የቢቢሲ ዜና የርእስ ለውጥና ያሰራጨው ዜና ይዘት የምእራባዊያን ሀገር የማፍረስ ፍላጎታቸው ማሳያ ነው

በጅቡቲ የአሜሪካ ጦር አዛዥ ለቢቢሲ የሰጡት አስተያየትና ቢቢሲም የዜና ርእሱን የቀያየረበት መንገድ የአሜሪካኑን ልክ የለሽ ጣልቃ ገብነት ከማሳየቱም በላይ ሚዲያው ከሙያ ስነምግባር ውጭ አፍራሽ ፍላጎቱንም ያሳየበት መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ገለልጸዋል።
እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ ምዕራባዊያኑ ሀገራት በሶሪያ፣ በኢራቅ እና በየመን ያደረጉትን አገር የማፍረስ ተግባር በኢትዮጵያ ለመድገም ማሰባቸውን በሚዲያዎቻቸው አስቀድመው መናገር ከጀመሩ ቆይተዋል።
ከሰሞኑ ቢቢሲ ባሰራጨው ዘገባ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላለው ቀውስ ወታደራዊ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ናት በሚል በጅቡቲ የሚገኘውን የአገሪቷን የጦር መሪ ምንጭ አድርጎ ቢዘግብም ከሰአታት በኋላ ቢቢሲ ዜናውን አስተካክሎ በትግራይ ያለው ቀውስ ለቀጣናው ስጋት ነው ስትል አሜሪካ ገለጸች በሚል እያስነበበው ይገኛል።
በዚህ ዙሪያ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያነጋገራቸው በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮምንኬሽን መምህሩ አቶ በለው አንለይ እንደገለጹት፤ ቢቢሲ ዜናውን በዚህ መንገድ ማስተካከሉ ተራ ሥህተትን ማረም ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም። እንደቢቢሲ አይነት ግዙፍ ሚዲያ ስራውን በዘፈቀድ ይሠራል ተብሎም አይታመንም።
የቢቢሲ የመጀመሪያው ዘገባ ምዕራባዊያን አገራት በሶሪያ፣ በኢራቅ እና በየመን ያደረጉትን አገር የማፍረስ ተግባር በኢትዮጵያ ለመድገም ማሰባቸውን በሚዲያዎቻቸው አስቀድመው መናገር መጀመራቸውን ያሳያል ያሉት መምህሩ፤ ምናልባትም ከመጀመሪያው ዜና በኋላ የኢትዮጵያዊያንንም ሆነ የተቀረውን ዓለም ምላሽ ሲመለከቱ ካሰቡት ውጭ ስለሆነባቸው ዜናውን ለማስተካከል ተገደዋል ነው ያሉት።
ዓለም አቀፉ ሚድያ ተቋማቱ የሀገራቸውን መንግስት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አንዱ ክንፍ በመሆናቸው የመንግስታቸውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማስፈጸም እንጂ ለጋዜጠኝነት መርሆች ግድ የላቸውም ያሉት መምህሩ፤ ቢቢሲ ሰሞኑን ኢትዮጵያን በተመለከተ የሰራውና በኋላም ማስተካከያ ያደረገበት ዘገባ የዚሁ ዘመቻ አንዱ አካል ነው ብለዋል።
የቢቢሲ የቀደመው ዘገባ ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ በቀጣይ ሊስሩት ያሰበውን ጉዳይ በግልጽ ያሳየ ነው ያሉት መምህሩ፤ ምዕራባውያኑ በሌሎች አገራት ላይ የሚወስዱት እርምጃ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ቅቡልነት እንዲያገኝ የሕዝብ አስተያየት ቅርጽ የመስጠት ሥራን በሚዲያዎቻቸው ይሠራሉ፤ አሁን ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውም ይህንኑ መሆኑንም አስረድተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መስራች እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት መስራችና መቀመጫ በሆነች አገር ላይ የዚህ አይነት አማራጭን ማሰብ ፍጹም ተገቢነት የጎደለውና ከዓለም አቀፍ ህግ እና መርህም ውጭ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያዊያን የምዕራቡን ዓለም ፍላጎትና አካሄድ አሁን ካለውም በላይ ሊረዱና የአገራቸውን ክብርና የግዛት አንድነት ማስጠበቅ ይገባቸዋል፤ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃንም የአገራቱን ሴራ እግር በእግር ተክታትለው ማጋለጥ አለባቸው ሲሉም ነው መምክር በለው አንለይ ያብራሩት።
“አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያኑ ሀገራት የኢትዮጵያ ህዝብን የቆየ የአልደፈርም ባይነት ሥነልቦና በደንብ ስለሚረዱት ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው በቀላሉ እንደማይወጡ ያውቁታል” ያሉት መምህሩ፣ ለዚህም ነው ዓለም አቀፉ የሚድያ ተቋማቱ የመዋለል ሁኔታ የሚታይባቸው ሲሉ አብራርተዋል።
በአብዱረዛቅ መሐመድ
(ኢ.ፕ.ድ)
ተጨማሪ ያንብቡ:  በዝቋላ ገዳም አራት መነኮሳት መገደላቸውንየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክስርቲያን አስታወቀች

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share