Part 20 -ሁለት መቶ ሺ!፣ የመጨረሻው መጀመሪያ? እና የክትባት ግዴታ – ፀጋዬ ደግነህ (ዶ/ር)

ለተከበራችህ ወገኖች                                                          5ኛው ማዕበል

የኮሮና ልምድ ከጀርመን –  ሁለት መቶ ሺ!፣ የመጨረሻው መጀመሪያ? እና የክትባት ግዴታ      28.01.2022

ካለፈው በመቀጠል የኦሚክሮን ማዕበል በጀርመን ከተከሰተ ጀምሮ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ጀርመንን እያጥለቀለቀ ይገኛል። በጀርመን እና በጎረቤት አገሮች የሚመዘገበው በወረርሽኝ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው። በአለፉት ሰባት ቀናት ውስጥ ከ100,000 ነዋሪዎች መካከል የተገኘው ኢንፌክሽን በአማካይ በእጥፎች በመጨመር ከ1017 በላይ አሻቅቧል። ይህም በአለፈው ጽሁፌ ላይ ታህሳስ መጀምሪያ ውስጥ 340 ነበር። የሚያዙትም በቀን በሰኔ እና በሐምሌ ከመቶዎች፣ በመስከረም ወደ 15ሺዎች ጨምሮ፣ በህዳር መጨረሻ ላይ እስከ 70ሺዎች በላይ ሲወጣ አሁን በቀን በ27.01.2022 እስከ ከ228ሺዎቹ በሪኮርድ አሻቅቧል! ቢሆንም ህይወታቸው በቀን የሚያልፈው ከሌሎች ወራቶች ጋር ሲተያይ በአንጻሩ እጅግ ወርዷል ለምሳሌ በ24 ሰዓት  ውስጥ 188 ሰዎች ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ህይወታቸው ማለፉ ተመዝግቧል። ይህ ቁጥር በታህሳስ ከ500 በላይ ደርሶ ነበር። ወረርሽኙ ቢበዛም በህይወት ላይ የሚያደርሰው ግን አደጋ ቀንሷል። ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በጀርመን ከ9,238,931  በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል።  ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ የሟቾች ቁጥር 117,314 ደርሷል። ይህ ሁሉ ሆኖ የጀርመን ኢኮኖሜ በጥሩ ሁኔታ አገግሟል። መንግስት በአንድ በኩል የክትባት ግዴታን ሲያስብ በሌላው በኩል ደግሞ ሎክዳውኑን ለማላላት በመስራት ላይ። አውሮፓ ውስጥ እንግሊዝ እና ዴንማርክ ሎክዳውኑን በእጅጉ ለማላላት ወስነዋል።

  1. ማህበርዊ ግንኙነት

ቁጥራቸው ከበዛ ሰዎች ጋር ከቤት ውጭ ካሉ ሰዎች ጋር ከመገናኘት በፊት በኮሮና ቫይረስ ኢንፌክሽን አለመኖሩን ለማረጋገጥ ሙሉ በሙሉ መከተብ ወይም ማገገም መስፈርቱ ነው። አየር በሚያስተላልፉ በቤት ውስጥ አዳራሾች ውስጥ ለሁሉም ክስተቶች የተከተቡ እና ያገገሙ የሚለው ደንብ የጸና ነወ። ግድበቶች በጀርመን ግዛት ተመሳሳይ ቢሆኑም እንደየፌደራል ስቴቱ ይለያያሉ። ለምሳሌ በበርሊን በቤት ውስጥ የሚፈቀደው ቢበዛ 50 ሰዎች ሲሆኑ ይህም ሙሉ በሙሉ ለተከተቡ ወይም ላገገሙ ብቻ ነው የሚፈቀደው። ከቤት ውጭ የግል ስብሰባዎች በአጠቃላይ የተሳታፊዎች ቁጥሩ ከ200  በላይ ማለፍ የለበትም ይህም ከሆነ ሙሉ በሙሉ ለተከተቡ ወይም ላገገሙ  ብቻ ነው የሚፈቀደው። ህጻናት እና ወጣቶች በኮሮና ምርመራ ፖዘቲቭ ከሆኑ የክፍል ጓደኞቻቸው ጋር ከተነካኩ በለይቶ ማቆያ ውስጥ መግባት እንደሌለባቸው ተወስኗል። ለምሳሌም ለጉዳይ ሲገባ ለመመዝገቢያ የሚጠቀመው Luca አፕልኪሽን ስራውን አቁሟል። በባቫሪያ በስፖርት ዝግጅት እስከ 10ሺ ተመልካቾች ተፈቅዷል።

  1. የተከተቡ ወይም ያገገሙ 2„ጂ“ ደንብ
ተጨማሪ ያንብቡ:  የማይግሬን ራስምታትን ለማስታገስ (በዶ/ር ሆነሊያት ኤፍሬም)

በብዙ ከተማዎች፣ ወረዳዎች የተከተቡ ወይም ያገገሙ የ2ጂ (Geimpfte und Genesene / Vaccinated and Recovered)  ደንብ የጸና ነው። ያገገሙ የሚለው ከ6 ወር ወደ 3 ወር እንዲወርድ ተወስኗል። ምግብ ቤቶች፣ የቲያትር ቤቶች፣ ሲኒማ ቤቶች፣ ሙዚየሞች፣ የመዋኛ ቦታዎች፣ የአካል ብቃት ማዕከላት፣ የውስጥ ክፍሎች፣ የተወሰኑ የመዝናኛ ቦታዎችን ወዘተ መግባት የሚፈቀድላቸው ክትባቱን የወሰዱ እና ያገገሙ እንዲሁም እንደየሁኔታው ተጨማሪ የቀኑን ፈጣን የናሙና ምርመራ የሚያቀርቡ ብቻ ነው። ለምሳሌ ምግብ ቤቶች በክሊኒኮች፣ በሆስፒታሎች በቤተ አረጋውያን እና የመሳሰሉት ቦታዎች የሚሰሩት ከክትባት በተጨማሪም በየጊዜው መመርመር ይኖርባቸዋል። ሶስተኛ ማጎልመሻ የተከተቡ ከሆነ ግን በምግብ ቤቶች ለመመገብ የቀኑን የናሙና ምርመራ ማድረግ አያስፈልጋቸውም። በህክምና ወይም በጤንነት ምክንያቶች በተረጋገጠ መስፈርት መከተብ ያልቻሉ ሰዎች 2G በሚተገበርበት ቦታ ላይ ዕለታዊ አሉታዊ የናሙና ምርመራ ውጤት ማቅረብ ያስፈልጋቸዋል። በህዝብ ማመላለሻዎች ለመገልገል የሚችሉት የተከተቡ ወይም ያገገሙ ወይም የቀን ምርመራ ውጤት ያቀረቡ ናቸው። ይገኛል፣ የዕለት ዕለት ችርቻሮ ዘርፉን የ2ጂ ደንብ እስካሁን ድረስ አይመለከተቸውም። ቀኝ አክራሪው „አማራጭ ለጀርመን“ የተሰኝው ፓርቲ ይህንን 2ጂ ህግ በመቃወም በጀርመን ከፍተኛው ፍርድቤት ያቀረበው ክስ ከቀናት በፊት ውድቅ ሁኗል።

  1. የክትባት ግዴታ

ከሶሻል ዲሞክራቶች፣ ከአረንጓዴ እና ሊበራሎች የተወጣጣው የሶስትዩሹ የጥምር መንግስት ክትባትን በተመለከተ የተለያዩ አማራጮችን በማቅረብ ፓርላማው ተወያይቶበታል። ይህ ውይይት በከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ የተደረገ ነበር፣  ከፍተኛ የሆኑ ሰላማዊ ሰልፎች እና ማስፈራራቶች እየተካሄዱ ይገኛል። የክትባት ግዴታው ለመንግስት ፈታኝ ሆኗል። የጀርመን ፓርላማ ከተወያየ በኋላ በሚቀጥለው መጋቢት ላይ ይወስናል። ለፓርላማው የቀረቡት የክትባት ግዴታ አማራጮች 1ኛ እድሜ ከ18 ዓመት በላይ የሆኑት፣ 2ኛ ዕድሜ ከ50 በላይ ለሆኑት፣ 3ኛ በጭራሽ አያስፈልገም የሚሉ ናቸው። የመከተብ ደጋፊዎች የሚሉት በሽታውን በማስተላለፍ የሌላውን ሰው ጤንነት እና አካል ላይ ጉዳት ማድረስ የሰውን መብት እና ማህበርሰቡን ሰላም መጣስ ነው ሲሉ፣ ተቃዋሚዎች ደግሞ የጀርመን ህገመንግስት ስለግለሰብ መብት እና የሰው አካልን የመጠበቅ የሰጠውን ነጻነት የሚቃረን ነው ይላሉ። ሌላው ግልጽ ያልሆነው አንከተብም ባሉት ላይ ምን አይነት ቅጣት ይጣላል የሚለው ነው። እስካሁን በጤና እና እንክብካቤ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ እና እንደየስራው ባህሪይ የሚመለከታቸው የመከተብ ግዴታ እንዳለባቸው ይታወቃል።

  1. በኮሮና፣ ትይዩ የተከሰተው ጉንፋን

ወቅታዊው የሆነው በተለይም ከቅዝቃዜ ጋር የተያያዘው ጉንፋን በብዛት በጀርመን እየታየ ሲሆን ኮሮና መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ደጋግሞ መመርመር አስፈላጊ ነው። በአብዛኛው ለጥቂት ቀናት የሚከሰተው ጉንፋን የመከላከል አቅም የተዳከመ ሰው ከያዘው በመጀመሪያው ቀናት ከበድ እንደሚል ኢክስፐርቶቹ ያስረዳሉ። ቢሆንም በማንኛቸውም ዓይነት ምልክት የኮቪድ ናሙና ምርመራ ይመከራል።

  1. ኮሮና እና የPCR ምርመራ
ተጨማሪ ያንብቡ:  ደም ብዛት የያዘህ ጨው አብዝተህ በመመገብህ ነው ተባልኩ፤ እውነት ይሆን?

የኦሚክሮን ልውጥ ተህዋሲ የኮሮናን ኢንፌክሽኖችን ቁጥር ከፍ በማድረጉ የተነሳ ላቦራቶሪዎቹ ለ PCR ምርመራዎች ከአቅማቸው በላይ ሆኗል። በሳምንት ከ2.5 ሚሊዮን በላይ PCR  ምርመራዎችም ይካሄዳሉ። ለPCR ምርመራ እስከ 3 ሰዓታት ድረስ ሰልፎች ሰዉ ይቆማል።  በዚህም የተነሳ የPCR ምርመራ ቅድሚያ መስጠት ይገባል በማለት  – የፌዴራል እና የክልል መንግስታት ሰኞ ጥር 24፣ 2022 ተስማምተዋል። ስለዚህም PCR የሚመረመሩት ከፍተኛ ተጋላጭ ለሆኑ ታካሚዎች፣ ለኮሮና ተጋላጭ ቡድኖች፣ ለሚንከባከቧቸው እና ለሚያክሟቸው ሰራተኞች ነው፣ ለምሳሌ የሕክምና ሰራተኞች እና የአረጋውያን እንክብካቤ ተቋማት ሰራተኞች። ቀሪው ሰው PCR ያልሆነ የፈጣን ምርመራን ብቻ ያደርጋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌሎች አገሮች የተለየ አካሄድ እየወሰዱ ይገኛል። በተለይም ኦስትሪያ ለ PCR ትኩረት በመስጠት በሰፊው ስታቀርብ ለምሳሌ በዋና ከተማው በቪየና ውስጥ ሁሉም ዜጎች ከክፍያ ነጻ PCR በየቀኑ መመርመር ይችላሉ።

  1. የሌላ ሀገራት ልምዶች – የክትባት ግዴታ

ከየካቲት ወር ጀምሮ ከ14 ዓመት እድሜ ጀምሮ ለሁሉም ኦስትሪያውያን ክትባቱ የግድ ይሆናል። ጥሰቶች እስከ 3,600 ዩሮ ቅጣት ያስቀጣሉ። በጣሊያን ከጥር ጀምሮ ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው ሁሉ መከተብ አለባቸው። ቫቲካን ከየካቲት 8 ጀምሮ ለሁሉም ነዋሪዎች እና ሰራተኞች ክትባት መስጠት ግዴታ ነው። ኢንዶኔዢያ ያልተከተቡ ሰዎች ላይ ቅጣት አስቀምጧል። እስከ 300 ዩሮ የሚደርስ ቅጣት ማለት ከአማካኝ ወርሃዊ ገቢያቸው ሁለት እጥፍ ይቀጣሉ።

ታጂኪስታን እና  በቱርክሜኒስታን ግዴታ ሲሆን፣ በኢኳዶር ከ5 ዓመት እድሜ ጀምሮ መከተብ ግዴታ ነው።

የክትባት ግዴታን ለተወሰኑ ቡድኖች ያጸኑ አገሮች ደግሞ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ኮስታሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጂየም፣ ግሪክ፣ ላቲቪያ፣ እንግሊዝ፣ ሃንጋሪ፣ ሩሲያ፣ ስሎቬኒያ፣ ካዛክስታን፣ ፓኪስታን ሲሆኑ፣ ከአፍሪካ ደግሞ ዚምባብዌ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋምቢያ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ ናቸው።

  1. የክትባት ይዘት

4,12 ቢሊዮን (52,8 %) የአለማችን ህዝብ ሲከተብ፣ በየቀኑ እስከ 28 ሚሊዮን ህዝብ ይከተባል። አፍሪካ እስካሁን ከ10% በታች ብቻ ሰው ነው ሁለት ጊዜ የተከተበው። ለቁጥር ያህል ጀርመን 61.2 ሚሊዮን (73.5%)፣ ቻይና ወደ 1.22 ቢሊየን (88%)፣ ሕንድ 693 ሚሊዮን (50.2%) ፣ ዩናይትድ ስቴትስ 210 ሚሊዮን (63.8%)፣ ብራዚል 149 ሚሊዮን (70.2%)፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ 9.27 ሚሊዮን (93.7%) ሲከትቡ ከአፍሪካ ለመጥቀስ ሞሮኮ 23,2 ሚሊዮን (62,7%) ደቡብ አፍሪካ 16.5 ሚሊዮን (28.1%)፣ ኢትዮጵያ 1,6 ሚሊዮን ሰዎች (1.4%) ሁለት ጊዜ ደግመው ተከትበዋል። ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር ሂደቱ በኢትዮጵያ  ዝግምተኛ ነው።

ጀርመንን ጨምሮ በብዙ አገሮች ሁለት ጊዜ ተከትበው ሶስት ወር ላለፋቸው የማጠናከሪያ ሶስተኛ  ክትባት  COVID booster shots ሲሰጥ፣ በጀርመን የወሰዱት 51.7% ደርሷል።

  1. የኮሮና ልምድና ከጀርመን እና የመጨረሻው መጀመሪያ?

የተከተቡትንም ጨምሮ በኮቪድ የሚያዙት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቢበዛም የኮቪድ ተህዋሲ የሚያደርሰው አደጋ ሆስፒታል ከሚገቡት እና ከሚሞቱት አኳያ ሲታይ በአንጽሩ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ የኮቪደ ወረርሽኝ መጨረሻ ተቃርበ ወይስ ሌላ ልውጥ ተህዋሲ ይመጣ ይሆን በሚል ተስፋ እና ስጋት መሃል እንገኛለን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የደ/ሰ/መ/ቤ/ክ ፓሪሽ ፕሮግራም አመታዊ ሄልዝፌር (በሚኒሶታ ለምትኖሩ ወገኖቻችን ነፃ የህክምና ምርመራና ትምህርት ቀን)

 ከ2020 ጀምሮ በተከታታይ ወደ 20 የሚጠጉ ጽሁፎችን በጀርመን የገባውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ አቅርቢያለሁ። ሊጠቅም ይችላል ያልኩትን በመጭመቅ ከዚህም ከዚያም በማሰባሰብ ያለውን ቴከኒካዊና ተቋማዊ ልምድና አስተያየትን ለማስጨበጥ በመሞክር የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ አስተዳድራዊ እና ጤናዊ  ውጣ ውርዶችን፣ መሻሻሎችን፣ መልሶ ማገርሸትን፣ እርምጃዎችን አስመልክቼ በጀርመን፣ በኢትዮጵያ እና በቀሪው ዓለም ለሚገኙ ለማካፈል  ሞክሪያለሁ። ለደረሱኝ አስተያየቶችም አመሰግናልሁ። ለወደፊት እንደ ቀደሙት ቶሎ ቶሎ ባይሆንም እጅግ አሳሳቢ እና የተለየ ሁኔታ ከአጋጠመ ለማካፈል እሞክራልሁ፣ ማስተላለፌ ይቀጥላል።

ኮሮና በውቅረ ሃሳብ ደርጃ ቀልሎ የተወሰደበት እና የሰው ጎርፍ ያለ ኮሮና መከላከል እርምጃ መታየት በተለመደበት ኢትዮጵያ ወረርሽኙ ከፍተኛ አደጋ እንደ አውሮፓ አለማድረሱ ትልቅ ፋታ ነው። የወረርሽኙ አደጋ አንሶ እስኪጠፋ ድረስ በዚህ እንዲቀጥል ፈጣሪን እንለምናለን።

ከመልካም የጤንነት እና የሰላም ምኞት!

“አንድ ሰው አንድ እንቁላል ቢኖረው እና ሌላ እንቁላል ካለው ሰው ጋር ቢቀያየር የሚኖረው ያው እንድ እንቁላል ነው፣ ግን እውቀቱን ቢቀያየር ድርብ ያገኛል።”

  – የቻይናዎች አባባል

ከመልካም የጤንነት ሰላምታ ጋር
ፀጋዬ ደግነህ (ዶ/ር)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share