የአንዳንድን ሰው ጥጋብና ጥጋቡ የሚወልደውን ትዕቢታዊ ዕብሪት ብዙም አንጥላው፡፡ ለጊዜው ሊያናድደን ቢችልም የተደበቁ እውነቶችን ገሃድ ያወጣልና ጥጋብ አንዳንዴ አወንታዊ ጎን አለው፡፡
በመሠረቱ ጥጋብ በአግባቡ ካልተያዘ እጅግ አደገኛ ነው፡፡ በርካታ ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች የጥጋብ ውጤቶች ናቸው፡፡ ብዙ ሰዎች ጥጋብ አይችሉም፡፡ ወዲያው ነው ፍልት የሚልባቸውና ገንፍሎ የሚወጣባቸው፡፡ ገንፍሎ ሲወጣ ደግሞ አንድም ለበጎ ነው፤ አንድም ለመጥፎ ነው፡፡ ሁለቱም ጥቅምም ጉዳትም አላቸው፡፡ እንደውነቱ ጥጋብን የሚቆጣጠር ሰው ትልቅ ሰው ነው፡፡ የዓለማችን ቅርጽ እንዲህ እንዳሁኑ ተበለሻሽቶ ልናይ የቻልነው በዋናነት ጥጋባቸውንና ያን ተከትሎ የሚከሰተውን ዕብሪታቸውን መቆጣጠር ያልቻሉ የሀገራት መሪዎችና አጃቢዎቻቸው በሚፈጥሩት ዐመፅና ሁከት ነው፡፡
ሽመልስ አብዲሣ ይሄን ድስት አፉን – ይቅርታ ለጠያፍ አነጋገሬ – ይሄን በከፈተው ቁጥር የሚቆንስ ሰታቴ አፉን ዘግቶ የልቡን በልቡ ይዞ የሚለውን ነገር በተግባር ብቻ ቢገልጥ ኖሮ ስለኦሮሙማ የአሁንና የወደፊት ዕቅዶች የምናውቀው እምብዝም በሆነ ነበር፡፡ እርሱ ግን ስላልለመደበትና በአለቃው በአቢይ አህመድ በተደጋጋሚ ቢመከርምና ቢገሰጽም ተፈጥሮውን ሊለውጥ ባለመቻሉ የውስጣቸውን ምንም ሳያስቀር መዘክዘኩን እንደቀጠለ ነው፡፡ ስለሆነም በድብቅ የሚነጋገሩትን ምሥጢር አጋጣሚ ባገኘ ጊዜ ሁሉ እንደሚፈጭ እህል አደባባይ አውጥቶ እያሰጣ እኛንም ታዛቢንም ማስደመሙን ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያ እንደዚህ ያለ ደንቆሮ መውለዷ በአንድ በኩል በጸጸት ቢያቃጥልም የተረኛ ዘረኞችን ፍላጎት ግልጽ በማድረጉ ረገድ ያለው ፋይዳ ግና አይናቅምና የሽመልስና የቡድኑ ጥጋብ በዚህ መልክ መውጣቱ አይጠላም፡፡ የወያኔው ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ (ጌቾ ምላሱ)ም የዚሁ ጠባይ ተጠቂ መሆኑን በተደጋጋሚ በሚዘላብዳቸው ንግግሮቹ የሚታወቅ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ማስታወሱ አይከፋም፡፡ ብዙ የወቅቱ ፖለቲካ አራማጆች ከግርጌ እስከራስጌ የዚሁ ዓይነት ባሕርይ እንዳላቸው ሊደብቁት የማይቻል እውነት ነው፡፡ የዱባ ጥጋብ መጥፎ ነው ይባላል፡፡ የዘረኝነት ስካርም ልክ እንደዚያው እንደዱባው ጥጋብ ነውና ክፉኛ አእምሮን እያሳተ ያጃጅላል፡፡
ሸመልስ መድረክ ካገኘ ነገርን መደባበቅ ወይ ማድበስበስ ብሎ አያውቅም፡፡ እንደዋና አለቃው በለበጣ እየሣቀ ሰውን የሚጎዳ ሸረኛ አይደለም፡፡ ሊደነቅ የሚገባው ግልጽነቱ በጣም የተለዬ ነው፡፡ የእነአቢይን ድብቅ ሤራ እያወጣ ፀሐይ የሚያሞቅ የክፍለ ዘመናችን እውነት ተናጋሪ ነው ብል አልተጋነነም፡፡ ነገሩ ሁሉ “ሳይደግስ አይጣላም” እንዲሉ ነው፡፡ በነገራችን ላይ አኩፓንክቸር የሚባል የቻይና ጥንታዊ ባህላዊ ህክምናን እዚህ ላይ ማስታወሱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ይህ ህክምና ነርቮችን በሹል ነገር (በደረቅ መርፌ) መነካካትና በሞተር ነርቮች አማካይነት መልእክት ወደዋናው የአንጎላችን ክፍል እንዲደርስ ሆኖ ዋናው የአንጎል ክፍል ደግሞ የታመመውን አካባቢ የሚያስተካክል ትዕዛዝ በሴንሰሪ ነርቮች አማካይነት በማስተላለፍ የታመመው አካባቢ እንዲድን ማስቻል ነው፡፡ ሽመልስም የተኛውን አማራ የሚቀሰቅሱ በርካታ መልእክቶችን በየጊዜው ይልካል፡፡ ነገር ግን እስካሁን የሽሜን መልእክት የሰማ አማራ የተገኘ አልመሰለኝም፡፡ “አውቆ የተኛ …” ዓይነት ነው የአማራ ሁኔታ ሲታይ፡፡ ትንሽ ጊዜ ማየቱ ደግ ነው፡፡ አማራ መሞትና አለመሞቱን ለማየት በበኩሌ ጥቂት ወራትን በትግስት መጠበቅ ሳይኖርብኝ አይቀርም፡፡ የዚህ ማኅበረሰብ የዘመናት መስተጋብራዊ ኅልውና ከሁሉም ዘውጎችና ማኅበረሰቦች ጋር የተጋመደ እንደመሆኑ የርሱ ትንሣኤ የሀገራችንም ትንሣኤ መሆኑን ማመን ከጀመርኩ ትንሽ ቆየሁ፡፡ አማራ ሞቶ የምትነሣ ኢትዮጵያ የለችም፤ ኢትዮጵያን ያለአማራ ማሰብም የሚቻል አይደለም፡፡ የጠላቶቹ ሤራ ለተወሰነ ጊዜ የተሳካ ቢመስልም ነገሮች በቅርቡ ይስተካከላሉ፡፡ በዚያ በወዲያኛው ዓመት ይሄው ሽመልስ የሚባል ገልቱ ከአባቶቹ ከወያኔዎች በወረሰው ሥልት ኦሮሞ ልሂቃንን ሰብስቦ በኦሮምኛ ቋንቋ ባደረገው ዲስኩር አማራንና አማርኛን ድባቅ እየመታቸው እንደሆነና የመጨረሻውን የአማራ ግብኣተ መሬትና የኦሮምያን ሥርዓተ መንግሥት ምሥረታ በትግስት መጠባበቅ እንዳለባቸው እንደነገራቸው ያ ልቦለድ የሚመስል የኦሮሙማ ትርክት በአማርኛ ተተርጉሞ ሰምተናል፡፡ ከዚያን ጊዜ በኋላ ይሁን በፊት ደግሞ በእሬቻ በዓል ላይ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ መስቀል አደባባይ መሀል ኢጆሌ ኦቦ አብዲሣ በቄሮዎች ታጅቦ ለሕዝብ ባደረገው ንግግር “እዚህ ቦታ ላይ አማራን ስብርብሩን አወጣነው” የሚል መልእክት ማስተላለፉ አይዘነጋም፡፡ ተመልከቱ – አንድ የሀገር መሪ እስከዚህን ወርዶ አንዱን ከአንዱ የሚያጋጭና የሚያፋጅ ንግግር ካደረገ ሌላው ተራ ዜጋማ እንዴቱን ያህል የባሰበት ዐረመኔና ጨካኝ፣ ቅን የዐመፃ ታዛዥም አይሆን? በዚህ መልክ በጭፍን የታዘዙ የትግራይ ወጣቶችና ጎልማሦች እኮ ናቸው ሰሞኑን የአማራን ክልል እንደአንበጣ ሲረመርሙት የከረሙት! እንደዚህ ያሉ ጭፍን የወያኔ ትግሬ ታዛዦች እኮ ናቸው አማራውን ባልጠበቀውና ባላሰበው፣ ባልተዘጋጀበትና ከባህልና ሃይማኖት ፍጹም ባፈነገጠ መንገድ መፈጠሩን እንዲራገም ያደረጉት፡፡ አማራ እንደወያኔ ቢጨክንና ዐውሬ ቢሆን ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ ቀላል ነው፡፡ የኅልውና አደጋው ተባብሶ ቀጥሎ መቆሚያ መቀመጫ ካሳጣው ደግሞ ያ ዓይነቱ ትዕይንት አይከሰትም ማለት አንችልም፡፡ ሰው ወድዶ ዐረመኔ አይሆንም፤ አማራ ወደዚያ ሁኔታ ሳይወድ በግዱ እየተገፋ ነው፡፡ ብዙ ሲገፋ የፖለቲካ ሤራውንና ድርጅታዊ ተንኮሉን ሁሉ ይበጣጥሰዋል፡፡
ሽመልስ አብዲሣ ሰሞኑን እንዲህ አለ፡- (ከፌስቡክ መንደር ታማኝ ምንጮች የተወሰደ)
“ልማትን የማረጋገጥ ጉዞ” በሚል ባለፈው ሳምንት በአዳሚ ቱሉ ግብርና ምርምር ማእከል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ እብዲሳ ባደረጉት ጉብኝት እንዲሁም በምስራቅ ሸዋ ዞን የመስኖ እርሻዎችን ከጎበኙ በኋላ እንደተናገሩት “ሌሎች ክልሎች በኦሮሚያ የስንዴ ልማት ላይ ጥገኛ ሆነው ይኖሩ ዘንድ ማረሻቸውን እንዲሰብሩ ጠንክረን መሥራት ይጠበቅብናል” ብለዋል።
“በቀጣይ ዓመታት በተለያዩ መስኮች በኦሮሚያ በሚደረጉ ልማቶች ከውጪ የሚገቡትን የተለያዩ ምርቶች በመተካት ሌሎች ክልሎች በኦሮሚያ ላይ ጥገኛ ሆነው ማረሻዎቻቸውን እንዲሰብሩ ጠንክረን በመሥራት በኢኮኖሚ ኦሮሚያን ከሌሎች ክልሎች በላይ በመስራት እኛን እንዲለምኑን ማድረግ አለብን” ያሉ ሲሆን ጨምረውም “ሌሎች ክልሎች በግጭት ውስጥ ስለሆኑ ካሁን በኋላ ለማምረት የሚችሉበት ዕድል ከመመናመኑም በላይ በጦርነት ስለደቀቁ ለማምረት ከገቡበት ችግር ለመውጣት ከ20 እና 30 ዓመት በላይ ስለሚወስድባቸው ይህንን ዕድል መጠቀም ይገባናል” ብለዋል።
አክለውም “ዳግም ላይነሱ በጦርነት የተሰበሩ አከባቢዎችን ጥገኛ የምናደርጋቸው ተመልሰው ወደ እርሻ እንዳይገቡ ለማድረግ በከፍተኛ ደረጃ ስለምንሠራ ለወጣቶች በነጻ ትራክተርና መሬት በማደል ኦሮሚያን በምርት ለማሳደግ እየተሰራ ሲሆን ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ ሌሎች ጦርነት ላይ ሲሆኑ እኛ በተለየ መልኩ ከፍተኛ የልማት ሥራዎች ሠርተን እየቀደምናቸውና ነገም ጥገኞቻችን እንዲሆኑ እየሰራን ነው” ብለዋል። መረጃው በምሥራቅ ሸዋ የሚገኙ ነዋሪዎች ያደረሱን ነው።
ይህን መሳይ ሰው ከየት ይገኛል? ችግሩ ሰሚ ጆሮ ማጣቱ እንጂ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ኦሮሞም ይሁን አማራ፣ ትግሬም ይሁን ጉራጌ … ይህን ዓይነት የዕብድ ንግግር እንደሰማ በቅድሚያ ተናጋሪውን በሰንሰለት አሥሮ ወደሚቀርበው ጠበል ወይም የአእምሮ ህሙማን መታከሚያ ሆስፒታል መውሰድና የሚድን ከሆነ ማሳከም፣ በመቀጠል ደግሞ የርሱን ንግግር በማድመጥ በዕብሪታዊ የሥነ ልቦና ስካር የጦዙ ቄሮዎችን ወደ ጠባይ ማረሚያ ማዕከላት ወስዶ የአእምሮ ጤንነታቸው እንዲመለስላቸው መጣር ይገባ ነበር፡፡
በመጨረሻም አንድ ቅሬታ ላስፍርና ላብቃ፡፡ ባለፈው ሰሞን “ወያኔ ትግሬን ሰው ከማድረግ፣ እባብን ዕርግብ ማድረግ ይቀላል” በሚል ርዕስ አንድ ጽሑፍ በድረ ገፆች ልኬ ባስነበብኩበት ወቅት ባሮቲዩብ የተሰኘ አንድ ታዋቂ የዩቲዩብ ቻናል በድምጽ ካስደመጠንና በ24 ሰዓታት ውስጥ ወደ 10 ሽህ የሚጠጉ ተመልካቾችን ካሳየን በኋላ ወዲያውኑ ከዩቲዩብ አውርዶታል፡፡ ለምን እንዳወረደው ባውቅ ደስ ይለኝ ነበር፤ ግን አድራሻው የለኝም፡፡ በመሠረቱ ታዲያ እውነት የሚጎመዝዘው ወገን ካለ ወይንም በአንድ ወይ በሌላ ምክንያት “እገሌን አስቀይም ይሆናል” በሚል ከእውነት መንገድ የሚያፈነግጥ ቢኖር ከመነሻው ጽሑፉን መርምሮ መተው እንጂ ከተነበበ በኋላ በዚህ መልክ በማውረድ “በሞራላችን ላይ ለመረማመድ” ባይሞክር ጥሩ ነው እላለሁ፡፡