ለቸኮለ! ሰኞ ነሐሴ 10/2013 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

ዐበይት ዜናዎች

1፤ የሕወሃትን ጦረኛ አካሄድ ለመመከት መንግሥት “ብሄራዊ የሀገር ሉዓላዊነት እና የሕዝብ ደኅንነት ማስከበር ዘመቻ ግብረ ኃይል” እንዲያቋቁም ኢዜማ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል፡፡ ግብረ ኃይሉ ሀገርን ከሕወሃት ጥቃት የማዳን ዘመቻ የሚወጣ፣ ከመንግሥት ውጭ ያሉ አካላትን ያካተተ እና መንግሥት የሚመራው ሆኖ መዋቀር እንዳለበት ፓርቲው አሳስቧል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ መንግሥት ባሁኑ ሰዓት እወሰደው ያለው ርምጃ በፌደራል መንግሥቱ ስር በመከላከያ ሠራዊት የተማከለ ዕዝ እንዲመራ ኢዜማ አበክሮ ጠይቋል፡፡

2፤ ሕወሃት በአጎራባች ክልሎች ላይ የከፈተውን ጦርነት ሕዝባዊ ስላደረገው የአማራ ክልል ሕዝብም ጦርነቱን ሕዝባዊ እንዲያደርገው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ዛሬ በሰጡት መግለጫ ጥሪ ማድረጋቸውን መግለጫውን የተከታተሉ ዜና አውታሮች ዘግበዋል፡፡ የሕወሃት ተዋጊዎች በሰሜን እና ደቡብ ጎንደር እንዲሁም በሰሜን ወሎ ጥቃት እንደፈጸሙ የገለጹት አገኘሁ፣ በጦርነቱ ከ500 ሺህ ሕዝብ በላይ ከቀየው እንደተፈናቀለ፣ ሴቶች እንደተደፈሩ እና በርካታ ንብረት እንደተዘረፉ ተናግረዋል፡፡

3፤ የተመድ ቅርንጫፍ ድርጅቶች በኢትዮጵያው ጦርነት ወገንተኛ የፖለቲካ አጀንዳ ያራምዳሉ እየተባለ የሚነገረው ነገር እጅጉን እንዳሳሰበው ተመድ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ውንጀላው በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን እና በማኅበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት ሲሰራጭ እንደከረመ የገለጠው መግለጫው፣ ድርጅቱ ከሚመራባቸው መርሆዎች መካከል ገለልተኛነት አንዱ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ገዥ መርሆዎቹን መሠረት በማድረግ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ሰብዓዊ ዕርዳታ እያቀረበ መሆኑንም ድርጅቱ አክሎ ገልጧል፡፡ በተያያዘ ዜና፣ በክልሉ ከደባር እና ደሴ ከተሞች ለተፈናቀሉ ከ9 ሺህ በላይ ሰዎች አስቸኳይ ዕርዳታ እያቀረበ እንደሆነ ዩኒሴፍ በትዊተር ገጹ ገልጧል፡፡ በጦርነቱ ከ674 ሺህ በላይ ነዋሪዎች እንደተፈናቀሉ ድርጅቱ አመልክቷል፡፡

4፤ የተመድ ስደተኞች ኮሚሽን ከ20 ሺህ በላይ ኤርትራዊያን ስደተኞችን ክትግራይ ክልል የማስወጣት ሂደት መጀመሩን የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ለደይሊ ኔሽን ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡ ስደተኞቹ ማይ ዓይኒ እና አዲ ሐሩሽ በተባሉት ስደተኛ መጠለያዎች ተጠልለው የቆዩ ሲሆኑ፣ አሁን የሚዛወሩት በአማራ ክልል ዳባት ወረዳ ወደተሠሩት አዲስ ስደተኛ መጠለያዎች ነው፡፡ አዲሱ የዳባት ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ 25 ሺህ ስደተኞችን ማስተናገድ ይችላሉ፡፡

5፤ አዲስ ባንክ መመስረት የሚፈልጉ አካላት ብሄራዊ ባንክ ያስቀመጠውን መስፈርት የሚያሟሉበት የጊዜ ገደብ እንዲራዘም ያቀረቡትን ጥያቄ ባንኩ እንዳልተቀበለው ፎርቹን ዘግቧል፡፡ ባንኩ ያስቀመጠው መስፈርት አዲስ የሚቋቋሙ እና የባለቤትነት ድርሻ መሸጥ የጀመሩ አዲስ ባንኮች በመጭው መስከረም የመጀመሪያ ሳምንት ከሚጠናቀቀው ቀነ ገደብ በፊት 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል እንዲያስመዘግቡ የሚጠይቅ ነው፡፡

6፤ አዲስ አበባን ከባሕር ዳር እና ጎንደር የሚወስደው ዋና መንገድ እስካሁንም በድንጋይ ናዳ ምክንያት እንደተዘጋ መሆኑን የአማራ ክልል ብዙኀን መገናኛ ዘግቧል፡፡ በተለምዶ አባይ በረሃ ተብሎ በሚታወቀው ቦታ መንገዱ ላይ የተከሰተውን የቋጥኝ ናዳ ለማስወገድ የባለሥልጣኑ ባለሙያዎች ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ መንገዱ ለተሽከርካሪዎች ዝግ የሆነው ከዐርብ’ለት ጀምሮ ነው፡፡

7፤ የሰሜናዊ ኬንያዎች መርሳቢት እና ኢሴሎ ግዛቶች የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት ከኢትዮጵያ የታች አስተዳደር ባለሥልጣናት እና የጎሳ መሪዎች ጋር በትብብር ለመስራት ማቀዳቸውን የኬንያ ጋዜጦች ዘግበዋል፡፡ ሁለቱ ግዛቶች የነደፉት ዕቅድ ከሚጎራበቷቸው የኢትዮጵያ የድንበር አካባቢዎች ጋር ድንበር ዘለል የሴት ልጅ ግርዛትን የማስቀረት መርሃ ግብር ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል ነው፡፡ በኬንያ የሴት ልጅ ግርዛትን የሚከለክለው ሕግ ጠበቅ ያለ በመሆኑ፣ ድንበር አካባቢ ያሉ አንዳንድ ኬንያዊያን አርብቶ አደሮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ልጆቻቸውን እንደሚያስገርዙ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡

8፤ የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ ከአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጀፍሪ ፊልትማን ጋር እንደተወያዩ በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡ ጅቡቲ በሚገኘው የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት የተካሄደው ውይይት በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ዙሪያ ያተኮረ እንደነበር ወርቅነህ ጠቁመዋል፡፡ ልዩ መልዕክተኛው በሰሜን ኢትዮጵያ ለቀጠለው ግጭት መፍትሄ ለማፈላለግ ወደተባበሩት ዐረብ ኢምሬቶች፣ ጅቡቲ እና ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ ባለፈው ሳምንት መገለጹ ይታወሳል፡፡

[ዋዜማ ራዲዮ]

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.