“የአሸናፊነታችንን አይቀሬነት ቅርብ የሚያደርገው ውስጣዊ አንድነታችን እና የማይናወጥ ጽናታችን ነው!” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ❝የአሸናፊነታችንን አይቀሬነት ቅርብ የሚያደርገው ውስጣዊ አንድነታችን እና የማይናወጥ ጽናታችን ነው❞ ብለዋል።

አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ያስተላለፉት መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል:-

ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዓላማ ያነገቡ የውስጥም ሆኑ የውጭ ጠላቶቻችን የጥቃት ፍላጻዎቻቸው በአንድም በሌላም ምክንያት የአማራ ሕዝብ ላይ ይወረውራሉ፡፡

ሁሉም ጠላቶቻችን አማራነት ከኢትዮጵያዊነት ተነጥሎ ሊታይ የማይችል መሆኑን ቢያውቁም ኢትዮጵያን ለማንኮታኮት ያላቸውን ፍላጎት አማራን እና አማራነትን በማድቀቅ ለማሳካት ሲራወጡ ይስተዋላሉ፡፡ ለዚህ እውነታ የፋሽስት ጣሊያንም ሆነ የባንዳው የትግራይ ወራሪ ኃይል ትህነግ ታሪክ ተጨባጭ ማስረጃዎች ናቸው፡፡

ላለፉት 40 ከዚያ በላይ ዓመታት በአማራ እና አማራነት ላይ የጥፋት ዘመቻውን ሲያጧጡፍ የኖረው ትህነግ ዛሬም ህልውናችንን የማጥፋት ዓላማ አንግቦ በወራሪነት እየተስፋፋ ከበራችን ቆሟል፡፡

ከሁለት አሰርት ዓመታት በላይ እየገደለን የኖረው ትህነግ አሁንም ሊገድለን ወደ መንደሮቻችን ሰርጎ ገብቷል፡፡ በተንቤን በርሃ ሊቀበር ከቋፍ ደርሶ የነበረው ከሞት የተረፈ ፍርስራሽ ኃይል በውስጥ ባንዳዎችና በውጭ ኃይሎች የተረባረበ ጥገና እየተንፏቀቀ ከበራችን ደርሷል፡፡

ይህ ሁኔታ በራሱ እንዴት የሚል ጥያቄ ያጫረባቸው በርካታ ወገኖች እንዳሉ ቢታወቅም የምንገኝበት ግዜና ሁኔታ ለጥያቄና መልስ ማዋል ተገቢነትም ሆነ አዋጭነት የለውም፡፡

ስለሆነም የዛሬውን ቀን የትህነግ ፍርስራሽ ኃይል ከተንቤን በርሃ ወጥቶ እንዴት ወደ ደጃፋችን ሊቀርብ ቻለ ብሎ ለመጠየቅ ሳይሆን ከደጃፋችን ላይ ተበትኖ እየዋጀጀ የሚገኘውን ጠላት ለመቅበር እንጠቀምበት፡፡

ለዚህ አይቀሬ ተግባራችን ደግሞ ከሁሉም በፊት ከእያንዳንዱ አማራ ልብ ውስጥ ጽናት ሊኖር ይገባል፡፡ የአሸናፊነታችንን አይቀሬነት ቅርብ የሚያደርገው ውስጣዊ አንድነታችን እና የማይናወጥ ጽናታችን ነውና፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰኔ 15 የሰማታት ቀን ነው!

አሚኮ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share