ጠላቶቻችንን በደማቅ የአሸናፊነት ታሪካችን ብቻ ሳይሆን በብሩህ ተስፋችንም ጭምር ፊታቸው ጠቁሯል₋ኢዜማ

Habesha | zehabesha.infoጠላቶቻችንን በደማቅ የአሸናፊነት ታሪካችን ብቻ ሳይሆን በብሩህ ተስፋችንም ጭምር ፊታቸው ጠቁሯል፡፡

በዚህም ዛሬም እንደ አራዊት እርስ በእርስ ሊያናክሱንና ሊያጠፋፉን፤ ማንነታችንን እና ክብራችንን ሊያዋርዱ ጦርነት ከፍተውብናል፡፡

ኢትዮጵያውያን በአሸናፊነት የምንቋጨው ጦርነት ላይ ብንሆንም ጦርነቱን በአጠረ ግዜ አለመጨረስ የሚያስከትለብን ፈተና ከባድ ይሆናል፡፡

የተራዘመ ጦርነት እንደ እሳት ነበልባል ሀገራችንን እና ህዝቦቿን ይበላል፡፡

ለውጭ ጠላቶቻችንን የበረታ ጫና ተጨማሪ ዕድል ይሰጣል፡፡

ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳቱም እጅግ የበዛ ነው፡፡

ስለሆነም መላው ኢትዮጰያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች የህልውና ጦርነቱን በአጭር ግዜ ግቡን እንዲመታና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ባረጋገጠ መልኩ እንዲቋጭ ዛሬ ነገ ሳትሉ የሚጠበቅባችሁን የዜግነት ግዴታ እንደምትወጡ አንጠራጠርም፡፡

የዜግነት ግዴታችንን ስንወጣ የሀገራችን ፓለቲካ በብዙ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ዘንግተን አይደለም፡፡ ያለን የፖለቲካ አመለካከት ልዮነቶች እንደተጠበቁ ሆነው በተለይ በእንዲህ ያለ ግዜ ለሀገር ህልውና በጋራ መቆሙ ምርጫ የሌለው ግዴታችን በመሆኑም ጭምር ነው፡፡

ሀገሬን እና ህዝቤን እወዳለሁ የሚሉ ሁሉ በተግባር የሚፈተኑበት ግዜው አሁን ነው፡፡

ሲተቹና አስተያያት ሲሰጡ የነበሩ ሁሉ የተናገሩትን ፈፅመው ሀቀኞች መሆናቸውን የሚያረጋግጡበት ቀን ደርሷል፡፡

ጥሬው ከብስሉ የሚለይበት ከንግግር ያለፈ ተጨባጭ ሥራ ሰርተን በታሪክ ፊት በእውነት የምንመዘንበት የታሪክ አጋጣሚ ከእጃችን ላይ ነው፡፡

ኢዜማ ለመላው የፓርቲው አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና ለመላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በጋራ ሊያጠፋን የመጣውን ኃይል በህብረት ለመደምሰስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

በመላው ኢትዮጵያ የምትገኙ አባላትና ደጋፊዎች ይህን ዘመቻ ሊያጠናከርና ሊደገፍ በሚችል አደረጃጀት ውስጥ በመቀላቀል፤ በገንዘብና በጉልበት ተግባራዊ ድጋፍ በማደረግ እውነተኛ ደጀን በመሆን፤ እንዲሁም የአካባቢያችንን ፀጥታ በንቃት በመጠበቅና አጥፊዎችን በአግባቡ ለሕግ በማቅረብ ብሎም ከተሳሳተ ፐሮፖጋንዳ ራሳችንን በመጠበቅ ይህን የፈተና ወቅት በፅናት እንድንወጣ አደራ እንላለን፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የዐማራ የህልውና ትግል መርህ የትግል ጥሪ

በዚህ አሰቸጋሪ ወቅት ከፊት ሆነው እየተዋደቁ ያሉ ጀግኖችን ሁሉ በርቱ ታሪካችን ደማቅ ድላችንም አንፀባራቂ እንደሚሆን አትጠራጠሩ እያልን ወደ ግንባር የዘመቱት ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ ለጉዳዩ ክብደት የሰጡት ትኩረት ተገቢ ነው እያልን በዚህ ሂደት ውስጥ የጸጥታውን መዋቅር በአንድ ወጥ አመራር አሰልፈው የሀገራችንን ድል ያፋጥኑታል ብለን እንተማመናለን፡፡ ስለዚህም ወጥ በሆነ የዕዝ ሰንሰለትና በተጠና ሀገር አቀፍ የውጊያ ስልት ሃገራችንን ለመጠበቅ ቆራጦች መሆናችንን እንገልጻለን፡፡

ኢትዮጵያውያን ፣ ትውልደ ኢትዮጵያውን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በዓለም አደባባይ ተገኝታችሁ ለምትወዷት ሀገራችሁ ሉዓላዊነት እያደረጋችሁ ላለው እጅግ የሚያስመካ ተግባር ኢዜማ ከፍ ያለ ክብር አለው፡፡

አንዳንድ የውጪ ሀገር መንግስታት እና ተቋማት ኢትዮጵያዊያን የሀገራችንን ህልውና ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመመከት እያደረግን ያለው ተጋድሎ ላይ እያሳረፉ ያሉትን ያልተገባ ጫና እንዲያቆሙ ድምጻችሁን አሰምታችኋል ፤ ድጋፋችሁን የሚሹ ወገኖቻችሁንም ሳትሰስቱ እየረዳችሁ ነው።

ካለንበት ውስብስብ ችግር አንፃር ሲታይ እናት ሀገራችሁ ከመቼውም ጊዜ በላይ የእናንተን አቅም እና ድጋፍ አሁንም ትሻለች። ያለእናንተ አስተዋፅዖ የተሟላ ድል ሊገኝ እንደማይችል በተግባር ተረድተናል፡፡

ስለሆነም የምዕራባውያንን የተዛባ አመለካከት በማጥራት እንዲሁም ሊፈጠር የሚችለውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቅረፍ በሚያስችል ደረጃ የተደራጀ እና ወጥነት ያለው ድጋፍ ለማድረግ ከወትሮው በላቀ ሁኔታ በያላችሁበት የዓለም ጥግ እራሳችሁን እንድታዘጋጁ አደራ እንላለን፡፡

በመጨረሻም ከልዩነቶቻችን፣ አለመግባባቶቻችን እና የጎደሉን ነገሮች በፊት ኢትዮጵያ ሃገራችን ትቀድማለች፡፡ በተለይ የፖለቲካ ልዩነቶችን ለመፍታት የሀገራችን ህልውና ቀዳሚ ነው።

የመጣብንን የጋራ ጠላት በጋራ መክተን የሀገረ መንግስቱን ቀጣይነት ካረጋገጥን በኋላ ልዩነቶቻችንን ለመፍታት እና ቅሬታዎቻችንን ለማከም በጠረጴዛው ዙሪያ እንቀመጣለን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ የኢትዮጵያ የውይይትና መፍትሄ መድረክ (EDF) እና እምቢልታ ድርጅት በጋራ ያወጡት መግለጫ

በዛም ወቅት ሀገራችንን የመፍረስ ስጋት ጫፍ ላይ ያደረሳት የፖለቲካ ስርዓት እና አካሄድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዳይመለስ መስራት ሀላፊነታችን ይሆናል፡፡ አሁን ላይ ከምንም ምድራዊ ጉዳይ በላይ ቅድሚያ የምንሰጠው ሃገራችንን ማዳን፣ ኢትዮጵያችንን መጠበቅ ነው! ይህንንም ስናደርግ እንደ ሀገር አብሮ መኖራችንን በማያቆሽሽ እና የወደፊት አብሮነታችንን በማይጎዳ ሁኔታ እንዲሆን አሁንም አበክረን እናሳስባለን፡፡

አሁን ያለንበት ወቅት ሁሉን አቀፍ አርበኝነትን የሚጠይቅ መሆኑን ግምት ውስጥ በመክተት የኢዜማ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ህዳር 15 ቀን 2014 .ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ አባላት እና ደጋፊዎቹ ግንባር ድረስ በመዝመት፣ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት እና ሌሎችንም ተግባራት በመከወን የሀገርን ህልውና የማረጋገጥ ስራ ለመስራት ውሳኔን አስተላልፏል፡፡

1 Comment

  1. ኢትዮጵያዊያን ከግል በመነጨ የሃሳብ ልዪነትና ከውጭ በመጣ የፍልስፍና ዘይቤ ተላትመው አይተናል። አልፎ አልፎ በግጦሽና በሌሎችም ነገሮች ህዝባችን በዚህም በዚያም የሚነሱ ትናንሽ ትንኮሳዎችን በራሱ ህሳቤ በማርገብ ለዘመናት አብሮ ኑሯል። አሁን በወያኔ የመጣው የክፋት ዶፍ ግን በምድሪቱ ታይቶ የማይታወቅ ነው። ወያኔዎች ሽንኮች ናቸው። በምድር ላይ እሾህና አሜኬላ ዘርተው ስንዴን ለመሰብሰብ የሚሹ የወስላቶች ስብስብ። አዎን ከበረሃ ከተማ ገብተው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሃብት ያካበቱ፤ በልተው ለበላተኛ ያካፈሉ፤ ዘርፈውና ሰርቀው ሲያሻቸውም ገድለው በውጭ ሃገር ዘመድ አዝማዳቸው ሳይቀር የንግድ ቤቶችንና የተንጣለለ መኖሪያ ቤቶችን የገነቡት በዝርፊያ እንጂ ከባንክ ተበድረው አዙረው ለመክፈል ፈርመው ባወጡት አይደለም። ያለፈውን ታሪካችን እያራከሱ፤ የአኖሌን ሃውልት ያቆሙልን ለኦሮሞ ህዝብ ገዷቸው ሳይሆን የከፋፍለህ ግዛ ስሌታቸው እንዲጎለብት የተጠቀሙበት ብልሃት ነው። አጼ ሚኒሊክ ይህን ሰራ ያን አረገ እያሉ የሚያላዝኑት እነዚህ የእይታ ሽባዎች ሰው በኖረበት ዘመን መመዘን እንዳለበት እንኳን ጭራሽ አይገባቸውም። ይኸው እንሆ እኛ የማንመራትና የማንፈነጭባትን ሃገር ሲኦል ድረስ ወርደንም ቢሆን እናፈርሳታለን ያሉን በዚህ ማፊያ አስተሳሰባቸው ነው። ሰው በቃሉና በተግባሩ ይመዘናል። አንዳንድ በቃሉ ይንጣጣና ተግባሩ ላይ የለም። ሌላው ሙያ በልብ ነው በማለት ቃሉን መዝኖ ተግባሩን ይፈጽማል። ባጭሩ አሁን ሃገራችን ያለችበት ሁኔታ ከዳግመኛው የጣሊያን ወረራ የከፋ ነው። ላስረዳ ታገሱኝ።
    ወያኔ ከአዲስ አበባ በመፈርጠጥ መቀሌ ከመሸገ በህዋላ ሙሉ ሥራ አድርጎ የያዘው ለጦርነት መዘጋጀት ነበር። ለነገሩ ሃሳቡና ሎጅስትኩ እየተቆፈረና በሰራዊቱ ስም እየተገዛ መደበቅ ከተጀመረ ቆይቷል። የነቁባቸውንም በመርዝ፤ በመኪና አደጋ በማስመሰል፤ በጥይት በዚህም በዚያም አሰናብተዋቸዋል። ቀደም ብለው እየዘረፉ ባከማችሁት ገንዘብ በየዓለማቱ ለዝናብ ቀን መጠለያ የሚሆኗቸውን ዲፕሎማቶች፤ ላብይስት፤ ጋዜጠኞችና ሌሎችም የሰው ልጆች መብት ተሟጋች ነን የሚሉትን ሁሉ አስቀድመው አዘጋጅተዋል። በዚህ ስልታቸው ሁሌ በሃሳብ የዘገዪና በገንዘብ ለተገዙ ነጮችን የሚነግሯቸው አማራ ጨቋኝ ነው፤ አማራ ነው የኢትዮጵያ የመከራ ምንጭ እያሉ ነው። ይህ አስተሳሰባቸው ደግሞ ገና ጫካ ሳይገቡ ጀምሮ አብሯቸው የኖረና የትግራይን ህዝብንም የጋቱት የውሸት አተላ ነው።
    አሁን እንሆ አሜሪካና ሌሎችም የአውሮፓ ሃገሮች አብረው የሚያናፉት ከዚህ ቀደም ብሎ በተዘረጋው ወጥመድ ተጠልፈው ነው። ወያኔ ሰርቆ ሌሎችን የሚያጎርስ ለሃገርና ለወገን ምንም ደንታ የማይሰጠው ለመሆኑ የትግራይን ህዝብን የአኗኗር ሁኔታ አይቶ መፍረድ ይቻላል። የትግራይ ህዝብ በወያኔ ግፍ የተፈጸመበት፤ በፍርሃት የታሰረ፤ በራሱ አስቦ እንዳይኖር የተከለከለ ህዝብ ነው። አንድ የተራዶ ሰራተኛ እንዳጫወተኝ ” አስራራቸው ሁሉ እንደ ቀድሞዋ አልባኒያ ነው” ብሎኛል። እዚያም ለሥራ ጉዳይ ሂዶ ስለነበር ለማነጻጸር አስችሎታል። አዎን በበረሃ እያሉ እኮ አልባኒያዊ ኮሚኒዝም ነው የምናራምደው በማለት ይደነፉ ነበር። ሴራቸው ረቂቅ ነው። የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ጽ/ቤት ከአዲስ አበባ እንዲነሳ የሚወተውቱት ራሳቸው ወያኔዎች ናቸው። ዞረው ተመልሰው ደግሞ ተሟጋች መስለው ይታያሉ።
    ኢዜማ የወያኔን ሴራና የውጭ ሃገሮችን ክፋት ጠንቅቆ የሚያውቅ ድርጅት ነው። በቅርቡ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፤ ፕ/ር ብርሃኑ የሰጧቸውን ቃለ መጠይቆች ረጋ ብሎ ላዳመጠ የውጭና የሃገሩ ቤቱ ሴራ በተለይም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፓሊሲን ሃገር አፍራሽነት ቁልጭ አርጎ ያሳያል። ይህ የትግራይ ወራሪ ሃይል የሚፈጽመው በደልና ዝርፊያ ለውጭ መንግስታት አፍጦ ይታያቸዋል። ግን ከደም አፍሳሾች ጋር መሰለፍን መርጠዋል። በተደጋጋሚ እንዳልኩት በዲሞክራሲና በሰላም ስም ስንት ሃገሮች እንደፈረሱና ሃብታቸው በመዘረፍ ላይ እንዳለ መገንዘብ አይከብድም። ጋላቢውንና ተጋላቢውን ለይቶ አልጋለብም ያለው ጠ/ሚሩ አሁን ወደ ጦር ግንባር መዝመቱን ተከትሎ ስሙንና ይህን ተግባሩን ለማጥላላት የሚሹ ቅራ ቅንቦዎች ለይቶላቸው ከወያኔ ጎን ተሰልፈው ቢዋጉ ይሻል ነበር። በውጭ ሃገራት ከተሞች ተሸጉጠው የጠ/ሚሩን ውሳኔ ለማጠልሸት የሚነዙት ወሬ እግዚኦ ማህረነ ያስብላል። የሚምር ካለ። ሲዘፈን ለሚያለቅስ፤ ሲለቀስ ለሚዘፍን ትውልድ ምን መድሃኒት ይገኛል? ጠ/ሚሩ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው እንቁ ልጆች መካከል አንድ ነው። የተናገረውን እያደረገ ነው። አሁንም መልሼ ማለት የምፈልገው ሰው በቃሉና በተግባሩ ይመዘን። አሁን የጠ/ሚሩን ወደ ጦር ግንባር መሄድ የሚያጣጥሉት ለምን የስንዴ ማሳ በጦርነት ጊዜ ይጎበኛል እያሉ ሲለፈልፉ የነበሩ ጅላ ጅሎች ናቸው። በአንድ እጅ ጠበንጃ በሌላው አካፋና ዶማ ይዞ ታግሎ የሚያታግል እንጂ ዋሽንግተን ላይ ተቀምጦ ከነጭ ጋር እያሽካካ በዘሩና በጎሳው የተሰለፈ የጠባብ ብሄርተኛ ቡድን ለምድራችን አያሻትም። አቶ ስዬ አብርሃ ልጆቹንና ሚስቱን አሜሪካ ላይ በሰላም እያሳደገና እያስተማረ ለትግራይ ህዝብ እሞታለሁ ሲል ወንድምየው በደቡብ ሱዳን በገንዘብና በቁሳቁስ ወያኔን ለመርዳት ሃተፍተፍ ሲል መስማት እንዴት ያማል። ለዚህ ነው ወያኔዎች ቢታጠቡ ከዘር ፓለቲካቸው አይጠሩም የምንለው።
    በማጠቃለያው የተጻፈ ሁሉ አይታመንም፤ ሰማሁ ያለ ሁሉ የሰማውን አያወራም። ያወራ ሁሉ እውነትን አይናገርም። መታወቅ ያለበት እንኳን እንደ ሃበሻው ምድር ያለው ሃገር ይቅርና በሌላው የሃገር ለሃገርም ሆነ የእርስ በእርስ ፊልሚያ ቀዳሚዋ ሟች “እውነት ራሷ” ናት። እስቲ አስቡት ስንት ጊዜ ነው ወያኔ የኢትዮጵያን ክፍለ ጦር የደመሰሰው? ቀሪ ይኖር ነበርን? ስንት ጊዜ ነው የኢትዮጵያ ሰራዊት ለወሬ ነጋሪ አንድም ሳይቀር ጨረስናቸው ያለን። ይህ ሁሉ ቱልቱላ ነው። የሞተው ይሞታል፤ የቆሰለው ይቆስላል፤ የሚሸሽው ይሸሻል። ግን በዚህ ሁሉ የዝብርቅርቅ ወሬ ቁም ነገሩ ኢትዮጵያ በወታደራዊና በጦርነት መስኩ ያላገኘችውን ድል በድርድር ማግኘት አትችልም። በጦርነቱ ወያኔን ዳግም እንዳይነሳ አርጎ በመቀጥቀጥና መቀሌ በመግባት ያለምንም ርህራሄ የወያኔ ሰዎችን በማሰር የትግራይን ህዝብ ነጻ ማውጣት ብቻ ነው መፍትሄው። ያኔ ያለ ምንም ጫና መገንጠልም ከፈለጉ ወይም አብረው መኖር ካሻቸው መንገድ ክፍት ነው። ጭንቅላታቸው ላይ ጠበንጃ ተደግኖ ባርነት ወይስ ነጻነት ቢባሉና ወያኔ ተገነጠልን ቢል ያ ህዝብ የማያባራ መከራ ውስጥ ራሱን ይከታል። የትግራይ ተወላጆች የሆኑ መገንጠልን የማይሹ እልፎች አሉና! በመጨረሻም የጠ/ሚሩ ወደ ጦር ግንባር መሄድ እሰየው ያሰኛል እንጂ ቡራከረዪ አያስብልም። ያው እኮ ነው አስለቃሿ እንዳለችው ነው።
    ያን ማዶ ተራራ እርጥቡ ጋረደው፤ ገብቶ የነደደው ደረቅ ደረቁ ነው። ሞት ቁርጠኝነት ይጠይቃል። እያለቀሱ መሞት ጅልነት ነው። እርጥቦቹ እንሰነብታለን በሉ። ሌሎች ነደው ለሃገርና ለወገን ብርሃን ያብሩ። እናንተ የከተማና የመንደር አውደልዳዪች ዝም በሉ! በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share