አዲሱ ኢትዮጵያ ካቢኔ ጂኦግራፊያዊ ፍትሃዊነት ዳሰሳ – ዳንኤል ካሣሁን (ዶ/ር)

/

መስከረም 24 ቀን 2013 ዓም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አዲሱን ካቢኔ ፓርላማው እንዲያጸድቀው ሲያቀርቡ የእያንዳንዱን እጩ ስም፣ የትውልድ ሥፍራ፣ የጋብቻ ሁኔታ፣ የትምህርት ዝግጅት፣ አንዲሁም የሥራ ልምድ መረጃዎችን ይፋ አድርገው ነበር። ከዚህ ቀደም “ብሄር” የሚለው መገለጫ ባልተለመደ መልኩ በ “ትውልድ ሥፍራ” መተካቱ ፖለቲካዊ አንድምታዎች እንደሚኖሩት ቢታመንም መረጃው ለዚህ አጭር የዳሰሳ ጥናት መነሳሳትንና ለትንታኔው ሂደት ደግሞ አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል።

የአንድ እጩ የትውልድ ሥፍራ መገለጹ መረጃውን መሬት ላይ ለመቸከል[1] እና ካርታ ላይ እንደ ነጥብ ለማንጠብ ያስችላል። ያ ማለት ደግሞ የእጩውንና የ”ተጓዳኝ ጉዳያትን”[2] በሳይንሳዊ የትነት[3] መንገድ በመጠቀም የሹመቱን ሥፍራዊ ፍትሃዊነት[4] ለመተንተን ዕድል ይፈጥራል። በውጤቱም የምልከታ መረጃን[5] ተጠቅሞ ቀለል ባለ መንገድ ግንዛቤን ያስጨብጣል። በቀጣዩ ቀናት የ61 ሚኒስቴር ዴኤታዎች በተሾሙበት ወቅት የትውልድ ሥፍራቸው ይፋ ይደረጋሉ ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር። ሆኖም መረጃው ባለመካተቱ በዚህ ዳሰሳ ላይ የቀረበው ትንተና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በ23 የካቢኔ አባላት የትውልድ ሥፍራ ላይ ብቻ ተመርኩዞ ነው።

በርካታ መንግሥታት የካቢኔ አባላቶቻቸው ስብጥር የአገራቸውን መልክ እንዲመስል ሙከራ ቢያደርጉም ብዝሃዊነታቸው ፍጹም ሆኖ አያውቅም። ለምሳሌ የአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ምክትላቸውን ጥቁሯን ሴት ካመላ ሐሪስን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኋይት ሃውስ ማምጣታቸውንና ብዝሃነት ያላቸውን የካቢኔ አባላት በማዋቀራቸው “የእኔ አስተዳደር ስብጥሩ አሜሪካንን እንዲመስል የገባሁትን ቃል እየጠበቅሁ ነው” ብለው ተናግረው ነበር። ከባይደን ቀደም ብሎ ቢል ክሊንተንም ሆነ ባራክ ኦባማ የበኩላቸውን ጥረቶቸ አድርገዋል። ሆኖም ግን የቅርቡን የአሜሪካ ታሪክ ስንመለከት እንደ ዶናልድ ትራምፕ ካቢኔ ኢ-ብዝሃዊነት አልታየም። 24 አባላት ካሉት የትራምፕ ካቢኔ 19ኙ ነጫጭ ወንዶች ነበሩ።

የተፈጥሮ አካባቢ ብዝሃነቱ ከበረከተበት አገር፣ በተደራቢነት የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህል ብዝሃነት ከተነባበረበት አገር፣ አንዲሁም የፖለቲካው ቅኝት ዋልታ ከረገጠበት አውድ የካቢኔ አባላትን ፍትሃዊነት ማረጋገጥ ፈታኝ መሆኑ አይዘነጋም። ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ሌሎች “አካታችና ፍትሃዊ” ብለው የገለጹት ካቢኔ ውክልና የራሱ ውስንነት እንዳሉትም መዘንጋት የለበትም።  የካቢኔው እጩዎቹ የተዘገኑት በምርጫው ከተሳተፉት ወደ 33 ሚሊዮን ሕዝብ (የትግራይና ሶማሌ ክልሎችን ሳይጨምር) ውስጥ ሳይሆን ቁጥራቸው አራት ሚሊዮን ገደማ ከሚገመቱ የብልጽግና ፓርቲ አባላት መሃል ነው (በዘመነ ኢሕአዴግ ሕወሓትን ጨምሮ ወደ 5 ሚሊዮን አባላት እንደነበሩ ልብ ይሏል)። ይህ ማለት ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ከተሰጡት ሶስት ቦታዎች በስተቀር በካቢኔ አባልነት ለመመረጥ ዕድል የነበራቸው ድርሻ ሲሰላ ከመራጩ ሕዝብ ውስጥ ከ12% (4/33 X100) በታች ካለበት የብልጽግና ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኞች ቋት ውስጥ ነው። እርግጥ ነው መራጩ ሕዝብ ድምጹን ለብልጽግና ፓርቱ ሰጥቷል የሚል መከራከሪያ ሊቀርብ ይችላል። ሆኖም ግን ፖለቲካዊ ተምሳሌትነቱ ታይቶ ካልተወደሰ በቀር የካቢኔው ርዕዮተ ዓለማዊ ስብጥሩ ብዝሃነት እንደጎደለው መካድ አይቻልም። ሌሎች መንግሥታትም ቢሆኑ የሚያደርጉት ይህንኑ ስለሚሆን ላይደንቅ ይችላል። ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ብዝሃነት ሲባል ርዕዮተ ዓለማዊ፣ ጾታዊ፣ ባህላዊ፣ ሥፍራዊ ወዘተ ሲሆን በዚህ ዳሰሳ የመናተጉረው በሥፍራዊ ፍትሃዊነቱ ጉዳይ ላይ ይሆናል።

 

የኢትዮጵያ ምድር ውክልናና ፍትሃዊነት።

የካቢኔ አባላቱ የትውልድ ሥፍራ ሥርጭት በተለይም በካርታው ውስጥ በሚታየው ትሪያንግል ውስጥ ተሰባስቦ ተገኝቷል (ምስል 1)። ሥርጭቱን ስንመረምር ከርዝመቱ (በሎንጂቲዩድ) አንጻር ከደቡባዊው ነጌሌ (5.33 ዲግሪ ሰሜን) እስከ ሰሜናዊው አዲግራት (14.27ዲግሪ ሰሜን)፣ በስፋቱ (በላቲቱዩድ) አንጻር ደግሞ ከምዕራቡ ቄለም (34.80 ዲግሪ ምስራቅ) እስከ ምስራቁ ገለምሶ (40.52 ዲግሪ ምስራቅ) ተሰራጭቷል። የሰሜን-ደቡብ ስርጭቱ የተሻለ መመጣጠን ቢታይበትም የምዕራብ-ምስራቅ ስርጭቱ ግን መበላለጥን ያሳያል። በውጤቱም የካቢኔው ስብስብ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ አጋድሎ ይታያል። ሆኖም ግን ይህንን ካርታ ብቻ ተመርኩዞ ከድምዳሜ መድረስ ለስህተት ይዳርጋል። ምክንያቱም የኢትዮጵያ አየር ንብረት፣ አፈር፣ የውሃ አካላት፣ አፅዋት፣ የመሬት አቀማመጥ፣ ወዘተ ከሥፍራ ሥፍራ እንደሚለያይ ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሰፋፈርም አንድ ወጥ ሆኖ የተሰራጨ አይደለምና። ስለዚህ የካቢኔውን የትውልድ ሥፍራ ጂኦግራፊያዊ ፍትሃዊነት ለመገምገም ከሌሎች ተያያዥ መረጃዎች ጋር አነባብሮና አሰናስሎ መተንተን ያስፈልጋል።

12

ምስል 1፡ የአዲሱ ካቢኔ አባላት የትውልድ ሥፍራ ሥርጭት። በምስሉ የካቢኔው አባላት በትሪያንግሉ ውስጥ ብቻ ተወስነው ሲገኙ በሥርጭቱም ወደ ምዕራብ የአገሪቱ ጎን አመዝኗል።

 

ቆለኛ ወይንስ ደገኛ?

ከባህር ጠለል በላይ የሚኖረው ከፍታ የአየር ንብረትን በቀጥታ ከሚወስኑ ምክንያቶች አንዱና ዋንኛው ነው። በተለይ በኢትዮጵያ የከፍታ ተጽዕኖ ወደር የለውም። የአየር ንብረት የሰውን ባህሪ ከሚቀርጹ አንዱ ነው”[6] እንዲሉ በቅርቡ ከቻይና፣ አውስትራሊያ፣ ብሪታኒያና አሜሪካ በተሰበሰበ የናሙና መረጃ ላይ በተካሄደ ሳይንሳዊ ጥናት እንደተረጋገጠው ወይና ደጋዊ የሙቀት መጠን ባላቸው አካባቢዎች ያደጉ ሰዎች በተስማሚነት፣ በህሊና ተገዥነት፣ በተረጋጋ ስሜታዊነት፣ ወዘተ የላቀ ውጤት አስመዝግበዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጠቢቡ ሰለሞን የፈተናት ሴትና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፎክሩት እርጉሞች! - በበላይነህ አባተ

የከፍታ መጠንን ተመርኩዞ ኢትዮጵያን በአምስት ቀጣናዎች መክፈል ይቻላል። በረሃ (ከ500 ሜ. በታች)፤ ቆላ (ከ500–1,500 ሜ.)፣ ወይና ደጋ (ከ1,500–2,300 ሜ.)፣ ደጋ (ከ2,300–3,200 ሜ.)፣ ውርጭና ቁር (ከ3,200 ሜ. በላይ) ናቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብ አሰፋፈርም ከከፍታው መጠን ጋር ጉድኝት ቢኖረውም ትስስሩ በወጥነት “ቀጥተኛ ጉድኝት”[7] አይደለም። ለምሳሌ በወቅታዊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር (2020 በዩናይትድ ኔሽንስ ትንበያ) ላይ በተመረኮዘ ትንተና 81% የሚሆነው ሕዝብ የሰፈረው በወይና ደጋና በደጋ ቀጣናዎች ውስጥ ነው። በዚሁ ተመሳሳይ ሥፍራ የ95.7% የካቢኔው አባላት ዕትብት ተቀብሯል። በወይና ደጋው 55.7% የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ የሰፈረበት ሲሆን፣ በዚሁ ሥፍራ 80% የካቢኔ አባላት መፍለቃቸው በማወቅም ይሁን በሌላ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የካቢኔ ምልመላ ወይና ደጋ-ተኮር ያስመስለዋል። ጉዳዩ ከቀደምት የ“አካባቢያዊ ፍጹም ወሳኝነት”[8] መርሆ ጋር ይመሳሰል ይሆን? እንደ ጥንታዊ ግሪኮች አሰራር ከልከኛ የአየር ሙቀት ሥፍራ የሚመጡ ሰዎች ጥሩ ጭንቅላት (ከፍተኛ አይ ኪው) ይኖራቸዋል ተብሎ ስለሚታመን ለአስተዳዳሪነት፣ ለዳኝነት፤ ለእንደራሴነት እንዲታጩ ይደረግ ነበር። በተቃራኒው ወደ ፅንፍ የተጠጋ ሙቀትም ሆነ ቅዝቃዜ ከሚበረታባቸው ሥፍራ የሚመጡ ሰዎች ከጭንቅላት ይልቅ ከፍተኛ የአካል ጥንካሬ ያካበቱ ናቸው ተብሎ ስለሚታመን አካላዊ ብቃትን ለሚጠይቁ የሥራ ዘርፎች (ለምሳሌ ውትድርና፣ ቦክሰኛ፣ ወዘተ) ይታጩ ነበር። ሆኖም ግን ይህ አመለካከት በጊዜ ሂደት ድክመቱ ታውቆ፣ አካባቢ የራሱ ተጽዕኖ ቢኖረውም ሰዎች በሳይንስና ቴክኖሎጂ አየታገዙ ከጊዜ ወደ ጊዜ አኗኗራቸውንና አካባቢያቸውን የበለጠ ለኑሮ አመቺ እያደረጉ በመምጣታቸው “አካባቢን መግራት ይቻላል”[9] በሚል መርህ ተተክቷል።

13

ምስል 2፡ የኢትዮጵያ ሕዝብና የካቢኔው ትውልድ ሥፍራ ሥርጭት ከምድር ከፍታ ጋር ያለው ትስስር። ሕዝቡና ካቢኔው በተመሳሳይ መልኩ ከከፍታው ጋር የሚያሳዩት ቀጥታና ተገላቢጦሽ ኝኙነት የደወል ቅርጽን የያዘ[10] ሲሆን የመካከለኛው (1,500–2,300 ሜ.) ቀጣና ለመኖሪያ አመቺ ሥፍራ ሆኖ ይታያል።

 

ከመሃል ነው ከዳር አገር?

በበርካታ ታዳጊ አገራት በመሃልና በዳር አገር መሃል የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል ልዩነት ጎልቶ ይታያል። አልፎ አልፎ ጉዳዩ ውጥረትን ፈጥሮ የፖለቲካ አጀንዳ ስለሚሆን ጉዳዪ በርካታ የአካዳሚ ዘርፎች ይጠናል። ከነዚህም ውስጥ አንዱ “የማዕከል-ተጓዳኝ” ሞዴል (Core-Periphery Model)[11] ነው። የዳር አገር አካባቢ ከስልጣኔም ሆነ የሃብት መጠን ብዙውን ጊዜ ኋላ ቀር ስለሚሆን በተግባርም ባይሆን በቃል ደረጃ “ለዳር አገር ተቆርቋሪ ነኝ” የሚሉ በርካታ ፖለቲከኞች በኢትዮጵያችንም ነበሩ፣ ይኖራሉ። ጥያቄው የአዲሱ ካቢኔ ሲሰባሰብ ትኩረቱ ከመሃል ነው ከዳር አገር? የሚል ነው።

በዚህ ጥናት “የሕብረ ቀለበታዊ ቋት” (Multiple Ring Buffer Analysis)[12] የሚባል የመረጃ ማጠናቀሪያ መንገድን በመጠቀም የካቢኔው አባላት ትውልድ ሥፍራ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ያላቸውን የርቀት ጠባይ በየ150 ኪሜ ርቀት ነጥሎ ለማስላት ተሞክሯል። በዚህ ዘዴ “ርቀት” ሲባል ጠመዝማዛውን የአውራ ጎዳና ተከትሎ የሚለካ ሳይሆን በወፍ በረር የቀጥታ መስመር ተለክቶ ነው። በውጤቱም 91% የሚሆኑት የካቢኔ አባላት ትውልድ ሥፍራ ከአዲስ አበባ 450 ኪሜ ርቀት ውስጥ ተገኝቷል (ምስል 3)። በተመሳሳይ በዚህ የርቀት ክልል ውስጥ 86% የኢትዮጵያ ሕዝብ ይኖርበታል። የሚገርመው ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ምክትላቸውን ጨምሮ የበርካታ ዕጩዎች (43.5%) መገኛ ከአዲስ አበባ ከተማ ርቀቱ ከ150 እስከ 300 ኪሜ ባለው ሥፍራ መሆኑ ነው። በአንጻሩ ከ600 ኪሜ ርቀት በኋላ አንዳችም እጩ አለመኖሩ ርቀቱ ከመሃል አገር እየረዘመ ሲሄድ የካቢኔ አባል የማፍለቅ አቅሙ እየሟሸሸ[13] ስለሚሄድ ይሆን? በጥቅሉ ሲታይ አዲሱ ካቢኔ ብዙም የመሃል ብዙም የዳር አገር እጽዕኖ ያልጎላበት ስብስብ ይመስላል። በተጨማሪም ከአዲስ አበባ ከተማ ባለው ርቀት የተስተዋለው የካቢኔ ሥርጭት ጠባይ ከአጠቃላይ የህዝቡ ሥርጭት ጋር በአያሌው የተዛመደ ነው ማለት ያስደፍራል።

14

ምስል 3፡ ከአዲስ አበባ ከተማ በተለያየ የርቀት ቀጣና ውስጥ የሚገኘው የካቢኔ አባላት ትውልድ ሥፍራና የአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሥርጭት ምጥጥን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በኢሬቻው ማን ተጠቀመ? ማንስ ተጎዳ? - አሊጋዝ ይመር

 

ከለውጡ ባለውለታዎች መሃል?

ከ 2006 እስከ 2010 ዓም ድረስ የኢሕአዴግን መንግስት በመቃወም በመላ አገሪቱ በሚባል መልኩ ያልተቋረጠና ጠንካራ አመጽ እንደተካሄደ ይታወሳል። ሆኖም ግን በሁሉም ሥፍራ የሚኖር ዜጋና ማኅበረሰብ በእኩል መጠን አልተፋለመም፣ አልታሰረም፣ አልደማም፣ አልሞተም በሚል የታሪክ ሽሚያ ውስጥ የገቡ እንደነበሩ አይካድም። “ለድሉ መገኘት ብዙ መስዋዕትነት (የአንበሳውን ድርሻ) ከፍለናል” ከሚሉ አካባቢዎች ጋር የካቢኔው ድርሻ ትስስር (ኮረሌሽን) ይኖረው ይሆን የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። በተጠቀሱት ዓመታት በኢትዮጵያ የተመዘገቡ 3,070 ግጭቶች ነበሩ። ልክ እንደ ምስል ሶስት በየ150 ኪሜ ርቀት ተለይቶ የግጭቱ መጠን በመሰላቱ ውጤቱ በሰንጠረዥ 1 ቀርቧል። የቀጣና ሁለት (ከ300–450 ኪሜ) አና ሶስት (ከ150–300 ኪሜ) የግጭት መጠኑ ድምር 64.5% ሲሆን በተጓዳኝ የካቢኔው የትውልድ ሥፍራ ድርሻም በተመሳሳይ 65.5% ሆኗል። ሆኖም ግን ከትስስር መረጃ ላይ ተንስቶ ምክንያታዊ ግንኙነትን (causal relationship) መበየን አይቻልም። ተጨማሪ ጥናት ይጠይቃልና።

ሰንጠረዥ 1፡ ከአዲስ አበባ ከተማ በተለያየ የርቀት ቀጣና ውስጥ የተመዘገበው የግጭቶችና የካቢኔ አባላት ብዛት ንጽጽር በመቶኛ። ግጭቶቹም ሆነ የካቢኔው አባላት በሁለተኛውና በሶስተኛው (150–450 ኪሜ) ዞኖች በርክቶ ይታያል።

15

የስበት ማዕከሉስ የት ነው?

አንዳንዴ በፖለቲካው ዙሪያ የባስልጣናቱ “አስኳል”[14] የት ይሆን ያለው? ተብሎ ይጠየቃል። የስርጭቱ ዕምብርት የፖለቲካውን ስበት እንዲሁም ፍትሃዊነትን ቀምሮ ስለሚያሳይ የመረጃው ተፈላጊነት አያጠያይቅም። አልፎ አልፎ የአገር አንድነት አደጋ ላይ የሚወድቀውም ሆነ የመገንጠል ጥያቄ የሚመነጨውም ባመዛኙ ከዚህ ሁነት በመነሳት ነው።

የኢትዮጵያን የሚሸፍን አንድ ግዡፍ ጎጆ ቤት ቢሰራ “የምሶሶው ችካል”[15] ሊያርፍ የሚችለው ከወለንጪቲ ከተማ በስተምስራቅ አቅጣጫ 23 ኪሜ ገደማ ርቆ ነው (ምስል 4B)። የካቢኔ አባላቱን የትውልድ ሥፍራ ኮርድኔቶች አማካይ ሥፍራ ስናሰላው ደግሞ ማዕከሉ የሚያርፈው ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ አቅጣጫ ሆኖ ከጊንጪ ከተማ በስተሰሜን ወደ 37 ኪሜ ርቆ ነው (ምስል 4A)። በሁለቱ ማዕከላት መሃል የ191 ኪሜ ገደማ ክፍተት መኖሩ የካቢኔው አባላት የትውልድ ሥፍራ አማካይ ቦታ በእጅጉ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ ማጋደሉን ያሳያል። እንደ ካቢኔው የማጋደል መጠን የተጋነነ ባይሆንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሥርጭት የስበት ማዕከልም ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ የተሳበ ብቻ ሳይሆን ከ2005 (ምስል 4D) እስከ 2020 (ምስል 4C) ባሉት ጊዜያት እንኳ የስበቱ ማዕከል ወደ ደቡብ አቅጣጫ በጥቂቱ መንፏቀቁን መገንዘብ ይቻላል። በኢትዮጵያ የግዛት ታሪክ የአስተዳደር ማዕከሉ ከአክሱም ተነስቶ በጊዜ ሂደት ወደ ደቡብ አቅጣጫ መጓዙ የአገሪቱን የህዝብ ብዛት ምጣኔ በዕጅጉ ስለቀየረው የስበት ማዕከሉ ወደ አዲስ አበባ መጎተቱ ይታወሳል። በሃገሪቱ ባለው የተበላለጠ ዲሞግራፊ ሳቢያ የሕዝቡ የስበት ማዕከል በአንድ ቦታ የማይጸና ነው። ከምስራቅ ይልቅ ወደ ምዕራብ ማዘንበሉ በተሻለ ሁኔታ የአግሮ እኢኮሎጂካል ሃብት ያለበት ሥፍራ በመሆኑ ሊሆን ይችልላል። ብግለሰቦች የግል ተተሳሽነትም ሆነ በመንግስ አዝማችነት ሰፈራ ሲካሄድ መዳረሻም ምዕራብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ መሆኑን ልብ ይሏል። አሁንም ወደ ደቡብ አቅጣጫ ቀጥሎ የመጓዙ ምስጢርም ከሰሜኑ ይልቅ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ እድገት በፍጥነት በማደጉ ሊሆን ይችላል። በዚህ ጥናት ላይ ቀደም ባሉ ዓመታት የነበሩ የሕዝብ ሥርጭት መረጃዎች ቢታከሉበት ደግሞ እጅግ በተሻለ ሁኔታ የ“ጊዜ ሂደት ለውጡን”[16] መገንዘብ ይቻላል።

16

ምስል 4፡ የካቢኔ አባላት የስበት ማዕከል ከአገሪቱ አጠቃላይ የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ሥርጭት ማዕከላት ጋር ያለው ጉድኝት። በካርታው የካቢኔው አባላት ትውልድ ሥፍራ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ በእጅጉ አዘንብሎ ይታያል።

 

የወንዜ ልጅ?

የአገራቸን ወንዞች ለማኅበረሰቡም ሆነ ለዜጎች እንደ አንዱ የቁርኝት መገለጫ ሆኖ ስለማገልገሉ “የወንዜ ልጅ” የሚባለውን ዘይቤ መጥቀስ ይቻላል። የኢትዮጵያን ግዛት ለማካለል ከሚቀርቡ አማራጭ መስፈርቶች አንዱ ተፋሰስን መሰረት ያደረገ በመሆኑ የካቢኔ አባላቱን የተፋሰስ ቁርኝት መመርመሩ ተጨማሪ መረጃን ያፈልቃል። በጥናቱ ውጤት ከ15 ወንዝ ሸለቆዎቻችን መሃል እንደ የአባይ ተፋሰስ በርካታ የካቢኔ አባላትን ያበረከተ የለም። የአባይ ተፋሰስ ስምንት እጩዎችን (34%) ሲያፈልቅ በሁለተኛ ሥፍራ ከሚገኘው የአዋሽ ተፋሰስ እጩዎች ብዛት በእጥፍ ይልቃል። ሁለቱ ተፋሰሶች 28% የሚሆነውን የአገሪቱን የቆዳ ስፋት ሲሸፍኑ በካቢኔ ድርሻ ግን 52% ይሸፍናሉ። የሸበሌና የገናሌ ተፋሰሶች 20.3% የአገሪቱን የቆዳ ስፋት ሸፍነው ሳለ እያንዳንዳቸው አንድ እጩ ብቻ ነው ያበረከቱት። የብላቴ፣ የደንከል እና የኦሞ ተፋሰሶች እያንዳንዳቸው ሁለት የካቢኔ አባላትን ሲያቀርቡ የተከዜ፣ የመረብ፣ የሰገን፣ የአትባራና የአንገረብ ተፋሰሶች አንዳችም እጩ ማቅረብ አልቻሉም። ዋናው ነገር የስፋት መጠን ሳይሆን ተፋሰሱ የሚገኝበት ሥፍራ ተያያዥ ጉዳያት (ከአዲስ አበባ ከተማ ካለው ርቀት፣ ከከፍታ መጠን፣ ከአየር ንብረት ቀጣና፣ የሕዝብ ብዛት፣ የስበት ማዕከልነት፣ ወዘተ) ይመስላል ወሳኙ ነገር።

ተጨማሪ ያንብቡ:  «ደሸት» የብርሃን እውነት! -ወለላዬ ከስዊድን

 

ማጠቃለያ

ስምንቱ የካቢኔ አባላት ሴቶች መሆናቸው ከሌሎች ሃገራት አንጻር የፆታ ፍትሃዊነትን ይጠቁማል። የተሿሚዎቹን ዕውቀትና ክህሎት በምሉዕነት ባያመላክትም በትምህርት ዝግጅት ከፍ ያለ ደረጃ ተስተውሏል። ከኦነግ ፓርቲ እጩ በስተቀር ሌሎቹ የማስተርስ ወይንም የፒኤችዲ ዲግሪን ያነገቡ ናቸው። ለሶስት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የሚኒስትርነት ሥልጣን መጋራቱም ለአካታችነቱ አስረጅ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል። በዚህ አጭር ዳሰሳ የቀረበው ትንተና የካቢኔ አባላቱ የትውልድ ሥፍራ ሥርጭት ከአዲስ አበባ ከተማ ካለው ርቀት፣ ከከፍታ መጠን፣ ከአየር ንብረት ቀጣና፣ ከአጠቃላይ የሕዝብ ሥርጭት፣ ከተፋሰስ፣ ከግጭት ሥፍራ እና ከስበት ማዕከል ጋር ያለውን ትስስር ተተንትኗል። ሆኖም የተገኘው መረጃ የትስስር (correlation) እንጂ ምክንያታዊ ግንኙነት (causal relationship) አይደለም። መግፍዔውን (ገፊ መንስዔ) ለመመርመር ግን የዳሰሳው ውጤት የመላምት ማፍለቂያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። ሆኖም በዚህ ጽሁፍ ሊጠቀስ የሚችለው የካቢኔ ፍትሃዊነቱ መጠነኛ መፋለስ ቢያሳይም የጂኦግራፊያዊ ሥርጭቱ ከሞላ ጎደል ፍትሃዊ ነው። የ61 የሚኒስቴር ዴኤታዎቹ የትውልድ ሥፍራ መረጃ በዚህ ጥናት ተካቶ ቢሆን ኖሮ የተሻለ ውጤት ሊገኝ ይችል ነበር። ይህ አጭር ዳሰሳ ያመነጨው መረጃ ወደፊት በቀጣይነት ለሚመሰረቱ ካቢኔዎች “የመነሻ ማመሳከሪያ”[17] ሆኖ ለተሻለ አካታችና ወካይ የካቢኔ ምስረታ በጎ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

 

የግርጌ ማስታወሻ

[1] “መቸከል” geo tagging የሚለውን ቴክኒካዊ ቃል ወክሏል። ትርጓሜውም በተለያዩ የመረጃ ምንጮችን (ለምሳሌ ፎቶዎች፣ ቪዲዮዎች፣ ዌብሳይቶች፣ የጽሁፍ መልዕክቶች፣ ወዘተ) በጂኦ ኮርድኔት አበልፅጎ ስርጭታቸውን በካርታ ላይ ለማስፈርና ሥፍራዊ  ትንተና ለማካሄድ  የሚያስችል ዘዴ ነው።.

[2]  “ተጓዳኝ ጉዳያት” spatial attributes የሚለውን ቴክኒካዊ ሃረግ ይወክላል።

[3] “ሳይንሳዊ የትነት” የሚለው ሃረግ “የት” ከሚለው ቃል መንጭቶ the science of where የሚለውን ቴክኒካዊ ሃረግ ወክሏል።

[4] “ሥፍራዊ ፍትሃዊነት” spatial representativeness የሚለውን ቴክኒካዊ ሃረግ ይወክላል።

[5] “የምልከታ መረጃ” visual information የሚለውን ቴክኒካዊ ሃረግ ይወክላል።

[6] “የአየር ንብረት የሰውን ባህሪ ከሚቀርጹ አንዱ ነው” የሚለው አባባል Climate molds character ከሚለው የተለመደ አባባል በቀጥታ ወደ አማርኛ የተመለሰ ነው።

[7] በጽሁፉ “ቀጥተኛ ጉድኝት” የሚለው ገለጻ linear relationship የሚለውን ሃረግ ለመተካት ነው። ትርጓሜውም የስታቲስቲካዊ ቃል ሆኖ የሁለት መረጃዎች (variables) ጉድኝት በግራፍ አማካይነት ሲታይ ቀጥተኛ መስመርን የሚፈጥር ነው። ይህ ማለት አንዱ ቫርያብል ከፍ ወይንም ዝቅ ሲል ሌላኛው ቫርያብልም አብሮ በተመሳሳይ ከፍና ዝቅ ይላል።

[8] የ“አካባቢያዊ ፍጹም ወሳኝነት” Geographical determinism የሚለውን ቴክኒካዊ ሃረግ ይወክላል። ትርጓሜውም የሰው ልጅ ታሪክ፣ ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ ወዘተ እጣ ፈንታ የሚወሰነው በሚኖርበት አካባቢ (አየር ንብረት፣ መልክዓ ምድር፣ ወዘተ)  ነው የሚል እሳቤ ነው። ይህ ፍልስፍና ለቅኝ ገዢዎች አመቺ መሳሪያ ሆኗል ይባላል።

[9] “አካባቢን መግራት ይቻላል” የሚለው ሃረግ Geographical possibilism የሚለውን ቴክኒካዊ ሃረግ ይወክላል። ትርጓሜውም ምንም እንኳ የተፈጥሮ አካባቢ በሰዎች ህይወት ላይ ጫና ቢኖረውም ባህልና የኢኮኖሚ እድገትን ግን በሁለንተናዊነት አይወስነውም የሚል የፍልስፍና ነው። ይህ መርህ ቀድሞ የነበረውን “አካባቢያዊ ፍጹም ወሳኝነት” የተካ ነው።

[10] “የደወል ቅርጽን የያዘ” የሚለው ሃረግ bell-shaped curve የሚለውን ቴክኒካዊ ሃረግ ለመግለጽ ነው።

[11] የ“ማዕከል-ተጓዳኝ” ሞዴል centre–periphery model የሚለውን ቴክኒካዊ ሃረግ ለመግለጽ ነው።

[12] የሕብረ ቀለበታዊ ቋት ዘዴ multiple ring buffer analysis  የሚለውን የGIS ቴክኒካዊ ዘዴ ነው።

[13] የማፍለቅ አቅሙ እየሟሸሸ የሚለው ሃረግ distance decay effect የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ለመግለጽ ነው።

[14] አስኳል nucleus የሚለውን ቃል ለመተካት ነው።

[15] “የምሶሶ ችካል” centroid የሚለውን ቃል ለመተካት ነው።

[16] የ”ጊዜ ሂደት ለውጥ” temporal trend የሚለውን ቴክኒካዊ ሃረግ ለመግለጽ ነው።

[17] “የመነሻ ማመሳከሪያ” benchmark የሚለውን ቃል ለመተካት ነው።

የጸሐፊው ኢሜይል አድራሻ፡ daniel.kassahun@gmail.com

2 Comments

  1. Dear Writer,

    In my opinion, the whole analysis is uselles. As an Amhara, I feel that I do not care whether there are Amahra propsperty party officals in Ahmed`s cabinet or not. Why? Becaue no Amhara propsperity offical and even ABN offical stands for Amahra people. They are there simply to fill their “borch”. I do not mind if the positions occupied by these officals are given to Somalis, Afaris or people Gambella. Think about Gedu Andargachew and Belete Molla. The peole who sent them to the parliament are under the yoke of TPLF, dying in hundreds, if not thousands, every day, and these politicians are enjoying life in Addis, doing nothing to help their people.
    The other important issue is how many parliament members do you think truly represent the geographic areas they come from and stand for the interests of the people who elected them? Parliament members from Amhara region in particular are useless and again I do not mind if these seats are given to citizens from other regions of the country.

    In Ethiopia, sadly, most things, including religion and our politics, are fake and full of lies. Simply used to fill “borch”.

    I hope you consider my points.

    Meseret.

  2. personally ,i appreciate you to explain the cabinets nation-wide representation and geographical birth place.however,was this study is important at this time for us as we are endowed diversified culture,language,religion,…. ?

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share