የአገር እንድነት እንዲከበር ሰው አይበደል – ጆቢር ሔይኢ ከሁስተን ቴክሳስ

08/20/2021

ከርዕሳችን በደል  የሚለውን ቃል ወስደን ትርጉሙን ብንመለከት፣ ጥፋት ወይም ኃጢአት  የሚል ሆኖ እናገኘዋለን።ብዙ ጊዜ በሰው ላይ በዕውቀትና በድፍረት የሚደረገውን  በደል ያመለክታል። የእስራኤል ሕዝብ የነቢያትን ቃል ባለመስማቱ፣  ለሰባ አመት በስደት በማቀቀ ጊዜ። ዳንኤል  በጌታ በአምላኩ ፊት ወድቆ እንዲህ ሲል ጸለየ፣ “ከሚወዱህና ትእዛዝህን ከሚፈጽሙ ሁሉ ጋር የፍቅር ቃል ኪዳንህን የምትጠብቅ፣ታላቅና የተፈራህ አምላክ ጌታ ሆይ፤እኛ ኀጢአት ሠርተናል፣ በድለናልም፣ክፋትን አድርገናል፣ ዐምፀናልም፣ከትእዛዝህና ከሕግህ ዘወር ብለናል።

ለንጉሦቻችን፣ ለልዑሎቻችንና  ለአባቶቻችን እንዲሁም ለምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ በአንተ ስም የተናገሩትን አገልጋዮችህን ነቢያትን አልሰማንም። “አሁንም አምላካችን ሆይ፣የአገልጋዮችህን ጸሎትና ልመና ስማ።ጌታ ሆይ ስለ ስምህ ስትል ፊትህን ወደ ፈረሰው መቅደስ መልስ።”አምላክ ሆይ፣ጆሮህን አዘንብልህ ስማ፣ዐይንህን ገልጠህ መጥፋታችንንና ስምህ የተጠራበትን ከተማ ተመልከት፡፡

ልመናችንን የምናቀርበው ስለ ጽድቃችን ሳይሆን፣ስለ ታላቅ ምሕረትህ ነው። ጌታ ሆይ፣ አድምጥ!ጌታ ሆይ፣ይቅር በል! ጌታ ሆይ፣ስማ! አድርግም፣ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቶአልና አምላኬ ሆይ፣ ስለ ስምህ ስትል አትዘግይ” በማለት ተማጽኖ ነበር።

እኛስ፣ ፈጣሪ አምላካችንን አልበደልንምን? በእናቱ ሆድ ያለን ሕጻን በውርጃ አልገደልንም? ጣኦት በማምለክ አላመነዘርንምን?   ለሥልጣን ስንል  ወንድሞቻችንን አልገደልንምን፣ አስረን  አልገረፍንምን? በጉቦና በምልጃ የሌላውን ሰው ሀብትና ንብረት አልዘርፍንምን? ይህ ትናንት የነበረ ዛሬም ያለ የወል ታሪካችን ነው።እኛ ብንክድ ጌታ ለማንም አያዳላምና እርሱ ይመሠክርብናል። አላስተዋልነው ይሆናል እንጂ፣ ተምቹ፣ጎርፉ፣ድርቁ በሽታው የቁጣው ምልክቶች ናቸው።ለዚህም ነበር ቤተ ክርስቲያንንም መስጊድንም  ከፊቱ  የዘጋው።

ለመሆኑ እኛ ማን ነን? ፈጣሪ አምላክ በመልኩና በአምሳሉ ፈጥሮ፣መንፈሱን እፍ ብሎበት ሕያው ያደረገውን ሰው  የምናስገድለው፣ ቃየን ወንድሙን አቤልን በገደለው ጊዜ፣ እግዚአብሔር አምላክ ቃየንን አለው፣ “የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። እንግዲህ የተረገምህ ነህ፣የወንድምህን ደም  ከእጅህ ለመቀበል አፏን በከፈተች መሬት ትሰደዳለህ፣  ብታርሳትም ፍሬዋን አትለግስህም፣በምድር ላይ ኮብላይና ተንከራታች ትሆናለህ”አለው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የ​ህወሓት የበላይነት እና የዓረና ውስልትና | ስዩም ተሾመ

ቃየንም እግዚአብሔርን፣”ቅጣቴ ልሸከመው ከምችለው በላይ ነው፣እነሆ ዛሬ ከምድሪቱ አባረርኸኝ፣ከፊትህም እሸሸጋለሁ፣በምድር ላይ ኮብላይና ተንክራታች እሆናለሁ፣የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል” አለው።

በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር  “እንደዚህ አይሆንም፣ማንም ቃየንን ቢገድል፣ ሰባት ዕጥፍ  የበቀል ቅጣት ይቀበላል “አለ። እኛም ከዚህ ከጌታ ቃል አንጻር ያለፈውን ታሪካችንና ተግባራችንን ብንመርምር፣ሰባት ዕጥፍ የበቀል ቅጣት እየተቀበልን ነው ያለነው።

ይሁን እንጂ ሥልጣን የሕዝብ፣ መሬት ማንም በልቶ የማይጨርሳት  የተፈጥሮ ሀብት መሆኗ ከገባን፣ ለምንድን ነው ለጦርነት እሳት የምንማገደው? በተለይ ደግም፣ ይህ ተግባራችን  ፈጣሪ አምላካችንን የማያስደስት ከሆነ፣ለምንድን ነው ለገላጋይ የምናስችግረው? ሰባት ዕጥፍ የበቀል ቅጣት ለልጆቻችን ለማውረስ  ይሆንን?

ጌታ የተሰወረን ገልጦ የሚያይ፣ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው  የሚክፈል እውነተኛ ዳኛ ነው። በመሆኑም በውሸት ራሳችንን መካብ ትተን፣ እንደ ዳንኤል፣ስለ ጽድቃችን ሳይሆን ስለ ታላቅ  ስሙ ብሎ ይቅር እንዲለን፣ ሁላችንም  ከበደላችን በመታቀብ፣ እፊቱ ራሳችንን ማዋረድ ይገባናል።

በዚህ ረገድ  የበደልነው ፈጣሪ አምላካችንን ብቻ አይደለም፣ሰውንም በድለናል። ፈጣሪ አምላካችን ይቅር እንዲለን፣ እኛም እርስ በርስ ይቅር ልንባባል ይገባናል። ስለሆነም በቅድሚያ የእምነት አባቶች  እርስ በርስ ይቅር በመባባል በምሳሌነታቸው ሊያስተምሩን ይገባል።ከዚያም ሊገስጹን፣ ተቆጥተው ሊያስታርቁን በእግዚአብሔር ተሰጥተውናል።ኢትዮጵያ አንድ የምትሆነው እኛ ልጆቿ ተስማምተንና ተከባብረን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በፍቅር ስንኖር ብቻ ነው።ፍቅር ባለበት ሁሉ እግዚአብሔርም ይኖራልና።

ጆቢር ሔይኢ ከሁስተን ቴክሳስ፣

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.