እንደ ቃየን፣ አንገዳደል! – ጆቢር ሔይኢ ከሁስተን ቴክሳስ

09/02/2021

ቃየን በወንድሙ ተመቅኝቶ በገደለው ጊዜ፣ እግዚአብሔር አምላክ ቃየንን አለው፣ “የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። እንግዲህ የተረገምህ ነህ፣የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፏን በከፈተች መሬት ትሰደዳለህ፣ ብታርሳትም ፍሬዋን አትለግስህም፣በምድር ላይ ኮብላይና ተንከራታች ትሆናለህ” አለው።

ቃየንም “ቅጣቴ ልሸከመው ከምችለው በላይ ነው፣እነሆ በምድር ላይ ኮብላይና ተንክራታች እሆናለሁ፣የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል” ባለ ጊዜም እግዚአብሔር፣ “እንደዚህ አይሆንም፣ማንም ቃየንን ቢገድል፣ ሰባት ዕጥፍ የበቀል ቅጣት ይቀበላል “ሲል አዘዘ።ስለዚህም በቀል የእግዚአብሔር ብቻ ነው።

የእስራኤል ሕዝብም የነቢያትን ቃል ባለመስማት በአምላኩ ላይ ባመጸ ጊዜ፣ ለሰባ አመት በስደት ተጋዘ። ሰባው አመት እንደ ተፈጸመም ዳንኤል በጌታ በአምላኩ ፊት ወድቆ፣ እንዲህ ሲል ጸለየ፣ “ከሚወዱህና ትእዛዝህን ከሚፈጽሙ ሁሉ ጋር የፍቅር ቃል ኪዳንህን የምትጠብቅ፣ታላቅና የተፈራህ አምላክ ጌታ ሆይ፤እኛ ኀጢአት ሠርተናል፣ በድለናልም፣ክፋትን አድርገናል፣ ዐምፀናልም፣ከትእዛዝህና ከሕግህ ዘወር ብለናል።

ለንጉሦቻችን፣ ለልዑሎቻችንና ለአባቶቻችን እንዲሁም ለምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ በአንተ ስም የተናገሩትን አገልጋዮችህን ነቢያትን አልሰማንም። “አሁንም አምላካችን ሆይ፣የአገልጋዮችህን ጸሎትና ልመና ስማ።ጌታ ሆይ ስለ ስምህ ስትል ፊትህን ወደ ፈረሰው መቅደስ መልስ።”አምላክ ሆይ፣ጆሮህን

አዘንብልህ ስማ፣ዐይንህን ገልጠህ መጥፋታችንንና ስምህ የተጠራበትን ከተማ ተመልከት፡፡

ልመናችንን የምናቀርበው ስለ ጽድቃችን ሳይሆን፣ስለ ታላቅ ምሕረትህ ነው። ጌታ ሆይ፣ አድምጥ!ጌታ ሆይ፣ይቅር በል! ጌታ ሆይ፣ስማ! አድርግም፣ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቶአልና አምላኬ ሆይ፣ ስለ ስምህ ስትል አትዘግይ” በማለት ተማጽኖ ለእስራኤል ምህረትን አስገኝቷል።

እነሆ እኛም ፈጣሪ አምላካችንን በድለናል፣ በእናቱ ሆድ ያለን ሕጻን በውርጃ ገድለናል።ለጣኦት አማንዝረናል፣በፈጣሪ ስም በውሸት ምለናል። በማታለል በልጽገናል።ሰዎችን በብሔር፣በቋንቋ በእምነት ከፋፍለን አድሎ ፈጽመናል። አስረን በመግረፍና በመግደል አሰቃይተናል።ከባለ ጉዳይ ጉቦ በመቀበል አድሎ ፈጽመናል።የገበሬውን ሀብትና ንብረቱን ዘርፈናል።በዚህም ሕፃናትን ያለ አሳዳጊ፣አረጋዊያንን ያለጧሪ በማስቀረት ፈጣሪ አምላካችንን በድለናል።

በመሆኑም ተምችና ኩኩባ ተልኮብናል። ጎርፍ፣ድርቅና በሽታውም የቁጣው ምልክቶች ናቸው።ይህም እንደሚሆን ቀድሞ በነቢያት ተነግሯል። በቅዱሳት መጻሕፍትም ተጽፏል።ስለዚህም ነበር ቤተ ክርስቲያንና መስጊድም ሳይቀሩ በኮቪድ የተዘጉት።ሕዝባችን በጦርነት ተማግዶ፣ ከመኖሪያ ቄዬው ተፈነቃቅሎ ለረሐብና ለቸነፈር የተጋለጠው።

ሐቁ ይህ ከሆነ ለምንድ ነው፣በንሰሓ የማንመለሰው? በማን ላይ ነው ደረታችንን ይምናሳብጠው?ለምንድን ነው ለገላጋይ የምናስችግረው? በእርዳታ እህል ላይ በር ዘግተን ወገኖቻችንን በረሃብ የምናማቅቀው። ሰባት ዕጥፍ የበቀል ቅጣት፣ወይስ የሰባ አመት ስድትን ነው የምንሻው?

ፈጣሪ አምላካችን እንደሆን የተሰወረን ሁሉ ገልጦ የሚያይ፣ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው የሚክፈል እውነተኛ ዳኛ ነው። በመሆኑም

በውሸት ራሳችንን ማታለሉን ትተን፣ስለ ጽድቃችን ሳይሆን ስለ ቅዱስ ልጁ ስሙ ብሎ ይቅር እንዲለን፣ ሁላችንም ከተጨማር በደል ታቅበን፣ በንጹህ ልቦና፣ ራሳችንን እፊቱ እናዋርድ።

በዚህ ረገድ የበደልነው ፈጣሪ አምላካችንን ብቻ አይደለም፣ሰውንም በድለናል። ፈጣሪ አምላካችን ይቅር እንዲለን፣ እኛም እርስ በርስ ይቅር ልንባባል። ስለሆነም በቅድሚያ የእምነት አባቶች እርስ በርስ ይቅር በመባባል በምሳሌነታቸው ሊያስተምሩን ይገባል።ከዚያም ሊገስጹን፣ ተቆጥተው ሊያስታርቁን ተሰጥተውናል።

የእግዚአብሔር አምላክ ፈቃድ እርሱ ፈጥሮ በሰጠን መሬት፣ አማራ ትግሬ ሱማሌ አፋር ሳንባባል ሁላችንም እርስ በርስ በመከባበር፣ተስማምተን በፍቅሩ እንድንኖር ነው።በትዕቢት ዓይናችንን ጋርዶ ደም እያፋሰስ ሰላም እየነሳን ያለው፣ የዘር ጠላታችን የሆነው ዲያብሎስ ነው። በመሆኑም የእግዚአብሔር መንፈስ በፈቅሩ ሞልቶ ሰላሙንና በረከቱን በመፍሰስ በጸጋው እንዲሸፍንን ያለማቋረጥ እንማጸነው።እርሱ ቸር ነውና ስለ ቅዱስ ልጁ ስሙ ሲል ያደርገዋል፣አሜን!

ጆቢር ሔይኢ ከሁስተን ቴክሳስ፣

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.