የእናት ሃገር ጥሪን ሰምቶ
የዘመተው ሁሉን ትቶ
የዚያን ወታደር የዚያን ሚሊሻ
የጅግና ገድሉን የማስታወሻ
ካራማራ ጽፋዋለች
በደም ቀለም ከትባዋለች
ዳግማዊ አድዋ ብላዋለች
በልቧ ጽላት ቀርጻዋለች
ጠይቅ ሂድና ገድሉን
የዚያን ወታደር ውሎን
የከፈለውን ዋጋ ብዛት
የሃገር ፍቅሩን ጥልቀት
ይመስክር ቀብሪደሃር
ይናገር ደገሃቡር
ቃሉን ይስጥ ድፍን ምስራቅ
ህያው ግዑዙ ይጠየቅ
ካራ ማራ……….
የምስራቁ ዘማች
ጀግናው ሰራዊት ከታች
ካራማራን ሲያያት
በአረማሞ ሲያናግራት
አንቺ ካራማራ………
ሰንሰለታማው ተራራሽ
ስራ ነገርሽ መልክሽ
አድዋን አድዋን አወደኝ
በደስታ እምባ ዋጠኝ
ምናቤ የኋሊት ፈረስ ጋልቦ
ነፍሰ ስጋየን ሁሉ ሰብስቦ
ደርሶ ነሸጠኝ ወሸቦ
ደግሞ ደጋግሞ ደርቦ
ያምማል እያለ የዘመተው
ጉሮ ወሸባው ያባተው
የካቲት ወሩ ገጠመ
ታሪክ ራሱን ደገመ
ካራማራ ……….
እኔም በተራዬ
አሰኘኝ እኮ ሆ ብዬ
ሆ ብዬ እመጣለሁ ሆ ብዬ በድል
ጥንትም ያባቴ ነው ጠላቴን መግደል
ለበጎ ከሆነ ለቁም ነገር ጉዳይ
ጎረቤት ወዳድ ነን እንግዳ ተቀባይ
ግን ሃገራችንን ክፉ ሚያስባትን
ቆራጥ ነን ልጆቹዋ አንወድም ጥቃትን
ይሄ ነው ምኞቴ እኔ በህይወቴ
ከእራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ
አገሬ መመኪያዬ ክብሬ
አትደፈሪም ዳር ድንበሬ
ካራማራ…….
ጸሃይ የምስራቁን ድል ብትሰማ
ማልዳ ወጣች የምስራች ልታሰማ
ወደዚህ ጎራ አዘነበለች
ለድል ዝማሬው መብራት ያዘች
አንቺ ካራማራ……
የኢትዮጵያ ባንዲራ
የረገበብሽ ካራ ማራ
አንቺ አገሬ አካሌ ገላዬ
የሃገር ፍቅር ወለላዬ
ሃገር ድንበሬን ጠላት ሊረግጥ
በልዑሌ ላይ ሊያላግጥ
ዚያድባሬ ሲነሳ
የትቢት ግሳት ሲያገሳ
ተነሳ ያገሬ ሰው…..
የገበሬ ሚኒሻው
አየር ወለዱ ተስፈንጣሪው
ተወርዋሪ ጀት አብራሪው
መድፈኛና ታንከኛው
እግረኛና ውሃኛው
ሳንጃ ልጦ
ተገልብጦ
እሳት ጎርሶ
እሳት ለብሶ
ወግቶ ጥሎ
ትግል ውሎ
ጉሮሮ ለጉሮሮ ተያይዞ
የዚያድባሪን አንገት ጠምዝዞ ይዞ
ስንዝር ሳያስነካ የሃገሩን ድንበር
ደማቅ ታሪክ ጻፈ ያ ጀግና ወታደር
ካራማራ……..
ካራ ማራ ተራራ ላይ
የምስራቁ ድል መቋጫ ላይ
የሃገሩን ባንዲራ ተክሎ
የክብር ሰላምታውን ሰጥቶ
ሃገሩን ያኮራው ያ ጀግና
ቀና ያረገን እንደገና
ክብርና ሞገስ ይልበሰው
ያገር ምርቃት ይውረሰው
በዚህ ሰው ጽናት በዚህ ሰው ወኔ
ይኸው ቀና እንዳልኩ አለሁኝ እኔ
ካራ ማራ …….
የየካቲት ድል ተሽከረከረች
አድዋ ድሌ ካራ ማራም ላይ ይሂው አበራች
ጉሮ ወሸባየ ጉሮ ወሸባ
ዘማች ድል አርጎ ሲገባ
የኣድዋ ዘማች ልጆች
የካራማራ ባለ ድሎች
አንጸባራቂ ኮከቦች
እነሆ ………
ለዋላችሁት ውለታ
ለፈጸማችሁት ግዴታ
የወርቅ አንኮይ
በብር ጻህን ላይ
የምስጋና ነዶ እቅፍ ኣበባ
ዘማች ድል አርጎ ለገባ
ለተሰዋው ለቆሰለው
ምስጋናየ ብዙ ነው
እጥፍና ድርብ ነው
አድናቆቴ ብዙ ነው !
እጥፍና ድርብ ነው!
መጋቢት፣ 2014 ዓመተ ምህረት