March 5, 2022
19 mins read

የዩክሬን ወረራ (በአንድ ኢትዮጵያዊ ዕይታ) – አንዱ ዓለም ተፈራ 

11rrreeeቅዳሜ፣ የካቲት ፳ ፮ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፬ ዓ. ም. (03/05/2022)
አንዱ ዓለም ተፈራ፤

አንዳንድ ጊዜ፤ በፖለቲካ ዓለም ውስጥ፤ የአንድ ጉዳይ ክብደት በጣም ያየለ ይሆንና፤ የሌሎችን ጉዳዮች መሳካትም ሆነ መኮላሸት ዋጋ ሳይሠጡ፤ በጭፍን ያንን አንድ ጉዳይ ብቻ የሞትና የሽረት አድርጎ መሰለፍ አለ። ይህ ምርጫ በግለሰቦችና በስብስቦች መካከል በየጊዜው የሚታይ ክንውን ነው። ምን ጊዜም ግን፤ ከምናቀነቅነው ጉዳይ በላይ፤ በዓለም ዙሪያ ያለነውን ሰዎች በሙሉ የሚነካ ሰብዓዊነት መኖሩን መዘንጋት የለብንም። ለዚህ ነው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እምነት፤ ሰብዓዊ መብቶች ሁሉን አቀፍና ምንጊዜም መነካት የሌለባቸው! ተብለው የተቀመጡት። እኛም እኒህን መብቶቻችን ብለን በየጊዜው አንግበን እናውለበልባቸዋለን። ለዚህ ጽሑፍ መነሻው የሩሲያ ዩክሬንን መውረር ነው። ይሄንን ወረራ በተመለከተ ሁለት የአመለካክት መስመሮች በኛው መካከል ብቅ ብለዋል። የመጀመሪያው ወረራውን የሚቃወመው ክፍል ሲሆን፤ ሌላው ወረራውን ትክክል ነው! ብሎ የሚቀበለው ነው። እኒህን ሁለት መስመሮች ትኩረት እንሥጣቸው።

በመጀመሪያው መስመር ግንዛቤ፤ በሰላም የምትኖረዋ ዩክሬን የተደረገባት ወረራ፤ “ትክክል አይደለም!” ብሎ ይፈርጃል። ዩክሬን የተባበሩት መንግሥታት አባል የሆነች አንድ ነፃ አገር ናት። ፵ ሚሊዮን ሕዝብ ይኖርባታል። በውስጧ ከዩክሬናዊያን ሌላ፤ የሩሲያ ትውልድ ያላቸው ዩክሬናዊያን አሉ። ልክ በኦጋዴን ሶማሊያዊ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉት ሁሉ። ኬንያም ውስጥ ሶማሊያዊ ኬንያዊያን እንዳሉት ማለት ነው። ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ስትነጻጸር፤ በጣም ትንሽና ደካማ አገር ናት። የዚህ ግዙፍ አገር የሆነው የሩሲያ መሪ፤ ብላዲሚር ፑተን፤ ከመሬት ተነስቶ፤ በአገሪቱ ደቡብ ምሥራቅ በኩል በሚኖሩት ሩሲያዊያ ዩክሬናዊያን ውስጥ፤ የመንግሥት ተቃዋሚ ቡድን አቋቁሞ፤ የሽምቅ ውጊያ እንዲያደርጉ ይደግፋቸዋል። ይህ ረዘም ላለ ጊዜ ቆይቷል። ከስምንት ዓመታት በፊት፤ ይሄንን አሳቦ ክሬሚያ የተባለችውን የዩክሬን ክፍል፤ ቆርጦ በመውረር፤ የሩሲያ ግዛት ውስጥ ያጠቃልላታል። አሁን ደግሞ፤ “ዩክሬን! ወደ የስሜን አትላንቲክ የውል ድርጅት (ኔቶ) መግባት የለብሽም!” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ይሠጣታል። ባለፈው፤ “የእብሪተኞች በረት፣ የጉልበተኞች ሜዳ” በሚል ርዕስ፤ ይሄንን ጉዳይ የሚመለከት ጠቅለል ባለ መልኩ አንድ ጽሑፍ አውጥቼ ነበር። ከዚህ የተለየ አቋም የያዙ ግለሰቦች፤ ወረራውን ትክክል ነው! በማለት ጽሑፍ አውጥተው ተመለከትኩ። መሠረታዊ ግንዛቤንና የፖለቲካ መስመር ማራመድን፤ ለይቼ እመለከታለሁ። የኔ አመለካከት የሚሰፍረው፤ ወረራውን በሚያወግዘው ሰፈር ነው።

እንግዲህ የዚህ መስመር አቀንቃኞች፤ ዩክሬን አርፋ በተቀመጠችበት ቦታ፤ ሩስያ ግዙፍነቷን መከታ አድርጋ፤ ያለ አግባብ ትንሿንና ደካማዋን አገር ወረረች! የሚል ነው። ዩክሬን የኔቶ አባል አይደለችም። ለመሆን ምኞት አላት፤ ነገር ግን መሟላት ያለባቸው ብዙ ነገሮች ስላሉ፤ አባል ለመሆን ብዙ ጊዜ ይፈጅባታል። ይቺ ትንሽ አገር፤ እንኳንስ በሩሲያ ላይ ጠብ ልትጭር፤ እኒህ ሩሲያ የፈጠረቻቸውን ሽምቅ ተዋጊ ተቃዋሚዎቿን እንኳ ማስወገድ አልቻለችም። መሪዋና ሕዝቡ ባጠቃላይ ባልጠበቁበትና ባልተዘጋጁበት ሰዓት፤ ሩስያ ወረረቻቸውና ብዙ በደል አደረሰችባቸው። አሁን ሩሲያ፤ የዩክሬን ከተሞችን መቆጣጠር ይዛለች። የሩሲያ መሪ፤ ቭላዲሚር ፑተን፤ በራሱ የሠራዊት መሪዎችና ሚኒስትሮች እንኳ በጣም የተፈራና፣ አንድ ብቻውን አዛዥ ናዛዥ አምባገነን መሪ ነው። ዛሬ በዩክሬን ላይ የተከሰው፤ ፑተን ፈልጎና መርጦ የወሰነው ጦርነት ነው። ደካማና ትንሽ አገርን በመውረር፤ ፑተን ለአውሮፓና አሜሪካ ዛቻ ለመላክ ወደደ። አውሮፓም ሆነ አሜሪካ፤ ይቺን አገር ከሩሲያ ወረራ አላዳኗትም፤ አይድኗትምም! የኔቶ አባል አይደለችም። ፑተን፤ “አሜሪካና አውሮፓ፤ ሩሲያን ለመውረርና ለማጥፋት፤ ዩክሬንን መስፈንጠሪያ ሊያደርጓት አቅደዋል!” የሚል ወንጀል ነው በዩክሬን ላይ የሰነዘረው። የፈጠራ መረጃ ማቅረብ ለኬጆቢ ምልምል መቸ ይሳነዋል! በፑተን እምነት፤ በሩሲያና በኔቶ አባል አገራት መካከል ያሉት የቀድሞ የሩሲያ ተነጂ አገራት፤ ሩሲያን ከኔቶ ወረራ የሚከላከሉ አጥሮች እንጂ ነፃነት ያላቸውና የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው መወሰን የሚችሉ አገሮች አይደሉም።

ዛሬ ፑተን በዩክሬን ላይ ከፍተኛ ጥፋት እያደረሰ ነው። እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ፤ የዩክሬናዊያንን ስደትና ዕንግልት ስመለከት፤ የፋሽስቱ ጣሊያን አገራችንን ለሁለተኛ ጊዜ ዘምቶ፤ ለአምስት ዓመታት በወረራው ጊዜ ያደረገው ግፍና በደል ከፊቴ ተደቀነ። ጣሊያን በኢትዮጵያዊያን ላይ የናፓልም ቦምብ ሲያዝነብ፣ በባዶ እግራቸው፤ ለጣሊያን ሆዳቸውን የሸጡ ባዳዎች ጠርሙስ ስብረው በከሰከሱበት መንገድ ጣሊያንን ሊወጉ ጀግኖች አርበኞቻችን ለወራት ሲጓዙ፣ ፋሽስቱ አርበኞቻችንን እያደነ ሲገድልና ያልቻላቸውን እያታለለ ሊይስገባ ሲሞክር፣ የገደላቸውን በሰቀለበት ቦታ አንጠልጥሎ ሲደነፋ፣ አንገታቸውን ቆርጥ ይዞ ፎቶ ሲነሳ፣ በትሬኮላታ የሰፈረበትን ሁሉ ሲያጥርና የአርበኞቻችን እንቅስቃሴ ዕንቅልፍ ሲነሳው፣ ሕዝቡን እያስገደደ የሱ የጦር መንገድ ጠራጊ፣ መኖሪያ ቤቶችን አናጭና የሱ ፓስታ ቀቃይ ሲይደርግ ታየኝ! በኛ አርበኞችና በፋሽስቱ መካከል የነበረው ያልተመጣጠነ የጦር መሳሪያ ልዩነት አንጀቴን እንደበላው ሁሉ፤ ዛ ያንኑ በዩክሬን ሕዝብ ዓየሁ! የኛ ንጉሠ ነገሥት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መድረክ ላይ፤ ለመንግሥታት አቤቱታቸውን ያሰሙትን፤ የሩሲያ መሪ ፕሬዘዳንት ዘለንስኪ አቤት ሲል አስታወሰኝ! ለኔ፤ የሩሲያን ወረራ ወይም የዩክሬንን መወረር የመደገፍ ምርጫው፤ ኢትዮጵያን መደገፍ ነው ወይንስ ፋሽስቱን ጣሊያን መደገፍ ነው ከሚለው ጋር እኩል ነው የሆነብኝ!

የፑተን እብሪት ጣራው አስፈርቶኛል። “ኑክሌር አለኝ!” ብሎ ሲደነፋ፤ የመንደር ጉልበተኛ እንጂ የአገር መሪ አልመስለኝም። ማን ሩሲያ ኑክሌር እንዳላት የማያውቅ አለ! ለትንሹም ለትልቁም፤ “ዓለምን የሚያጠፋ መሳሪያ አለኝ!” ብሎ ማስፈራራት! ከምን የመጣ ነው! ልክ እንደፎከረውም፤ በአውሮፓ ውስጥ ታላቁን የኑክሌር መብራት ማመንጫ፤ ሮኬት ተኮሰበት! እብደት፤ ሌላ ትርጉም ካልተሠጠው በስተቀር፤ በጥሬ መልኩ ይሄ ነው። መቼም በዩክሬናዊያን ላይ እየደረሰ ያለውን ስቃይ መዘርዘሩ፤ ከሕፃናት ዕንግልት እስከ አሮጊቶች አገር ለማዳን ከታንክ ፊት መጋደም፤ አንጄትን ደግሞ ደጋግሞ በስለት ይቆርጣል። ዩክሬን የሩሲያ ተቀጣይ አካል አይደለችም። ዩክሬን ሩሲያን የምታሰጋ አገር አይደለችም፤ አቅሙም፣ ፍላጎቱም የላትም። የዩክሬን ሕዝብ ከሩሲያ ሕዝብ ጋር የተዛመደና የተዋለደ ነው። እብሪተኛው ፑተን፤ የዩክሬን መሪዎችን፤ “ናዚዎች!” ይላቸዋል። የዩክሬን መሪዎች ናዚን የተዋጉት የዩክሬን አርበኞች የልጅ ልጆች ናቸው።

በያዝነው ዘመን፤ የዜና ማሰራጫ ተቋማት ከፍተኛ የሆነ ጉልበት አላቸው። የውሸት ዜናዎችንና አሳሳች መረጃዎችን ማሰራጨት፤ የውጊያው አካል ናቸው። በተለይ የመንግሥት ዜና ማሰራጫዎች ብቻ ባሉባቸው አገራት፤ ሕዝቡ ትክክለኛ መረጃ ስለማያገኝ፤ የጉዳዮች መሠረታዊ ዕውቀት አይኖረውም። እናም በጭፍን ይነዳል። ጭፍን የመንግሥቱ ደጋፊም ይሆናል። ሕዝቡ አምኖ ስለሚቀበልም፤ ያንን እንጂ ሌላ መስማት አይፈልግም። ከሕዝቡ መካከል ለየት ያለ አመለካከት ያለው፤ “ዓይንህን ላፈር !” ይባላል። አብዛኛው ሕዝብ ተነጂ መንጋ ይሆናል። መንግሥት ያለው ሁሉ ትክክል፤ ሌላው የሚለው ሁሉ ሃሰት! ተብሎ ይወሰዳል። ዓለም አሁን ባለችበት ደረጃ ግን፤ የዜና መለዋወጫው ምጥቀ ጥበብ ዕድገቱ በጣም ዘልቆ ስላበበ፤ መረጃን እንደ ድሮው አፍኖ የመያዝ ጉልበቱ እየተዳከመ ነው። ማስረጃውም፤ በተለያዩ የሩሲያ ከተሞች እየተካሄደ ያለው የወረራው ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ነው። እኒህ ለሰልፍ የወጡ ግለሰቦች፤ በሕይወታቸው ሙሉ በሙሉ ፈርደው ነው የተነሱት። በሩሲያ፤ መንግሥቱን ተቃውሞ መኖር በጣም አስቸጋሪ ነው። ሥራ ለማግኘትም ሆነ ቤት ለመከራየት፤ ከፍተኛ ችግር ይፈጠርባቸዋል። የፑተን መንግሥት የፈለገውን ማድረግ የሚችልበት ሁኔታ ላይ ነው ሩሲያ ያለችው። ይህን ሁሉ “ይሁንበት! ከሰብዓዊነት አይበልጥም!” ብለው ነው ቆራጦቹ ለሰልፍ የወጡት። እዚህ ላይ ማስመር የምፈልገው፤ አምባገነኖች የሚወድቁት፤ በራሳቸው ሕዝብ ግፊት መሆኑን ነው። የአምባገነኖች አረመኔነት በገፋ ቁጥር፤ የመግዛት ዕድሜያቸው እያጠረ ይሄዳል።

የእኛና የነሱ የሚለው የፖለቲካ ግንዛቤ፤ ለሁሉም ጦርነቶች መሽከርከሪያ ነው። ወደኛ አገር ስመለከት፤ ተመሳሳይ የሆነ ክስተት አለ። የክልል ፖለቲካውና ከዚያ ጋር ተያይዞ የመጣው፤ ባንድ አገር በምንኖር አንድ ሕዝብ ውስጥ፤ የእኛና የነሱ የሚል ከፋፋይ የፖለቲካ አመለካከት፤ ኢትዮጵያዊነትን እየሸረሸረ፤ ወደ መውደቂያ ገደሉ ጫፍ አድርሶታል። የየክልሉ መንግሥታት፤ የሕዝቡን ኢትዮጵያዊነት እምነት እየለጎሙ፣ የክልሉን የልዩነት ማንነት እያጎሉ፣ ከኢሕአዴግ ስሙን ብቻ ወደ ብልፅግና ፓርቲ ለውጠው፤ ኢትዮጵያዊነትን መሸራረፉን ቀጥለውበታል። ይህ ክልላዊነት፤ ጠንቁ ብዙ ነው! የጠባብነት አባዜ፤ ዛሬ ብዙዎችን ለክፎ በየጎራቸው ቢሸጉጣቸው፤ ልንገረም አይገባም። በተጨማሪ፤ ጠባብነት፤ እንኳንስ በመንግሥት ደረጃ ተገፍቶበት፤ በመንደር ደረጃም ቢሆን፤ የግብረገብነት ልጓም ካልሸበቡበት፤ መጠፋፊያ መርዝ ነው። “ሆ!” ብሎ የተነሳ የጥቂት ፅንፈኞች ስብስብ፤ ባጭር ጊዜ ውስጥ መሰሎቹንና ግድየሌሾችን እያቀፈ፤ ከፍተኛ ጥፋት ያስከትላል። ይሄ የክልል ጠባብ አመለካከት፤ የራሱ የሆነ ጠመዝማዛ አዝቃጭ መንገድ አለው። የበለጠ የሚያጠብ! አንዱ ጠባብ ከሌላው ጠባብ ጋር ብቻ እየዋለ፤ ለውጪ ሃሳብና ለአዲስ አመለካከት የብረት መዝጊያ አበጅቶ፤ በሂደቱ ራሱን አግቶ፤ ከመታደስና ከማደግ ይልቅ ባለበት ጫጭቶና ሟሽሾ፤ ወደ በለጠ መርዝነት ያለው አመለካከት ይነጉዳል። ይህ የምርጫ ጉዳይ ነው። ማንም ተገዶ ጠባብ አይሆንም። ፈቅዶና ፈልጎ ነው ጠባብ የሚሆነው።

የሩሲያ ዩክሬንን መውረር የሚደግፉ፤ ጠባብ የሩሲያ ተጠቃሚነት አቀንቃኞችና ደጋፊዎች ወይንም ደግሞ፤ ለሌሎች ስቃይ ደንታ የሌላቸው ሰዎች ናቸው። የዩክሬን ሕዝብ ቆርጦ፣ ባለው ደካማ አቅሙ የሩሲያን ወረራ ለመከላከል መጋፈጥ፤ ከፍተኛ የሆነ አገር ወዳድነት ነው። ኢትዮጵያዊያን ከዚህ መማር ያለብን፤ ስብስባችንን አስፍተን፤ ተጠናክረንና በዝተን፤ ይልቁንም ከመሰሎቻችን ጋር ተቃቅፈን ሀብታምና ጉልበተኛ መሆን ነው። አሁን ባለው የዓለም ፖለቲካ፤ ጉልበትና ገንዘብ ከመቼውም በላይ ገዢ ነው። የዓለም ፖለቲከኞች አሁን የተጨነቁት፤ ለሚሰቃየው የዩክሬን ሕዝብ ሳይሆን፤ እብሪተኛውንና ሀብታሙን ፑተንን እንዴት አድርገን አቆላምጠን፤ ወረራውን እንዲተው እናድርገው ነው። ፑተንን የሚነካው የለም። ባለጉልበትና ባለዘይት ነዋ! ይብላኝ ለዩክሬን እናት!

ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊያን ናት። ልጆቿ ይታደጓታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከቴዎድሮስ ሐይሌ ትግል ዘርፈ ብዙ ጎኖች አሉት:: ዲፕሎማሲ ሚድያ የፖለቲካ ; ካድሬዎች ; ወታደራዊ ባለሙያዎች ;የሕዝብ አደረጃጀት እና ሌሎችም ተጏዳኝ ዘርፎችን እና ሌላም ብዙ ተቋማዊ ባህሪያት እንደ ትግሉ ጸባይና ሁኔታ ሊያካትት ይችላል::

የአማራ ሕዝባዊ ድርጅት ያደረገው ውይይት ወይስ ድርድር?

January 27, 2025
ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)  ጥር 19፣ 2017(January 27, 2025) ሰሞኑን እስክንድር ነጋ “እመራዋለሁ የሚለውን የፋኖ ክንፍ” በመወከል ከአቢይ አህመድ አገዛዝ ጋር፣ እሱ እንደሚለው ውይይት፣ በመሰረቱ ድርድር እንዳደረገ በተለይም እነ ሀብታሙ አያሌው በሚቆጣጠሩት የኢትዮጵያ 360 ዲግሪ ሚዲያ ሰምተናል። ከመንግስት ጋር

እስክንድር ነጋ በታዛቢዎች አማካይነት ከአቢይ አህመድ ጋር የሚያደርገው ድርድር የአማራውን ህዝብ የተሟላ ነፃነት የሚያጎናፅፈው ወይስ ለዝንተ-ዓለም ኋላ ቀር ሆኖና ኑሮው ጨልሞበት እንዲቀር የሚያደርገው ?

ትግላችንን ለዳግም ባርነት ለሚያመቻቹን የብልጽግና እሳቤ አራማጆች አሳልፈን አንሰጥም!!! ቀን፦ ጥር 18/2017 ዓ.ም ትግላችን የኅልውና፣ የፍትሕ፣ የነጻነት፣ የሰብዓዊ ክብር ሆኖ እያለ ከፋፋይነት፣ ብልጣብልጥነት፣ አወናባጅነት፣ ከምንም በላይ በሕዝባችን ላይ የፖለቲካ ቁማርተኝነት እሳቤዎችን ከጀርባቸው

በወቅታዊ ጉዳይ ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ መግለጫ

January 26, 2025 ጠገናው ጎሹ ከቅኝ አገዛዝ (colonial rule) ነፃ መሆንን ከማወጅ ያለፈ የውስጥ ነፃነት ፣እኩልነት፣ ፍትህ እና እደገት/ልማት እውን ማድረግ ባለመቻል ምክንያት በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም የኋላ ቀርነት እና ለመግለፅ

አህጉራችን እና እኛ

ከሰሞኑ ታዛቢዎች በተገኙበት ከመንግስት ጋር ውይይት እንዳደረገ እና ለድርድር ዝግጁ እንደሆነ የገለፀው በእስክንድር ነጋ የሚመራው የፋኖ ክንፍ ድርድሩ በውጭ ሀገራት እንዲሆን እየጠየቀ መሆኑ ታውቋል። የመሠረት ሚድያ ምንጮች እንደተናገሩት ታጣቂ ክንፉ ድርድሩ በአውሮፓ

በእሰክንድር ነጋ የሚመራው ፋኖ’ ከመንግስት ጋር ለመደራደር ተዘጋጅቷል

January 26, 2025
Go toTop