኩልነት እና የመደራጀት መብት ለኢህአዴግ አባልነት እና ቤት ለቤት ቡና እያጣጡ የተነገራቸው መልሰው ከማውራት ከቅያስ ወይም ከጎሮ ከድሬነት ያለፍ ተሳትፎ ከተደራጁበት ሳይሆን ከደራጃቸው አካል ያተረፉት ነገር የለም፡፡ ከላይ የተጠቀሰው አሳብ ለመረዳት እና ለመታዘብ ብዙ መራቅ አያስፈልግም በህገመንግስቱ መሰረት ተደራጅተዋል የተባሉ ማናቸውም እንዲሁም በየትኛውም ቦታ የሚገኙ የሴት ማህበራት ከመንግሰት ተፅኖ ውጪ ላለመሆናቸው ከማህበራቸው የስም አወጣጥ ጀምሮ ተግባራቸው በመመልከት በቀላሉ ማህበሩ እና ማህበርተኞችን እነማን እንደሆኑ ለመረዳት ይቻላል፡፡
ለዚህ ፁሑፍ መነሻ የሆነው አሳብ ዘንድሮ ተከብሮ ሳይሆን ተደፍሮ ለማለት በሚያስችል ሁኔታ ማርች 8 መሰረት ያደረግ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የባለፈው እሁድ ማርች 8 አስመልክቶ የሴቶች 5 ሺህ ኪ.ሜ ሩጫ ውድድር ተካሂዶአል፡፡ በውድድሩ ላይ ቁጥራቸው የበዛ ሴቶች ተሳትፈዋል ፤ከተሳታፊዎቹ ብዛት ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ በአነስተኛ እና ጥቃቅን መንግስት ያደራጃቸው ሴቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሴቶች አደባባይ ይዘው የወጡት አሳብ ጥቃቅን መሆኑ በእርግጥም ማህበርተኞቹ ምን ያህል አንድ ለአምስት ‹‹እደተጠረነፉ›› የሚያሳይ ነው፡፡ የጉዳዩ አሳሳቢነት የሚጀምረው እነኚህ ጢቂት ‹‹የተጠረነፉ›› ሴቶች በነፃነት ቀናቸው ነፃነት የተነፈጋቸው መሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እሩጫው ላይ የተሳተፉት በራሳቸው ፍቃድ ሳይሆን በድረጅታቸው ትዕዛዝ ነው ሊያስብል የሚያስችል የተለያየ ‹‹ልማታዊ›› የሆነ መፈክሮችን ሲያሰሙ ተደምጠዋል፡፡በመንግሰት ልዩ ድጋፋ የተደረገላቸው እነኚህ ሴቶች ለሚደግፉት ሳይሆን ለተገደዱበት ዓላማ የመሰላቸውን መፈክር እና ቀረርቶ በማሰማት እንዲሁም የተለያዩ ፖስተሮችን በመያዝ በዕለቱ ሲንቀሳቀሱ ታይተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ለመንግስት ደጋፊዎች የተፈቀደው ለሌሎች ለመንግሰት ተቃዎሚ ሴቶች ፖሊስ ያደረገው ክልከላ እና እስራት ክስተቱን አስገራሚ ብቻ ሳይሆን አሳሳቢያ ደርገዋል፡፡ እንደሚታወቀው ማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ነው፤ ይህ ቀን ሴቶች ተሰባስበው ከበሮ ይዘው የሚደልቁበት ቀን ሳይሆን ለነፃነታቸው ቀደምት ሴቶች ያደረጉትን ተጋድሎ በመዘከር ያሁኖቹ ሴቶች ለበለጠ እኩልነት እና ነፃነት በጋራ የሚቆሙበት የቃል ኪዳን ቀን ነው፡፡ ይህም እንደሆነ የተረዱ ሴቶች በነፃነት ቀናቸው ስለነፃነታቸው ከፍ ባለ ድምፅ ሲዘምሩ ማየት ምንኛ መታደል ነው ! ይህን በድፍረት ላደረጉት የሰማያዊ ፓርቲ ወጣት ሴቶች አድናቆት ሊቸራቸው እና ድጋፍ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ሴቶች በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ በአደባባይ ታፍሰው ለእስር የበቁት በእኔ ዘመን ይህ የመጀመሪያ ነው ፡፡የኔ ዘመን ደግሞ 23 ዓመት ሙሉ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ የበላው ጅብ አልጮው ብሎ ተቸግረን የከረምንበት ወቅት ነው፡፡ እርግጥ ነው ይህ የሆነበት ምክንያት ለማወቅ እና ለመዘርዘር ሰፊ ጥናት ያስፈልጋል፡፡ የችግሩ አሳሳቢነት እንደተጠበቀ ሆኖ እንቢ ለነፃነቴ በማላት አደባባይ በመውጣት የሰማያዊ ፓርቲ ወጣት ሴቶች ‹‹ እኔ የጣይቱ ልጅ ነኝ ! እስክንድር ይፈታ ! እርዮት ትፈታ ! አብበከር ይፈታ ! አንዱአለም ይፈታ ! መብራት እና ውሃ ናፈቀን ! ፍትህ እንፈልጋለን ! ›› እና የመሳሰሉትን መፈክር በልበ ሙሉነት በማሰማት ያሳዩት ቆራጥነት ታሪክ መቼም የሚዘነጋው አይደለም፡፡ በይበልጥ ደግም በዚሁ የፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ብቻ ለእስር መዳረጋቸው የመንግስት ስርዓት ምን ያህል አምባገነን እና ጨቋኝ እንደሆን በግልፅ የሚያሳይ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ብአዴንና ሌሎቹ ኢትዮጵያን በማጥፋት ላይ ከሚገኘው ሕወሃት ጋር እየተባበሩ ያሉት ወገኖች በድንቁርና ነው
Share