የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ከጋና አቻው ጋር የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል

241340829 3018050295104096 7866609971674758464 n

ነሃሴ 28፤2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ኳታር ለምታስናግደው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የምድብ የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከጋና አቻው ጋር ያደርጋል።
እ.አ.አ በ2022 በኳታር አስተናጋጅነት የሚካሄደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የሚደረገው የአፍሪካ (ካፍ) ዞን የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከትናንት በስቲያ ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ የወንዶች ብሔራዊ ቡድን በምድብ ሰባት ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካና ዚምባቡዌ ጋር መደልደሉ ይታወቃል።
ለምድብ ማጣሪያው የደረሰው ከሁለት ዓመት በፊት ሌሴቶን በደርሶ መልስ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ጥሎ በማለፍ ነው።
በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመሩት ዋልያዎቹ ዛሬ ከምሽቱ 4 ሰዓት በኬፕ ኮስት ስፖርትስ ስታዲየም 15 ሺህ ተመልካች በተገኘበት ከጋና ብሔራዊ ቡድን ጋር ይጫወታሉ።
ብሔራዊ ቡድኑ በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ከነሐሴ 4 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በአዳማ አበበ በቂላ ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ዋልያዎቹ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ባደረጓቸው ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ያደረጉ ሲሆን ከሴራሊዮን አቻው ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ ሲወጣ የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድንን 2 ለ 1 አሸንፏል።
ብሔራዊ ቡድኑ በኢትዮጵያ ያደረገውን ዝግጅት አጠናቆ ነሐሴ 24 ቀን 2013 ዓ.ም 23 ተጫዋቾችን ይዞ ወደ አክራ ማቅናቱ የሚታወስ ነው።
በቀድሞው የጋና ብሔራዊ ቡድን የአማካይ ተጫዋች ቻርልስ አኮኖር የሚመሩት ጥቋቁሮቹ ኮከቦች ለዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታው ልምምድ ማድረግ የጀመሩት ነሐሴ 25 ቀን 2013 ዓ.ም ነው።
የጋና ብሔራዊ ቡድን ከኢትዮጵያና በቀጣይ ከደቡብ አፍሪካ ለሚያደርገው ጨዋዎች 32 ተጫዋቾችን ጠርቷል።
ጥቋቁሮቹ ክዋክብቶች በሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም ባደረጓቸው የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ከኮትዲቭዋር ጋር ባደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ ሲለያዩ በሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን 1 ለ 0 ተሸንፈዋል።
የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ባደረጋቸው ያለፉ አምስት ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
በአንጻሩ የጋና ብሔራዊ ቡድን ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ያሸነፈው አንድ ጊዜ ሲሆን ሁለት ጊዜ ተሸንፎ ሁለት ጊዜ አቻ መውጣቱ ቁጥራዊ መረጃዎች ያሳያሉ።
የኢትዮጵያና የጋና ብሔራዊ ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ ጨዋታቸውን ያደረጉት እ.አ.አ በ2017 ሲሆን፤ በግብጽ አስተናጋጅነት እ.አ.አ በ2019 በተካሄደው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በተደረገው የደርሶ መልስ የማጣሪያ ጨዋታ ጥቋቁሮቹ ኮከቦች 2 ለ 0 እና 5 ለ 0 ማሸነፋቸው የሚታወስ ነው።
ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች እስካሁን እርስ በእርስ ባደረጓቸው ሶስት ጨዋታዎች የጋና ብሔራዊ ቡድን ሶስቱንም በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል።
ኢትዮጵያ በፊፋ ወርሃዊ የአገራት ደረጃ 137ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን ጋና 52ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ዛሬ በኬፕ ኮስት ስፖርትስ ስታዲየም የሚደረገው ጨዋታ የሞሮኮው ጂዬድ ሬድዋኔ በመሐል ዳኝነት የሚመሩት ሲሆን ረዳት ዳኞች በተመሳሳይ ከሞሮኮ ናቸው፤ጋምቢያዊው ጎሜዝ ማርቲን የጨዋታው ኮሚሽነር ሆነው ተመድበዋል።
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) በኮቪድ-19 ወረርኝኝ በማስመልክት ባወጧቸው መመሪያዎች አማካኝነት ባሳለፉት ውሳኔ መሰረት ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በሚያደርጉት ጨዋታ 2 ሺህ 250 የጋና ደጋፊዎች ጨዋታው ስታዲየም በመግባት ይመለከታሉ።
ዋልያዎቹ በሚገኙበት ምድብ ሰባት ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ዚምባቡዌ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ይጫወታሉ።
የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ቀጣይ የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታውን ጳጉሜን 2 ቀን 2013 ዓ.ም በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከዚምባቡዌ አቻው ጋር የሚጫወት ሲሆን፤የጋና ብሔራዊ ቡድን ቀጣይ ጨዋታውን ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም ከደቡብ አፍሪካ ጋር ያደርጋል።
በ10 ምድብ ተከፍሎ የሚካሄደው የአፍሪካ(የካፍ) ዞን የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ከየምድቡ አንደኛ ሆነው የሚያልፉ 10 አገራት በሚወጣላቸው እጣ መሰረት እርስ በእርስ በሚያደርጉት የደርሶ መልስ ጨዋታ በአጠቃላይ ድምር ውጤት የሚያሸንፉ አምስት አገራት ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ ያልፋሉ።
የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን እ.አ.አ በ2014 በብራዚል አስተናጋጅነት ለተካሄደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በአፍሪካ ዞን ማጣሪያ የመጨረሻው ዙር ቢደርስም በናይጄሪያ አቻው በድምር ውጤት 4 ለ 1 ተሸንፎ ለዓለም ዋንጫው ማለፍ ሳይችል መቅረቱ የሚታወስ ነው።
እ.አ.አ በ2022 በሚካሄደው በኳታር አስተናጋጅነት በሚካሄደው 22ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ 32 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ።
EBC
ተጨማሪ ያንብቡ:  Barcelona edges out Manchester United as highest earning team from the 2010-11 Champions League

1 Comment

  1. ጫወታውን አየሁት። ያው እንደተለመደው ኳስ አሳልፎ መስጠት ዛሬም አልተለመደም። ሁሌ ያለ ጉልበትና ቴክኒካዊ ችሎታ ኳስን ያለ ልክ በተናጠል ተጫዋች እግር ሥር ማንከባለል ተላላፊ በሽታ ሆኗል። በተረፈ ከተከላካይ መስመር መሳሳትና ከበረኛው እንቅልፋምነት ባሻገር የጋናው ጫወታ መልካም ነበር። እንኳን እንደ ጅቡቲ 8 ለባዶ አልተሸነፉ።
    ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ለሚኖራቸው ቀጣይ ጫወታ ፈጣን አጥቂዎችንና እይታ ሰፊ የሆኑ የማህል ተጫዋቾች ኳስ አስተላላፊዎችን ከነቃ በረኛ ጋር ካሰለፉ ድል ሊቀናቸው ይችል ይሆናል። በተረፈ ያው እንደተለመደው ሌላ አራት ዓመት ጠብቆ ማየት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share