ሰው የአፈር ውጤት ነው ፡፡ አገር  ደግሞ  የተሰዳጁ  ሰው  ውጤት  ናት . ( እናም  ድንች  ቢናገር  ምን  ይገርማል ? )

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

መቆዘምያ

የድንቾች ቅዱስ መጽሐፍ ከትንቢተ መዋሰዕት የተወሰደ ጥቅስ

ምዕራፍ 26

  1. እንዴትያምርብናል?

በሚሞቅ ለስላሳ አፈር ውስጥ ተኝቶ የሰው ልጆችን መጠበቅ !

  1. ከፈጠረንአምላክትዕዛዝ አለመውጣት ምንኛ ውብ ነው !

ከመጀመሪያው የክፉዎችን ጎዳና ዘግቷልናል ፡፡

13 . በጠዋት የወፎች መዝሙር ወደጆሮአችን ፤ በምሽትም ጓጉነቸሮች ሊሞቁን በምድር ውስጥ ይጠጉናል ፡፡

14 . ሁላችንም በተጠንቀቅ ቅዱስ ሞትን ተጣጥበን ፤ድምጻችንን ከፍ አድርገን ፤ በመዘመር እንጠብቃታለን ፡፡

15 .ዓለም በዚህ ዕድላችን ይቅና ፤ ለስጋት የተፈጠሩ ያልቅሱ ፤

16 . እኛ በአምላካችን ፈቃድ ፤ሥጋታችንን ጨርሰናል ፡፡

ኦሜጋውን እንጠብቃለን ፡፡ ይጣፍጠናልም ፡፡

ከተወዳጁ ታላቁ ደራሲያችን ከአዳም ረታ ” የድንች መዋስዕት ” ከተሰኘ ፤ አጭር ልብ ወለድ የተወሰደ ፡፡” አለንጋና ምስር ” ከተሰኘ የአጭር ልብ ወለድ መድብሉ ገፅ 163 ፡፡

መዋስዕት ፦ ማለት ቅዱስ ያሬድ የጻፈው የዜማ መጽሐፍ ሥም ነው ፡፡ በዓላትን በይበልጥም ደግሞ  ሙታንን አስመልክቶ በዜማ የሚባል የምስጋና ፀሎት ነው ፡፡ ( ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች  ጥናትና ምርምር መአከል መዝገበ ቃላት የተወሰደ )

mekone shawel
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ሰዎቹ ሁሉ ስደተኛ ነን። ተሰደን ነው በየአህጉሩ ና በየአገሩ የበዛነው ።  እውነቱ  ምንኖርበት አገር በትውልዳችን ታሪክ የተነሳ መጤ መሆናችን ነው ፡፡እውነቴን ነው ፡፡  ለዚኽች ምድር እንግዳ ነን ፡፡  አልፎ ሄጅ ነን ፡፡  ታይቶ ጠፊ ነን፡፡ እንደ  ድንች ዓይንት ንሮ ጥንት አልኖርንም ፡፡  ዛሬስ ? አላውቅም ፡፡  አዳምን ጠይቁት ፡፡

ሰው ሲፈጠር ሙሉ ነጻነትና ከልካይ አልነበረውም ፡፡ አድርግ አታድርግ ባይ ፣ ጠባቂ ፣ ፖሊስ ወዘተ ፡፡ ፈፅሞ አልነበረውም ፡፡ ያለ ከልካይ ነበር የሚኖረው ፡  ምክንያቱም ቁጥሩ እጅግ ጥቂት ስለነበር የምግብ እጠረት አልነበረበትም ፡፡ ሳያከማች ምድር ያፈራቸውን ይመገብ ነበር ፡፡ ያውም ከአውሬ ጋ እየተፋለመ ፡፡

ነገር የመጠው ና አድርግ አታድርግ የሚባል ህግ ሰው ራሱ የፈጠረው ሰው በመዋለድ ብዛት እየበዘ ሲመጣ ና የአብሮነት መስተጋብሩ እየተናጋ በመምጣቱ ነው ፡፡ ኑሮውን ሲያዘምን በዘመናዊነቱ ውስጥ ስስት እና ስግብግብነት እያየለ በመምጣቱ የገዛ ወገኑን በህግ ሥም መበዝበዝና መጨቆን ጀመረ ፡፡…

ቀስ በቀስም ፣ ሰው እጅግ ጨካኝ እየሆነ መጣ ፡፡ ፈጣሪውን እንኳን ረሳ ፡ ለምሳሌ ፣ የብሉይ ኪዳኑ ሙሴ አስርቱን ትእዛዝ ፤ ፈጣሪአቸውን ለረሱት ስደተኛ ወገኖቹ ከሲና ተራራ ከፈጣሪ ዘንድ ከማምጣቱ በፊት ህግ አልነበረም ፡፡ በክርስቲያኑ ዓለም መንገድ ማለቴ ነው ፡፡ በሌላውም ዓለማዊ ዓለም ደግሞ የሃሙራቢ ህግ ነበር የሚታወቀው ፡፡ አይን ያጠፈ አይኑን ያጣ ነበር ፡፡

ህግ ከመኖሩና ሰው በጉልበተኛ ገዢዎች ከመተዳደሩ በፊት ፣ድሮ ፣ ድሮ ሰው  ከአንዱ አገር ወደ አንዱ አገር ፤ ከአንዱ አህጉር ወደሌላው አህጉር ያለከልካይ የመዘዋወር መብት  ነበረው ፡፡ እናም እያንዳንዱ የዛሬው ሰው ለሚኖርበት አገር መጤ ነበረ ፡፡ የጥንት ሰዎች ” ወላጆቻችን ” መጤ ነበሩ ። ዛሬ በየአህጉሩ ፣ በዘመን ብዛት ከተራራ ከሚገዝፈው ዓመታት ክምር ሥር  እነማን ናቸው  በሩካቤ ግንኙነት የእኛን ትውልድ ሀ ብለው የጀመሩት ?  ማናችንም አናውቅም ።

በእርግጠኝነት የምናውቀው ና በግልጽ  ለመናገር የምንችለው ነገር ቢኖር ፣ሰው እና ሰው ( አዳምና ሄውን ) በሩካቤ ነው ፣ ሰውን ያባዙት ። የዛን ጊዜው ሰውም  እንደ ዛሬው እልፍ ቋንቋ አልነበረውም ። ቅድመ ቋንቋው ምልክት ና ጩኸት ነበር  ።…ደግሞም  በሥልጣኔ የደረጀ ባለመሆኑ የዕለት ምግቡን ለማግኘት  በራቁትነት የሚከወከው ምሥኪን ፍጡር  እንደነበር  በተከታታይ ምርምርና ጥናት የተረጋገጠ ነው ። ( ከክርስቶስ ልደት በፊት ያለውን ታሪክ በጥሞና አንብቡ ፡፡ በኃይማኖትም አንፃር ፈትሹ ፡፡ ( በመዠመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ ፡፡ ዘፍጥረት 1፤ 1 ከሰው በፊት ምድር ነው የተፈጠረቸው ፡፡ )

በሣይንሱ እንደሚታወቀው ና በኃይማኖትም እንደሚታመነው ሰው ሲፈጠር ራቁቱን ነበር ። ለዓመታትም የኖረው ራቁቱን ነው ። ሰው ከፍጥረቱ ጀምሮ ያለ  ሆዱ ጠላት አልነበረውም ። ሆድ የሚባል ጠላቱ በተፈጠረበት በአንድ ሥፍራ ተረጋግቶ እንዲኖር አላደረገውም ፡፡ እናም ከፍጥረቱ ጀምሮ ምግብ ለማግኘት ይቃብዝ  ነበር ፡፡ በመዋለድ ምክንያትም ሲበዛ ደግሞ ፣ የምግብ እጥረት አጋጠመው ፡፡  በወቅቶች መፈራረቅና በተፈጥሮ ጨካኝነት በአቅራብያው የሚበላው አጣ  ፣ የሚኖርበትን ቀዬ ትቶ እግሩ ወደ ወሰደው ተሰደደ ። …

ሰው ልጅ ፣ከምግብ ና መጠለያ ፍላጎት አንፃር ብቻ  አንድ ቦታ ተረጋግቶ መኖር አልቻለም ። የተፈጥሮ ጦርነት ኃያል ነበርና ፣ ይህንን ከባድ ጦርነት  ለመቋቋም ከአንዱ ቦታ  ደሌላ ቦታ ተሰዶ መኖር ግዴታው ነበር ፡፡እናም ዛሬ በተለያየ ዓለም ሰውን በተለያየ መልክ ልናየው ቻልን  ። ( ራሳችንን ማለት ነው ፡፡ ተረኩ ፡፡ )

በነገራችን   ላይ ዓለም እኮ ሥትፈጠር አሁን በምናያት ቅርፅ አልነበረችም ። አህጉሮቹ በሰባት የተከፈሉት በተፈጥሮ አሥገዳጅነት ነው ። ከ1000 ዓመት በኋላ ደግሞ ይህንን 7 አህጉር 10 ወይም 14 የሚያደርጋ ወይም በተቃራኒው  3 እና 4 የሚያደርግ የተፈጥሮ ክስተት ቢኖር የዛን ዘመን ሰዎች እነዳይገርማቸው ። ማንም የተፈጥሮ ሂደትን ሊያቆም አይችልም ። በመጨረሻም መሬት እንደ ሸማ መጠቅለሎ አይቀሬ መሆኑንም አይዘንጉት ። ምክንያቱም  ይህ ዓለም ፣ መላው ህዋ በማያቋርጥ ሂደት ውስጥ በመሆኑ ፣ በማያቋርጥ ሂደቱ ውሥጥ የሚከሰቱ የህዋው   ክስተቶችም አሉና ከነዚህም መካከል እየተመዘገዘጉ ወደ ምድር አቅጠጫ እየወረዱ ያሉ የኮኮብ ሽራፋች አሉና በቅርብ ዓመታተ ውስጥ ከሰማይ  ምድር ላይ ከወደቁ ደግሞ የምድራችንን እንደ ጨርቅ መጠቅለልን የሚያውጁ ይሆናሉ ። ( ወደ አሥራ አራት አህጉር መሸንሸኗ ቀርቶ ፣ የምድር ታሪክ እንዳልነበረ ሊሆን እንደሚችልም ሳይንቲስቶቹ ከገመቱ መሰንበታቸውንም አትርሱ  ። የዮሐንስን ራዕይም አንብቡ ፡፡ እንደነበረ የሚቆይ የለም ና ቶሎ፣ቶሎ ብላችሁ ስራችሁን በጊዜ ስሩና ሬጫችሁን ጨርሱ ፡፡.. )

እሥቲ ሰማይን ቀና ብላችሁ ተመልከቱ ። በጠራው ሰማይ ላይ የምታዩት አንድ ሽራፊ ኮኮብ ይቅርና የኮኮቡ ንቁጥ  መሬት ላይ ቢወድቅ ፣ የሰው ልጅ ታሪክ እንደሚያበቃለት ስንቶቻችሁ ተራ ሟቾች ናችሁ የምትገነዘቡት ?

 

ተራ ሟች ሰው ግንዛቤውና ትውስታው በጣም አጭር ነው ፡=

እንኳን ይህንን የህዋው ሣይንሥ ይቅርና ፣ ስለጥንት አባቶቹና እናቶቹ ስደተኝነት ፈጽሞ አያውቅም ። ይህንንም የምትረዱት ፤ ከሰባት ትውልዱ በኋላ የሚጠረው የትውልዱ ሥም ካለመኖሩም በላይ ፣ 4000 ኛ ትውልዱ  አውሮፓዊ ፣ ኤስያዊ ፣ ደቡብ ወይም ሰሜን አሜሪካዊ ፣አውስትራሊያዊ ፤ አፍሪካዊ ፤ አልያም ከአንታርቲክ ጫፍ የመጣ … ሊሆን ይችላል ። ምክንያቱም በዛን ዘመን ” ዳር ድንበሬ ነው ፤ ያለ ቪዛ አትገባም ፡፡ ” የሚሉ ድንበር ጠባቂዎች አልነበሩም ። የተፈጥሮ ጨካኝ ዱላን ሸሽተው ፤ ለመሰንበት በማለት   እግሬ አውጪኝ ብለው ፣  እግራቸው ወደወሰዳቸው ፣ በደመ ነፍስ ተጉዘው ህይወት ማሰንበቻ ምግብና መጠለያ ባገኙበት ፣ለኑሯቸው አመቺ  የሆነ ሥፍራ ፣ በዛሬው አጠራር ደግሞ  አገር ይደርሳሉ ፡፡ ልብ በሉ በዕውቀት  የሚጓዙ ሥልጡኖችም አልነበሩም ፡፡  ጉዟቸው ደመ ነፍሳዊ የሆነ  የሞት ሽሽት ያዘለ ነበር ፡፡ ህይወትን የማቆየት ተጋድሎን ያነገበ ነፍስን  ለማቆየት ብቻ የሚደረግ ሽሽት … ፡፡

የሰው ትውስታ በጣም አጭር በመሆኑ እና በአሁን እና በዛሬ ላይ በማተኮሩ እንጂ ፣ በማሥተዋል እኔ ማነኝ ብሎ ቢጠይቅ ኖሮ ያለፉት እውነተኛ አባት ና እናቶቹን ስደት ይገነብ ነበር ፡፡ እናም እርሱም  ለዚች ዓለም እንግዳና ስደተኛ መሆኑንን በመረዳት ወድማማችነቱን በመገንዘብ በፍቅር ይኖር ነበር ።

ይህንን እውነት በአንክሮ በማንሰላሰል እውነቱን ቢገነዘብ ኖሮ ሰው ሁሉ ፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን በልቡ ያነግስ ነበር ፡፡ ዛሬ ሰው በሚኖሩበትም አገር ፣  በሥልጣኔው ” ሴጥኖ ” ፣ ባለው ጦር መሳርያ ተመክቶ ፣ የድሃውን አገር መንግስት አያስፈራራም ፣ ዜጎቹም እርስ በእርስ እንዲጨራረሱ የእብድ ገላጋይ አይሆንም ነበር ፡፡ ባለፀጋ አገሮቹም የገዛ ወገኖቻቸውን የሆኑትን  የደሃ አገር ሰዎች የበለጠ ደሃ እንዲሆኑ ያለማቋረጥ አይበዘብዟቸውም ነበር ፡፡

እርግጥ ነው ፣ በዝባዦቹም ሆኑ ተበዝባዦቹ እንደ ጭቃ ጠፍጥፈው የሰሩት መሬት የለም ። ዛሬ አገሬ ነው ያሉት ግዛት ውሥጥ በየፊናቸው የተገኙት ፣ በህይወት ለመሰንበት ሲሉ ” አባትና እናቶቻቸው ”  በጀልባ ፣ በመርከብ ና በእግር  ተሰደው ነው ። …

ስደተኛ ይሁኑ እንጂ ፣  ከአፈር የተደባለቁትን  አባትና እናቶቻቸውን ስደተኝነት ሥለማይገነዘቡ ከመሬት የበቀሉ ይመስላቸዋል ፡፡…አንዳንድ የፖለቲካ ሊሂቃንም፣ ሰዎችን እንደ እንጉዳይ ከመሬት የፈሉ እጽዋቶች አስመስለው ፣ በመሬት ባለቤትነታቸው እየተመፃደቁ ሲናገሩ ሳስተውል ፣ የእኛ የሰዎች ጅልነት ያስደምመኛል ፡፡ ( በየክፍለ ዓለሙ ያለ አገር ሁላ  የተመሰረተው በስደተኞች ነው ፡፡ ያውም በታላቅ ተጋድሎ ፡፡ )

ከመጀመሪው አዳም ና ከጎን አጥንቱ ከተወሰደቸው ሔዋን በስተቀር ማንም ከአፈር የተፈጠረ የለም ፡፡ ማነው ከቶ ፣ በአሜሪካ ፣ በሩሲያ  በአውሮፖ ህብረት አፈር  ፤ ከአረቡ ዓለም አሸዋ ና ቤንዚን ፤ ከቻይና ና ሩሲያ  ምድር ፤ ከህንድ ፣ ከፓኪስታን ፣ ከባንግላዴሽ ፤  ወዘተ። አፈር ላይ የበቀልኩ እና መራመድ የቻልኩ ሰው ነኝ የሚለን ? ከቶስ ማነው ? ከአፍሪካ ቅቤ መሬት ውስጥ የበቀልኩ ወየም የተገኘው ጥቁር እንቁ ነኝ ፡፡ አልማዝ ነኝ ፡፡ ወይም ዋርካ ፤ ዝግባ ፤ ወይራ ወይም ደሞ አደይ አበባ ነኝ ። በማለት አገር በቀልነቱን አስረግጦ ሊያስረዳን የሚችል ? ? ?

 

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.