የድልና የክብረ-በዓላችንም ለማክበር ተሰባስበን እንወጣለን፤ ስሜታችን፡ ቁጭታችን፣ ብሶታችን፣ በአጠቃላይ ገዥዎቻችን የሚያደርሱብንን የጭቆናና የጎሰኝነት አገዛዝ በተለያየ መንገድ ለመግለጽና ለመቀዎም እንሞክራለን። ጀምበር ስታዘቅዝቅ እንደ ”ጨው ዘር” ወደ የመጣንበት እንበተናለን። ከዚያም ከኑሮ ውድነት እስከ ወገኖቻችን እልቂትና ስለ ተረኞች ጎሰኝነት በየጓዳችንና በየመሸታ ቤቱ በማማት እንጠመዳለን። ገዥውቻችንም እንዳልሰሙ ሰምተው ወይም እንደተለመደ ”የቁራ ጩኽት” ቆጥረውት ወይም እንቅስቃሴው ከአንድ ቀን ሆሆታ! እንደማያልፍና ለስልጣናቸው ምንም ስጋት እንደሌለው ስለሚረዱ፣ አገዛዛቸውን አጠናክረው ይቀጥሉበታል። እኛም ሌላ የክብር ወይም የድል በዓል እስኪመጣ ድረስ የሚደርስብንን የመደርተኝነት አገዛዝንና የኑሮ ውድነት ሁሉ እያስተናገድን፤ አጋጣሚውን መድረክ ካገኘን ‘እያጨበጨብን”፤ ” ኗሪ ሳንሆን አኗኗሪ በመሆን” እንቀጥላለን።
የአድዋ ድል 126ኛ ዓመት ሲከበር በተለይም በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገራችን ትልልቅ ከተሞች የታየው የአንድነትና የአብሮነት ስሜት ላስተዋለው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በጎልበተኛ ጎሰኞችና ኢትዮጵያንም አምርረው በሚጠሉ መንደርተኞች የሚገዛ አይመስልም። ይህ ብቻ አይደለም ይህ ህዝብ ጎሰኞችን ጠራርጎ፤ ለሁላችን የምትሆን፣ በአንደነትና በእኩለነት ተከባብረን የምንኖርበትን የመንግሥት አሰተዳደር መመስረት የሚያስችል አቅም እንዳለው የሚያመለከት ነው።
ይሁን እንጂ እውነታው አገራችን የሚዘውሯት የጥቁር ህዝብ ድል የሆነውን የአደዋ ድልን እንኳ’ የሚቀበሉትና የሚያከብሩት እያቃራቸው መሆኑ፤ ከሚኒልክ አደባባይ አውጥተው፤ አደዋ ድልድይ ለማክበር የሄዱበት የጠባብነት መንገድ ምስክር ነው። ጠ/ሚ አብይ አህመድ በኢትዮጵያ ስም እየማሉና እየተገዘቱ፤ አንድ ቀን እንኳ ተሳስተው በሚኒሊክ አደባባይ የአበባ ጉንጉን አስቀምጠው አያውቁም። ታዲያ የአንደነትና የኢትዮጵያዊነት ብሎም የአፍሪካ አብሪ – ኮኮብ የሆነውንና አሁን በቆምንበት የነጻነት ምድር ክብር ሳይሰጡ ፣ ህዝብን ከፋፍለው በጎሳ ህግ-መንግሥት እየገዙ ”አፍሪካዊ በመሆኔ እኮራለሁ” እያሉ ይመጻደቃሉ።
ታዲያ ዋናው ችግር ያለው በርግጥ’ ከ”ነሱ ሳይሆን፤ ከ’ኛ ለመሆኑ ምስክር የሚሆነው፣ በድልና በክበረ – በዓል የምናሰመውን ተቃውሞ፡ የምንፎክርለትን ኢትዮጵያዊነት፣ የምናውለበለበውንና የምንለብሰውን አረንጓዴው፡ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ ዓላማችንን ለምን ተደራጅተንና አደራጅተን አንታግልለትም? በጣም የሚያቅለሸልሸው ደግሞ፤ አባት አርበኞች ባለ አምባሻውን ሰንደቅ ዓላማ አንግበው ያዙኝ -ልቀቁኝ ሲሉ ማየት ነው። ለየትኛው ዕድሜ ይሆን?– የታገሉለትንና መሰዋት ሆኖ ለማስከበር የዘመቱለትን ሰንደቅ ዓላማ አስጥሎ ወያኔ የሰፋውን ሰንደቅ ዓላማ የሚያስዝ ?
በተለይም የአዲስ አበባ ህዝብ ”ፊኒፊኒ ኬኛ” ተብሎ ህገ ወጥ ከንቲባ ከተሾበት ቀን ጅምሮ እሰክዚህ ሰዓት ድረስ በህዝቡ አንድነትና ህልውና ላይ ብዙ ተሰርቷል። የሁላችንም የሆነችውን መዲና የኦሮሙማን የበላይነት ለማረጋገጥ፤ የኮደሚኒየም ቤት ከማደል ጅምሮ አስከ ኦሮሚያ ፍርድ ቤት እስከ ማቋቋምና የከተመዋን ፓሊስ ለመቆጣጠር፤ ብሎም ”ቁመንልሃል” የሚሉት ህዝብ በትምህርትና በህክምና እጦት እየተሰቃየ፡ አዲስ አበባ ላይ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየወጣ የመዲነዋን ዲሞግራፊ እንቀይረዋለን እንዳሉትም እየቀየሩት ነው። የእዲስ አበባን ሁኔታ ሳስብ፤ በአሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን የነበረው፤ የነባር አሚሪካን ወይም የቀይ ኢንዲያና ‘’የሞድክ’’ ባላባት፣ ስለ ወራሪ አውሮፓዊያን የተናገረውን ያስታውሰኛል፤
”አውሮፓዊን ወደ አገራችን ሲመጡ ብዙ ቃል ገብተውልናል፤ ከገቡት ቃል ሁሉ ግን በተለይም አንዱን ፈጽመውታል። ‘መሬታችሁን እንወስደዋለን ” ብለው ነበር፤ አዎ–ቃል እንደገቡት መሬታችን ወሰዱት።” ነበር ያሉት።
አዲስ አበቤ ከሌላው አካባቢ በተሻለ ደረጃ የመደራጀት፣ የመናበብ አቅምና መብቱን የማስከበር ችሎታ አለው። የገዥዎቻችን ሰምቶ አዳሪዎችም ሆነ አቀንቃኞች የማያታልሉት ከወያኔ ዘመን ጅምሮ የጎሳን ፓለቲካ አደገኛነት የተረዳና አንቅሮ የተፋ ነው። ይሁን እንጂ የፍርሃት ይሁን በኑሮ ውድነት መደንዘዝ ወይም የአንድነት አቀንቃኞች ”ዳግማዊመይሶን” በመሆን ከጎሳ ገዥዎቻችን ጋር በማበራቸው ፤ ከክብረ በዓላት ውጭ የሚሰማ የትግል ድምጽ ወይም መፈክር ሌላ ከዚህ ግባ የሚባለ ትግል የለም።
መቸም ተረኞች በሌላ ቦታ እንደሚያደርጉት እንደ አውሬ እያደኑ ለመግደል ግዜው ባይደርስላቸውም፣ በእነ ”ነውሩ – ክብሩ” እንደ አዲስ አበቤ የተሰደበና የተዋረድ ዜጋ የለም። ወንጀሉ ደግሞ ከኢትዮጵያዊነት ማማ አለመውረዱ ነው። ባልተውለዱበትና ባላደጉበት መዲና፣ እንወክለሃለን ብለው፤ ክቡርን የሰውን ልጅ ማንነት የሚያንቋሽሹና የሚሳደቡት፤ ”ፓርላማና ምክርቤት ” በሚሉት ውስጥ ያለምንም ተጠያቂነት በሥልጣን ላይ መቆየታቸው ሳያንስ፤ አሁንም ከአባይ የረዘም ነውረኛ መንደርተኛ ምላሳቸውን አልሰበሰቡም።
ታዲያ ለዘመናት የተገመደውን ህብረ-ኢትዮጵያዊነት ከማጥፋት ጀምሮ፡ በኑሮ ውድነት አየተጠበሰ፣ ከማህበራዊ አገልግሎት እስከ አየር- መንገድ ድረስ በተረኞች ተይዞ ፤ ክወለጋ እስከ ቢንሻንጉል፤ ከሰሜን ሸዋ እስከ መተከል የሰው ልጅ በማንነቱ እየረገፈ፣ ብሎም በወያኔ ጦርነት ብናሸንፍም፡ በገዥዎቻችን የፓለቲካ ውሳኔ እየተሸነፍንና ሌላ እልቂት እየተደገሰልን፣ ኦነግ-ሸኔ ዘር ማጽዳቱን እያሰፋ ወደ መዲናችን እየተጠጋ ፤ በዚህ ሁሉ መሃል በክብረ-በዓል ከምናሳየው መፈክር ውጭ ዝምታ እንበለው ፍርሃት፣ ወደድንም ጠላንም የጎሰኞች መፈንጫ መሆንን መርጠናል።
ፍርሃታችንም ይሁን ዝምታችን ግን ለገዥዎቻችን የልብ-ልብ እየሰጣቸው፣ በአንደንታችንና በኢትዮጵያዊነታችን ላይ በመሳለቅ፤ የጎሳ የበላይነታቸውንና ተርኝነታቸውን ከምንግዜውም በበለጠ አጠናከርው በመቀጠላቸው፤ የአዲስ አበባም ሆነ የአገራችን ህልውና ፈተና ላይ ወድቋል። ግን እስከ መቼ?
”—ፍርሀታችን በልጦ፣ ከሞት ፍርሀት
በቁም እንሞታለን በማይቀረው ሞት።
ሞት እንደሆን ላይቀር፣ በዚህ ቢሉት በዚያ
እንዴት ሀገር ይጥፋ፣ የሌለው መተኪያ።–”
አለን ፔተን ” ከፍርሀት ባርነት፤ከባርነት ፍርሀት፣ የሚገላግለን ጎህ መቼ ይቀድ ይሆን? ማን ያውቃል?” ይለናል፤ “እሬ በይ አገሬ”’ በተሰኘው መጸሀፉ መደምደሚያ ላይ። አዎ አለን ፔተን እንዳጠየቀው ”ማን ያውቃል?” …፡እሱ ነጻ ደቡብ አፍሪካን ለማየት ባይታደልም ወገኖቹ ግን አሁን በነጻነት ይኖራሉ። የግዜ ጉዳይ እንጅ እኛም በክበረ-በዓል ብቻ ከሚደረግ መፈከር ወጥተን፤ ፤ ከፍርሀት ባርነት፤ ከባርነት ፍርሀት ተላቀን፣ ተደራጅተንና አደራጅተን፤ የጎሰኞች አገዛዝ አስወግደን፤ አዲስ አበባ የሁላችን መዲና ፡ ሁሉም ዜጎቿ ልዕልነዋ በተከበረች ኢትዮጵያ፣ በፍትህ፣ በእኩልነትና በባለቤትነት የምንኖርበት የ’ጋራችን ሀገር፣ በጋራ ኃላፊነት እንገነባለን። ማን ያውቃል?
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!
——-//——-ፊልጶስ
የካቲት -2014