ጀግንነት የሁለት ፊደላት ፍጥረት ነው ። ሥራ!

(ልክ የዛሬ ወር ነበር ረ/አውሮፕላን አብራሪ ሀይለመድህን አበራ ሲዊዘርላንድ – ጄኔባ ላይ የሠራው – ጀግንነትን)

ሥርጉተ ሥላሴ (ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ)

ዕለተ ሰኞ 17.03.2014 ብሄራዊ ቀኔ ቅኔዬም ነው – ለሥርጉተ። ነገ ደግሞ በብሄራዊ ደረጃ እንዲከበር ይሠራበታል። የነፃነት ቀን በአዬር መንገዳችን ልዩ ምልክት ይሆናል። ከሥራ የተፈጠረው ጀግንነት መጠነ ሰፊ አክባሪም በቂ አድማጭም አለው። በጣም በእርግጠኝነት። ቀለሙ ሰንደቁ ነውና። ረዳት አውሮፕላን አብራሪ ሀይለመድህን አበራ ተገኘ የፈጸመው ተግባር በእግረመንገድ የተከወነ ሳይሆን በውስጡ ባለው ፈቃደ እግዚአብሄር ነው። ገሃዱ ይህ ነው።
(„የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል። እግዚአብሄር ግን አካሄዱን ያቃናለታል። ምሳሌ ምዕራፍ 16 ቁጥር 9)
ወጣቱ ሀይለመድህን አበራ ውስጡ የተሰማውን ጥልቅ ስሜት በሰለጠነ ህሊና ገለጸ። ይህ ደግሞ ክህሎት ነው። ስሜት ለሰጠው እውነት ለመገዛት ወስኖ ፈጣን ምላሽ ሰጠ። የገለጸውም ለሰላማዊ የነፃነት ትግል ትርጉም በሚሰጥ ሁኔታ ነበር። ከዚህ በኋላ ነው ቴክኒካል ነገሮችን ማዬት የሚቻለው። ያስተዋለውን እውነታ ከምክንያታዊ ጭብጦች ጋር አጋብቶ አበለጸገው። ስለሆነም ክህሎቶ በሥነ – ጥበብ ቁመትና ወርድ መለካት አለበት እላለሁ እኔው ሥርጉተ ሥላሴ። በሊቀ -ሊቃውንታት ዓይንም ሊዳሰስ ይገባዋል ባይም ነኝ። የበራ አፈፃፀሙ በራስ የመተማመን ጉልበቱ ነበርና። ረዳት አውሮፕላን አብራሪ ሀይለመድህን አበራ የተነሳው ከገሃዱ አለም ማዕከላዊ ጭብጥና ከነባራዊ ሁኔታውም ነው። በዚህ ሂደት የብዙኃኑ ስሜትና ፍላጎት በአኃቲነት በውህደት ተጋብተዋል።
ሙያ በሥልጠና የሚገኝ ቢሆንም አገልግሎቱ ለህዝብ ስሜት ቅርብ ሲሆንና ማደማጥ ሲችል፤ የሙያው ክህሎት ሆነ ብቃቱ ውስጥን ገላጭ ስለሚሆን ውጤቱን ዓይነ – ገብ ያደርገዋል። ወጣት ሀይለመድህን አበራ እሱ ራሱ የገህዱ ዓለም ታዳሚ በመሆኑ ቅርበቱን የበለጠ ጉልህ ስለሚያደርገው እርምጃው የለማ ትራስ ሆነ ድልዳል አለው። በሥልጠና ያገኘው የክብር ስያሜም ከተግባር ሥራው ጋር ሆኖ ቋሚ ትምህርት ቤት ሊሆን መቻሉ በቂ አድናቂና ቋሚ የድርጊቱ አድማጭ እንዲያገኝ ጉልበት ሆኖታል።
ስሜቱን ኮርኩሮ ለዚህ የላቀ ተግባር ያበቃው ሚስጢር አዳራን ከብዙኃን ውክል ስሜት ጋር ሚዛን ላይ አስቀምጦ የደፋውን እርምጃ የችሎቱን ድምጽ መውሰዱ ነው። ዬሚመጣውን ማናቸውንም መስዋዕትነት አዝናንቶ ለማስተናገድ የቆረጠው የህሊናውን አድማጭነት፤ እንዲሁም ከወገኖቹ የሚያዬውን ብቻ ሳይሆን መሆን የሚችለውን የውስጡን ፍላጎት አድምጦ መወሰን መቻሉና ከዛ ላይም መነሳቱ የአቅሙን ብቃት በጉልህ ያብራራል። የብልህነቱን ጥልቀት ለማዬት አጅግ በርካታ የዝምታ ክንውኖችን ማንሳት ቢቻልም ጸጋውን አውቆ በጥዋቱ ተግባር ላይ ማዋሉ ዘመናትን ሊያሻግር የሚችል ዓምደ ተመክሮ ነው – ለእኔ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የፋኖን ባህሪ፣ ሂደትና እድገት አስመልክቶ - አንዱ ዓለም ተፈራ

ጀግናዬ ሀይለመድህን አበራ ዛሬ በውል ሊታዬን ያልቻለም ሚስጢር በውስጡ እንደ ጸነሰም ለእኔ ይሰማኛል። በጥሞና የመረመረው፤ የገጠመኝ ዘለላዎቹን ሁሉ ንጹህ ጥሬ ሀብቱ እንዲሆኑ አድርጎለታል። ፊድ ባኮቹ ከውጣ ውረዱ ማሳ ያፈሰውን ትልቁና ብቸኛ የወርቅ እንክብል በመሆናቸው „እኔስ? ምን?“ የሚሉትን የህሊና ጥያቄዎች፤ የግራ፣ የቀኝና የማህል ዳኛ፤ እንዲሁም አቃቢ ህግ፤ በተጨማሪም ጠበቃ ሆኖ በሙሉ ልብ ብይን ሰጥቶበታል። የተከደነ ሲሳይ ይሏችኋል ይህ ንጡርነት፤ መረቅነት፤ ክውንነት ነው። ፍላጎቱን ከመንፈሱ ጋር፤ ስሜቱን ከተፈጥሮው ጋር፤ ድርጊቱን ከኃላፊነቱ ጋር አስማምቶ ሙቀት ሸልሞናል። ቅዝቃዜና ብርድ በእሱ የጭምትነት ተልዕኮ የሉም። ጥበቃ አስቀድሞ የደነገገላቸው ተግባራቱ ጥናታዊና ምርምራዊ ናቸው። ፍልስፍናዊና አምክኗዊ ማለትም ይቻላል።
„አሻምን“የገለጸበት መንገዱ ከዚህ በፊት ያልታዩ፤ ፈጽሞም ሊታሰቡ የማይችሉ ክጥፋትና ከትርምስ የዳኑም ናቸው። ይህ „ፍቅር“ የሚባለው የመስዋዕትንት የቆረጠ አርበኛ የሚሻ የኑሮ፤ የህይወት፤ የነፃነት፤ የመብት፤ የብሄራዊ ግዴታ አስኳል ታዬ። አውነታዎች ከሚታዩ ገጠመኞች አውድማ
ለሰንደቅዓላማ፤ ለዳር ደንበር፤ ለህግ የበላይነት፤ ጧሪ ጠዋሪ ላጡ የአደራ ውርስና ቅርሶቻችን ሁሉ ከፍቶ ገብሯል። ወጣቱ ሀይለመድህን አዬር ላይ ሆኖ ከአንዱ ገጸ ባህሪ ወደ ሌላው ገጸባህሪ ሲሸጋገር በቁጥብነት፤ በድንበር፤ ልኩን ለክቶ ሊገለጽ በማይችል ርጋታና በስክነት፤ ሥራን ከግድፈት በብልህንት ነጻ በማውጣት ጀግንነትን ነፍስ ዘራበት። ላላጣጠመው የወጣትንት ቀንበጥ ህይወት መራራን ጽዋ በፍጥነት ቀድሞ እራሱን ሰጠበት። ከምንም ነገር ጋር ንክኪ የሌለው „ፍቅር“ ማለት ይህ ነው።
እኛ አብዛኞቻችን የተሳነን ደግሞ ይህን ማድረግ ይመስለኛል። የምንፈልገውን ሆነ የምንወደውን ነገር እራሱ በቅጡ የማወቅም ተዛነፍ ዕያታ ነው ያለን። ፍላጎታችንም በነፍሳችን ውስጥ ተጠላይ ነው ወይንም ጭሰኛ። አብዛኛውን ጊዜ ጥግና ሳቢያ መፈለግ። ይህም ማለት እኔን የሚኮለኩሉ ጉዳዮች በመጡ ቁጥር ወይ ኮማ ውስጥ መሆን ወይንም ኩብለላ ያሰኘኛል። በዬፌርማታው መሽሎክ። ስለሆነም ፍላጎት ሲባዝን፤ ወይንም ሳይረጋ ወይንም አፈር ሳይለብስ ክው ብሎ ደርቆ በኖ ይቀራል። ፍርፋሪና እንጥፍጣፊ የተሰናበተበት ምኞት። ምክንያቱም ቋሚ ፍላጎትን በውስጥ የማነፅ፤ በጽናት አበክሮ የማበቀል ብቃቱ ውሽልሽል ስለሚሆንም ነው። ልጅም፣ ታናሽም የሆነው የትናንት አንድ ፍሬ „ሥራ“ በአጽህኖትና በተደሞ የሰበከው ይህንኑ የውስጥ ግድፈታችን እንድናርም ነው። አንድ ፍጥረት የ30 ዓመት ወጣት ትንፋሽን ሳቢና ጉልበታም አቅም ኖሮት እንዲህ የዓለም አጀንዳና ፊኖሚና ለመሆን በቃ። በቃ! ያበቀለው የሥነ – ህይወት ዋርካ። እራሱን ለፍላጎቱ የማስገዛት ጥንካሬውም አይነታ ብሂል ነው የመሆን አንጎል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ግልጽ ደብዳቤ!

ገና በጋሜነት በኩብልና፤ እጅግ በሚያሳሳው አፍላነት ዕድሜው ለተሰጠው ጸጋ ራሱን የሚያስገዛ ፍጡር ፍላጎቱና አሱ ህይወትን በፍጥነት መረዳቱ ብቻ ሳይሆን፤ በጥልቀት የማጤን፤ ስለነገ ብቁ ግንዛቤ የመኖር ብሩህ ህሊና ላላቸው ፤ እንደ ረዳት አውሮፕላን አብራሪ ሀይለመድህን አበራ ተገኘ ላሉ ብቻ የተሰጠ መክሊት ነው። ድርጊቱ ከገሃዱ ዓለም ጭብጥ ገዝፎ የወጣ በመሆኑ ጥልቅ ተግባሩ ጀግና ሊያሰኘው መቻሉ ቢያንሰው እንጂ የሚበዛበት ሊሆን ከቶም አይገባም። ድምጽን በዳጣ አንባገነን ለተገፋ ብዙሃን ህዝብ ለዘመኑ ፍትህ ርትህም ነው። በዚህ ሥም ነገ ሚሊዮኖች ይጠሩበታል። ታሽቶና ነጥሮ የወጣው ተግባሩ ውበቱ ያለው ከእውነታው ማዕከል በመሆኑ ፈተናን የመርታት አቅሙም የዚያኑ ያህል ጉልበታም እንደሚሆን ባለሙሉ ተስፋ ነኝ።

ህይወት ወይንም መኖር ሲባል በማህበረሰቡ የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ በንቃትና በባለቤትነት ስሜት መሳተፍ ማለት ነው። በሌላ አገላለጽ አንዲህ ላቅ ብሎ ለተሰጣቸው ሰዎች የህብረተሰቡ ችግር፣ ሰቆቃ ሆነ መከፋትም ከሌላው የህብረትሰብ ክፍል ይልቅ ቀድሞ ያሳስባቸዋል – ይታያቸዋልም። ለዚህም ነው መግቢያ ላይ ሥራው በሥነ – ጥበብ ዓይን ሊታይ ይገባዋል ያልኩት። ስለሆነም ሃይላችን የህዝባችን የመንፈስ ውጥረታዊ ፍርሃት፤ ዬየጓዳው ጃንቦ ስጋት፤ የተስፋ ድርቀት፤ ዬህልም ርቀትን በጥንቃቄ በማስተዋል፤ መቼቱንም አዋቅሮ ለራሱ ሳይሰስት፤ ግጭቶችንም በማስማማት ለወቅቱ ዬተፈቀደለትን የሙሴነት ተስጥዖ ሳያልፈው ወይንም ሳይዘለው ወይንም ሳያፍነው በመሆን በዝምታ ድባብ ቀደሰው። ስለዚህ ለእኔ ከጀግንነትም አልፎ የህይወቴ ነው ማህደሬም።
ወጣት ሀይለመድህን የህውከት ጦሮ የሚንጠውን አዬር ራሱ ነፃ አውጥቶታል። ማህል ላይ የተገተሩ ዥንጉርጉር፤ ስርክራኪ፤ ሸውራር ተዛነፍ ፍላጎቶችን ሁሉ በዝምታ በማረቅ፤ መስመራቸውን በፍጥነት እንዲያስተካክሉ በማድረግ የኃይል አሰላለፉን እንደ ገና ሪባይዝ በማደረግ ጥንቃቄና ጥራትን አውጆለታል። እንዲሁም ካለገላጋይ ከቁንጨጮ ላይ ወጥቶ የሚያተራምሰውን የግል ኢጎም ዘቅዝቆ አንጠልጥሎታል። ለሌላው መኖር – ክብርም ለህዝብ ፍላጎት መቅድምነት በማለት ወጤታማ ተግባር ከውኗል። ስለሆነም ጀግናዬ ሀይለመድህን አቅምን ሳያባክን የአደራን ጥሪ „እሺ“ ብሎ ስለፈቀደ እንሆ ተወደደ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሳኦል በሽታ - አስቻለው ከበደ

እንደ መቋጫ – „ጀግናችን አጀንዳችን“ ብዬ በጻፍኩት ላይ „አመላችሁ ነው። የሰሞናት ነው፤ የወረት ነው“ የሚል አስተያዬት ከአንድ የጹሑፌ ታዳሚ አንብቢያለሁ። የተከበሩ የሀገሬ ልጅ ጹሑፌን ጊዜ ወስደው ስላነበቡልኝ ከፍ ያለ ክብር አለኝ። አመሰግነወትምአለሁ። ልነግረውት የምሻው ቁምነገር ግን አለኝ። ያዳምጡኝ። ሥርጉተ ሲዊዘርላንድ እያለች የማነን ጎፈሬ ታበጥር ይመስለወታል? ሥራዬ ምን ሆነና?! „ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት“ መደበኛ የህይወቴ አጀንዳዎች ናቸው። ጠረኖቼ ትንፋሾቼም መሆኑንም ልግለጽልዎት እሻለሁ። በጣም በእርግጠኝነት ልነግረዎት የምሻው ለእኔ ወጣት ሀይለመድህን መስቀሌ መሆኑን ነው — ተግባባን ወዳጄ።
ከሚያዚያ 10 ቀን 2014 ጀምሮ ደግሞ በቅኔው ንጉሥ በጸጋዬ ድምጽ ራዲዮ ፕሮግራሜ በዬ15 ቀኑ ቋሚ ዓምድ ይኖረዋል „የተስፋ ማህጸን“ www.lora.ch.tsegaye. ይጠብቁኝ። ግን እርሰዎ „የኢትዮጵያ ምድር ጦር፤ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል፤ የኢትዮጵያ አዬር ኃይል፤ ኢትዮጵያን ያስቀደሙ የሲቢክስ ማህበራት፤ ድርጅቶች ሁሉ በነቂስ እዬተለቀሙ ወያኔ በዱድማ ህሊናው ሲንዳቸው ከቶ የት ነበሩ?!“ የአንጋፋው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ሙሴ ሰማዕት አሰፋ ማሩ በጠራራ ጸሐይ በባሩድ ሲንድ —- በደል አይረሳም ያገረሻል እሺ። ይበሉ እንደ አውሮፓውያኑ ሰዓት አቆጣጠር ከ15 እስከ 16 ሰዓት ሚያዚያ 10.2014 አዬር ላይ እንገናኝ። ለሚመድቡልኝ ጊዜም በቅኑ መንፈስ የቅድሚያ ምስጋና ተላከ – ለእርሰዎ- ለጌታው።

ውዶቼ የእኔዎቹ ብትክትኮች፤ አፋፍ ላይ የተንጠለጠሉ፤ ማጣፊያ ያጠራቸው፤ እንደሚሉን ሳንሆን እንደ ፍላጎታችን ጠንካሮች እንሁን። ቀዳዳውን ሁሉ የምናሸፍንበት ዘመን መሆን አለበት። በተለይም ሴቶች፤ እሺ ልዕልቶቼ። ክብረቶቼ የሀገሬ ልጆች ዛሬ በአጭር ትጥቅ ዕይታዬን አጋርቼ ሽው ልል ነው …. የጀግንነት የአንደኛ ወሩ „የተስፋ ማህጸን“ ዝክረ ሀይለመድህን በዚህ መልክ ማህሌት ተቆመለት። ሙሉቀን ከድንግል እግር ሻማ ይበራል። ወገኖቼም ፌስቡካችሁን ቲውተር አካውንታችሁ በጀግናቹሁ አንቆጥቁጡት። ፈቅዳችሁ ለሰጠችሁኝ ጊዜ አከበርኳችሁ። ወደድኳችሁም። መልካም የተግባር ጊዜ – ለሁላችንም። ሥራችን – እንሥራ!

እግዚአብሄር ስለሚሰጠን የመንፈስ ማረፊያ ጀግና አድናቆታችን ለዘለአለም ነው!
ፈተናን ከመፈጠሩ በፊት አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጥር ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

2 Comments

  1. Are you sick and delusional. Are you attempting to read what is not written. The guy(co-pilot) has a paranoid personality, nothing more nothing short. He is a sick person who needs medical attention (a mental asylum and not a political asylum) . Go ask your mummy to tuck you in and keep on dreaming that the sick person of the EAL is the Don Quixote of Ethiopia.

  2. ጀግና የሚያሰኝ ምንድነው እስቲ ንገሩን ጠላት ገድሎ ነው? ማርኮ ነው? ጓደኛውን ከጠላት ታድጎ ነው? አገሩን የሚያኮራ ነገር ሰርቶ ነው? የህዝብን ንብረት እና ተሳፋሪዎች ወደ አልተፈለገ ቦታ መውሰድ ጀግንነት ከሆነ እውነትም የጀግና ትርጉም ጠፍቶባቹሃል ብቻ ሳይሆን ተምታቶባችሃል ውድ አገራችን አለኝ የምትለውን ተቅዋም ጥላሸት በመቀባት ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ ነበር የተንቀሳቀሰው ባይሳካለትም ይህ ነውረኝነት ነው እንጂ ጀግንነት አይደለም እሱ የበላበትን ወጪት ሰባሪ ብቻ ሳይሆን ከሃዲ ነው የምታደንቁት ከልብ ከሆነ (የአይጥ ምስክር ድንቢጥ እንዲሉ) ለ20 ዓመት የሚሆነውን ስንቅ አዘጋጁለት

Comments are closed.

Share