የመስጊድ ኢማሞች የሚሾሙት በመንግስት በራሱ መሆኑን መንግስት አመነ!!!

ሕዝቡ ሳያውቀው ሕገ መንግስቱ ተቀይሮ ይሆን?

መንግስት ‹‹እኔ በሾምኳቸው የመስጊድ ኢማሞች (አሰጋጆች) አልሰገዳችሁም›› በሚል ንጹሀን ሙስሊም ግለሰቦች ላይ ክስ ያቀረበበት ሰነድ ተገኘ!!!
ከፍርድ ቤት የውስጥ ምንጮቻችን የተገኘውና በፌደራል አቃቤ ህግ አቶ ብርሀን አለባቸው ፊርማ በታህሳስ 4/2006 የተጻፈው ይኸው የክስ ሰነድ ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አዲስ ከተማ ምድብ የቀረበ ሲሆን ሁለት መስጂድ ውስጥ በኢማምነት ያሰገዱ ሙስሊም ግለሰቦችንም ተከሳሽ አድርጎ አቅርቧል፡፡

ሰነዱ እጅግ አስገራሚውን ክስ ሲያብራራ አንደኛና ሁለተኛ ተከሳሽ በቁባ መስጂድ የአህባሽ ተከታዩን ኢማም ተከትሎ ለመስገድ ፍቃደኛ ያልሆነውን ህዝበ ሙስሊም ማሰገዳቸውንና በዚህ ተግባራቸውም ‹‹የሃይማኖት ሰላም ስሜት›› መንካታቸውን ገልጿል፡፡ ቃል በቃልም ሁለተኛ ተከሳሽ ‹‹መንግስት በሾመው ኢማም ቦታ ላይ በመቆም ሳይፈቀድለት የእነሱን ተከታዮች በማሰገድ ሰላማዊው ሙስሊም እንዳይሰግድ በማድረግ…›› ወንጀል መስራቱን ገልጿል፡፡
እስካሁን ‹‹መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም የሚለውን ህገ መንግስታዊ መርህ አልጣስኩም›› እያለ ሲከራከር የቆየው መንግስት በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲጋለጥ የቆየ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን አሁን ግን መከራከሩ እንደማያዋጣው አውቆ በማን አለብኝነት ‹‹እኔ የሾምኩትን ኢማም አልተከተላችሁም›› በሚል ፍርድ ቤት ችሎት ማሰየም መጀመሩ ‹‹ህገ መንግስቱ አንድ ቀን ይከበር ይሆናል›› ለሚሉ ወገኖች ትልቅ መርዶ ይዞ መጥቷል፡፡ የአገሪቱ ‹‹የፍትህ›› አካላት የሆኑት ዳኞች እና አቃቤ ህጎች መንግስት የሾመውን ኢማም ተከትላችሁ አልሰገዳችሁም›› በሚል ኢ-ህገ መንግስታዊ ክስ ላይ በይፋ መሰየማቸውም ለሀገሪቱ የፍትህ ስርአት የቁልቁለት አዘቅት መሆኑ አያጠራጥርም!
ህዝበ ሙስሊሙ ከ1987 ጀምሮ በመንግስት ሹመኞች ቁጥጥር ስር የዋለውን መጅሊስ ተቀባይነት የነሳውና ለመሪ ተቋሙ መመለስም እስካሁን እየታገለ ያለው መጅሊሱ የመንግስት ካድሬዎች መጫወቻ በመሆኑ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን በመጅሊሱ ስም የሚካሄዱት ሁሉም ተግባራት በመንግስት የሚሾፈሩ መሆናቸውም የአደባባይ ምስጢር ሆኖ ቆይቷል፡፡ የዛሬውን ዜና ልዩ የሚያደርገው ግን መንግስት ‹‹ሽብርተኝነት›› እና ሌሎች የማስመሰያ ስሞች ሳያስፈልጉት ‹‹እኔ የመረጥኩልህን እምነት አልተከተልክም፤ እኔ በሾምኩልህ ኢማም አልሰገድክም›› ሲል በግልጽ በሰነድ ጭምር ምስክር ጠርቶ ችሎት ፊት ሰዎችን ማቆሙ ነው፡፡ ይህም ይፋ መውጣቱ መንግስት የደረሰበትን የሃይማኖታዊ አፈና ደረጃ ለመላው ዓለምና ለሰብአዊ መብት ተከራካሪ ተቋማት ይበልጥ ይፋ የሚያደርግ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡
አዎን! የመንግስት ሃይማኖታዊ ጭቆና በምንም መልኩ መደበቅ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ይህ ግን ከሁለት አመታት በላይ ኢ-ፍትሀዊነትን ሲታገል የቆየው ህዝበ ሙስሊም የበለጠ በትግሉ ላይ እንዲጠናከር የሚያደርገው እንጂ ተስፋ የሚያስቆርጠው አይደለም፤ ህዝብ ተስፋ አይቆርጥም! ህዝበ ሙስሊሙ የሃይማኖት ነጻነቱ እስኪከበርና የዜግነት መብቱን የሚጋፉ አሰራሮች እስኪቀረፉ ድረስ በጽናት መታገሉን ይቀጥላል፤ ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለምና!!!
ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ህብረት ለአገራችን ኢትዮጵያ የህልውና ዘመቻ ህብረት - ዘመቻ ህልውና
Share