ግርማ ብሩ (ከቤተክርስቲያኑ መሥራቾች መካከል አንዱ)
ደብረሰላም መድሃኔዓለም ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ በብዙ ውስብስብ ችግሮች ያለፈ ሲሆን ከዓመታት በፊት በማን ሥር መሆን አለበት ተብሎ 3 ምርጫ ቀርቦ ነበር። ይኸውም ሃገር ቤት በወያኔ ሥር በሚገኘው ሲኖዶስ፣ ኒውዮርክ በነበሩት አቡነ ይስሃቅ እና 3ኛው ገለልተኛ እንዲሆን ሲሆን በጊዜው በስብሰባው ቦታ በነበርነው አባላት በውጭ የሚገኘው ሲኖዶስም በደንብ ባለመጠናክሩ ገለልተኛ ሆኖ እንዲቆይ ተስማምተን ቤተክርስቲያኑ ለተወሰኑ ዓመታት ገለልተኛ ሆኖ ቆይቷል። ሆኖም ለቤተከርስቲያኑ ምስረታና ዕድገት በጊዜው ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉት አባ ፍቅረማርያም የአሁኑ (አቡነ ዳንኤል) ወደ ሃገር ቤት ተመልሰው ጳጳስ ከሆኑ በኋላ የደብረ ሠላም መድሃኔዓለም ገለልተኛ ሆኖ መቀጠል አጠያያቂ ሆኗል።
አቡነ ዳንኤልን ከመጀመሪያው ከአሪዞና ያገኋቸውና ያስመጣኋቸው እኔ ነበርኩ። ከልቤ እወዳቸዋለሁ። አከብራቸዋለሁም። ወደ ሃገር ቤት ሲመለሱና ሲሰናበቱም ያለምንም ቅሬታ ተሰናብቻቸዋለሁ። ወሳኔያቸውንም አክብሬያለሁ። ለምን ከዚህ በጊዜው ቤተክርስቲያኑን ለመመስረት ብዙ ስለተቸገሩ የአሜሪካ ኑሮም ከዕድሜያቸው አንጻር ከባድ ስለሆነ ምናልባት ሃገር ቤት የተሻለ ሊኖሩ ይችላሉ በሚል አልተቃወምኳቸውም።
ሆኖም ሃገር ቤት የጵጵስና ማዕረግ ካገኙ በኋላ መድሃኔዓለምን በአቡነ ጳውሎስ ሲኖዶስ ሥር ለማድረግ ብዙ ሙከራ አድርገዋል። ሚኒሶታ ድረስ በመምጣትም የቅስናና የድንቁና ሹመት ሰጥተዋል። በአቡነ ጳውሎስ ስምም ቀድሰዋል። አስቀድሰዋል።
እርግጥ በጊዜው የነበሩ የሥራ አስፈጻሚ አባላት አስቸኳይ ስብሰባ አድርገው ድርጊቱን እንዳወገዙና ለካህናቱ እንዳስጠነቀቋቸው አውቃለሁ።
ከዛ በኋላም ቢሆን ከመዘምራንም ይሁን ከአመራር አባላት መድሃኔዓለምን በአቡነ ጳውሎስ ሥር አድርገው ልዩ ጉርሻ ለማግኘት እላይና እታች የሚሉ አሉ። ይህ የሚያሳየን ለአባላት የሚሰጡትን ዝቅተኛ ክብር ነው። ይኸን ቤተክርስቲያን ለመመሥረት ምን ያህል ከወያኔና ከሻዕቢያ ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ እንደተናነቅን በየጊዜው የነበራችሁ ምዕመናን ምስክሮች ናችሁ። ታዲያ ይኽ ብዙ መስዋዕት የተከፈለበትን ቤተክርስቲያን ያለ ምእመናኑ ፈቃድ ለጥቅማቸው የሚሯሯጡ አይሁዳዎች ለወያኔ አሳልፈው ለመስጠት እንቅልፍ አጥተዋል።
ዛሬ ወያኔ እንኳን ራሱ የሚሾማቸውን ጳጳሳት ቀርቶ በየገዳማቱ እየገባ የራሱን ተወካይ ለማስቀመጥ መነኮሳትን በመደብደብና በማሰቃየት ላይ ይገኛል። የሚመረጠው ፓትሪያርክ የግድ ከትግራይ መሆን አለበት በሚል ግትር አቋሙ ሃገር ቤት የሚገኙትን ካህናት እንዳሰቃዩ ከህዝብ የተደበቀ አይደለም።
ታዲያ ይኸን ድርጊት እንኳን ለመንጋው የቆመ ካህን ይቅርና ማንም አማኝ ቢሆን ሊቀበለው የማይችል ድርጊት ነው። ዛሬ ከካህናትም ይሁን ከም እመናን ለጥቅማቸው የሚስገበገቡና ለሕዝቡ ርህራሄ የሌላቸው አውሬዎች አይጠፉም። በየቤተክርስቲያኑ ምእመናን እንዳይገናኙ በዕምነት እያሳበቡ አጥሮችን ይጋርዳሉ። ምእመናኑም እውነታውን ተገንዝቦና አንድ ሆኖ ሃገር ቤት ያለውን ሁኔታ እንዳያስተካክል አንዳንድ ወያኔ የሚነዛውን የውሸት ፕሮፓጋንዳ ተቀብለው ያራግባሉ።
ወያኔ ሕጋዊውን ፓትሪያርክ በህመም ምክንያት በገዛ ፈቃዳቸው ለቀዋል የሚለውን የፈጠራ ወሬ እውነት አለመሆኑን እያወቁ ምዕመናኑን ወደ ፈለጉት መንገድ ለማሽከርከር አንዳንድ ካህናት ይጠቀሙበት ነበር። ነገር ግን ያ ውሸት እንዳይቀጥል የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተር የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ ግልጽ አድርገውታል።
አቡነ መርቆሪዎስ በህመም ሳይሆን ከሳቸው ምክንያት እንደወረዱ ከደብዳቤያቸው ተረድተናል። በየጊዜው ለፈጸሙት ስህተትም ይቅርታ ጠይቀዋል። አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዚዳንት ግርማም አቡነ መርቆሪዎስ በታምራት ላይኔ ምክንያት እንደረዱና ወደ ስልጣናቸው እንዲመለሱ ተናግረው ነበር። ሆኖም የወያኔ አመራር አባላት ምኞት ባለመሆኑ የሚሾመው ሰው የግድ በትውልድ ትግሬ መሆን ስላለበት ይሄ ልሆን አልቻለም። ታዲያ ይኽንን ሁሉ አግባብ ያልሆኑ ምክንያቶች እያሉና ሁኔታው ሳይስተካከል ቤተክርስቲያንም ሆነ ምዕመናኑን ወያኔ ባስቀመጠው ፓትርያርክ ስር ለማስገባት የሚደረገው ሩጫ እውነት ም እመናን ለመጥቀም ነው? ወይስ ለሰሩት ውለታ ለመሾም ለመሸለም? ይህን ችግር ለመፍታት ወሳኙ ምዕመናኑ ነው። አይመለከተኝም፤ አያገባም የሚለውን ሃሳብ ወደ ኋላ ትተን ገንዘባችንና ጉልበታችንን እንዲሁም ሰዓታችንን ያጠፋንበት ስለሆነ በአንድነት ተነስተን መብታችንን ማስከበር የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ሲሆን በዚህ በተሳሳተ መንገድ የሚሄዱትም የማያዳግም ትምህርት ያገኛሉ።
እግዚአብሔር ቤተክርስቲያናችንን እና ሕዝባችንን ይጠብቅ።
ግርማ ብሩ
ከሚኒሶታ ደብረ ሰላም መድሃኔዓለም ቤ/ክ መሥራቾች መካክል አንዱ