እግር ኳስ ቆሸሸ! የፖሊሶች ምርመራ ውጤት መላው አውሮፓን አስደንግጧል

The Beautiful Game የእግርኳስ ሌላይኛው ስሙ ነው፡፡ ስያሜው የስፖርቱን ቆንጆ ገፅታ ያጎላል፡፡ የውቡ እግርኳስ አን..ት መጥፎ ሶንካፍ ግን አልነቀል ብላ እስካሁን አለች፡፡ ማራኪው እግርኳስ ከአስቀያሚው ‹‹የጨዋታ ውጤት አስቀድሞ የመወሰን›› ሴራዎቹ እንደተጣባ ቀጥሏል፡፡ የ2014ቱ የዓለም ዋንጫ ዝግጅት ሲጧጧፍ የአውሮፓ ፖሊስ ኢንተለጀንስ ኤጀንሲ (ዩሮፓል) በሌላ ከባድ ስራ ተጠምዶ ነበር፡፡ Operation veto የሚል ስያሜ ባገኘው በዚህ ዘመቻ ፖሊሶቹ ባለፉት 19 ወራት ብዙ መዝገቦች አገላብጠዋል፣ ሰዎች አነጋግረዋል እንዲሁም የምስጢር ክትትሎች አድርገዋል፡፡ ባለፈው  የደረሱበትን ውጤት ይዘው በመገናኛ ብዙሃን ፊት ሲቀርቡ ይፋ ያደረጉት መረጃ አስደንጋጭ ነበር፡፡ በዓለም ዙሪያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ 680 ያህል ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች መጭበርበራቸውን አስታወቀ፡፡

ከ680ዎቹ ጨዋታዎች መካከል 150 ያህሉ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች በብዛት በአፍሪካ፣ እስያ እና ላቲን አሜሪካ የተደረጉ ሲሆኑ 380 ያህሉ ደግሞ በአውሮፓ የተከወኑ ነበሩ፡፡ እነዚህ ጨዋታዎች በዓለም ዋንጫ ማጣሪያዎች፣ በአውሮፓ ዋንጫ ማጣሪያዎች እንዲሁም በሁለቱ የቻምፒየንስ ሊግ ግጥምያዎች የተመዘገቡ ናቸው፡፡ በሀገር ውስጥ ሊጎች ከታች እስከ ላይ ዲቪዚዮኖች ከተደረጉት ጨዋታዎች በዚሁ ማጭበርበር የተነካኩ ጥቂት አይደሉም፡፡

ሆኖም ዘሄግ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት የተገኙት የዩሮፓል ባለስልጣናት ሁሉንም ጥያቄዎች ለመመለስ ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡ ከሪፖርተሮች ከተሰነዘሩላቸው ጥያቄዎች መካከል እንዳልሰሙ ሆነው ያሳለፏቸው ጥቂት አልነበሩም፡፡ ለምሳሌ ከተጠቀሱት 680 ጨዋታዎች ምን ያህሎቹ ቀድሞ የተደረሰባቸው እና የትኞቹ አዳዲስ ስለመሆናቸው ተዘርዝሮ አልታወቀም፡፡ ጉዳዩ ገና በፖሊስ የአሰራር ሂደት ውስጥ መሆኑን ሰበብ በማድረግም ከጉዳዩ ጋር የተያያዙትን ክለቦች  እና ግለሰቦች ማሳወቅ አልፈለጉም፡፡

ይሁን እንጂ ባለስልጣናቱ ከሰጧቸው መረጃዎች አንደኛው የሰሚዎቹን ጆሮ ያቆመ ነበር፡፡ በቻምፒየንስ ሊጉ ተገኘ ከተባሉት ጨዋታዎች አንደኛው በእንግሊዝ መካሄዱ ተነገረ፡፡ ይህም የሆነው ባለፉት ሶስት ወይም አራት ዓመታት ውስጥ እንደነበር መገለፁ ደግሞ ይበልጥ ትኩረት ሳበ፡፡ ይህ መረጃ የማህበራዊ ድረገፆችን ሲያደርስ እና ከጉዳዩ ጋር የተያያዘው ክለብ የትኛው የእንግሊዝ ክለብ ይሆን? የሚለውን ጥያቄ የተለያዩ አስተያየቶችን ሲያስተናግድ ጋዜጣዊ መግለጫው ገና አልተጠናቀቀም ነበር፡፡ በተጠቀሱት ዓመታት በቻምፒየንስ ሊግ እንግሊዝን የወከሉት ማንቸስተር ዩናይትድ ማንቸስተር ሲቲ፣ አርሰናል፣ ቼልሲ እና ሊቨርፑል ብቻ ነበሩ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰማያዊ ፓርቲ እሁድ ያስመረቀውን ቲያትር በቪሲዲ ለህዝብ ሊያደርስ ነው

ስድስቱም ክለቦች ታላላቅ ከመሆናቸውም በላይ በዓለም እጅግ በተከበረው እና በተወደደው ፕሪሚየር ሊግ የሚወዳደሩ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ መጠነ ሰፊ ተከታይ ያላቸው ናቸው፡፡ በእርግጥ የተጭበረበረው ጨዋታ በእንግሊዝ መካሄዱን እንጂ የወንጀሉ ተሳታፊ ባለሜዳው ክለብ ወይም እንግዳው ክለብ ስለመሆናቸው ምንም ግልፅ አልተደረገም፡፡

ነገር ግን የተለያዩ ዋንጮች በእንግሊዝ ተደረገ የተባለው ጨዋታ ሊቨርፑል የሀንጋሪውን ዴብሬቼን የገጠመበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከሁኔታው ጋር ተያይዞ ስሙ መነሳቱን ያልወደደው ሊቨርፑል ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ በ2009 ተደረገ ስለተባለው ጨዋታ ከፖሊስ ባለስልጣናት ምንም አይነት ጥያቄ ቀርቦለት እንደማያውቅ አስታውቋል፡፡ የእንግሊዝ እግርኳስ ማህበርም በግሉ በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት መረጃ እንደሌለው ይፋ አድርጓል፡፡ የአምስት ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮኖቹ በመግለጫቸው ‹‹ሊቨርፑል እግርኳስ ክለብ ከዩሮፓል ወይም ከአውሮፓ እግርኳስ ማህበር የደረሰው ምንም አይነት ጥያቄ ወይም ምርመራ የለም›› ብለዋል፡፡

የእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር በቃል አቀባዩ በኩል በሰጠው መግለጫም ‹‹ኤፍኤው በቻምፒየንስ ሊግ በእንግሊዝ ተደረገ ስለተባለው ጨዋታ ምንም አይነት በመረጃ የተደገፈ ሪፖርት አልደረሰውም›› ብሏል፡፡ ከዚህም በተቃራኒው ግን የዩሮፓሉ ዳይሬክተር ሮብ ዌይንራይን በበኩላቸው ከወዲሁ ማንም ራሱን ከወንጀሉ ነፃ ማድረግ እንደማይችል ሲገልፁ ‹‹በእንግሊዝ ያሉ ሰዎች በሀገራቸው ምንም አይነት ተመሳሳይ ወንጀል ወይም ሴራ አይኖርም ብለው ካሰቡ ተሳስተዋል›› ብለዋል፡፡

በእርግጥ ብዙው የዩሮፓል ምርመራዎች ያተኮሩት ሌሎች አካባቢዎች ላይ ነው፡፡ ኤጀንሲው የጨዋታን ውጤት የመወሰኑ ስራ እየተፈፀመ ያለው በስፋት በተዘረጋ እና በተሳሰረ መረብ ነው፡፡ በምርመራው ወቅት በዚህ መንገድ ወንጀለኞቹ ለጉቦ እስከ 3 ሚሊዮን ዶላር ማውጣታቸውን እና በትርፍ መልክ 11 ሚሊዮን ዶላር ኪሳቸው ማስገባታቸው ታውቋል፡፡ ይህንን አስመልክቶም ዌይንራይት ሲናገሩ ‹‹የጨዋታን ውጤት አስቀድሞ የመወሰን ማጭበርበር ይህንን ያህል ከፍ ባለ ደረጃ ሲከወን አይተን አናውቅም፡፡ ይህ ለእግርኳሱ የሀዘን ቀን ነው›› ብለዋል፡፡

የጨዋታን ውጤት አስቀድሞ የመወሰኑን ስራ በበላይነት የሚመሩት ሰዎች በጉቦ የሚይዙት ዳኞችን እና ተጨዋቾችን ብቻ ሳይሆን በዩሮፓል ውስጥ የሚገኙ ባለስልጣናትንም ጭምር ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአጠቃላይ 425 ሰዎች በተጠርጣሪነት ስማቸው የተያዘ ሲሆን ወደ 50 የሚሆኑት ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ በ2008 እስከ 2011 በተካሄደ ጨዋታዎች ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢሌኒ ገብርመድን ECEX ጉድና የጎንደር ዩኒቨርሲቲው የክብር ዶክትሬት ቁማር - ሰርፀ ደስታ

የወንጀሉን ስራ በዋናነት የሚያስፈፅመው መቀመጫውን በእስያ ያደረገ እና በ15 ሀገሮች ክንፉን የዘረጋ የተቀናጀ ቡድን መሆኑን የዩሮፓል ሰዎች ይፋ አድርገዋል፡፡ ይህ ተጠርጣሪ ቡድን ለአንድ ሰው በጉቦ መልክ እስከ 136 ሺህ ዶላር ድረስ ሲከፍል ነበር፡፡ የጨዋታውን ውጤት አስቀድሞ ለመወሰን የግጥምያውን ውጤት አስመልክቶ የግምት ውርርድ ውስጥ ይሰማራል፡፡

ካናዳዊው ጋዜጠኛ ዴክለን ሂል በአፍሪካ እና መካከለኛው አሜሪካ የሚካሄዱ ጨዋታዎችን ጤናማነት ይጠራጠራል፡፡ ቀደም ሲል በብሔራዊ ቡድኖች ላይ ተመሳሳይ ችግር እየተስፋፋ መምጣቱን ሲናገር የቆየው ሂል ‹‹The fix soccer and organized crime›› በሚል መፅሐፉ ጉዳዩን እጅግ አብራርቶታል፡፡ የዩሮፓል የምርመራ ቡድንም በሪፖርቱ የዚህ ጋዜጠኛ መረጃዎች እንደ ግብዓት ተጠቅሞበታል፡፡

‹‹150 ያህል ኢንተርናሽናል ግጥሚያዎች ከጉዳዩ ጋር ንክኪ እንዳላቸው ከታወቀ በግሌ በጉቦ የሚያዙት ዳኞች እና ተጨዋቾች ብቻ እንዳልሆኑ እንዳስብ ያደርገኛል›› የሚለው ሂል ‹‹የቡድኖቹ መሪዎችና ባለስልጣናትም ይኖሩበታል›› ሲል ያክልበታል፡፡

የዩሮፓል ሰዎች ወንጀሉን በበላይነት ይመረዋል የተባለውን የእስያ ቡድን ይፋ ባያደርጉም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው እና ማንነታቸው እንዳይገለፅ የሚፈልጉ የህግ ባለሙያዎች ጣቶቻቸውን ወደ ሲንጋፑራዊው ዳን ታን ይጠቁማሉ፡፡ እንደ ሰዎቹ አገላለፅ ከሆነ ይህ ግለሰብ ከ1999 ጀምሮ በተመሳሳይ ተግባር ላይ የተሰማራ እና አቅሙ እየበረታ የመጣ ሰው ነው፡፡ እንዲያውም ዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም ኢንተርፖል ሰውየው ካለበት ታድኖ እንዲያዝ የእስር ማዘዣ ቢፃፍበትም ታን እስካሁን በቁጥጥር ስር አልዋለም፡፡

ዩሮፓል የምርመራ ውጤቱን ይፋ ከማድረጉ ጥቂት ቀደም ብሎ እንኳን ትልልቅ የሚባሉ ተመሳሳይ ማጭበርበሮች ይፋ ሆነዋል፡፡ ባለፈው የፈረንጆች ወር እንኳን ፊፋ ደቡብ ኮሪያ ውስጥ በተመሳሳይ ወንጀል ላይ ተባብረዋል ያላቸውን 41 ተጨዋቾች ቀጥቷል፡፡ ባለፈው ዲሴምበርም ፊፋ የደቡብ አፍሪካን እግርኳስ ፌዴሬሽን ቀጥቷል፡፡ ሀገሪቱ የ2010ሩን የዓለም ዋንጫ ከማዘጋጀቷ ቀደም ብለው የተደረጉ አራት ነጥብ የሌላቸው ጨዋታዎች ውጤት መወሰኑን ፊፋ ደርሶበታል፡፡ በ2006 በተመሳሳይ የእግርኳስ ቀውስ ተመትታ የነበረችው ጣልያን ከስድስት ዓመታት በኋላ ሌሎች ቅሌቶች ተገኝተውባታል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ የራያ ተወላጆችና ወዳጆች ማህበር የተሰጠ መግለጫ

ከወራት በፊት ይፋ በወጣ መረጃ መሰረት ጀርመኖችም ከ12 ያላነሱ ጨዋታዎች ከዋንጫቸው ስር በተመሳሳይ ሁኔታ ማካሄዳቸው ታውቋል፡፡ ሆኖም ከእነዚህ ውስጥ ምን ያህሉ ጨዋታዎች ከ680ዎቹ መካከል እንዳካተቱ አልታወቀም፡፡ በዩሮፓል በዚህ ቅሌት የከፋ አሀዝ የተመዘገበባት ሀገር ቱርክ ነች፡፡ በዚህች ሀገር 79 ጨዋታዎች በተመሳሳይ ችግር ተይዘዋል፡፡ ቀጣይዋ ጀርመን በ70 እና ስዊዘርላንድ በ41 ጨዋታዎች መረጃ ተገኝቶባቸዋል፡፡ መጠኑ እንደዚህ አይዘርዘር እንጂ ቤልጅየም፣ ክሮኤሺያ፣ ኦስትሪያ፣ ሀንጋሪ፣ ቦስኒያ እና ሄግዞጉቪና፣ ስሎቬኒያ እንዲሁም ካናዳ ሌሎቹ ሀገራት ናቸው፡፡

እግርኳስ በጠባብ ጎሎች ልዩነት የሚሸናነፉበት ስፖርት መሆኑ ለወንጀል የተመቸ አድርጎታል፡፡ አንድ ወይም ሁለት ተጨዋቾችን በጉቦ መያዝ በቀላሉ የ90 ደቂቃውን ውጤት ማስለወጥ ይችላል፡፡ በካናዳ ታች ዲቪዚዮኖች ይህ ተግባር እየበረታ መምጣቱን የታዘበው ኃይል በአሜሪካው ሜጀር ሊግ ስኮር ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ ተጨዋቾች በአወራራጅ ድርጅቶች የጉቦ ጥያቄ እንደቀረበላቸው እንደማውቅ ያስረዳል፡፡

የዌልሱ አሰልጣኝ ክሪስ ኮልማን የቅርብ ጊዜ የዩሮፓል መግለጫን ከሰማ በኋላ ስሜቱን አልደበቀም፡፡ ከእንግሊዝ በተጨማሪ በስፔን እና ግሪክ ተዘዋውሮ የሰራውን ኮልማን ከብሪታኒያ ውጪ ብዙ የታዘባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ ይናገራል፡፡ በስፔን ሪያል ሶሲዬዳድን በ2007 እና በ2008 እንዲሁም የግሪኩን ላሪላ በ2010 እና በ2011 ሲያሰለጥን አንዳንድ ተጨዋቾች እና ዳኞች ‹‹የእብደት የሚመስሉ›› ግራ አጋቢ ነገሮች ሲያደርጉ አይቷል፡፡

‹‹አንዳንድ ጊዜ የማያሳምን ነገር ስታይ ፀጉርህን እያከክህ ለራስህ የሆነ ነገር አለ ትላለህ፡፡ በተረፈ የተሰማህን ነገር ይፋ ለማውጣት ብትፈልግ እንኳን ተጨባጭ መረጃ አይኖርህም፡፡ በተለይ አሰልጣኝ ወይም ተጨዋች ስትሆን ጉዳዩ ይበልጥ አንድ ይሆንብሃል፡፡ ሌሎች ሰዎችም አያወሩትም›› ይላል፡፡

የቀድሞው የፊፋ ፀጥታ ጉዳዮች ኃላፊ ክሪስ ኢታን እግርኳስ አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መካተቱን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ስፖርት ከወንጀለኞች የከፋ ጥቃት እየደረሰበት ይገኛል፡፡ አሁን አወራራጅ ድርጅቶችን የሚቆጣጠር ጠንካራ መንግስትም ሆነ ተቋም እንደሌለ በግልፅ እየታየ ነው፡፡ የጨዋታ ውጤትን አስቀድሞ የወሰንን ወንጀል ያባባሰው የመንግስታት ቸልተኛነት ነው፡፡ አሁን እግርኳስ ተወርሯል፡፡ ከዚህ ነፃ እንዲሆን ጦርነቱ መጀመር አለበት፡፡

 

1 Comment

Comments are closed.

Share