“ከሽብርተኛው” ትህነግ ጋር ድርድር በምን ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ይደረጋል? –  አክሎግ ቢራራ (ዶር)

/

የመጨረሻ አላማውስ ምንድን ነው? –

      አክሎግ ቢራራ (ዶር)

“ትግል በባህሪው ዳገት እና ቁልቁለት ያለው እልህ፣ ጽናት አና ብልሀት ይጠይቃል። ይህ ነባራዊ አደጋ ከሁሉም በላይ በትግራይ ህዝብ ላይ የተቃጣ ነው።  ህ.ወ.ሓ.ትን ለማጥፋት ነው። ይህ አደጋ ከአንድ ወገን የመጣ አይደለም::   ከአሀዳዊያን ሀይሎች እና ከኢሳያስ ቡድን ጋር በአንድ ተጣምሮ የመጣ ነው።  እነዚህ አንድ ላይ የገጠሙ የተቀናጁ የትግራይ ህዝብ ጠላቶች ...ትን ለማጥፋት የሚቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። ሙሉ በሙሉ ታግለን እስክናሸንፋቸው ድረስ የሚያጋጥመው ፈተና ቀላል አይሆንም። እኛ ደግሞ ጠላቶቻችንን ለመደምሰስ እና ለማጥፋት ተገደንም ቢሆን መሰማራት አለብን። “

የትግል ልዩ ምዕራፍ እድገቶች እና የምከታችን ቀጣይ ስትራቴጂዎች፣ ስልቶች እና አቅጣጫዎች (ቁጥር – ሁለት) የህ.ወ.ሓ.ት ጽ/ቤት መስከረም 30/2013 ዓ.ም፤ መቐለ

ባለፉት አምሳ ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱ ባልፈጠረው ስርአታዊና መዋቅራዊ ተግዳሮቶች፤ ባልሰራው ሃጢያት ሲቀጠቀጥ፤ ሲነገድበት፤ ሲከበርበት፤ ስቃይ ሲከፈልበት፤ ሲጨፈጨፍበት፤ ሴቶቹ ሲዋረዱበት፤ ከቀየው ሲባረርበት መቆየቱ የአደባባይ ምስጢር ነው። ዲሞክራሲ፤ ሰብአዊና ማህበረሰብዊ መብቶች፤ የሕግ የበላይነት፤ የዜጎች ያልተገደበ እኩልነት ወዘተ ይከበሩ ሲባል አስርት ዓመታት አልፈዋል። በመሬት ላይ የሚታየው ሃቅ ግን የተለየ ነው።

ራሴን ደጋግሜ የምጠይቀው፤ ይህ ሁኔታ ባለባት በኢትዮጵያ የአገሪቱ መንግሥት ዋና ሃላፊነትና ተጠያቂነት በምን ላይ ነው? የሚለውን ነው። በእኔ እምነትና በሌሎች አገሮች ልምዶች መስፈርት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ዋና ሃላፊነት ሕግንና የአስተዳደር ስርዓትን ያለምንም ማመንታትና ዘውጋዊ ወይንም ፓርቲያዊ አድልዎ ማስከበር ነው። እድገትንና ልማትን ከዜጎች ሰብአዊ፤ ማህበረሰባዊና ዲሞክራሳዊ መብቶች ገንጥሎ ማየት አይቻልም። ሽብርተኛነት በገነነበት አገር ሁሉ ፈሰስ የሆነው ካፒታል ይወድማል። የሚወድመው በሽብርተኞች ነው። ሽብርተኛ ሽብርተኛ የሆነበት ዋና ምክንያት በሕግ የበላይነት፤ በሰላም፤ በአብሮነት፤ በአገር እርጋታ ስለማያምን ነው። ሽብርተኛ ፀረ-ሕገ መንግሥት፤ ፀረ-ሕዝብ፤ ፀረ-ዲሞክራሲ ነው። በዚህ ላይ ብዢታ ካለ፤ ችግሩ የሽብርተኛው ሳይሆን የባለሥልጣናቱ ነው።

በአሁኑ ወቅት፤ በኢትዮጵያ ትህነግ/ህወሓት፤ ኦነግ/ሸኔ፤ የጉሙዝ ነፃ አውጭ ግንባር በተከታታይ በአማራውና ብልፅግናን ትደግፋላችሁ ብለው ኢላማ ባደረጉባቸው ንጹህ ኢትዮጵያዊያን ላይ ከመቸውም በባሰ ደረጃ እልቂትና ውድመት እያካሄዱ ነው። በክልል ደረጃ ሆነ በፌደራል የመንግሥታት መሪዎች የመጀመሪያ ሃላፊነት እልቂትና ውድመት በሚያካሂዱት አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ነው። ሽብርተኞች በክልል ሆነ በፌደራል ተቋማትና ባለሥልጣናት ውስጥ ምሽግ ሰርተው ድጋፍ የሚያገኙ ከሆነ እልቂትና ውድመት ሊያቆም አይችልም።

ኢትዮጵያ አሁንም በማህበረሰባዊ እድገትና ልማት መስፈርቶች ስትገመገም፤ ድሃና ኋላ ቀር ከሆኑት አገሮች መካከል አንዷ ናት። ብልፅግና ወይንም ልማት ያልተቀዳጀበት መሰረታዊ ምክንያት ምንድን ነው? ብየ ስመራመር፤ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ኃብት ባለቤት ባለመሆኗ ወይንም ሕዝቧ ታታሪና የራሱን ህይዎት ለማሻሻል ቆራጥ ባለመሆኑ ወይንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ስርጭትና እምነት ቅይጥ ወይንም ድብልቅ በመሆኑ (diverse) አይደለም ወደሚለው ድምዳሜ ከደረስኩኝ ዓመታት አልፈዋል።

በባለሞያዎች የተደረጉ ግዙፍ ምርምሮችና ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ የኢትዮጵያ መሰረታዊ የዘመናዊነት ደካማነት መሰናክል ሰው ሰራሽ የሆኑት የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ፤ የፋይናንስ፤ የባህል ወዘተ ተቋማት ክፍተት ነው።  ለምሳሌ፤ “The Origins of Power, Prosperity and Poverty: Why nations fail,” Daron Acemoglu and James Robinson, እንዳሳዩት፤ የፖለቲካ ልሂቃን “ተቋማትን አዳክመው ወይንም ሽባ አድርገው የራሳቸውን ስልጣንና ጥቅም” ካራመዱ፤ ካጠናከሩና  ሌላውን እንዳይሳተፍ ካደረጉ ዘላቂና ፍትሃዊ ልማት ሊኖር አይችልም። በኢትዮጵያም በዘውግ ልሂቃን ልዩነቶች የተነሳ የእርስ በእርስ ጦርነት፤ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት ሽሚያ ምክንያቶች ሰላምና እርጋታ ከተበከለ እና ፍትህ ተቋማዊ ካልሆነ ድህነት ስር እየሰደደ ይሄዳል።

አንድ ዓመት ተኩል የፈጀውና አሁንም ያላቆመው፤ እንዲያውም በሚያሳስብ ደረጃ ትህነግ/ህወሓት በአፋርና በአማራው ሰርቶ አደር ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚያካሂደው ጭካኔ የተሞላበት ወረራና እልቂት አሳሳቢና አደገኛ መሆኑን ብዙ ተመልካቾች ያሳስባሉ። ትህነግ/ህወሓት በአፋር የሚያካሂደው የመሬት ወረራ፤ ነጠቃና ይገባኛልነት ጦርነት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚና የንግድ ጉረሮ ለማነቅ ጭምር ነው። በተመሳሳይ ደረጃ የሚቀጥለው የጭካኔ ጦርነት እንደ ገና የሚካሄደው የሱዳንን በር ለማስከፈትና ተወስደውብኛል የሚላቸውን “የምእራብ ትግራይ” ለም መሬቶች–ወልቃይት፤ ጠገዴ. ጠለምትን–በመሳሪያ ኃይል ለመመለስ ይሆናል። ይህንን በሚመለከት ትህነግ የውጭ መንግሥታት፤ በተለይ የግብፅ ድጋፍ አለው። የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናትም ድጋፍ ቢኖረው አልደነቅም።

ትህነግ/ህወሓት ለሕግ የበላይነት ተገዢ አይሆንም

የትህነግ የመጨረሻ ግብ ምን እንደሆነ ለማወቅ የሚቻለው የድርጅቱን መርህ፤ ስልት፤ ስትራተጂና ፍኖተ ካርታ በቅርብና በጥንቃቄ ለመመልከት ሲቻል ነው። ይህ ወደ የት ያመራል? የሚል ጥያቄ ማቅረብ ወቅታዊ ነው። አራት መሰረታዊ ክስተቶችን ልጥቀስና ወደ ዝርዝሩ ላምራ።

አንደኛ፤ በጭፍጨፋውና በእልቂቱ፤ በስነልቦና ጦሩነቱ፤ በማህበረሰባዊ ኢኮኖሚ ውድመቱና በሚያስደነግጥ ደረጃ ግዙፍ በሆነውና ገና ባልቆመው የትግራይን ወጣት ትውልድ ጭምር ለግቡ መስዋእት ከፋይ በመደረጉ መስፈርቶች ስገመግመው ትህነግ/ህወሓት የሚዋጋው ለምና ወሳኝ መሬቶችን ነጥቆና ወደ ትግራይ አጠቃልሎ፤ ለነፃነት/ለመገንጠል እንጂ ለፍትህ፤ ለዲሞክራሲና ለአብሮነት አይደለም። አብሮ ለመኖር የሚፈል ኃይል ይህንን የመሰለ ጭካኔና ውድመት አይፈጽምም። ትግራይ በተባበሩት መንግሥታት መስፈርት በኩል ገና እውቅና ባያገኝም፤ de facto “ነፃ መንግሥት ነኝ” ብሏል። በመርህና በመንፈስ መስፈርት ሲታይ፤ ትህነግ ከኢትዮጵያ ሃገረ-መንግሥት ራሱን ከገነጠለ ዓመታት አልፈዋል።

ሁለተኛ፤ ከላይ የጠቀስኩትን ክስተት የሚያጠናክረው የትግራይ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና የእስልምና ኃይሞኖት አመራርና ተቋማት ከኢትዮጵያ ተገንጥለዋል የሚለው ውሳኔ ነው። ትህነግ እምነቶችን የፖለቲካ ዋሻ ካደረጋቸው ዓመታት አልፈዋል። በተቋም ደረጃ ስመለከተው ሁሉቱንም እምነቶች ተገንጥለዋል የሚለው ውሳኔ የሚያሳየው ትግራይ ራሷን እንደ አዲስ ነጻ አገር ማድረጓን ነው። የትህነግ አመራር ይህንን ውሳኔ እንዳደረገና አቅጣጫው ሊያስከትል የሚችለውን ከፍተኛ አደጋ አስቀድሞ ማመዛዘን የነዋሪው ሕዝብ፤ የክልሎችና የፌደራል መንግሥት ባለሥልጥናት ሃላፊነት ነው።

ሶስተኛ፤ እስካሁን በትህነግ ላይ የተደረገው የመከላከልና ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከአደጋ የመታደግ ጥረት በኦነግ/ሸኔ ላይ አልተደረገም። ይህ ሽብርተኛ ቡድን በሰሜን ሸዋ፤ በምእራብ ወለጋ፤ በጉጂ፤ ከጉሙዝ አመፃዊያንና ከትህነግ ጋር በመተባበር በቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ በተደጋጋሚ የሚያካሂደው ብሄርና እምነት ተኮር እልቂት እና ውድመት እየተስፋፋ ሂዷል። ይህ ሽብርተኛ ቡድን በመሳሪያ ኃይል እንዴት ሊጎለምስ ቻለ? እንዴት ሊስፋፋ ቻለ? ማን ይደግፈዋል? ማን ችላ ብሎታል? የፌደራሉና የሚመለከታቸው የክልል ባለሥልጣናት ለምን ይህንን ሽብርተኛ ቡድን በተከታታይ አያወግዙትም? ለምን ለመደመሰስ አልቻሉም? ለሚጨፈጨፉት ንጹህ ኢትዮጵያዊያን፤ በተለይ ለእናቶች፤ ለህፃናት ወዘተ ለምን የሃዘን መግለጫ አይሰጥም? እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ አስፈልጊ ሆኖ አየዋለሁ።

አራተኛ፤ የምእራብ አገሮች፤ በተለይ የአሜሪካ መንግሥት በተደጋጋሚ ለምን ትህነግን/ህወሓትን ይደግፋል? ብለን የምንጠይቀው ግለሰቦች በሰከነ ደረጃ ያልተመራመርነው ሃቅ አለ። ይኼውም፤ ትህነግ/ህወሓት ከተመሰረተበት ወቅት ጀምሮ የአሜሪካን ፖሊሲና ፕሮግራም መሪዎችና ጫና ፈጣሪዎች ለአሜሪካ፤ ለመላው የምእራብ እና ለአረብ አገሮች ያስተማረውና ያሳሰበው ለእናንተ ዘላቂ ጥቅም የሚያዋጣችሁ የኤርትራንና የኢትዮጵያን መንግሥታት አዳክማችሁ፤ ቢቻል በታትናችሁ የትግራይን ጉዳይልክ ዱሮ “የኤርትራ ጉዳይ እያላችሁ እንዳስተጋባችሁት ሁሉ ለእኛ ድጋፍና እውቅና መስጠት ነው በሚል መርህ መሆኑን ግንዛቤ አለኝ።

ባጭሩ፤ ትህነግ የትግራይ ጉዳይ የእናንተም ጉዳይ ነው  በሚል ድጋፍ አግኝቷል። “የትግራይ ጉዳይ” በተናጠል የምእራብ አገሮች ጉዳይም ከሆነ እና በአፍሪካ ቀንድ “ትግራይ የሚባል አገር ከተመሰረተ የአፍሪካን ቀንድና የቀይ ባህርን ቀጠና ሙሉ በሙሉ ይቀይረዋል። ትህነግ ከአፋርና ከአማራው ክልል በመሳሪያ ኃይል ነጥቆ የምስራቅ፤ የሰሜንና “ምእራብ ትግራይ” ብሎ የሰየመውን ሁሉ ካጠቃለለ እና በሰሜን በኩል ደግሞ አፋርን አዳክሞ ከኤርትራ የባህር በር ካገኘ፤ ይህ አዲስና ለአሜሪካ ታማኝ የሆነ አገር ተፈጠረ ማለት ነው። የአሜሪካ መንግሥት ይህንን ቢያደርግ  አንገረም። ዩጎስላቭያን እናስታውስ።

የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት ጨፍጫፊና አውዳሚ የሆነውን ሽብርተኛ ትህነግን/ህወሓትን የሚደግፉበት ምክንያት በዚህ ከራሳቸው የረዢም ጊዜ ጥቅም ስሌት መሰረት እንደሆነ በበኩሌ አልጠራጠርም። ብሳሳት ግን ደስ ይለኛል። የአሜሪካ ባለሥልጣናት የኤርትራን መንግሥት፤ የአማራውን ልዩ ኃይልና ፋኖን በተከታታይ ከትግራይ “ውጡ” ሲሉ እውነት ለሰብአዊ መብት መከበር አስበው ነው? ብየ ራሴን እጠይቃለሁ። ይህን ግንዛቤ የሚያጠናክረው ደግሞ አሁን በአሜሪካ ምክር ቤት H.R. 6600 ተብሎ የሚጠራው የሕግ ረቂቅ ነው። ይህ ከፍተኛና አደገኛ ጣልቃ ገብነትን የሚያሳይ ረቂቅ ካለፈ ሊከሰት የሚችለው አደጋ ምንድን ነው?

የእያንዳንዱን ሰው ሰብእነትን፤ ሰብአዊ ፍጥረትነትን የመቀበል/አለመቀበል፤ የማክበር/ ያለማክበር፤ የማፍቀር/ ያለማፍቀር ወዘተ ጥያቄ የጉራጌ፤ የአፋር፤ የአኟክ፤ የወላይታ፤ የኦሮሞ፤ የሶማሌ፤ የአማራ፤ የድሃ ወይንም የኃብታም፤ የሴት ወይንም የወንድ ወዘተ ጉዳይ አይደለም። የእያንዳንዱ የሰው ፍጥረት ሰብአዊ መብት ጥያቄ ነው። ይህ ሁኔታ ሲደጋገም፤ የዓለም መንግሥታት፤ በተለይ የአሜሪካ የፖሊሲና ውስኔ ሰጭዎች በጋራ ሆነው በኢትዮጵያ ላይ ተከታታይ ትኩረትና ጫና ቢያደርጉ አያስደንቅም። በአሁኑ ወቅት፤ በአሜሪካ ምክር ቤት ዲሞክራቱ ግሬገሪ ሚክስ (Gregory Meeks) እና ሪፐብሊካኑ ሚካኤል ማኮል (Michael McCaul) Ethiopia Stabilization, Peace and Democracy–እርጋታ፤ ሰላምና ዲሞክራሲ” ተብሎ የተሰየመውን፤ በይዘቱ ቀረብ ብየ ስመራመረው ፀረ–ኢትዮጵያ የሆነ፤ ትህነግን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር አቻ ለአቻ አድርጎ ያካተተ አዲስ የሕግ ረቂቅ ያቀረቡበት መሰረታዊ ምክንያት እነዚህ ግድፈቶች በኢትዮጵያ ይታያሉ በሚል እሳቤና አመለካከት ነው። እልቂቶቹና ውድመቶች መካሄዳቸውና የኢትዮጵያ መንግሥት ሃላፊነቱን በቅጡና በአግባቡ ለመወጣት አለመቻሉ እንዳለ ሆኖ፤ ይህ አመለካከት ግን የተዛባና አደገኛ መሆኑን እቀበላለሁ።

  1. ሕጉ ካለፈ፤ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ስለ “ዲሞክራሲ፤ ሰብአዊ መብት መከበር፤ ስለ ጥላቻ ንግግሮች፤ ስለ ሃላፊነትና ተጠያቂነት” እቅድ እንዲያዘጋጂ ሥልጣን ይሰጣል።
  2. የአሜሪካ ፕሬዝደንት “ጦርነቱ እንዳያቆም መሰናክል በሆኑ፤ እርቅና ሰላም እንዳይደረግ በሚጎተጉቱ፤ የሰብአዊ  መብት ወንጀል በሚፈፅሙና የዘውግ/እምነት ጥላቻ በሚገፏና በሚያሰራጩ፤ ሙስና እንዲባባስ በሚያደርጉ፤ የጦር መሳሪያ ለተቀናቃኝ አካላት በሚያቀብሉ ወዘተ “ግለሰቦች” ላይ የእቀባና ሌላ እርምጃ እንዲወስዱ ያስገድዳል።
  3. ጦርነቱ እስካላቆመ ድረስ፤ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚሰጠውን የደህንነት መሳሪያ ድጋፍ እንዲያቆም፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም ለሚደረገው ውይይት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲሰጥ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ እርምጃ እንዲወስድ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ግጭት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ሁሉ ሰብአዊ እርዳታ ያለ ምንም መሰናክል እንዲከናወን እንዲደረግ ማመቻቸት እና የኢትዮጵያ መንግሥት “የጦር ወንጀል በፈፀሙት ላይ” ጥናት፤ ምርምርና ግምገማ እንዲያካሂድ ግዴታውን ይወጣ የሚሉ ውሳኔዎችና ትእዛዞች ተካተዋል።
  4. የአሜሪካ መንግሥት፤ ጦርነቱ እስካልቆመና የዜጎች መብቶች እስካልተከበሩ ድረስ፤ ከሰብአዊ ረድኤት ወይንም ድጋፍ በስተቀር፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ ብድር ወይንም ሌላ የገንዘብ እርዳታ እንደ ዓለም ባንክ እና አይኤምኤፍ  ከመሰሉት ድርጂቶች እንዳይሰጣቸው ማድረግ።
  5. የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በሰዎች ወይንም ዜጎች ላይ የተፈጸመ የጦርነት ወንጀል እና ሰብአዊ እልቂት (Genocide) እንዲያጣራ፤ እንዲመዘግብና እንዲያስታውቅ።
ተጨማሪ ያንብቡ:  አባ መላ እና መላ ያጣው ንግግራቸው (በዳጉ ኢትዮጵያ)

ምክር ቤቱ ይህንን የውሳኔ ረቂቅ ሲያዘጋጅ የኮንግሬስ አባል ማሊኖውስኪ የተናገሩት “በኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት በዓለም ደረጃ ከፍተኛ ቀውስ ካስከተሉት መካከል አንዱ ነው፤ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑት አካላት ሁሉ ተጠያቂዎች ናቸው” ብለዋል።

በእኔ ግምገማ ግን፤ ይህ የጅምላ ውንጀላ ኢ-ፍትሃዊና የኢትዮጵያን ሉዐላዊ መብት የሚፃረር ነው። ጦርነቱን የጀመረውና ወደ አፋርና ወደ አማራ ክልል ያስፋፋው፤ ለብዙ ሽህዎች እልቂት፤ ለህሊና የሚቀፍ ውድመት፤ ለብዙ ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን ከቀያቸው መባረር ዋና ምክንያ የሆነውን ትህነግን/ህወሓትንና የኢትዮጵያንና የኤርትራን መንግሥታት ሃላፊዎች አቻ ለአቻ ማቅረብ ፍትሃዊና ሚዛናዊ አይደለም።

የኢትዮጵያ ፌደራል እና የክልል ባለሥልጣናት ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው የሚለውን እያሰመርኩበት፤ ይህ ረቂቅ ግን በፊት ቀርበው ከነበሩ ረቂቆች የባሰና ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ህዝብ የሚቀጣና የሚያስቆጣ ነው። በአሜሪካ የምንኖር ኢትዮጵያዊያን በማንኛውም ዘዴ ተቃውሞ ማሰማት አለብን። እኔ የምፍራው ይህ ረቂቅ ከፀደቀ በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል የቆየው ግንኙነት በማይመለስበት ደረጃ እንዳይናድ ነው። ጥያቄው፤ የአሜሪካ ምክር ቤት ለምን ይህንን ኢ-ፍትሃዊ ረቂቅ ለውሳኔ አቀረበ? የሚለው ነው።

የአሜሪክ መንግሥት በተከታታይ ትህነግን እየደገፈ የሚያደርገውን ጫና ለምታገለው ለኔና ለሌሎች ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተሟጋቾች ይህ አዲስ ረቂቅ ሕግ የተለየ ሆኖ አላየውም። በተለያዩ የባይደን መንግሥት ዘመን እስካሁን ይኼ ሶስተኛ መሆኑ ነው። ይህ ረቂቅ በሴናቱ ታይቶ ካለፈ ከፍተኛ ጫና እንደሚያስከትልና የአሜሪካንና የኢትዮጵያን መንግሥታት የቆየ ግንኙነት/ ወዳጅነት እንደሚጎዱት እገምታለሁ።

በዚህ ትንተናየ ግን እኔን የሚያስጨንቀኝ፤ የውጩ ጫናው አይደለም። በተከታታይ በንጹህ ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚካሄደው ዘውግ ተኮር ግፍ፤ በደልና እልቂት ነው። ይህ ሁኔታ ካላቆመ የአሜሪካ መንግሥት ሊወስደው የሚችለው አቋም ደጋፊዎችን እንደሚስብ እገምታለሁ።

የአሜሪካ መንግሥት ወገንተኛነት ፍትሃዊና ሚዛናዊ አይደለም።

አንድ አፍጋኒስታን የሆነ ምሳሌ ላቅርብ። የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል በአፍጋኒስታን የቆየው ለሃያ ዓመታት ነው። በዚህ ወቅት፤ በግምት ብቻ በሚነገረው 176,000 አፍጋኖች ተገድለዋል። The New Yorker የተባለው መጽሄት በ መስከረም 2021 ባቀረበው ተከታታይ ዘገባ እንዲህ ብሏል። “በአፍጋኒስታን ጦረነት ግልፅ የሆነው አሜሪ በአፍጋን ነገዶች መካከል ያለውን መከፋፈል ለመፍታት አልሞከረችም። ሁሉን አቀፍ ተቋማት አልፈጠረችም። የፈጠረችው ሁለት አፍጋኒስታኖችን ነው። አንዱ በግጭትና በእልቂት የተበከለ። ሁለተኛው የአሜሪካን ተልእኮ ተቀብሎ ኃብት ያካበተና ተስፋ ያለው።” ኢትዮጵያም የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት በትህነግ/ህወሓት መራሹ ዘመነ መንግሥት ያደረጉት ተመሳሳይ ነው።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ስለ ሰብአዊና ዲሞክራሳዊ መብት ተቆርቋሪ ነን ይላሉ። አፍጋኒስታን የሆነው ምን ያህል ፍትሃዊነትና ሚዛናዊነት ያሳያል? ባለሥልጣናቱ መብትን የሚተረጉሙት ከራሳቸው ጥቅም አንጻር ኒው። አናንድ ጎፓል (Anand Gopal) “The Other Afghan Women,”  ኒው ዮርከር መጽሄት እንዲህ ብሏል። “Can the rights of one community depend, in perpetuity, on the deprivation of rights in another? የአንዱን ማህበረሰብ መብት ለማስከበር የሌላውን መብት ለዘላለም ማፈን ወይንም መካድ ተገቢ ነው?” ይህንን ጥያቄ ይጠይቅና በአንድ አካባቢ የሚኖሩ የአፍጋኒስታን ሴቶችን አስተያየት ይጠይቃል። ካሊዳ የተባለች ሴት እንዲህ ብላለች። “አሜሪካኖች ለእኛ መብት አላስከበሩም፤ አላመጡም….እንዲያውም፤ አሜሪካኖች አፍጋኒስታንን ከመልቀቃችው በፊት ታሊባኖችን ለመግደል ነው በሚል ሰበብ ቤታችን በዳይናማይት አፈራረሱት– በጦርነቱ የተገደሉት ወጣቶች፤ ሴቶች፤ ሽማግሌዎች ቁጥር አይታወቅም። እኔ ብዙ ዘመዶቸን አጥቻለሁ። በአየር ኃይል የሚገደለው አፍጋን ታሊባን ከሚገድለው ይበዛል….”

ቁም ነገሩ፤ አሜሪካኖች ጣልቃ በገቡበት አገር ሁሉ ታሪካቸው ተመሳሳይ ነው። ጨፍጭፈውን ይክዳሉ። ወግነው ገለልተኛ ነን ይላሉ። በኢትዮጵያም አንዱን ዘውግ ከሌላው በመለየት፤ ከፍተኛው እልቂት የተካሄደው በትግራይ ነው ይላሉ። በአፋርና በአማራው ክልሎች የተካሄደውንና አሁንም የሚካሄደውን እልቂትና ውድመት ትኩረት የሚነፍጉበት ምክንያት ሁሉን ነገር የሚያዩትና የሚፈርዱት ከጥቅማቸው አንጻር ስለሆነ ነው። በወለጋና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚጨፈጨፈውን ሕዝብ ትኩረት የማይሰጡበትም ምክንያት መለያየት የፖሊሲያቸው አካል ስለሆነ ነው። በአጭሩ፤ የመብት ጥያቄ ከፖለቲካ ግብ ጋር የተያያዘ መሆኑ ግልጽ ነው።

ድርድር ለማን?

በአፋርና በአማራው ንፁህና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ላይ በተከታታይ የሚካሄደውንና ለትግራይ ወጣት ትውልድ የእልቂት መሰረት የሆነውን የትህነግ ጦርነት በሰላም፤ በውይይትና በድርድር ለመፍታት የሚደረገው ጥረት መልካም ነው። እርቅና ሰላም ለሁሉም ይበጃል። ሆኖም፤ ተደራዳሪዎቹ ሁሉን ነገር “በምስጢር ይዘነዋል፤ ጥረታችን ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም፤ ሉዐላዊነት፤ ለመታደግ ነው” የሚሉት ብሂል ለኔ ግልፅነት ይጎድለዋል። የኢትዮጵያ ተራ አገር ወዳድ ዜጋ ድርድር በምን ላይ ነው? ለማን ጥቅም ነው? ማንን ይጎዳል? ማን ከሂደቱ ያተርፋል? ኢትዮጵያን ከተከታታይ ስርዓት ወለድና መዋቅራዊ ተግዳሮቶች ሊያላቅቃት ይችላል ወይ? የሚሉት ጥያቄዎችን ቢያነሱም ቅሉ፤ ጥያቄዎቹ አልተመለሱም። በእኔ እምነት መመለስ አለባቸው።

ትህነግ/ህወሓት ተወግዶ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስር ዶር ዐብይ አሕመድ ስልጣን ሲይዙ፤ እኔና እኔን የመሰሉ ለአስርት ዓመታት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ሲሟገቱ የቆዩና ድምፃቸውን አጥፍተው ኖረው ለውጥ ሲመጣ ብቅ ብቅ ላሉት ሁሉ በጋራ፤ ኢትዮጵያን “ከጨለማና ከአንድ ዘውግ የበላይነት” ዘመን ወደ ብሩህ፤ ፍትሃዊ፤ ሁሉን አሳታፊና ዲሞክራሳዊ አቅጣጫ የሚያሻግር እድለ ተፈጥሯል በሚል ተስፋ እንሽከርከር ነበር። በተለይ፤ በውጭ ግንኙነትና ፕብሊክ ዲፕሎማሲ፤ የውጭ ምንዛሬ በመሰብሰብና ለልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች በመለገስ፤ የሕዳሴ ግድብን ስኬታማነት በመታደግ ወዘተ ያልተቆጠበ አስተዋፆ አበርክተናል። በምንኖርበት አገር፤ በተለይ የአሜሪካ የመንግሥት ባለሥልጣናት ቆም ብለው እንዲያስቡ ለማድረግ ተችሏል። ለምሳሌ የበቃ (The No MORE Movement that a long time ago was stated as Enough (በቃ) ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በቃ አሁንም እንደ ገና መንቀሳቀስ አለበት። ምክንያቱም፤ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ወደፊት ሊወስኑ የፈለጉት የኮንግሬስ ረቂቅ ሕግ ከሆነ በኢትዮጵያና በኤርትራ ባለሥልጣናትና አመራሮች ላይ ከፍተኛ ጫና ይደረጋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያ ወታደራዊ ወጪ ከሃያ አምስት ቢሊዮን ብር ወደ መቶ ቢሊዮን ብር ተመነደገ! - ሚሊዮን ዘአማኑኤል 

የብልፅግና ጣጣ

ይህ ሁሉ ጥረት ተደርጎ ግን ራሱን ከኢህአዴግ ወደ ብልፅግና ፓርቲ የቀየረው ገዢው ፓርቲ መሪዎችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያላቸውን ግልፅነትንና ሃላፊነትን መርህ አልተወጡም። የሚታየው ክስተት ብዢታ፤ ብልጣ ብልጥነት፤ አስመሳይነት፤ የበላይነት ሽሚያ፤ የአመራር ወላዋይነት፤ ፖለቲካዊና ማህበረሰባዊ አለመተማመን፤ እርስ በእርስ መፈራራት፤ ከጥቅምና ከፖለቲካ ሥልጣን ጋር የተቆራኘ ዘውጋዊነት ወዘተ በግልጽና በሚያስፈራ ደረጃ ይንፀባረቃል። ሕዝቡ የችግሩ ፈጣሪ ስላልሆነ፤ ችግሩ በግልፅ ቢነገረው መፍትሄውን ለመፈለግም በባለቤትነት አጋር ሊሆን ይችላል። ግልፅነት ከሌለ ግን የዳበሳ ጉዞ ይሆናል።

ከትህነግ/ህወሓት አፋኝ፤ አምካኝና በሙስና የተጨማለቀ መርህ ወደ ተሻለ የፖለቲካ አቅጣጫ መሸጋገር ለኢትዮጵያ ህልውናና ለመላው ሕዝቧ ዘላቂና ፍትሃዊ ልማት ወሳኝ ነው በሚል ለውጡን ስንደግፍ ለቆየን ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ ብዢታና አሳሳቢ ሁኔታ እንደተከሰተብን ለመካድ አልችልም። ይህ ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ እንጂ እየተሻሻለ አልሄደም። ብልጣ ብልጡ ትህነግ በየአካባቢው የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ያሰራጫል። ሕዝብ ከሕዝብ ጋር እንዲጠፋፋ ይቀሰቅሳል። በአፋር ላይ የሚካሄደው በቂ አይደለም በሚል ስልት፤ ችግሩ ወደ ሶማሌ ክልል እንዲዛመት እየገፋ ይገኛል። አማራውና ኦሮሞው እንዳይተማመን፤ “እሳትና ጭድ” ሆኖ እርስ በእርሱ እንዲጋጭ የማይሰራው ሴራ የለም። ለዚህ የሚበጀው እውነተኛ ጠላትን ከእውነተኛ ወዳጅ መለየት ነው የሚል እምነት አለኝ። አማራጮቹም ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን የሚመጥኑ መርሆዎች ካልሆኑ የበላይነቱን የሚይዙትና አጀንዳውን የሚወስኑት ትህነግ/ህወሓትና ኦነግ ሸኔ ይሆናሉ።

መርሆዎች ስል የተሻለ የፖለቲካ ባህልና አመለካከት፤ የተሻለ አቅጣጫ፤ የተሻለ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካና የልማት ፍኖተ ካርታ፤ የተሻለ የውጭ ግንኙነት አቅጣጫ፤ የተሻለ ሕገ መንግሥትና የአስተዳደር መርህ፤ የተሻለ የስራ ፈጠራና የማምረት እቅድ፤ ወዘተ በአገር ደረጃ ለኢትዮጵያና ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ይቅረብ ማለቴ ነው።

በመሬት ላይ የሚታየው ሃቅ፤ እየጎለመሰና የበላይነቱን እየያዘ የመጣው የፖለቲካ ኃይል ትህነግ/ህወሓት መሰል ተተኪነት ሆኖ መንፀባረቅ መጀመሩ ነው። ይህንን ክስተት የሚያንፀባርቀው ምንድን ነው? የጦርነቱ ሂደት፤ ግልፅነትና ሃላፊነት ጥያቄ የሚያሳየው የኢትዮጵያ ምክርት ቤት “ሽብርተኛ” ብሎ የሰየመው ትህነግ በአጀንዳው ላይ ተፅእኖ ፈጣሪ ሆኖ ይታያል። ጦርነቱ ገና ሳይገባደድ “ህወሓት እንደ ዱቂት በኗል” እና ሰላም ወርዷል በሚል ሰበብ ምክር ቤቱ የአስቸኳይ አዋጁን መሳቡ ሌላው ምልክት ነው። ከዚህ የሚቀጥለው ውሳኔ ትህነግን/ህወሓትን “ሽብርተኛ ነው” የሚለውን ስያሜ ማንሳት ይሆናል የሚሉ ብዙ ተመላልካቾች አሉ።

ቢነሳም ባይነሳም፤ ድርጅቱ (ትህነግ) ከዓላማው ዝንፍ የሚል አይመስለኝም። ትህነግ/ህወሓት በ 30/21/2013 ዓ.ም. ባወጣው “የትግል ልዩ ምእራፍ እድገቶች እና የምከታችን ስትራተጂዎች፤ ስልቶች እና አቅጣጫዎች” ድምዳሜ የፌደራሉ መንግሥት እንደ ተዛባና እንደሚገረሰስ ይናገራል። “ጠላት በብዙ መልኩ ተዛብቷል፡፡ የተዛባውም ጠላት እድል ሳያገኝ ሙሉ በሙሉ መሰናበት/ መገርሰስ፣ መደምሰስ አለበት፡፡ አሁን ባለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ የኦሮሞ አመጽ የተሻለ አመራር አግኝቶ እየተጠናከረ እና እያደገ/ እየጨመረ ሲሄድ ሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰቦች ከዚህ በኋላ ህጋዊ መንግስት አይደለህም ብለው ወደ ትግል እና አመጽ ካመሩ ጠላት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል፡፡ እኛ የጀመርነው ትግል በሁሉም መልኩ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ገጽታዎቹን አቀናጅተን በሰፊው ከተሰማራንበት/ ከዘመትንበት ሀገር ደረጃ ለሚኖር ውጤት ጠቃሚ ሚና መጫወታችን አይቀሬ ነው፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ ለረጅም ጊዜ መቆየት የለብንም።”

ትህነግ/ህወሓት ፕሮግራሙንና አጀንዳውን ይፋ አድርጓል። ከኦነግ ሸኔ ጋር ቀጥተኛና ስትራተጂክ የሆነ የተግባር ግንኙነት እንዳለውም አሳውቋል። የትህነግን ዓላማ ከሚጋሩ፤ በተለይ ፀረ-አሃዳዊያን ከሚላቸው የዘውግ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሽግግር መንግሥት ለመመስረት እቅድ እንዳላቸው ይናገራል።

ቁም ነገሩ፤ ትህነግ/ህወሓት ለቆመለት ዓላማ ከፍተኛ መስዋእት ለመክፈል የተዘጋጀ ቡድን መሆኑን በተደጋጋሚ አስመስክሯል። የሚናቅ ኃይል አይደለም። ትግሉን የሚያካሂደውም በዘፈቀደ አይደለም። በጥናት፤ ሕዝብን በማስተማርና በማንቀሳቀስ፤ ሕዝቡን የትግሉ ባለቤት በማድረግ፤ በምርምር፤ በብልሃት፤ በመርህ ወዘተ ተደግፎ ነው። የኃይል አሰላለፍን ፋይዳ በሚገባ የተገነዘበ ሆኖ አገኘዋለሁ። በሰንዱ ላይ እንዲህ ይላል። “ያለንበት መድረክ እድሎችን ብቻ ሳይሆን ለከባድ ፈተናዎችም የተጋለጠ ነው፡፡ ትግል በባህሪው ዳገት እና ቁልቁለት ያለው እልህ፣ ጽናት አና ብልሀት ይጠይቃል፡፡ ይህ ነባራዊ አደጋ ከሁሉም በላይ በትግራይ ህዝብ ላይ የተቃጣ ነው፡፡ ህ.ወ.ሓ.ትን ለማጥፋት ነው፡፡ ይህ አደጋ ከአንድ ወገን የመጣ አይደለም፡፡ ከአሀዳዊያን ሀይሎች እና ከኢሳያስ ቡድን ጋር በአንድ ተጣምሮ የመጣ ነው፡፡ እነዚህ አንድ ላይ የገጠሙ/ የተቀናጁ የትግራይ ህዝብ ጠላቶች ህ.ወ.ሓ.ትን ለማጥፋት የሚቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ ሙሉ በሙሉ ታግለን እስክናሸንፋቸው ድረስ የሚያጋጥመው ፈተና ቀላል አይሆንም፡፡ እኛ ደግሞ ጠላቶቻችንን ለመደምሰስ እና ለማጥፋት ተገደንም ቢሆን መሰማራት አለብን፡፡ ስለዚህም ጠላትን ለመደምሰስ የምናደርገው ትግል እና ከእነርሱ ሊመጣብን የሚችል ተቃርኖ ለመመከት የሚጠይቀን ትግል ከባድ እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡”

እኔ የምጠይቀው ጥያቄ፤ የብልጽግና ፓርቲ አባል የሆኑ ፓርቲዎችና ባለሥልጣናት ይህ ቆራጥነትና ስልት የሚያስከትለውን የህልውና አደጋ በሚገባ ተገንዝበውታል? ከተገነዘቡትስ ተመጣጣኝ ወይንም ከዚያ የላቀ አደረጃጀትና የሚመክት እቅድ አውጥተዋል? ቆራጥነቱስ አላቸው ወይ?

ትህነግ/ህወሓት ዛሬም እንደ ትላንቱ ዋና ጠላት የሚላቸው “አሃዳዊያን” አማራውን መሆኑን መዘንጋት ጂልነትና ሞኝነት ነው። የኢሳያስ መንግሥት በራሱም ላይ ከትህነግ/ህወሓት አደጋ ይመጣል የሚለውን ወደ ጎን ትተው፤ ትህነጎች ትኩረት ያደረጉት የኤርትራ መንግሥት ከአሃዳዊያን ጋር ያለውን ጠንካራ ግንኙነትና በትህነግ/ህወሓት ላይ ሊመጣ የሚችለውን የህልውና አደጋ ነው። የትህነግ የመሬት መስፋፋት እቅድ ኤርትራንም ይመለከታል። ለምሳሌ፤ የባህር በር እንዲኖረው ከተመኘ ትህነግ መለስ ዜናዊ ፈቅዶና ፈርሞ ለኤርትራ ያስረከበውን አሰብን ይገባኛል ሊል ይችላል። ሌላው ህልም ትግራይ ተናጋሪዎች ሁሉ በአንድነት (ኤርትራና ትግራይ ማለት ነው) አንድ የትግራይ ተናጋሪ አገር ለመመስረት እቅድ ቢኖርስ?

ትህነግ “De facto” የትግራይ መንግሥት ብሎ ራሱን ከሰየመ፤ የሚቀጥለው እርምጃ ለዓለም መንግሥታት “ትግራይ ነጻ አገር ሆናለች” ብሎ ማወጅ ሊሆን ይችላል (De jure). ይህንን ደግሞ ለማድረግ ወልቃይትን፤ ጠገዴን፤ ጠለምትንና ራያን ማጠቃለል ግድ ይላል። ይህ አንዱ የድርድሩ ቅድመ ሁኔታ እንደሚሆን እገምታለሁ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የዘመን መለወጫ መልእክቶቻችንና መሪሩ እውነታ - ጠገናው ጎሹ

ትህነግ በሰነዱ ላይ እንዲህ ብሏል። “በማንኛውም ሁኔታ ስር የትግራይ የምከታ ውስጣዊ አቅም ወሳኙ ስትራቴጂያችን በሁሉም በማያዳግም መልኩ ለመመከት ወደ ሚያስችለው ደረጃ ለመሸጋገር እንረባረባለን፡፡ የውስጣችን ሁሉንም አይነት ተቃርኖ እየመከትን ስልጣን ላይ ያለውን ቡድን ለመገርሰስ፣ ከአብይ ቡድን በኋላ የሚኖረው ሂደት በተጽእኖዋችን ስር እንዲመራ እና በዋናነት ደግሞ የምናምንበትን የትግራይ ህዝብ ዘላቂ መፍትሔ የምናረጋግጥበትን በአጠቃላይ ሁሉም ነገር በፈለግነው እና በተነበይነው/ ባቀድነው/ ልክ እንዲጓዝ ወሳኙ ጉዳይ የመደራደር አቅማችንን ጫፍ ማድረስ ነው፡፡ በፍፁም የማንሳሳትበት እና የማንወድቅበት ስትራቴጂ ካለ ውስጣዊ አቅማችንን የማጠናከር ስትራቴጂ ይሆናል፡፡”

 

ለማጠቃለል፤

አንድ፤ ትህነግ/ህወሓት እስከመጨረሻው ጠላት ናቸው ብሎ የገመገሟቸውን ኃይሎች በሙሉ በማያዳግም ደረጃ የማውደም እቅዱን በተደጋጋሚ ይፋ አድርጓል። በአፋርና በአማራው ክልል ያካሄደው እልቂትና የኢኮኖሚ ውድመት ይህን ስልት ይደግፋል። ትህነግ/ህወሓት በማያሻማ ደረጃ የአፋርንና የአማራን መሬቶች ለመንጠቅና ለማጠቃልለል ያቀደውን ግብ ስኬታማ ሳያደርግ ለድርድር ራሱን አያጋልጥም። ስለሆነም፤ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ትህነግን/ህወሓትን ሙሉ በሙሉ ከመደምሰስ ውጭ ሌላ አማራጭ የላትም። ሕዝብ አገር አልባ ከሆነ  ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ፋይዳ ቢስ ሊሆኑ የሚችሉበት እድል ከፍ ያለ ነው። “ያልጠረጠረ ተመነጠረ” የሚለው ብሂል እንዳይከሰት እሰጋለሁ።

ሁለት፤ ትህነግ የዐብይን መንግሥት ማን ይተካዋል? ለሚለው ጥያቄም አንድ አይነት የፌደራሊስትና ኮ-ፌደራሊስት ኃይሎች ጥምረት መንግሥት እንዲመሰረት የሚስራ መሆኑን ጠቁሟል። የዐብይን መንግሥት ሕዝቡ መርጦታል። ሃላፊነቱን ግን በቅጡ እንዲወጣ እመክራለሁ። በተለይ በአፋርና በአማራው ክልሎች እንደገና ለሚካሄደው ጦርነት ሙሉ ድጋፍ የመስጠት ግዴታ አለበት። በተጨማሪ፤ ኦነግ/ሼኔን ሙሉ በሙሉ ለማምከን ግዴታውን እንዲወጣ እመክራለሁ። ያለፈው ታሪክ ግን ቁርጠኛነት አያሳይም። ለምሳሌ፤ ይህ ሽብርተኛ ቡድን ባንክ ሲዘርፍ ዝም ተባለ፤ አሁን ቀረጥ መሰብሰብ ጀምሯል የሚል ወሬ ይነገራል። ንጹሃንን ይጨፈጭፋል፤ ግን  ቆራጥ እርምጃ አልተወሰደም። የሃዘን መግለጫም ሲሰጥ አልሰማም። ለምን?

ሶስት፤ በማንኛው የፖለቲካ ሂደት “በዋናነት የምናምንበትን የትግራይ ህዝብ ዘላቂ መፍትሄ” ማረጋገጥ ግቡ መሆኑን አስምሮበታል። ለዚህ አማራጩ ትግራይን የሚወክሉትን በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት የሚያምኑትን ወገኖቻችን ማደራጀት፤ ማጠናከር እና ማማከር ውጤታማ እንደሚሆን እገምታለሁ።

አራት፤ የአሜሪካ ባለሥልጣናት በአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝና ለእነሱ ብሄራዊ ጥቅም የቆመ መንግሥት ስለሚፈልጉ ትህነግ/ ህወሓት በድርድርም ሆነ በአመፅ “ታላቋን ትግራይን መስርቻለሁና እውቅና ስጡኝ” ብሎ ቢጠይቅ ይሰጡት ይሆን ወይ? የሚለውን ጥያቄ ማስተናገድ አስፈላጊ ይሆናል። ቢያንስ ቢያንስ ወደ ፊት ሊከሰት ይችላል የሚለውን ሁኔታ በጥናትና በምርምር መገምገም ያስፈልጋል።

አምስት፤ በአሁኑ ወቅት ትህነግ/ህወሓት ለሰላምና ለድርድር “ዝግጁ ነኝ” ማለቱ ከላይ የተጠቀሰውን “ጠላትን የመደምሰስ” ግብን ፋይዳ ቢስ አያደርገውም። ትህነግ/ህወሓት የአማራውን ህዝብ ለይቶ “የትግራይ ሕዝብ የህልውና ጠላት ነው” ያለውን አጠናከረው እንጂ አልበረዘውም፤ አላሻሻለውም፤ አልሳበውም። የአማራው ሕዝብ ዋና ስራ በአንድነት፤ ለአንድ የህልውና አደጋ አደረጃጀትና አመራር ስልት መቀየስ ግድ ይላል። ፋኖን በማያሻማ ደረጃ መደገፍና ሚናውን ከፍ ማድረግ አስፈላጊ ነው። የፌደራሉ ባለሥልጣናት ሃቀኛውን ፋኖ ከባለጌው መለየት እንጂ የፋኖን ትጥቅ ማስፈታት ለኢትዮጵያ ህልውና አደጋ እንደሚፈጥር አምናለሁ። በፋኖ ስም የሚንግዱትንና ወንጀል የሚፈጽሙትን መለየት አግባብ አለው። ፋኖ በፈቃደኛነት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን፤ በተለይ በተከታታይ የእልቂት ኢላማ ለሆነው ለአማራው ሕዝብ መቆሙ ያስመሰግነዋል እንጅ ስጋት ሊፈጥር አይችልም።

ስድስት፤ ከዚህ ከፍተኛ እልቂትና ውድመት ካካሄደ ድርጅት ከትህነግ/ህወሓት ጋር የሚደረገው ምስጢራዊ ውይይትና ድርድር በምን መስፈርቶች ላይ ወይንም በምን ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ተመስርቶ ነው? የሚለው ጥያቄ አልተመለሰም። ድርድር ሲካሄድ ቀይ መስመር የሚሆኑ አስኳል ጉዳዮች ይኖሩ ይሆን? ከእነዚህ መካከል በኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት፤ ነጻነትና ሉዐላዊነት ድርድር ሊካሄድ ይችላል? በእኔ እምነት አይቻልም። ይህ ቀይ መስመር ነው። ዘውግ ተኮር እልቂት ቀይ መስመር ነው።

ሰባት፤ ለኢትዮጵያ ምን አይነት ድርድር ይጎድላታል? ተብየ ብጠየቅ፤ ልጆቿ፤ በተለይ በትህነግ ዘውጋዊ የፖለቲካ ባህል የታነፁት የፖለቲካ መሪዎቿ፤ ለፖለቲካ የበላይነት እንጂ ለሰው ልጅ፤ ዘውግ ወይንም እምነት ሳይለዩ፤ ለሚደረጉ ጥረቶች ያላቸው ቁርጠኛነት፤ ደፋርነት፤ ክብርና ፍቅር፤ የሚያሳዩት አመለካከትና ተግባር እጅግ በጣም በሚያሳፍር ደረጃ ወደ ታች መውረዱን እጠቅሳለሁ። ይህንን አገራዊ የፖለቲካ ድክመት ትህነግ/ህወሓት እና ኦነግ/ሸኔ እየተጠቀሙበት ነው። የአሜሪካ መንግሥትም ቢሆን ክፍተት መኖሩን ያምናል። ለምሳሌ፤ እኔ ባለሁበት ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ስናደርግ፤ “እናነተ እኮ አንድ አይደላችሁም። ኢትዮጵያዊያን ስትሉ ምን ማለታችሁ ነው? ዛሬ እናንተ ትመጣላችሁ፤ ነገ ትግሪዎች፤ ከነገ ወዲያ ኦሮሞዎች ወዘተ” እያሉ ይተቹናል።

ስምንት፤ የኢትዮጵያ ፌደራል እና ክልል ባለሥልጣናት በማያሻማ ደረጃ የጋራ ውይይት አድርገው የዓላማ አንድነት እንዳላቸውና እነዚህን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የምንላቸውን መለያ እሴቶች ሙሉ በሙሉ እንደሚጋሩ ይፋ ቢያደርጉ የምእራብ አገሮች መንግሥታት ሊያከብሯቸው የሚችሉበትን እድል ለመፍጠር ይቻላል። በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት እሴቶች ላይ ቃል ኪዳን የሚገባበት ወቅት ዛሬ መሆኑን አሰምርበታለሁ።

ወደ ኋላ ብናይ፤ እነዚህን እሴቶች እንዲሸረሸሩና እንዲበከሉ ያደረገው በዘውግና በቋንቋ የተዋቀረው ሕገ መንግሥትና የክልል አስተዳደር ነው። በድርድሩና በውይይቱ ይኼ መሰረታዊ ተግዳሮት ይነሳል ወይንስ አይነሳም? ከሆነ ለምን? እንዴት ከትህነግ/ህወሓት ሊለይ ይችላል?

ዘጠኝ፤ በግለሰብ ደረጃ ስከተታለው የኢትዮጵያ ምሁራንና ልሂቃን በአንድነት፤ ለአንድ አገርና ለአንድ ብሄራዊ ወይንም አገራዊ አላማ ለመቆምና ድምፅ  ለማሰማት አለመቻላችን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን እየጎዳ ነው። እየናደ ነው። ኢትዮጵያ በዘውጋዊ ፖለቲካ ባህል ራሷን ወደ ታች ዝቅ አድርጋለች ቢባል ስህተት አይሆንም። ይህ ክፍተት የሚሞላበት ወቅት አሁን ነው።

አስር፤ ይህንን ጎጅ፤ የሚያመክን፤ አገራችንና መላውን ሕዝቧን ዝቅ የሚያደርግ የማህበረሰባዊና የፖለቲካ ባህል የፈጠረው ማነው? የሚለውን እያንዳዱ ኢትዮጵያዊ ሊያስብበት ይገባል። ችግሩን የፈጠሩትን ኃይሎች መፍትሄውን ይሰጡናል ብሎ ማሰብ ራሱ ችግር ነው።

ትህነግና ኦነግ በጋራ ሆነው የመሰረቱት ኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ተቀብሎ ኢትዮጵያን በበላይነት ሲገዛ ራሱን አስር ጊዜ አድሳለሁ ብሎ ቢለፈልፍም፤ መሰረታዊ አስተሳሰቡን፤ ርእዩተ አለሙን፤ የኢኮኖሚ መርሆውን ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ በሚመጥን ደረጃ እንቅስቃሴ አላካሄደም። በተመሳሳይ፤ ብልፅግና ተብሎ የሚታወቀው ገዢው የፖለቲካ ፓርቲ አሁንም ቢሆን በዘውግ ስብስቦች ልሂቃን የተዋቀረና የሚመራ ነው።

በመጨረሻ፤ እኔን የሚያሳስበኝ ሕገ መንግሥቱና የኢትዮጵያ የአስተዳደር ካርታ ቅርፅ እንዳለ ከቀጠለ በትህነግ/ህወሓትና በኦነግ/ሸኔ አማካይነት የሚካሄደው ዘውግ ተኮር እልቂትና ውድመት የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት፤ ሉዐላዊነት፤ የመላውን ሕዝቧን አብሮነት፤ ደህንነት፤ ፍትሃዊና ዘላቂ ልማት እንዳይፈታተኑት ነው።

 

February 18, 2022

 

dr aklog birara 2
Dr. Aklog Birara former Sr. Advisor at World Bank,, Commentator at Center for Inclusive Development (ABRAW) and a regular contributor to Zehabesha.com

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share