ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓም(23-06-2025)
ታሪክ እንደሚመሰክረው የሰው ልጅ ሲፈጠር በነበረው የንቃተ ህሊና ደረጃ ምንም አይነት ሃይማኖት ሳይኖረው ሆዱን ብቻ እዬሞላ የሚኖር እንስሳ እንደነበር ጥናቶች ያሳያሉ። ከጊዜ በዃላ ባደረገው አካላዊና ህሊናዊ ለውጥ ከባቢውን የማወቅ ችሎታ ላይ ሲደርስ ስለአፈጣጠሩ ለመመራመር በቃ።የፈጠረው ሃይል እንዳለ በስነልቦናው ተገነዘበ።ፈጣሪውን ለማወቅ ግራ የተጋባው የሰው ልጅ ከእሱ የበለጡትን ግዙፍ ነገራት ሁሉ ማምለክ ጀመረ።በወንዝ፣ በዛፍ፣ በተራራ፣በጸሃይ በጨረቃና በከዋክብት ማምለክና ለእነሱም ይገባል ያለውን ግብር ወይም መስዋእት በማበርከት ምልክት የሚሆናቸውንም ጣኦት ሠራ።እስከአሁን ኢትዮጵያ በተባለችው መሬት ላይ የኖረው የሰው ልጅ ከዚህ የአምልኮት ደረጃ ላለመለዬቱ አሁንም ድረስ የሚካሄዱ የእምነት በዓላትና የሚደረጉ መስዋእቶች ማስረጃዎች ናቸው። የሰው ልጅ አስተሳሰቡ ሲለወጥ የእምነቱም መልክና ይዘት አብሮ ተለወጠ።ከህብረተሰቡ መሃል የማሰብና የማፍለቅ አቅም ያላቸው ግለሰቦች አዳዲስ የእምነት ፍልስፍና ለማዳበር ችለው ተከታይ አፈሩ።ከነዚያም ውስጥ የቡድሃ፣ሂንዱና የአይሁድ እምነቶች ቀዳሚዎች ናቸው።በጥንታዊት ኢትዮጵያ የሚኖረውም የሰው ልጅ እንደ ሌላው ከባቢ ነዋሪ ሕዝብ ይሆናል ብሎ በገመተው አምልኮ ስርዓት አልፏል። ከውጭ የመጡትንም እምነቶች ተቀብሎ አስተናግዷል።ከሦስት ሽህ ዓመት በፊት ቀድሞ የገባው ከንግሥት ሳባ የዬሩሳሌም ጉዞ ታሪክ ጋር የተያያዘ የአይሁድ ሃይማኖት መሆኑ በታሪክ ተመዝግቧል።ንግስት ሳባ ወደ አገሯ ስትመለስ ከንጉሥ ሰለሞን ተሰጣት የተባለውን የእምነቱን መመሪያ የሆነውን የሙሴ ጽላት(ታቦት) ተሸክመው በመጡት (በፈለሱት)በዃላም ላይ ፈላሻ የሚል ስያሜ ባገኙት አጃቢዎቿ በኩል የተስፋፋ መሆኑ አይካድም። ይህ እምነት ግን በሰሜኑ ክፍል በተወሰነ አካባቢ እንጂ በሌላው ያገሪቱ ክፍል አልተስፋፋም። የእምነቱ መኖር ከሦስት ሽህ ዓመት በዃላ ኢትዮጵያውያኑን የእስራኤል ዜጋ ናቸው በሚል ሰበብ ካገራቸው እንዲወጡ ያደረገ ሲሆን በእስራኤል ጦር ክፍል ውስጥ በመግባት እዬገደሉና እዬሞቱ ይገኛሉ።እንደ እውነቱ ከሆነ እምነትና ዜግነት አንድ አይደለም።የአይሁድ እምነት የሚከተል ሁሉ የእስራኤል ዜጋ ነው አይባልም።ክርስቲያኑ የዬሩሳሌም ዜጋ እስላሙም የሳውዲ ዜጋ እንደማይሆን ሁሉ።የቻይና ካቶሊክም ጣሊያናዊ እንደማይሆነው ሁሉ።የሚያሰጋው ነገር ቢኖር በኢትዮጵያ ውስጥ የሰፈነው ጎሳ ተኮር አገዛዝ አገሪቱን ለመበታተን ከዳረገ ነገ እስራኤል ላላት የመስፋፋት እቅድ የቀሩትን ፈላሻዎች ለመጠበቅና ለማዳን በሚል ሰበብ ዘው ብላ ገብታ የድርሻዋን ከመውሰድ እንደማትመለስ በፍልስጤማውያን አይተነዋል። በኢትዮጵያ በተለይም በወልቃይትና በሐረር ለመስፈር ከ80 ዓመት በፊት በአሜሪካኖችና በእንግሊዞች በኩል ለንጉሥ ሃይለሥላሴ መንግሥት የቀረበው ጥያቄ ውድቅ በመሆኑ እንጂ ቢፈቀድላቸው ኖሮ አሁን በጋዛ የሚካሄደው እልቂት በኢትዮጵያ ውስጥ ይሆን ነበር።ምስጋና ለነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ይሁን!
የአይሁድ ሃይማኖት ከሚስተናገድበት ቦታ ውጭ በሌላው የኢትዮጵያ መሬት የሚኖረው ሕዝብ ከአምልኮት ያለፈ በፍልስፍና የዳበረ እምነት አልነበረውም።ከጊዜ በዃላ የአይሁድን እምነት ተከትሎ በዚያው የፍልስጤም መሬት የተፈጠሩት የክርስትናና የእስልምና እምነቶች ከአንድ ቦታ ተነስተው ከባቢውንና ሌላውንም እሩቅ አካባቢ እያጥለቀለቁት መጡ።ኢትዮጵያም የነዚሁ ሃይማኖቶች ተከታይ ለማፍራት በቃች።በአይሁድ እምነት ላይ የክርስትናን በዛም ላይ የእስልምናን እምነቶች ደራርባ ያዘች።እነዚህ እምነቶች ከተነሱበት አካባቢ ባላት ቅርበት ሁሉንም ለማስተናገድ ችላለች።እንደመሪዎቹ ፍላጎትና ፈቃድ ሃይማኖቶቹ ሊስፋፉ ቻሉ።የማይካደው ነገር አይሁድም ሆነ ክርስትና እንዲሁም ኢስላም ሃይማኖቶች ከውጭ የመጡ መሆናቸው ነው።
የዚህ ጽሑፍ መነሻና ዓላማ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ሃይማኖቶች ታሪክ ለመተንተን አይደለም።የአይሁድም ይሁን የክርስትና ሃይማኖቶችን አመጣጥ ብሎም መስፋፋት ከበቂ በላይ ማስረጃና በግብርም የሚታይ ታሪክ ስላለ ወደ ዝርዝሩ አላመራም።የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ከእምነቶቹ ጋር የተያያዘ ብዙ የማይጣጣሙ ትርክቶች፣ማለትም አንዱን ጠቃሚ ሌላውን ጎጂ፣አንዱን ትክክል ሌላውን ስህተት፣አንዱን ሰላማው ሌላውን ጸረ ሰላም አድርጎ የማቅረብና የመሳል ድክመቶች ስለሚስተዋሉ፣የውጭ ሃይሎችም እነዚያን ተገን አድርገው ለመግባትና ፍላጎታቸውን ለማሟላት ኢትዮጵያውያኑን የመከፋፈልና የማጋጨት መሳሪያ ለማድረግ ስለሚጥሩ አደጋውም ስለሚያንዣብብ ከወዲሁ ነቅቶ ለመጠበቅ ይረዳል በማለት ነው።አቅም ስላላቸው በተለይም ለዚህ የተጋለጠው የእስልምና ሃይማኖት መሆኑን በማመን በኢትዮጵያ እንዴት እንደተስፋፋና ከክርስትና እምነት ጋር እንዴት ሰምና ወርቅ ሆኖ እንደኖረ በጥቂቱም ቢሆን ለማሳዬት ስለሆነ ወደዚያው አመራለሁ፣ይህ ማለት ግን ሌሎቹ አይመለከቱኝም ማለት ሳይሆን በክርስቲያኑ በኩል በእስልምና ሃይማኖት ላይ፣በሙስሊሙም በኩል በክርስትና ላይ ግልጽ ያልሆኑና አፍራሽ ጉዳዮች ስለሚታዩኝ ነው።ትክክልም ስህተትም ሊሆን ይችላል ግን ጉዳዩ መነሳቱ ሊመጣ ከሚችለው አደጋ ለመከላከልና ትክክለኛ ግንዛቤ ለመያዝ መንደ ርደሪያ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ። ከእስልምና በፊት በአይሁድና በክርስትና እምነቶች ዙሪያ ከበቂ በላይ ጽሑፎችና መረጃዎች ስላሉ ወደዚያ መግባቱን አልመረጥኩም።ይህ ማለት ግን ለእምነቶቹ እውቅናና ክብር የለኝም ማለት አይደለም።የሁሉም ሃይማኖት አስተምሮ ለሰው ልጆች ሰላም፣ፍቅርና እኩልነት ሆኖ በተግባርም እስከገለጹት ድረስ አከብራቸዋለሁ።የምቃወመው ቢኖር በእምነት ስም ሕዝብን ከፋፍሎ የንጹሃን ደም ማፋሰሱንና ወረራ ማካሄዱን ነው።የሰዎችን የመምረጥ መብትን መጋፋቱን ነው። ሃይማኖት የአምባገነኖችና የወራሪዎች ብሎም የዘራፊዎች ካባ መሆኑን ነው።ከላይ ከፍ ብሎ እንደገለጽኩት በተወሰነው የታሪክ ጉዞ የአይሁድ እምነት እንዴት እንደገባ በጥቂቱም ቢሆን ለማሳዬት ሞክሬያለሁ።
የክርስትና እምነትም በአራተኛው ክፍለዘመን ኤዛና በተባለው የአክሱም ንጉሥ ዘመን ፍሬምናጦስ በተባለው የሶሪያ መነኩሴና ነጋዴ በኩል እንደተስፋፋ በኽላም የንጉሡ አማካሪ በመሆን እንዳገለገለ ታሪክ መዝግቧል።በዚህም አልቆመም በግብጽ አሌክሳንደሪያው ኮፕቲክ ተቋም ሹመት ተሰጥቶት የመጀመሪያው ጳጳስ ለመሆን በቅቷል። ፍሬምናጦስ በአካባቢው አጠራር አባ ሰላማ በመባል የሚታወቅ ሲሆን የሱን ፈለግ ተከትለው ሌሎችም መነኮሳት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የክርስትናን ሃይማኖት አስፋፍተዋል።ከሃይማኖቱ ጎን ለጎን ስለ መንግሥቱ ደግነት በመስበክ ሕዝቡ እንዲቀበለውና እንዲያከብረው ያደርጉ ነበር።መንግሥትም ለደህንነታቸው ጥበቃና ዋስትና ይሰጣቸው ነበር።ወገቤን እከክልኝ ወገብህን አክልሃለሁ እንደማለት! ፖለቲካና ሃይማኖት በጋራ መቆማቸው ይህ ማሳያ ነው።
ወደ እስልምና ስገባ መጀመሪያ የእምነቱ መስራች የሆነውን የሙሃመድን ታሪክ ማንሳቱ ተገቢ ይሆናል።
ስለ “ነብዩ”ሙሃመድ ትውልድና አነሳስ እንዲሁም ከአገራችን ኢትዮጵያ ጋር የነበረውን ግንኙነት ካገኘሁት መጻጽፍ ውስጥ በመውሰድ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ።
የሙሃመድ አባት አብዱላህ፣እናቱ አሚና ይባላሉ፤አባቱ ከመወለዱ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሞት የተለዩ ሲሆን አይተዋወቁም።ሙሃመድ መካ በሚባለው ከተማ ተወለደ።በህብረተሰቡ ልማድ መሰረት አንድ ወንድ ልጅ ሲወለድ በሞግዚት እጅ ማደግ ስለነበረበት እናቱ የባኑ ሳድ ጎሳ ተወላጅ ለሆነችው ለሃሊማ ሳዲያ ለምትባለው አሳልፋ ሰጠችው።ሃሊማ አምስት ዓመት እስኪሞላው ድረስ ተንከባክባ ካሳደገችው በዃላ ለእናቱ መለሰችላት።ህጻኑ ሞሃመድ የስድስት ዓመት ዕድሜ እንዳለ ከናቱ ጋር ወደ መዲና ሄዶ ሲመለሱ በመንገድ ላይ፣ አብዋ ከተባለው ቦታ(መንደር)እናቱ በድንገት አረፈች።ከዚያ በዃላ ኩራሽ የተባለው ጎሳ መሪ የሆነው አያቱ አብድ አል ሙታሊብ ለማሳደግ ወሰደው።አያቱም ከሁለት ዓመት በዃላ አረፈ።ያልታደለው ሞሃመድ እንደገና በሌላው አጎቱ በአቡ ታሊብ ተወሰደ።አጎቱ አቡ ታሊብና የአጎቱ ሚስት ፋጡማ እንደራሳቸው ልጅ በፍቅር ዓይን እያዩ ተንከባከቡት።አጎቱ ለንግድ በሚሰማራበት ቦታ ሁሉ ወጣቱ ሙሃመድን ይዞት ይሄድ ነበር።በዚህም ስለንግድ በቂ ልምድ ሊቀስም ቻለ።ከንግዱ ባሻገር በንግግር ችሎታውና የሌሎቹን ጥቅም በማስከበር ረገድ በሚያደርገው ጥረት በሌሎቹ ነጋዴዎች እውቅናና መከበርን ለማግኘት ቻለ።ከልጅነቱ ጀምሮ ሃቀኛና መልካም ምግባር ያለው በመሆኑ ሁሉም ያከብረው ጀመር፤በሃቀኝነቱም “ሳድቅ”ወይም “አል አሜን”(እውነተኛው) የሚል ቅጽል ስም አወጡለት።
በሃያ አምስት ዓመቱ በጣም የተሳካለት ቀልጣፋ ነጋዴ ወጣው።በዚህ ችሎታው የተደነቀችው ከድጃ የተባለችው የአርባ ዓመቷ ከበርቴ የሷንም የንግድ ስራ ወጣቱ ሙሃመድ እንዲያካሂድላት ከማድረግም አልፋ በጋብቻ ሰንሰለት ለማሰር በመፈለግ እንዲያገባት በቅርብ ወዳጆቿ በኩል ሙሃመድን አስጠይቃ ፈቃደኛ በመሆኑ እንደ አገሩ ደንብና ባህል የሃያ ግመሎች ጥሎሽ ጥሎ አገባት።ከድጃ ከሙሃመድ በፊት ሁለት ጊዜ አግብታ የነበረች ሴት ናት።
ከሙሃመድ ጋር ተጋብተው አራት ሴቶችና ሁለት ወንዶች በጠቅላላው ስድስት ልጆች የወለዱ ሲሆን ፣የመጀመሪያው ልጃቸው ቃሲም በሁለት ዓመቱ አረፈ፤ሁለተኛ ልጁም አብዱላህ በህጻንነቱ ሞተ።አብዱላህ አባቱ ሙሃመድ “ነብይ”ከሆነ በዃላ በመወለዱ “ታያብ”እና “ታሂር”በመባል ይጠራ ነበር።ሴት ልጆቹ ዛይነብ፣ሩቅያ፣ኡምኩልቱምና ፋጢማ ይባላሉ።
የከባቢው ነጋዴዎች በያገሩ ለንግድ ሄደው ሲመለሱ፣ለጣኦት ምስጋናና ስለት ያቀርቡ ነበር።ይህ የስለት ቦታ ካባ የሚባለው በአይሁድ እምነት አባት በሆነው በአብርሃም የተመሰረተ የጸሎት ቦታ ነበር።አብርሃም የተቀበለው የአምላክ መልእክት የሰፈረበት ጽላት በአላማኞች ወድሞና ጠፍቶ በምትኩ በልዩ ልዩ 360 የጣኦት ምስሎች ተተክቶ ነበር። ጥቂት ሴቶችና ወንዶች የአብርሃም ትምህርትና እምነት ተከታዮች ብቻ በእምነታቸው ጸንተው ቀሩ። ይህን የጣኦት ማምለክና የስለት አቅርቦት ሙሃመድ ባለመቀበሉ ብሎም ባለስልጣኖቹ በድሃው ላይ የሚያደርሱትን በደል በመቃወምና በነጋዴዎች ላይ የተጣለውን ቀረጥና ግብር ለመክፈል ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ደሃውንና ነጋዴውን አስተባብሮ በስርዓቱ ላይ ተነሳ።ስርዓቱ የፈንጋዮች ስርዓት ስለነበር በባርነት መከራ የሚገፉትን ነጻ ለማውጣት በወሰደው እርምጃ የብዙዎችን ድጋፍ ለማግኘት ቻለ። በአይሁዶችና በክርስቲያኖች ብቻም ሳይሆን በራሱ ጎሳዎች በኩልም ትልቅ ተጽእኖ ደረሰበት።በሱና በቤተሰቡ ፣እንዲሁም በተከታዮቹ ላይ ብዙ መከራ ቢደርስም ከተጨማሪ ጥቃት ለማምለጥ ከተማ ለቀው ኮረብታማ በሆነው ቦታ ላይ ለመኖርና ለትግል መደራጀት ጀመሩ። የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት ለመከላከል የተገደዱት የሙሃመድ ተከታዮች ከተራራ እየወረዱ አጥቅቶ የመሰወር የሽምቅ ውጊያ ስልትን አዳበሩ።በዚህም መዲና የተባለችውን ከተማ በማከታተል አጥቅተው በመጨረሻው ላይ ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ችለዋል።
ነገስታትና ሃይለኞች ሲነሱ አነሳሳቸውን ከፈጣሪ ፈቃድና ትእዛዝ ጋር በማያያዝ ተከታይ እንዲኖራቸው ማድረግ የተለመደ ነበር።ሙሃመድም በሕልሙ በገብርኤል(ጅብሪል)በኩል ፈጣሪ እንዳነጋገረው የሚከተለው ታሪክ ያስረዳል።
የአርባ ዓመት ጎልማሳ ሆኖ በሂራ በሚባለው ኮረብታ ላይ ሲኖር መላከ ገብርዔል(ጅብሪል) ተገልጾለት የአምላክን ትእዛዝ አበሰረለት።መልእክቱንም እንዲያነብና እንዲደግም መልአከ ገብርኤል ጠየቀው፤ሙሃመድ ግን መጻፍና ማንበብ እንደማይችል መለሰ። ገብርኤል በፈጣሪ ሃይል የተነገረውን ሁሉ ሳያዛባ በቃሉ እንዲደግመው አደረገው።በዚህ የፈጣሪና የመልአኩ ገብርኤል ተአምር የተደናገጠው ሙሃመድ እየተርበደበደ እቤቱ በመግባት ለሚስቱ ነገራት።እሷም “እንደ አንተ ያለውን ደግና እውነተኛን ሰው አምላክ አይቀጣውም፤ አትፍራ! በማለት አጽናንታው የነብያትን ታሪክ በሚገባ የሚያውቀው ወረቃ ከሚባለው አጎቷ ጋር በመሄድ ሚስጥሩን አጫወተችው።ወረቃም ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው ነብይ እሱ ነው ብሎ ስለገለጸላት የመጀመሪያዋ አማኝ ሆነች።ከሷም ጋር ነጻ ያወጣው ባርያው ዘይድ ኢብን ሃሪታ፣አጎቱ አሊ ኢብን አቢ ታሊብና የአጎቱ ልጅ አቡበከር የመጀመሪያ የእስልምና ሃይማኖት በመቀበል የሙሃመድ ተከታዮች ሆኑ።
ይህን አዲስ መጥ የሙሃመድን ትምህርትና የእስላም ሃይማኖት የሚቃወሙት አረቦች፣አይሁዶችና ክርስቲያኖ ብቻ ሳይሆኑ ቁራኢሽ የተባሉትም ጎሳዎች የሙሃመድ ጸሮች በመሆን ያሳድዷቸው ነበር።ከሶስት ዓመት ግጭትና ጥቃት በዃላ እርቅ ወረደ።ይህ በእንዲህ እያለ የሙሃመድ ሚስት የነበረችውም ከድጃ በ65 ዓመቷ አረፈች። አላህ አንድ ነው፣ አይወልድም አይወለድም !ሙሃመድ መልእክተኛው ነው! የሚለው የመልአኩ ገብርኤል መልእክትና የሙሃመድ መመሪያ በዘንባባ ቅጠል፣በዛፍ ልጫና በከብት አጥንት ላይ እየተጻፈ ይሰራጭ ጀመር። ቃል በቃል ይተላለፍ የነበረው የሙሃመድ ትምህርትና የእስልምና መመሪያና ሕግ ሆኖ ፡ከጊዜ በዃላ በጽሁፍ ተጠራቅሞ በቁርዓን መልክ ለመቅረብ ቻለ።
እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው ነገር ቢኖር የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ለጸሎት ወደ መካ መዲና በሄዱ ጊዜ ካእባ በሚባለው ትልቅ ጥቁር ክብ(ቋጥኝ) ላይ የሚወረውሩት ድንጋይ የሚያሳየው ሙሃመድ በካእባ ውስጥ ይጠራቀሙ የነበሩት ጣኦቶች ፣የሰይጣን አምልኮ ናቸው በማለቱ ሰይጣኑን ለማባረርና ለማውገዝ የሚደረግ ሙከራ መሆኑን ነው።
የነብዩ ሞሃመድና የኢትዮጵያ ግንኙነት
የሙሃመድ ተከታዮች በኩራሽ ጎሳና የመካ ሹማምንትና ባለስልጣኖች ሲጠቁ ሙሃመድ ጥቂት ተከታዮቹን ያላችሁ ምርጫ ህይወታችሁንና ሃይማኖታችሁን ማትረፍ ነውና ፍትሕና ሩትህ ያለው የክርስቲያን ንጉሥ ወዳለባት አገር ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ ፣በዛም በሰላም ሃይማኖታችሁ ሳይደፈር ልትኖሩ ትችላላችሁ ብሎ አዘዛቸው።ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱት በሁለት ቡድን ሲሆን የመጀመሪያውን ማለትም አስራ ሁለት ወንዶችና አራት ሴቶች የነበሩበትን ቡድን የመራው ቡራህ አዝ ዙማር የሚባለው ነበር።በሁለተኛወ ቡድን ሰማንያ ሶስት ወንዶችና አስራ ስምንት ሴቶች ሲሆኑ የነብዩ ሞሃመድ የቅርብ ተከታይ የነበረው ጃፈር ኢብን አቢ ታሊብ የቡድኑ መሪ ነበር።
ስደተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ የነበረው ንጉስ “ናጋሲ”ወይም ባሕረ ነጋሽ ማለትም የባሕር ንጉሥ የሚባለው ሲሆን የስሙም መነሻ ምክንያቱ ቀይ ባሕርን ስለሚቆጣጠር ነው። ሙሃመድ ነብይ በሆነ በአምስተኛ ዓመቱ እውቅና የሰጠው ንጉስ አስሃማ የሚባለው የአክሱም ንጉሥ ነበር።ስደተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ንጉሱና ሕዝቡ በጋለ ፍቅርና መስተንግዶ ተቀብሎ እምነታቸውንም በነጻነት እንዲከታተሉ ፈቀደላቸው።የቁራሽ ጎሳ የነበሩት አሳዳጆች ስደተኞቹን ለማስመለስ ሁለት ጊዜ መልእክተኛ ልከው ነበር፤የኢትዮጵያ ንጉስ ግን አሳልፌ አልሰጥም በማለት ሙሉ ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ ጥያቄያቸውን ውድቅ አደረገ።በዚህም ውለታና ምክንያት ነው ነብዩ ሞሃመድ ለተከታዮቹ በምንም መንገድ ቢሆን ኢትዮጵያን እንዳያጠቁና በጦር እንዳይወጉ ትእዛዝ የሰጠው።ሌላው ነብዩን ከኢትዮጵያ ጋር ካስተሳሰረው ነገር አንዱ ቢላል የተሰኘው የከሊፋ ኡማህ ባሪያ የነበረው ኢትዮጵያዊ በሙሃመድ ነጻነቱን አግኝቶ የቅርብ ረዳትና ተከታይ በመሆኑ ነበር።በተጨማሪም ከመጀመሪያ ሚስቱ ከከድጃ በዃላ ያገባት የሃምሳ ዓመት ዕድሜ የነበራት ሳውዳህ ከመጀመሪያው በሏ ጋር በስደት በኢትዮጵያ ውስጥ የኖረች ሲሆን ነብዩ ሞሃመድን ባገባች ጊዜ የኢትዮጵያ ንጉስ የደስታ መልአክት በመላኩ ኢትዮጵያ በነብዩ ሞሃመድ ልብ ውስጥ ልዩ ቦታ ልታገኝ ችላለች።
ይህን የመሰለውን የመከባበርና የወዳጅነት ግንኙነት አንዳንድ የአረብና የሙስሊም የታሪክ ጸሃፊዎች የኢትዮጵያ ንጉስ የእስልምናን ሃይማኖት በመቀበል ሰልሟል ብለው አቅርበዋል።የኢትዮጵያ ንጉሥ የሙሃመድን ነብይነት ና የእስልምናን ሃይማኖት ማወቁ መስለሙን አያረጋግጥም።ይህማ ቢሆን ኖሮ ሙሃመድ ተከታዮቹን ኢትዮጵያን እንዳትወጉ አይላቸውም ነበር።ንጉሱ ቢሰልም ኖሮ፣ ቀሪው ሕዝብ የንጉሱን ሃይማኖት ተቀብሎ በሰለመ ነበር፤ኢትዮጵያም የክርስትናን ሃይማኖት ትታ እንደ ግብጽና ባቢሎን(ኢራቅ)ወይም ቱርክ የእስልምና ተከታይ አገር ትሆን ነበር።በዚያ ወዳጅነት የተመሰረተው ግንኙነት በሕዝቡ ኑሮ ላይ እንደ ባህል ተወስዶ፣ከሌሎቹ አገሮች በተለየ ሁኔታ እስላምና ክርስቲያን ተጋብቶ ለመዋለድና በአንድ አገር ዜግነት ለመኖር ችሏል።ሃይማኖቱን ከዜግነቱ ነጥሎ በአንድ አገር ልጅነት አምኖ ኖሯል።ይህን ለመበከልና ለማፍረስ ብሎም አገርን ለመውረር የሚሹ አገራትና ሃይሎች ግን ይህንን መልካም ታሪክ በሌላ ትርክት እዬበከሉት ብዙ ችግሮች ለመፍጠር ሞክረዋል፤ እዬሞከሩም ነው።በቱርክ የኦቶማን አገዛዝ ወቅት የእስልምናን ሃይማኖት በጉልበት ለማስፋፋት የተደረገው ዘመቻ በኢትዮጵያም ላይ ትልቅ ጠባሳ ጥሎ ሄዷል።የአሁኗ ጅቡቲና በባሕር ዳርቻ የነበሩት አካባቢዎች የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የሆኑት በቱርክና በግብጽ በሚዘወረው ወረራ ጋር በተያያዘ መንገድ መሆኑ አይካድም።የኢትዮጵያ ነገሥታት ከውጩ የክርስቲያን መንግሥታት ጋር በመተባበር የክርስትና ሃይማኖትንና አገራቸውን ከእስላማዊው ወረራ ለማዳን ችለዋል።በዚህም በሃይማኖት ስም የተዘረጋን የባርነት መረብ በጣጥሰዋል።ይህም እስላምና ክርስቲያን ኢትዮጵያውያንን በነጻነት እንዲኖሩ አድርጓቸዋል። ኢትዮጵያን አትንኩ የሚለውን የነብዩ ሞሃመድ አስተምሮ የተቃረነን የወረራ እርምጃ በጋራ አክሽፈዋል።
ነብዩ ሞሃመድ ከሃይማኖት ትምህርት ባሻገር ስለ ስነምግባር፣ሕግ፣ማህበራዊ ፍትህና ሰብአዊ መብት አስተምሯል።በዚህ ተግባር ላይ የተሰማራው ሙሃመድ በዘመኑ የነበረውን የአይሁድና የክርስቲያኖች አስተዳደር የሚፈጽሙትን በደል በመቃወምና በማጋለጥ በስርዓቱ የተማረረውን ሕዝብ ለአመጽ ቀሰቀሰው።በዚህ እምቢባይ እንቅስቃሴ ተከታዩ እየበዛ ስርዓቱን አርበደበደው፤በአንድ ከባቢ የተነሳው እንቅስቃሴ ሌላውን ከባቢ እያጥለቀለቀ አስተዳደሩን ከመዳፉ ውስጥ ለማስገባት ቻለ።የሙሃመድም ተከታዮች ሙሃመድን ከአምላክ የተላከ ነብይ አድርገው በማቅረብ “አላህ አንድ ነው፣ አይወልድም፣አይወለድም፣ ሙሃመድ መልእክተኛው ነው፣የመጨረሻው ነብይም ነው”በሚል መፈክር የወደደውን በውድ ያልወደደውን በግድ እያሰለሙ ከባቢውን ሁሉ ተቆጣጠሩ።
እዚህ ላይ የሁለቱም እምነቶች መሪዎች፣ ክርስቶስና ሞሃመድ በስርዓት ላይ የተነሱ የሕዝብ ትግል መሪዎች መሆናቸውንና የተጠቀሙበትም የትግል ዘዴና መንገድ የተለያየ፣ የሰላምና የአመጽ መሆኑን ከታሪክ እንረዳለን።ማለትም እዬሱስ ሰላማዊ ትግልን ሲከተል ሞሓመድ ግን አመጽን ጭምር ተጠቅሟል።አመጹንም ጅሃድ የሚል ስም አውጥቶለታል።ጅሃድ የሚለው ቃል ጃሃዳ ከሚለው አረብኛ ቃል የተወረሰ ሲሆን ትርጉሙም ጥንካሬንና ጥረትን ተጠቅሞ የሚፈልጉትን ማግኘት የሚል ሲሆን በግልጽ ቋንቋም የእስልምና ጠላትና ተቃዋሚ የሆኑትን በመውጋት የእስልምና ትምህርትን ተከትሎ ፣ ሃይማኖቱን በግድ ማስፋፋት ማለት ነው።
በጀሃድ ጦርነት ሕይወቱ ያለፈ ነፍሱ በአላህ ጎን እንደምታርፍም የሚገልጠው የቅስቀሳ ቃል ተከታይ ለማፍራት እንደ አንድ ስልት ሆኖ አገልግሏል።ይህ ስልት በእስላሙ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በአይሁዶችና ክርስቲያኖችም ዘንድ የተለመደ ነበር ፣ነውም።ለምሳሌ በቅርቡ በ12ኛው ክፍለዘመን እንግሊዞች ሳይቀሩ በንጉስ ሄንሪ ልጅ በሪቻርድ የተመራ ጦር አዝምተው ሳይሳካላቸው ቀርቷል።በመስቀል ጦርነት ስም በተደጋጋሚ የተደረጉ ዘመቻዎች እዬሩሳሌምን ከሙስሊሞቹ እጅ ለማላቀቅ አልቻሉም።በዬጊዜው በሙስሊሞቹ ከመሸነፍ በቀር አልተሳካላቸውም።በዚህ የመስቀል ጦርነት(ክሩሴድስ) ዘማቹ በደረቱ ላይ የመስቀል ምልክት አድርጎ ቢሞትም በደቂቃዎች ውስጥ ከፈጣሪ ጎን እንደሚቀመጥ አድርገው ይቀሰቅሱ ነበር።እውነት የመሰለው ተከታይ ግን እዬፎከረና እዬተሻማ የጦር ሜዳ በግ ሆኗል።
በእስላሞቹም በኩል በተመሳሳይ በዚህ የሃይማኖት(የጅሃድ) ጦርነት የሞቱ ነፍሳቸው በቀጥታ ከአላህ ጎን እንደምታርፍ ከመንገራቸውም በተረፈ፣ቤተሰባቸው ችግር ላይ እንዳይወድቅና ተንከባካቢ እንዳያጣ ሌላው የቤተሰብ አባል ወይም ባለጸጋ የሟች ሚስትን አግብቶ ልጆቹንና ቤተሰቡን እንዲንከባከብ፣እስከ አራት ሚስት ድረስ የማግባት መብት የሚሰጥ ሕግ አውጥተው ተጠቅመውበታል።ይህንንም ነብዩ ሙሃመድ ሳይቀር በተግባር አሳይቷል።በዚህ ሁለት አይነት ጠቀሜታ ተገኝቶበታል። ባላቸው ወይም አባታቸው የሞተባቸው ካለረዳት ወድቀው እንዳይቀሩ ሲያደርግ ሃይማኖቱን እንዲወዱና እንዲከተሉ ከማድረጉም ሌላ፣በጦርነት የወንዱ ቁጥር በመቀነሱና የሴቱ ቁጥር በመብዛቱ የነበረውን ችግር ለማሶገድ እረድቷል።አንድ ሙስሊም የተለያዩ ሴቶች አግብቶም በማሶለድ የሙስሊሙ ቁጥር እንዲያድግ ማድረጉም ሌላው ዘዴ ነበር። አሁንም የዚያው ልማድ ቀጥሎ ይታያል።
ከነብዩ ሞሐመድ በዃላ የእስልምና መሪዎች ባስተሳሰብና በጥቅም እዬተለያዩ መጡ።ልዩ ልዩ ስያሜ በመስጠትም እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ብቻም ሳይሆን የሚጨፋጨፉ ሆኑ።አሁን በእስላማዊ መንግሥታት በኩል የሚታዬው ልዩነትና ግጭት የዚያ ውጤት ነው።ሸይት፣ሱኒ፣ሱፊ፣አህማዲያ፣ኢባዲ፣ ዋሃቢ፣በረልፊ፣ዴዎባንዲ ዋናዋናዎቹ ሲሆኑ በያንዳንዳቸው ስር ደግሞ አያሌ ንኡሳን ወይም ኑፋቄዎች(SECTS) አሉ።የሙሃመድ አስተምሮ አንድ ሆኖ ሳለ በብዛት ጥቅምና ሥልጣን የቀፈቀፋቸው ናቸው።
በክርስቲያኑም በኩል ቢሆን በአንድ አምላክ ስም እዬማሉ፤በእየሱስ ክርስቶስ እያመኑ ኦርቶዶክስ፣ ኮፕቲክ ፣ካቶሊክ፣ፕሮቴስታንት–ወዘተ የሚሉት ለጥቅምና ለሥልጣን መንድርደሪያ የሆኑትን ፈልፍለው ለጥቂቶች መገልገያ በመሆን ሕዝብን እርስ በርሱ እንዲጨፋጨፍ ደም ሲፋሰሱ አይተናል።
በአንድ ፈጣሪ መኖር እያመኑ አንድ መጽሃፍ ቅዱስና አንድ ቁርአን ኖሯቸው በተለያዩ ስሞችና ሰፈሮች ተሰልፎ እርስ በርሱ መባላትና መጋደል አትግደል፣ሌላውን እንደራስህ ውደድ ያለውን የፈጣሪን መሪ ትዕዛዝ መጣስ ነው። ክርስቲያንም ሆነ ሙስሊም፣ቡድሃም ሆነ ሂንዱ፣አማኝም ሆነ አላማኝ ይወለዳል፣ይኖራል ይሞታል።ከዚህ የተፈጥሮ ሕግ የሚያመልጥ የለም።በሚኖርበት የሕይወት ዘመኑ በፍቅርና በእኩልነት ተሳስቦ ከመኖር( LIVING IN HARMONY UNDER SOCIAL JUSTIES) የተሻለ ሃይማኖት የለም!። ዓለም የሁሉም የጋራቤት የተፈጥሮ ሃብቷም ለሁሉም የሰው ልጆች ጥቅምና ኑሮ ማሻሻያ ሊሆኑ የሚገባቸው የተፈጥሮ ገጸበረከቶች ናቸው።ከቶም ቢሆን አንድ ነጠላ ቡድንም ሆነ ግለሰብ እዬዘረፈ ሊቆጣጠራቸው አይገባም።አንዱ በልቶና ተትረፍርፎት መሬት ጠበበኝ ብሎ በእብሪት ሲወጠር ሌላው የሰው ልጅ የበይ ተመልካች ሆኖ አንጀቱ ተጣብቆ በርሃብ እንዲሞት የትኛውም ሃይማኖት አይፈቅድም።በሃይማኖት ስም የሚነግዱ የጥቂቶች ሰይጣናት ምግባር ነው።የጦርነት ሁሉ መነሻ ይኸው እራስ ወዳድነት ያመጣው ጣጣ ነው። ወረራና አምባገነንነትን የሚፈለፍለው ይኸው እራስ ወዳድነት ሲሆን በጥቂት ጨካኝ ዘራፊዎች ፍላጎት ዓለማችን የምትሽከረከር ሆናለች። የአያሌ ሕዝብ ህይወት የፈሰሰባቸው፣አገራት የወደሙበት ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች መነሻውም ይኸው ነው። አሁንም እነዛው አልጠግብ ባዮች ዓለምን ለሶስተኛ ጊዜ ውድመት እዬጎተቷት ነው።ሃይማኖትን መንኮራኩር አድርገውታል።ይህንን አደጋ ለማሶገድ ሁሉም በአንድ ላይ መተባበር ይኖርበታል።በዬአገሩ ያሉትን አምባገነኖችና ተባባሪዎቹን ነቅሎ ማሶገድና ያገሩ ባለቤት መሆን ይኖርበታል።ያን ጊዜ ሰውነት የተላበሰ እውነተኛ ሃይማኖተኛ ይሆናል።
ወራሪዎች መጽሃፍ ቅዱስንና ቁርአንን ለራሳቸው በሚጠቅም መልኩ ጽፈው አትግደል ያለውን ቃል ሊገልህ የመጣውን ግደለው ብሏል እያሉ በማሳሳት የሚፈጽሙትን ጭፍጨፋ ህጋዊ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ፣የክርስትናና የእስልም እምነት እዬተበረዘ የወራሪዎች መሳሪያ በመሆን ላይ መምጣቱን ሁሉም ልብ ሊለው ይገባል።
ይህንን የሚረዳ የሰው ልጅ ሁሉ የማንኛውም ሃይማኖት ተከታይ ቢሆንም በዓለም ላይ የሚካሄደውን ዘርና ሃይማኖት ተኮር ግጭት እንቅስቃሴና ቅስቀሳ መቃወም ብቻም ሳይሆን ማሶገድ አለበት።
ሰላም ለዓለማችን ፣ እኩልነት ለሰው ልጆች ሁሉ ይሁን!!
አገሬ አዲስ
ጽሑፌን በሚከተሉት ግጥሞች እደመድማለሁ
ዓለም የሁሉም ናት
እግሬ እንዳደረሰኝ እሄዳለሁ የትም፣
ልቤ በፈቀደው በመረጥኩት ቦታ እኖራለሁ የትም፣
ዓለም የሁሉም ነች ከፈጠራት በቀር ባለቤት የላትም።
ጊዜውን ጠብቆ እያፈራረቀ፣
ይኖራል ነፍስ ያለው ቦታ እዬለቀቀ።
አንድ ጌዜ ሰሜን ሌላ ጊዜ ደቡብ፣
አንድ ጊዜ ምስራቅ ሌላ ጊዜ ምዕራብ፣
ይጓዛል ይሄዳል ለመኖር ሳይራብ።
እንዳዬሩ ጸባይ እንደሚፈልገው፣
ይሄዳል ይበራል ማን ቢከለክለው።
ክረምቱን የጠላ በጋውን ይመርጣል፣
በጋውን የጠላ ክረምቱን ይመርጣል፣
በፈለገው ቦታ ይወርዳል ይወጣል።
የግል ንብረቴ ነች ብለው የማይዟት፣
የሰው ብቻ ሳትሆን ዓለም የሁሉም ናት።
የእንስሳት የነፍሳት የሳር የቅጠሉ፣
የጋራ ሃብት ነች የፍጥረታት ሁሉ፣
የእኔ ናት የአንተ ናት የእሱ ናት አትበሉ።
ድንበር ስላኖረ ጉልበተኛ ሁሉ፣
መሬት ሰንጥቃችሁ የእኔ ነው አትበሉ፣
በዬብስ በውቅያኖስ የሚኖረው ሁሉ
የዓለም ባለቤት ነው ይኑር እንዳመሉ።
የምን መውጫ መግቢያ፣የምን ቪዛ ፓስፖርት፣
ይሂድ ይንቀሳቀስ ይድረስ ካሰበበት፣
ጥሎት ለሚሄደው ለአጭሩ ሕይወት
በወደደው ቦታ በመረጠው መሬት።
ምክንያት ሳታደርጉ ቀለምና እምነት
አንዱ አንዱን ሳይጎዳው አብሮ ይኑርበት።
ለጊዜያዊ ጥቅም ተፈጥሮ አትበድሉ፣ከባቢ አትበክሉ፤
በራስ ወዳድነት የእኔ ብቻ አትበሉ።
አጥፍቶ ለመጥፋት ሳትስገበገቡ፣
ተራራው መሬቱ ባህሩ ወደቡ
ከእናንተ ባለፈ የተተኪው ትውልድ መሆኑን አስቡ።
አገሬ አዲስ ሓምሌ 12 2016ዓም(july-19-2024)
ሁሉም ይሰደዳል!
የኑሮ ዋስትናው ብልሃቱ ሲገድ፣
ሲጨንቀው ሲጠበው የሚመርጠው መንገድ፣
ውሳኔው ይሆናል ከቦታው መሰደድ።
ለተሻለ ሰላም ለተሻለ ኑሮ ፣
እንኳንስ የሰው ልጅ ይሄዳል በረሮ።
የኑሮ ፈተና ችግር ሲያስገድደው፣
እንኳንስ የሰው ልጅ ወፍ ስደተኛ ነው።
አውሬው እንስሳቱ፣ትንሹም ግዙፉ
እግር ያለው በእግሩ ክንፍ ያለው በክንፉ፣
የተለመደ ነው ክፉ ቀን ሲገጥመው ተሰዶ ማለፉ።
በጋና ክረምቱን እያፈራረቅ፣
የነበረበትን ቦታ እዬለቀቀ፤
በጋውን የጠላ ክረምቱን ይመርጣል፣
ቁልቁለት ይወርዳል አቀበት ይወጣል፣
ጊዜውን ጠብቆ ይሄዳል ይመጣል።
የሰው ልጅ ዘላን ነው የተፈጥሮ መንጋ፣
ሰላሙን ደስታውን ምቾቱን ፍለጋ፣
ዛሬ እዚህ ነው ሲሉት ነገ ከሌላው ጋ
ሌላውን ሳይጎዳ እሱም ሳይጎዳ
ተሳስቦ ለመኖር ካለምንም ፍዳ
አብሮ ይኑርበት ሰው ለሰው አይደለም ጠላትና ባዳ።
አገሬ አዲስ ሓምሌ 20 ቀን 2016ዓም(July 27-2024)